Saturday, 07 November 2020 13:59

የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አንዳንድ እውነታዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የሪፐብሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ እና ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉበትና ለ59ኛ ጊዜ የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ፣ በፖስታ ድምጻቸውን የሚሰጡ ዜጎችን ድምጽ ለመቁጠር ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ፣ ለቀናት ይፋ ሳይደረግ ሊቆይ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ እጅግ የተካረረ ፉክክር የታየበት ምርጫ እንደሆነ በተነገረለት የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ መደበኛው ድምጽ በተሰጠበት ባለፈው ረቡዕ፣ ገና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድምጾች ተቆጥረው ባላለቁበት ሁኔታ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግስት ምርጫውን ስለማሸነፋቸው ፍንጭ የሚሰጥና ማጭበርበር ስለመፈጸሙ ያደረጉት ንግግር፣ ሪፐብሊካኖችን ክፉኛ ማስቆጣቱና ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል መሰጋቱ ተዘግቧል፡፡
45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለተጨማሪ አራት አመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበት ወይም ጆ ባይደን 46ኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሚሆኑበት የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ከመደበኛው የድምጽ መስጫ ጊዜ በፊት 100 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ቀድመው ድምጻቸውን የሰጡበትና በአገሪቱ ታሪክ ይህን ያህል ሰው ድምፁን የሰጠበት የመጀመሪያው ምርጫ ነው ተብሏል፡፡
በአሜሪካ የምርጫ ስርዓት መሰረት፣ አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ፕሬዚዳንት ለመሆን፣ የአገሪቱ ግዛቶች እንደ ሕዝብ ብዛታቸው ተከፋፍለው ከያዙት 538 አጠቃላይ ድምፅ ውስጥ 270 ድምፅ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡
እጅግ ውዱ ምርጫ
የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊና የኮንግረስ ምርጫ፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እጅግ ውዱ ምርጫ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው፤ የዘንድሮው ምርጫ በድምሩ 14 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን፣ ገንዘቡ ባለፉት የ2016 እና የ2012 ምርጫዎች ከወጣው ድምር ወጪ የሚበልጥ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው…
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የሚሸነፉ ከሆነ፣ በቀድሞ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በምርጫ የተሸነፉ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡ ትራምፕ ቀንቷቸው በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ደግሞ፣ የዘንድሮው ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ አራት ፕሬዚዳንቶች ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ዳግም የተመረጡበት የመጀመሪያው ምርጫ ይሆናል፡፡
ባይደን በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ፣ የትራምፕን መንበረ ስልጣን ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ዕድሜያቸው ከገፋ ወደ ስልጣን በመምጣት ይዘውት የነበረውን ክብረ ወሰን ጭምር የሚነጥቁ ይሆናል ተብሏል፡፡
ትራምፕም ያሸንፉ ጆ ባይደን አሜሪካ በታሪኳ የዕድሜ ባለጸጋውን ፕሬዚዳንት የምታገኝ ሲሆን ትራምፕ ካሸነፉ በ74 አመታቸው፣ ባይደን ካሸነፉ ደግሞ በ78 አመታቸው በዓለ ሲመታቸውን እንደሚያከብሩ ተነግሯል፡፡
“ትራምፕ ካሸነፈ አገር ጥዬ
እጠፋለሁ” ባዮች
“አነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አሸንፈው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን አገሪቱን የሚመሩ ከሆነ፣ ማቄን ጨርቄን ሳልል አገር ጥዬ እጠፋለሁ” የሚሉ አሜሪካውያን ዝነኞች መበራከታቸውን ሚረር ዘግቧል፡፡
ትራምፕን ደጋግሞ በመተቸት የሚታወቀው ጆን ሌጀንድ፣ ከእነዚህ ዝነኞች አንዱ ሲሆን ትራምፕ ካሸነፉ ከእነ ቤተሰቡ አሜሪካን ጥሎ እንደሚሄድ መናገሩ ተዘግቧል፡፡  
የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኙ ቶሚ ሊ በበኩሉ፤ ትራምፕ ካሸነፉ አገሩን ተሰናብቶ ወደ እንግሊዝ አልያም ግሪክ በማቅናት ቀሪ ህይወቱን በስደት እንደሚገፋ በፈጣሪ ስም መማሉ ተነግሯል፡፡
ሌላኛው የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ብሩስ ስፕሪንግስተን፣ በቅርቡ ከዴይሊ ቴሌግራፍ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ትራምፕ ካሸነፉ አገሩን ጥሎ እንደሚሰደድ ተናግሯል ተብሏል፡፡
በ2016 ትራምፕ ካሸነፈ አሜሪካን ጥለን እንጠፋለን ሲሉ በይፋ ተናግረው የነበሩት ሳሙኤል ጃክሰንና ሁፒ ጎልድበርግን የመሳሰሉ በርካታ ታዋቂ አሜሪካውያን፣ ትራምፕ ቢያሸንፉም፣ ቃላቸውን አክብረው ከአገር እንዳልወጡ የሚረር ዘገባ አስታውሷል፡፡


Read 2102 times