Saturday, 14 November 2020 10:39

“ከሞትና ህይወት የቱ ይሻልሃል” ቢባል፤ ሲያስብ ዘገየ!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  “አንድ ሃሳብ ላይ መድረስ አለብንና የመጨረሻ ሃሳብ ስጡበት”
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉስ  ልጆች ሶስት ልጆቻቸውን ጠርተው “እንግዲህ ልጆቼ፤ ዕድሜዬ እየገፋ፣መቃብሬ እየተቆፈረ፤ የመናዘዣዬ ክሬ እየተራሰ ያለሁበት የመጨረሻዬ ሰዓት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳቸሁ ውርስ ትወስዱ ዘንድ ለሃገራችሁ ልትሰሩላት የምትችሉትን ነገር ትነግሩኛላችሁ፡፡ በሃሳቡ የላቀና የበቃ ልጅ መንግስቴን ያስተዳደርል” አሉ፡፡
ስለዚህ ልጆቹ ተራ በተራ ተናገሩ፡-
አንደኛው እኔ የመንስግት የማስተዳር እድል ባገኝ፤
ሀ/ መልካም አስተዳደርን አነግሳለሁ
ለ/ ስልጣኔን አስፋፋለሁ
ሐ/ ደሃው እንዲማር የተጀመረው የትምህርት ሥርዓት በተሸሻለ ደረጃ የተለየ  መልክ እንዲይዝ አደርጋለሁ፡
ሁለተኛው
ሀ/ሌላ ዝርዝር ሳያስፈልገኝ ፣ሀገሬን የነካ ማንም ይሁን ማን ቢቻል በሰላም             አሊያም  በኃይል አቋሙን እንዲያሻሽል አደርገዋለሁ፡፡
ለ/ ያ አይሆንም ካለ ለአንዴም ለሁሌም አስቦበት ለሀገርና ለህዝብ እንዲቆም  እደራደረዋለሁ
ሐ/ ሁሉም ካላዋጣ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድበት አደርጋለሁ፡፡
ሶስተኛው ልጅ፡-  የእኔ ሃሳብ ፤ከማንኛውም ይለያል ፤በምንም ዓይነት ህዝቡን            ሳላማክር  ማናቸውንም፣ እርምጃ አልወስድም!
 ንጉስ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው፤ “እንግዲህ የአማካሪዎቻችሁን ሃሳብ ሰማችሁ፡፡ አንዳንድ ሃሳብ ስጡበት፡፡”
የመጀመሪያው --  ለዲሞክራሲ ቅድሚያ እንስጥ
ሁለተኛው------  አገር እየተወረረ ወዲያና ወዲህ የለም፤ እንዝመት
ሶስተኛው----የአፍሪካን መንግስታት ሃሳብ እንወቅ - ከተባበሩት  መንግስታት ህግና መመሪያ አንጻር እየሄድን  መሆናችንን  እንወያይበት የጎረቤቶቻችንን ሁኔታ ያገናዘበ ውሳኔ እንወስን…. አሉ
ንጉሱም፤ “የሁላችሁንም አስተሳሰብ አድምጫለሁ፡፡ ሁላችሁም፣ የበኩላችሁን ልባዊ አስተያየት ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፤ የለውጥ አየር የነፈሰባት አገር መቼም ቢሆን ጉዞው አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ሂደቱን ከነችግሩ መርምሬና መክሬበት አስተውዬዋለሁ፡፡ ውጤቱ እሩቅ ቢሆንም ለእርምጃ መቻኮሉ አያዋጣንም፡፡ ትዕግስት ዛሬም መራራ ናት፤ ፍሬዋም ግን ጣፋጭ  ነው!ስለዚህ አሁንም ታገሱ፡፡ ጊዜ ራሱ መልሶ ይሰጣል”   አሏቸው፡፡
በየትም አገር፣ ህይወት ከዳገትና ከቁልቁለት ተለያይታ አታውቅም። ጥጋ ጥጓን  ውስጧን፣ ጓዳ ጎድጓዳዎቿን ሳናስብ ሜዳ ሜዳውን ብቻ መሸምጠጥ አንችልም። ይህን ደግሞ ሲደርስና ስንደርስበት ብቻ ሳይሆን አስቀድመን ከባለሙያዎች ከሀገር ወዳዶች፣ ከምሁራን፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ከአመራሮቻችን ጋር ተመካክረን አደብ እንድንገዛበት ማድረግ ይኖርብናል። በእርግጥ አንድ የስነጥበብ ፈላስፋ እንዳለው “ በጦርነት መካከል ጎራዴ ምዘዝ እንጂ ግጥም ላንብብ አትበል።” ትክክለኛውን መሳሪያ ለትክክኛው ቦታ ምረጥ ማለቱ ነው! ዕውነት ነው፤ ግድም ነው።
ለውጥ እንዲኖር ከተፈለገ ለዋጩም ተለዋጩም እውቀትም፣ ንቃተ-ህሊናም ሊኖራቸው ያስፈልጋለ፤። ጂኒየስ (የላቀ -ሊቅ) እንጂ ጂኒ እና አልጂኒ በመባባል ለውጥ አናመጣም። የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ብቻውን መንጋጋጋሪያ መሆን እዲ ህዝብን አስተማሪም አጋዢም ሊሆኑ አይችሉም። በሁሉም ወገን ስንት የደም መስዋዕትነት የተከፈለባቸውን ትግሎች ዛሬ ለወግና እኛ ማለፊያና መስተዋት መወልወያ ብናደርጋቸው፣ ያለጥርጥር በደም የቀላ ቲቪና ሬዲዮ ብቻ ነው- ምርታችን፡፡በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሆኖም ለሁሉም ሰዓት አለው። ኢትዮጵያ ዛሬም “ምነው የጦርነቱንስ  ነገር ዝም አላችሁ?” ብላ እንደምትዘብትብን ቢያንስ ለህሊናችንና ለአሁን ህልውናችን ሊገባን ይገባል። ከዘመነ-መሳፍንት እስከ ዛሬ የፈሰሰውን ደም አይታለች! ወራሪ ሲመጣ ደም ፈሷል! በመሳፍንትና ሹማምንት ሽኩቻ ደም ፈሷል! በድርጅቶችና ፓርቲዎች ሽኩቻ ደም ፈሷል። በጎሳዎች ሽኩቻ ደም ፈሷል! በእርስ በርስ (ሲቪል) ጦርነት ደም ፈሷል! በሰላም መንገድ ላይ ናት በተባለ ማግስት ደም ፈሷል… ነገም እዚያው መንገድ ላይ መሆኗን  አልቀበልም የሚል ካለ የኢትዮጵያ ነገረ- ስራ ያልገባው ሰው ነው!
ዛሬ ስለ ሀገሩ የሚቆረቆር አሳቢ - አንጎልና ሩህሩህ አንጀት ያለው ዜጋ ይህን አይስተውም!
ለብዙ ዘመናት “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው!” አልን
“ከክፉ ተወልጄ ስፈጭ አደርኩ” አልን!
“ላግዝሽ ቢሏት መጇን ደበቀች” አልን!
“አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ፤ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ!” አልን።
“እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” አልን።
ብዙ አልን… አልን… አልን…
አሁን የቀረን አንድ አውራ ተረት፡-
“ከሞት ከህይወት የቱ ይሻልሃል? ቢባል፣ ሲያስብ ዘገየ!” የሚለው ነው።

Read 12795 times