Saturday, 14 November 2020 10:42

አሜሪካ ከምርጫው ማግስት….

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፈው ቅዳሜ…
አለም ለሳምንታትና ወራት አይንና ጆሮውን ጥሎ ከቆየባት ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ያልተጠበቀ ነገር ሰማ - በ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸንፋሉ ተብለው እምብዛም ግምት ያልተሰጣቸው ዲሞክራቱ ጆ ባይደን፤ ከእልህ አስጨራሽና አጓጊ ትንቅንቅ በኋላ ድልን መቀዳጀታቸውና 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸው እርግጥ ሆነ፡፡
ባይደን 76.3 ሚሊዮን ድምጾችን በማግኘት ወይም 50.7 በመቶ ሲያሸንፉ፣ ትራምፕ በበኩላቸው 71.6 ሚሊዮን ድምጾችን ወይም 47.6 በመቶ አግኝተው መሸነፋቸውን መገናኛ ብዙሃን ይፋ አደረጉ።
ገና የምርጫው ውጤት ሙሉ ለሙሉ ሳይገለጽ ጀምሮ "ምርጫው ተጭበርብሯል፤ ክስ እመሰርታለሁ" ሲሉ የሰነበቱት ዶናልድ ትራምፕ፤ ባይደን በምርጫው ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎም፣ ሽንፈታቸውን በጸጋ ለመቀበል ሳይፈቅዱ ሳምንት አልፏል።
ባይደን አሸናፊነታቸው በታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ከተለያዩ የአለም አገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት የተላለፈላቸው ቢሆንም፣ ተሸናፊው ትራምፕ ግን እንደ ወትሮው ልማድ ስልክ ደውለው የምስራች ሊሏቸው ይቅርና የምርጫ ውጤቱንና ሽንፈታቸውን በጸጋ ለመቀበል አለመፍቀዳቸውን “እጅግ አሳፋሪ” ሲሉ ነበር የገለጹት - ባይደን፡፡
በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የሆነው አዲሱ ተመራጭ፣ አዲሱ የፈረንጆች አመት በገባ በ20ኛው ቀን በደማቅ በዓለ ሲመት ቃለ መሃላ ፈጽሞ ስልጣኑን ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት እንደሚረከብ በህግ መደንገጉን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ስልጣን እስከሚረከቡበት ጊዜ ድረስ የሽግግር ቡድን እንደሚያቋቁሙም ጠቁሟል፡፡
ዘንድሮ ግን ነገሮች በተለመደው መንገድ የሚያመሩ አይመስልም፡፡ በአሜሪካ ታሪክ በምርጫ ተሸንፎ ስልጣን አልለቅም ያለ ፕሬዚዳንት አለመኖሩን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ትራምፕ ግን አፍ አውጥተው “አልለቅም!” ባይሉም ሁኔታቸው ወደዚያ የሚያመራ ይመስላል ብሏል፡፡
ምርጫው መጭበርበሩንና አለመሸነፋቸውን በተደጋጋሚ በመናገር የድምጽ ቆጠራው እንዲደገም ሲጠይቁ የሰነበቱት ትራምፕ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው እንደሚሟገቱ ኮስተር ብለው ማወጃቸውንና ከፍተኛ በጀት መድበው ለክርክር መዘጋጀታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የመራጩ ህዝብ ድምጽ ቆጠራ አሁንም ገና ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአንዳንድ ግዛቶችም የድምጽ ቆጠራው ዳግም እንዲከናወን ተወስኗል፡፡ የምርጫው ውጤት በሚመለከተው የአገሪቱ አካል ማረጋገጫ የሚሰጠውና የመጨረሻው ውጤት ይፋ የሚደረገውም ከአንድ ወር ጊዜ በኋላ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባይደን ምን አስበዋል?
በትራምፕ ቅጥ ያጣ የውጭ ግንኙነት ከተቀረው አለም በርካታ አገራት ያኳረፏትን አሜሪካ በአፋጣኝ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት እንደሚመልሷት ሲናገሩ የከረሙት ጆ ባይደን፣ ወደስልጣን ሲመጡ በቅድሚያ ያደርጓቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ነገሮች መካከል በትራምፕ እምቢተኝነት ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የወጣችውን አሜሪካ ወደ ስምምነቱ መመለስ እንደሚገኝበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በታላላቅና ሃብታም የአገሪቱ ኩባንያዎች ላይ ከበድ ያለ ግብር በመጫን የሚያገኙትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚጠቀሙበት የሚናገሩት ባይደን፣ አሜሪካውያን በሰዓት የሚያገኙትን ዝቅተኛውን ክፍያ ከ7.25 ዶላር ወደ 15 ዶላር ከፍ እንደሚያደርጉም በምርጫ ቅስቀሳቸው ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
አሸናፊው መንበሩን ለመረከብ
ምን ቀራቸው?
ፎርብስ መጽሄት እንደዘገበው፣ ባይደን በይፋ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የተወሰኑ ነገሮች ይቀሯቸዋል፡፡ አንደኛው ነገር ሁሉም ግዛቶች የመጨረሻውን የድምጽ ቆጠራ ውጤት አጽድቀው ማስረከብና፣ እስከ ታህሳስ 8 ቀን ድረስም እያንዳንዱ ግዛት ለፕሬዚዳንቱ ድምጽ የሚሰጡ መራጮችን መምረጥ ይገባዋል፡፡
መራጮቹ ለፕሬዚዳንቱ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተከትሎም የአገሪቱ ሴኔትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋራ ድምጹን በመቁጠር የመጨረሻውን አሸናፊ ይፋ ያደርጉና ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዝዳንቷ ቃለ መሃላ ፈጽመው በዓለ ሲመቱ ይከናወናል፡፡
80 በመቶ አሜሪካውያን የባይደንን
ድል ያምኑበታል
የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊነት በተለይ በትራምፕና በሪፐብሊካኑ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም፣ 80 በመቶ አሜሪካውያን ግን የባይደንን ድል እንደሚያምኑበትና ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ አንድ ጥናት ማመልከቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ አይፒኤስኦኤስ ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ 79 በመቶ ያህል አሜሪካውያን ባይደን አሸንፈዋል ብለው እንደሚያምኑ ሲናገሩ፣ 13 በመቶ ያህሉ አሸናፊው ገና አልተወሰነም ብለው እንደሚያስቡ፣ 3 በመቶው በአንጻሩ አሸናፊው ትራምፕ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በምርጫው ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት እንዲገልጹ ከተጠየቁት ሪፐብሊካን የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ባይደን አሸንፈዋል ብለው የሚያምኑ ሲሆን፣ ሁሉም ዲሞክራቶች ማለት ይቻላል በባይደን አሸናፊነት ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ እንደሌላቸው መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ምርጫው መጭበርበሩን የጠቆመ
 1 ሚ. ዶላር ይሸለማል
የቴክሳሱ ገዢ ሪፐብሊካኑ ዳን ፓትሪክ በዘንድሮው የአገሪቱ ምርጫ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ላቀረበ ወይም ጥቆማ ለሰጠ የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጡ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ትራምፕ ሁሉ በተደጋጋሚ የዘንድሮው ምርጫ ተጭበርብሯል ሲሉ የተደመጡት ፓትሪክ፣ በቴክሳስ ግዛት ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች ጭምር የምርጫ ማጭበርበር መፈጸሙን ለጠቆሙ ሰዎች ወይም ተቋማት ሁሉ ሽልማቱን ማዘጋጀታቸውን እንደተናገሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ትራምፕ ለመጽሐፍና ለቲቪ 100 ሚሊዮን ዶላር ቀርቦላቸዋል
ዶናልድ ትራምፕ ምንም እንኳን በምርጫው ቢሸነፉም፣ ቢዝነሱ ግን እንደ ፖለቲካው አክሳሪ እንዳልሆነባቸው ነው ዴይሊ ሜይል ባለፈው ረቡዕ የዘገበው። ዘገባው እንዳለው ከሆነ ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበራቸው የአራት አመታት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከኩባንያዎች የ100 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ቀርቦላቸዋል፡፡
“እንኳን ደስ ያለዎት!”
ዲሞክራቱ ባይደን በምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ አገራት መሪዎች ለተመራጩ የ“እንኳን ደስ ያለዎት!” መልዕክታቸውን በአፋጣኝ መላካቸው ቢነገርም፣ ባልተለመደ ሁኔታ አንዳንድ አገራት ግን በነገርዬው ያላመኑበት ይመስል ዝምታን መርጠው መቀጠላቸው ነው የተነገረው፡፡
ለባይደን የምስራች መልዕክት ካልላኩ የአለማችን አገራት መካከል የሩስያ፣ ሜክሲኮና ብራዚል መሪዎች እንደሚገኙበት የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤መሪዎቹ ለምን ዝምታን መረጡ ለሚለው ጥያቄ ሁነኛ መልስ ለመስጠት ቢያዳግትም አንዳንዶች ግን ከፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር እያያዙት እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
Read 3004 times