Tuesday, 17 November 2020 00:00

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ምን ይላሉ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  የህወኃት ቡድን የሚያዘው ልዩ ሃይል በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ በድንገት በፈጸመው አሰቃቂ ጥቃት ያላዘነና ያልተቆጣ ኢትዮጵያዊ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት፣በሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሃዘንም ቁጣም እንደተሰማቸው ነው የገለጹት፡፡ ምናልባት በዓለም ታሪክ በራሱ ወገን ወታደሮች ጭፈጨፋ የደረሰበት ብቸኛው ሰራዊት ሳይሆን አይቀርም የሚሉት የቀድሞ ሰራዊት አባላት፤ የሕወሃት ቡድን ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ነው የፈጸመው ሲሉም ያወግዛሉ፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ መንግስት በህወሃት ቡድን ላይ የጀመረው ህግን የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚያሳስቡት የቀድሞ ሰራዊት አባላት፤ከመንግስት ጥሪ በደረሳቸው ሰዓት ከመከላከያ ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ  አለማየሁ አንበሴ፤ሁለት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላትን በጉዳዩ ላይ አነጋግሮ ሃሳባቸውን አጠናክሮታል፡፡ እነሆ፡-


                 “ጦርነቱ ሳይራዘም በአጭሩ መቋጨት አለበት”
                        (ጀነራል አሰፋ አፍሮም፤ የቀድሞ ጦር ሃይል አባል)


            በሰሜን እዝ ላይ  በህወኃት የተፈጸመው ጥቃት እጅግ አሳዛኝ ክህደት ነው። ይሄ ጦር ላለፉት 21 ዓመታት ገደማ እዚያ ነው የኖረው። ህዝቡን በጉልበቱ እየረዳ፣ ከጠላት ሃይል እየተከላከለ የኖረ ነው። ከህዝብ ጋር አንድ ሆኖ የኖረ ነው። እንግዲህ በዚህ ሠራዊት ላይ ነው ጥቃት የተፈጸመው።
ሁላችንም እንደምናውቀው፣ ጠ/ሚኒስትሩ ጊዜውን በትክክል ባላስታውስም፣ ጦሩን ወደዚህ ለማሸጋገር ጥረት አድርገው ነበር፡፡ በወቅቱም ህዝቡ ለምኖ ነው ከትግራይ እንዳይወጣ ያደረገው ተባለ። ከክልሉ እንዲወጣ ፈቃደኛ አልነበሩም። ነገሩ የተጀመረው ያኔ ይመስለኛል። በሁለቱ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት እየተካረረ ሲሄድ፣ በመሃል የሃገርን ድንበር መጠበቅ ዋና ተልዕኮው የሆነው ጦር ነው የተጠቃው። ይሄ እጅግ አሳዛኝ ነው። በቅርቡ እንኳ አንድ አዛዥ ከዚህ ወደ እዙ ተልኮ አንቀበልም ብለው እንዲመለስ ተደርጓል ተብሏል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደረጉ ችግሮች በእጅጉ እያንዣበቡ እንደነበር ይታወቃል። መጨረሻ ላይ እንግዲህ ህውኃቶች ጦሩን አጥቅተው ጉዳት አደረሱበት። ጦርነቱም በዚህ ምክንያት ነው የተጀመረው። ስለዚህ መንግስት ተገድዶ የገባበት ጦርነት ነው። ውጤትም እያገኘበት ነው። ይህን ውጤትም እስከ መጨረሻው ከግብ ማድረስ ያስፈልጋል። በጦሩ ላይ የተፈጸመው ቅሌት ግን ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው። እጅግም አሳዛኝ ነው። እንደ አንድ የጦር መሪ በጣም ነው የማዝነው። ጦርነትን ማንም አይወድም። ነገር ግን የግድ ከሆነ ተገቢው ቦታ ላይ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡
አሁን እነሱ ውጊያ ከፍተዋል፤ አደጋ አድርሰዋል፡፡ ይሄን ካደረጉ በኋላ ድርድር መቀመጥ እንዴት ይቻላል? ይሄን የፖለቲካ ባለሙያዎች ናቸው መመለስ የሚችሉት። እኔ ማለት የምችለው ሰላማዊ ሰዎች በማይጎዱበት መንገድ ጠላትን ብቻ ለይቶ መምታት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል። እዚህ ላይ መንግስት በእጅጉ መጠንቀቅ አለበት። ጦሩ ዓላማና ዒላማውን አውቆ ብቻ ነው ማጥቃት ያለበት። በሌላ በኩል፤ መንግስት ይሄን እንቅስቃሴ ፈጣን ነው ማድረግ ያለበት። ጊዜ የሚገዛበት ከሆነ ውጤት አይመዘገብበትም። ጦርነቱ በፍፁም መራዘም የለበትም። በአጭሩ ነው መቋጨት ያለበት። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ወጪው ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡  አገሪቱ በኢኮኖሚ ትጎዳለች፣ ህዝቡም ይሰቃያል። ይሄ ችግር ጦርነት ደረጃ የደረሰውም በላይ በላዩ እየተደራረበ መጥቶ ነው። ስለዚህ በፍጥነት ማከናወን ያስፈልጋል።____________________               “ዛሬም ለአገራችን አንድነት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነን”
                           (ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ማህበር ሊቀ መንበር)


             ሕወኃት የሄደበት መንገድ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አስደንጋጭ ነው። ዱብ እዳ ነው። የማይጠበቅ ነው። ምክንያቱም አገር በሚመሩበት ወቅት ራሳቸው ያጠናከሩትን መከላከያ፣ ወልደው ያሳደጉትን ልጃቸውን መብላታቸው እጅግ ጨካኝ አረመኔ ያደርጋቸዋል። ሠራዊቱ የሃገር ጠባቂ ዘብ ነው። ህይወቱን ለሃገሩ ሊሰጥ የተዘጋጀ ነው። እነሱ ግን ለፖለቲካቸው ዓላማ ነው የጨፈጨፉት። ይሄ እጅግ አሳዛኝ ነው። ወታደር ለፖለቲካ ሳይሆን ለሃገር ነው ነፍሱን ሊሰጥ የተዘጋጀው። ይሄን የሃገር ሀብት ከኋላ እንደ ውሻ ነክሶ መግደል በአለም ታሪክ ውስጥ አላየሁም። ይሄ የመጀመሪያው ይመስለኛል። የመከላከያ ሰራዊትን የራስ ወገን የውርደት እርምጃ ሲወስዱበት፣ እንደ ወታደር የሚሰማን ስሜት እጅግ ጥልቅ ነው።
መንግስት ይሄን ጥፋት፣ ይሄን ውርደት ማካካስ የሚችለው በሚወስደው ህግን የማስከበር፣ ክብርን የመመለስ እርምጃ ልክ ነው። ጠቡ የተጀመረው ከራሱ ከህወኃት በመሆኑም መንግስ ይሄን ተንኳሽ ሃይል የመቅጣት ሙሉ ሞራል አለው። ማህበረሰብን ከጥቃት ለመከላከል ተገዶ የገባበት ግጭት  ነው። እንዲህ ያለው ተልዕኮ የጊዜ ቀጠሮ ተይዞለት፣ በሽለላ በፉከራ ተነስቶ፣ "ና ይለይናል" ተብሎ የተጀመረ አይደለም። ህዝብን የካደ ባንዳና ወራሪ ሃይልን የመመከት፣ ልክ የማስገባት እርምጃ በመሆኑ እኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ለመንግስት እርምጃዎች ሙሉ ድጋፍ እንሰጣለን።
ይሄ የወያኔ ጥቃት ከባንዳነትም ባለፈ የራስ ሃገርን ወራሪነትና የእናት ጡት ነካሽነት ነው። የአገርን ሉአላዊነት ለውጭ ሃይሎች ያጋለጠ ባንዳ ሃይል ነው። ቤተሰቡን ትቶ፣ አንድ አይነት ልብስ ለብሶ፣ ላንተ ነፍሱን ሊሰጥ በፍጹም አምኖህ መሃልህ የተገኘን ጠባቂህን እንዴት ትገድለዋለህ? ምን አይነት ጭካኔ ነው? ምን አይነት ክብረ ቢስነት ነው? እንዴት የራስህን ጠባቂህን አደጋ ትጥልበታለህ? ይሄ እጅግ የለየለት በሽታ ነው። ኢትዮጵያዊነትን የመጥላት በሽታ ውጤት ነው። ክፋትና ተንኮል ነው። የጭካኔ ጥግ ነው ያየነው። ይሄ እኮ ጀግንነት አይደለም። ፈሪነት ልክስክስነት ነው። ወያኔ ጫካ ሲገባ የነበረውን ማንነት በከፋ ውርደት እያጠናቀቀ ነው። እነሱ  የፈለጉት ኢትዮጵያን መበተን መገነጣጠል ነበር ግን ኢትዮጵያ አምላኳ ይጠብቃታል። ህልማቸው ሳይሳካ ከነ ቆሻሻ ታሪካቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መጥፊያቸው አሁን ደርሷል።
መንግስት እየወሰደ ያለው እርምጃ ልክ እና ትክክል ነው። እሽሩሩው በዝቶ ነበር። አንቀልባው እስኪበጠስ ነበር ያዘላቸው። እውነት ለመናገር አስተዋይ መሪ ስላለንና ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ሊታደጋት ስለወደደ ነው ይሄ ሁሉ ማባበል የነበረው። አሁን ግን እነሱ ጅራፉን ቀድመው አጩኸውታል፡፡ መንግስት ደግሞ በተሰጠው ስልጣን ህግ ያስከብራል፤ ሃገር ያስከብራል። ኢትዮጵያን በእንደዚህ አይነት መንገድ አዋርዶ፣ በርካታ ምስቅልቅል ነገር ውስጥ ከቶ መኖር አይቻልም።
የትግራይ ህዝብ ጨዋ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ኢትዮጵያዊነቱን የሚወድ፣ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ትልቅ ኩሩ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብና ወጣት ኢትዮጵያዊነቱን አስከብሮ የሚወጣበት፣ ሰንደቁን ከፍ አድርጎ የሚታይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። መንግስት አሁን እየወሰደ ያለውን እርምጃ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ይደግፋል፤ ጥሪ በቀረበለት ጊዜ ሁሉ መንግስትን ለማገዝ ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን። የቀድሞ ሰራዊት ማህበር 274 ቅርንጫፎች በመላ ሃገሪቱ አሉት፡፡ መንግስት ታስፈልጋላችሁ ባለ ጊዜ ሁሉ ፈጥነን እንገኛለን፡፡ ዛሬም ለሃገራችን አንድነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን።

Read 8539 times