Saturday, 14 November 2020 11:33

ከልብ የሰራን - ከልብ ማወደስ!

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(1 Vote)

  "ደረጀ ብዙ ነው፣ ነፍሴ ከበቂ በላይ በሙያቸው ለሀገራቸው ደክመዋል ብላ እጅግ ከምታከብራቸው ሰዎች መካከል ግንባር-ቀደም ተጠቃሽ ፀሐፊ ነው፡፡ በግጥሙ፣ በመጣጥፉ፣ በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ በድርሰቱ፣ በጋዜጣው፣ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥኑ አሻራዎቹን በትኗል፣ ስለ ሌሎች ብዙ ሲል ኖሯል፤ እንደ ሻማ ቀልጧል፤ ስለዚህ ሰው ብዙ ሲባል ግን አይሰማም፡፡"
          
          ‹‹ደ››
የደረጀ በላይነህ የ‹‹ደመና ሳቆች›› መጽሐፍን አንዴ ብቻ ነው ያነበብኩት…..ነዘረኝ….እንደ ብረት ምድጃ ‹‹ጂስሜ›› ሁሉ ነደደ፡፡ የአለማየሁ ገላጋይ ‹‹ቅበላ›› ልቦለዱን ያነበብኩ ጊዜ እንዲሁ አድርጎኝ እንደነበር አይዘነጋኝም፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁለተኛዬ መሆኑ ነው። ከዚያ በኋላ መጽሐፉን ከድኜ መልሼ መክፈት አልቻልኩም….ለወር፣ ለአመት……ከዚያም በላይ …..ደግሜ ካነበብኩት ይሄን ስሜቴን የማጣው መሰለኝ፡፡ ስለዚህ አለመድገሙን መረጥኩ፡፡ ስለ መጽሐፉ በፀጥታ ማሰላሰል ብቻውን ልብ ውስጥ ዜማ ያለው ‹‹ሙዚቃ›› ይፈጥራል። ያነቃንቃል እንዲል አዳም ረታ (አዳም ረታ ‹‹መረቅ›› ውስጥ ሆነ ብሎ ስም ገልብጦ ሲጠቅስ ያጋጥመናል፣ ለምሳሌ ታላቁን ደራሲ ‹‹ሀዲስ አለማየሁ››ን፣ አለማየሁ ሀዲስ ሲል ይጠራቸዋል፣ ጽምፃዊ ማህሙድ አህመድንም እንዲሁ! ነገር-ግን እንዲያም ሆኖ ያምርለታል፣ ይሰምርለታል፣ ይጣፍጥለታል)
‹‹በላይነህ ደረጄ›› እንዴት ቢተርከው ነው ልቤን እንዲህ የጠለፈው? አዎ የ‹‹ደመና ሳቆች›› ኪናዊ ውበትና የቋንቋ ልቀት ተቃቅፈው ያደሩበት የስነ-ጽሁፍ አልጋ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በርግጥ ይሄን የጥበብ ስራ ‹‹ቀመስኩት›› እንጂ አላኘኩትም፣ አልዋጥኩትም.. በአንድ ጊዜ ‹‹ቅምሻ›› ንባብ፣ የተብራራ ሀተታ ለመፃፍ ያዳግት ይሆናል። ‹‹ቤከን›› የተናገረው እኔ ላይ እውን የሆነ መሰለኝ፡፡ እውቁ ፈላስፋና ደራሲ ‹‹ፍራንሲስ ቤከን›› በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፡- አንዳንድ መጽሐፍ ለመቀመስ፣ አንዳንዱ ለመዋጥ፣ አንዳንዱ ለመላመጥና ለመመንዥክ፣ አንዳንዱ ከፍተኛ ‹‹ትኩረትና - ከበሬታ›› ለመሻት ይነበባሉ፡፡ ሂደት አላቸው ማለት ነው፡፡ ምናልባት ቤከን የኔ አይነት የንባብ እጣ-ፈንታ ገጥሞት ይሆን? ወደፊት ለአቅመ ጋዜጣ ስበቃ ብዙ የምልበት፤ በጥልቀት አንብቤና አጥንቼ የምተነትነው ግንባር ቀደም ዘውግ ‹‹ኖቭል›› እንደሚሆን አምኛለሁ፡፡ አንዳች ልዩ ነገር አይቼበታለሁ። የእቅዴም አንድ አካል ነው። የደመና ሳቆች፡፡
‹‹ረ››
ለአመታት ሳይሆን ለዘመናት ቢባል ይሻላል ... መጣጥፎቹን እንደ ጉድ ኮምኩሜለታለሁ፡፡ የ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ፈርጥ ነው፡፡ ምልክቷም ጭምር። ‹‹ቅዳሜ›› ሆኖ በአጋጣሚ እሱ ካልፃፈ የ‹‹አድማስ›› አደባባይ ጭር ይልብኛል፡፡ ጥልቅ ድብርት ይውጠኛል፡፡ ሌላ አምድ ገልጦ ማንበቡ ይተናነቀኛል፡፡ አይኔ በደመ ነፍስ ስሙን ፍለጋ ይንከራተታል፣ አንድ ‹‹አስራ-አራት›› ገጽ ዘልዬ ‹‹ጥበብ አምድ ላይ የርሱን ፅሁፍ በማሰስ እጠመዳለሁ፡፡ ከጻፈ ደግሞ ደስታዬ ከሁሉም አቅጣጫ ሙሉ ይሆናል። አሁን-አሁን አድማስን ያለ ደረጀ ማሰብ አይሆንልኝም፡፡
ዘወትር ቅዳሜ ጋዜጣው ላይ እንደ ቆሎ የፈሰሱ ‹‹ጥበብ-ነክ›› ጽሁፎቹን እንደ-ቡና ቁርስ በጥቁር ወፍራም ቡና ማወራረድ ለምጃለሁ፡፡ ደረጀ ማኪያቶ ይወድዳል፣ የማኪያቶ ሱሰኛ ነው፣ ማኪያቶን ‹‹እንደ ነጭ ውስኪ ነው የምቆጥራት›› ይላል፤ ብዙ ጊዜ በጽሁፎቹ ሳይጠቅሳት አያልፍም፡፡ እኔ ደግሞ የቡና ሱሰኛ ... የቡና ታርቲመኛ …. ከአቦል እስከ በረካ.. እዚያ እንኳን አልደርስም። እንደ እሸት ጽሁፎቹ ሁሉ ለማኪያቶ ያለውን ፍቅርም አንባቢው ላይ የማጋባት አቅም ተችሮታል፡፡ እውነት ለመናገር እኔም ይሄ ፍቅሩ ተጋብቶብኝ፣ አሁን-አሁን ቡናዬን ትቼ ‹‹ጠቆር ያለ ማኪያቶ›› የዘወትር ምርጫዬ ከሆነ ከራርሟል፡፡ ግድ የለም ሰው ከለመደውና ከሚወደው ብዙ ይለምዳል፣ ብዙ ይቀዳል፣ ከምንወደው እኮ ነው የምንማረው! ፍቅር በፍጥነት የመጋባትና የመዛመት ሁኔታው ተፈጥሯዊ ነው፤ ሰው የመሆን እውነታ ነው! ይሁን፡፡
በነገራችን ላይ..‹‹ታላቁ ጥቁር›› በተሰኘ የታሪክ ምርምር ሰነዱ ያደነቅነው.. ንጉሴ አየለ፤ በከባድ-ሚዛን ‹‹ስመ-ጥር›› የውጭ ደራሲያን ህይወትና አጉል ልማድ ዙሪያ በሚያተኩረው የትርጉም ስራው ‹‹ጣዝማ›› ውስጥ እንደነገረን ከሆነ፤ ባልዛክ በአንድ ቀን ውስጥ እስከ 50 ሲኒ ቡና ፉት የሚል ደራሲ ነበር፤ አጥብቀው የወደዱትን ለሞት ያደርሳል እንዲሉ ቡና ውስጥ በሚገኝ በ‹‹ካፊን›› መርዝ ሳቢያ ህይወቱ እንዳለፈች በታሪክ ይነገራል፡፡
ልጁ ዘርፈ-ብዙ አውራ ባለሙያ ነው። ብቅት ያለ ጋዜጠኛ፣ ይበል የሚያሰኝ ሀያሲ..ሌላም ሌላም፡፡ ... በተለይ ማህበራዊ ሂሶቹን እወድለታለሁ፡፡ ማህበራዊ ጉዳዮችን ሲያነሳ ብዕሩ ይስላል፣ ይሳላል … ያኔ ባለ-ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን ተመልካች እንኳን ብንሆን ፍንጣሪው አይምረንም። የጉልበታም ብዕሩ አቅምና ጉልበት የሚወጣው በዚህ ጊዜ ነው። ለዚህ እንደ አስረጂ የሚሆን ‹‹የጀግኖች እንባ በጆሲ አደባባይ›› ሲል ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት የፃፈውን መጣጥፍ መለስ ብሎ ማየት በቂ ነው፡፡
በኢትዮጵያዊነቴ የምኮራውን ያህል እንዳፍር ያደረገኝ የውርደታም ህዝብ ገመናውን ነቅሶ ራቁት ያሳየኝና ልቤ ውስጥ እንደ - አለት የተተከለ ‹‹ማህበራዊ ሂሱ›› ነው፡፡ ባሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ላይ ለንባብ በበቃው የዶ/ር አለማየሁ ዋሴ ‹‹ሰበዝ›› ውስጥ..ድንቁርናችን ከመግዘፉ የተነሳ ነውራችን ‹‹ክብራችን›› ሆነ (ገጽ 55) ሲል የወቀሰን ..ደረጀ፤ በብዕሩ በ ‹‹ሰማይ ጠቀስ ህንፃ›› የተጋረደ ነውራችንን ያሳየን ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው፡፡
‹‹ጄ››
ይሄ ‹‹ደረጄ በላይነህ›› የሚባል ልጅ እንዴት ያለ ገራሚ ነው ባካችሁ? ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላቀብኝ.. እያደገ የመጣበት መንገድ ከኔ ‹‹እውቀትና ግምት›› በላይ ነው፡፡
በለውጡ ሰሞን ... የጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹አብይ አህመድ›› የትውልድ መንደር (ጅማ፣ አጋሮ፣ በሻሻ) ተጉዞ በርሳቸው ከልጅነት እስከ እውቀት እንዲሁም በማህበራዊ ህይወታቸው ዙሪያ በቂ-ጥናት አድርጎ ‹‹ትንታጎቹ›› በሚል ርዕስ ያስጠረዘውን መጽሃፉን አስነበበን፡፡
ደረጀ ‹‹ማለፍያ››  አድርጎ ከትቦታል። ከጠቅላዩ ቤተሰብ ጋር በነበረው ቆይታ ያልተሰሙ አዳዲስ ጉዳዮችን በተዋበ ብዕሩ አቀብሎናል፡፡ይህ ብቻ አይደለም፣ የአጋሮንና የህዝቦቿን ማህበራዊ አኗኗርና መልኮቻቸውን፣ እንግዳ ተቀባይ ዜጎች መሆናቸውን ሁሉ ለመታዘብ ችለናል። ገጣሚው በአንድ ድንጋይ የሁለት ወፍ ሚናን ተጫውቷል። በዚህ አይነት አፍላ ጉልበቱን ግጥምን ለማቃናት ባይጨልፍ ኖሮ ብዙ ድንቃ-ድንቅ ነገሮችን ሊያስነብበን ይችል እንደነበር ተሰምቶኛል። እዚህ ጋ ወጣት ገጣምያንን በማውጣትና - በማብቃት እንዲሁም ‹‹ፋና›› የሚሆን አዳዲስ አቅጣጫዎችን በማሳየትና በማመላከት ረገድ ያለውን ደማቅና ጉልህ አበርክቶ ማሳነሴ እንዳልሆነ ይሰመርልኝ፡፡ ጋሽ ስብሃት ለአብ በዘነበ ወላ ‹‹ማስታወሻ›› ውስጥ የአንድ ሀያሲ ተልዕኮ አንድን የጥበብ ስራ ተደራሲ ካላየበት አንግል ተመልክቶ አቅጣጫ መጠቆምና ማሳየት ነው ሲል ተናግሯል፡፡ ይሄን የስብሃት ቃል.. ደረጄ በላልቶና በንስር አይኑ ጠልቆ በማየት እንዲያም ሲል በማሳየት ተግብሮታል፡፡
ደረጀ ብዙ ነው፣ ነፍሴ ከበቂ በላይ በሙያቸው ለሀገራቸው ደክመዋል ብላ እጅግ ከምታከብራቸው ሰዎች መካከል ግንባር-ቀደም ተጠቃሽ ፀሐፊ ነው። በግጥሙ፣ በመጣጥፉ፣ በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ በድርሰቱ፣ በጋዜጣው፣ በሬድዮ፣ በቴሌቭዥኑ ... አሻራዎቹን በትኗል፣ ስለሌሎች ብዙ ሲል ኖሯል፤ እንደ ሻማ ቀልጧል፤ ስለዚህ ሰው ብዙ ሲባል ግን አይሰማም፡፡ አረ ባለ እዳዎቹ ነን ጎበዝ.. በደረስንበት ንባብና እውቀት ልክ ... በርታልን፣ ኑርልን ... ልንለው ይገባል። ደረጀን በ‹‹ትንታጎቹ›› ውስጥ ያየሁትን ጥልቅ እይታና ደፋር ብዕሩን ከእንግዲህ እንደ-ዋዛ አናየውም፡፡ ለመጪው ጊዜ ስነ - ፅሁፋችንን ለማስጠራት የሚችልበት ድፍድፍ አቅምና ጉልበት እንዳለው በርካታ ጥበባዊ አሻራዎቹ ያሳብቁበታል፡፡ አንጋፋው ደራሲና ሀያሲ ‹‹አስፋው ዳምጤ››.. በአንድ ወቅት በታዛ መጽሔት ላይ በነበራቸው ቆይታ አድናቆትና ተስፋቸውን ችረውታል። በኔ ንባብና መረዳትም ቢሆን የደረጄ በላይነህ ዘመን ጠገብ ንባቡና የህይወት ልምዱ የሚጠቁመኝ ይህንኑ እውነት ነው። በርግጥ በላይነህ ደረጄ ወይም ‹‹ደረጀ በላይነህ›› ልቆብኛል፡፡


Read 748 times