Monday, 16 November 2020 00:00

መለኮታዊ እብደት

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)


             ቅጭም ያለው ገጽታው ዙሪያ ገባው ላይ አዚም ይረጫል፡፡ የባከነ ግማሽ ምዕት ዓመት፡፡ ሠርክ የአስኳላን ደጃፍ እየረገጠ፤ይኽው እነኾ የጡረታው ቀነ ገደብ   ቀርተውታል፡፡ መምህሩ፡፡
የክፍሏ ተማሪዎች፣ ከመምህሩ አንደበት የሚፈልቀውን ፍሬ ነገር ለመቃረም፤ እንደ ወትሮው እየተጠባበቁ ነው፡፡
“እብደት እንዴት ግሩም ነው? ጎበዝ፤” አለ ቁጭት ባኳተነው ቅላጼ፡፡
ቀለም ቆጣሪው፣ የመምህሩ አለወትሮው ከተነሳበት ርዕስ ጉዳይማፈንገጥ፣ የጤና አልመስል ብሎታል፡፡
“ጨርቅን ሳይጥሉ ማበድ፣ ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው፤ መምህር?” ጥግ ላይ ከመሸገ ብልህ ተማሪ፣ ቆስቋሽ ጥያቄ ተሰነዘረ፡፡
“የእኔ እብደት ከቀዬው ወግ ያፈነገጠ ነው፡፡ ነፍሴ የሥጋ ጨርቋን ጥላ እርቋናን ሆናለች፡፡ እላይዋ ላይ የተሸከመችውን የክፋት ጓዝ አሽንቀጥራ መለመላዋን ቆማለች፡፡ እንደ መርግ የተጫናትን ይህንን ግብዝ ገላ ወግድ ብላለች፡፡ እብደቴ ለዙሪያ ገባው በረከት ይሆናል፡፡”
“መምህር አልመሸቦትም ለማበድ?” ተማሪው መልሶ ሞገተ፡፡
“ዕድሜ በሁለት መንገድ  ይሰላል፤በቁጥር ጨዋታና በመንፈስ ከፍታ፡፡ በሁለተኛው መንገድ የእኔን ዕድሜ ሳሰላው፣ ዛሬ ይህቺን ምድር እንደተቀላቀለ እንግዳ ፍጡር ሆኜ ነው የሚሰማኝ፡፡ ገና ሮጬ ያልጠገብኩ ጨቅላ ነኝ፡፡”
መምህሩ አንደበቱን ሲለጉምና የከፍሉ በር በኃይል ሲደቃ በአንድነት ገጠመ፡፡
በእስኳላው አገዛዝ ቅያሜ የገባቸው ተማሪዎች፣ ለአመጽ የሚያነሳሳ መፈክር እያሰሙ ወደ ክፍሏ ዘለቁ፡፡ ፊታቸው እንደ ቋያ እሳት ይፋጃል፡፡ ወደ ኋላ የሚመለሱ አይመስሉም፡፡ የክፍሏ ተማሪዎች አመጻውን እንዲቀላቀሉ በመፈክር ማግባባታቸውን ተያያዙት ፡፡
“መምህር፣ገና የተናገሩት ነገር ከአፎት ሳይወድቅ፣ እብደቱ እኮ ተጀመረ”ተናዳፊው ተማሪ አንደበቱን ባላወሰበት ፍጥነት፣ ልክ ከአመጸኞች ጎራ ለመቀየጥ ተጣደፈ፡፡
መምህሩ በሁኔታው ድንገቴነት እየተደመመ፣ በአመጸኛ ተማሪዎች መሀል እየተጎሻሽመ ሾልኮ ወጣ፡፡
አመሻሽ ላይ
ለወትሮው ከውሃው ለመቀማመስ ጎራ  ይዞ የሚሰለፈው ግንባር ቦታ ላይ ከከተመች የመጠጥ ግሮሰሪ ነበር፡፡ ቤቷ ዱክትርናቸው ከስማቸው ቀድሞ ካልተጠራ ክንፈር በሚጥሉ ግብዝ ፊደላዊያን የሥራ ባልደረቦቹ የምትዘወተር ናት፡፡ የመለኮታዊ እብደት ለእንደዚህ ዓይነቱ ግብዝነት ፊት አይሰጥም፡፡ ከሳር ከቅጠሉ ጋር መፈገግ ነው ሰንደቁ፡፡ ቁንን ሰብዕናን እንደ አሮጌ ሸማ አውልቆ መጣል፣ ሲለጥቅ ቅለትን ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር መታጠቅ፡፡ ይኸ ነው የመለኮታዊ እብድት መንፈስ፡፡ ለዛሬ ገለል ማለት አሰኝቷል፡፡ የሆነ ተራ አልባሌ መሸታ ቤት ፈልጎ ከራሱ ጋር ሸንጎ መቀመጥን ተመኘ፡፡ አዝግሞ አዝግሞ ከአንዴት አውላላ ሥፍራ ላይ እንደ ቡግር ከበቀለች መሽታ ቤት ዘንድ ተመሰገ፡፡
የመሸታ ቤቷ ሆድ ዕቃ በሰው ቁንጣን ጭንቅ ጥብብ ብሏል፡፡ የአዳም ዘር በሙሉ የቀረ አይመስልም፡፡ ምርጊቱ የተከፈተው ፊልተር ጠላ ወደ ኋላ ይገፋተራል። ከመምህሩ ትይዩ የተሰየሙት ሴት አዛውንት፤ የሁሉንም ትኩረት የመሳብ አቅምን ተችረዋል፡፡ መቋሚያ ለመያዝ የሰነፉት መዳፎቻቸው አንኮላው ላይ ሲበረቱ ለጉድ ነው፡፡ በላይ በላይ ወደ ጉሮሯቸው በሚልኩት ጠላ ተበራተው በተቀመጡበት ቦታ እንደ ኮረዳ ንጥር ንጥር ይላሉ፡፡ ድንገት ለዐይን የደቀቀ ክንድ የሚያህል ሰው፣ ክምብል ክምብል እያለ ከመሸታ ቤቷ ተሞጀረ፡፡ ገና ትንፋሽ ሳይሰበስብ፤
“ለኃጣን ኮረሪማ፣ ለጣድቃን ባለ ግርማ ነኝ፣ እኔ የባሻ ግዛቴ የበኽር ልጅ ... ግድየለም፤ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ የማእዘን ራስ ትሆናለች፤” አለ፤ በስላቃዊ ቃና፡፡
መሸተኛው በሙሉ አውካካ፡፡
የመሸተኛው ስሜት ስስ ነው፡፡ ለመፈገግ ብዙም አያንገራግርም፡፡ መምህሩ እንደ ሸክም ተጭኖት የኖረውን ክብሩን ለማግኘት በምናብ ዳከረ፡፡ ከሥፍራው አጣው። ከመሸተኛ ጋር ትከሻ ለትከሻ እየተሻሸ፣ በቅለት ወጀብ እየተናጠ፣ ፊልተሩን መጋቱን ቀጥሏል፡፡
 “ከእዛች ግብዝ ግሮሰሪ፣ ይህቺ ፊልተር ቤት በስንት ጣዕሟ፡፡ ለኅጣን ኮረሪማ፣ ለጣድቃን ባለ ግርማ ነበር ያለው፡፡ ድንቅ ተቃርኖ……” በውስጡ አጉተመተመ፡፡
የቤቷ ዓይን ማረፊያ የሆነችው ራዲዮ ክንብንቧ ገሸሽ ተደርጎ፣ ልሳኗ ሲከፈት ኹካታው ተጨማሪ ጉልበት አገኘ፡፡ ከራዲዮኗ የሚወጣውን ድምጽ ከመምህሩ በቀር ልብ ያለ መሸተኛ ግን አልነበረም፡፡ በራዲዮኗ ላይ የእንድ ግብዝ  መምህር ቃለ ምልልስ ነው የሚደመጠው፡፡
መምህሩ ግለሰቡን በሴራ ጠንሳሽነቱን ነው የሚያውቀው፡፡ አስኳላውን በሹም ሽር ልቡን ከሚያጠፉት መካከል ቀዳሚው ነው። የረገጠውንሥፍራ ሁሉ በአድርባይነት መንፈስ ያራክሳል፡፡
በሰውዬው ሰበብ ግብዟ ግሮሰሪ ሥጋ ለብሳ ከፊት ለፊቱ የተገተረች መሰለው። ፊልተር ቤቷ የሰጠችው ቅለት መልሶ ሲወሰድበት ተሰማው፡፡ ሒሳብ ክፍሎ መሸታ ቤቷን ተሰናብቶ ወጣ፡፡
ከውሃው ከወሳሰደ በኋላ እሱነቱን ተነጥቆ፣ አንሶላ ከሚጋፈፋት ጉብል ጋር በሐሳብ መናጥ ነበር ልማዱ፡፡ ይህ ደመ ነፍሳዊ ስሜቱ ጠቅላይ ገዢው ሆኖ ግራ ቀኝ እያላጋው ለዓመታት ሰልጥኖበታል፡፡ እንደ ትራፊክ ባዘዘው አቅጣጫ ለመንጎድ አንገራግሮ አያውቅም፡፡ ዛሬ ግን ይህ ደመ ነፍሳዊ ፈላጭ ቆራጭነት የሚፈተንበት ቀን ላይ ይገኛል፡፡ ከመሸታ ቤቷ ከተለየ ጀምሮ ዘማዊት ደንበኛው እንደ ልማዷበእዝነ ኅሊናው እንደ ሰንደቅ እየተውለበለች ነው፡፡መለኮታዊ እብደቱን ባሰበ ቁጥር ግንአቅም እየከዳት መልሳ እንደጉም በና ትጠፋለች። ይህንን እንግዳ ኃይል በመጎናጸፉ የተነሳ በሐሴት ውስጥ ሲዳክር ይሰማዋል፡፡ ከሲታዋን ጎዳና በሰጎን ቅልጥሙ እየመተረ በአሸናፊነት ስሜት ስንኝ ደረደረ፡፡
በእኔነት በረሃ
ልጓም ለመጨበጥ፣
ክንዴ በዛለበት፣
ነፍሴን አማተርኩኝ
በመለኮት እብደት፡፡

Read 1560 times