Wednesday, 18 November 2020 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

  ሁለት ወንድማማቾች ነበሩ፣ ከእናታቸው ጋር የሚኖሩ። አንደኛው የእጅ ዓመል አለበት። እናታቸው ሌባው ማንኛው እንደሆነ ማወቅ ስለተቸገሩ ገንዘብ በጠፋባቸው ቁጥር ሁለቱንም በአለንጋ ይጠበጥባሉ።
በአንደኛው ልጅ በየጊዜው ያለጥፋቱ መገረፉ ስላበሳጨው አቄመ። በነገሩ አሰበበትና የሚገላገልበትን ዘዴ ተለመ። አንድ ቀን እናቱ ያስቀመመጡትን
ገንዘብ አንስቶ ከመሬት ወድቆ እንዳገኘ በማስመሰል
“እማማ” አላቸው።
“አቤት”
“ይኸን ገንዘብ መኝታሽ አካባቢ ወድቆ አገኘሁት” ብሎ ሰጣቸው።
“ውይ የኔ ነገር… ተባረክ ልጄ” አሉና መርቀው ተቀበሉት። በሆዳቸውም አሁን ሌባው ታወቀ! በማለት ደስ አላቸው። በዛው ሰሞን ይኸው ልጅ እናቱ ካስቀመጡት ገንዘብ ላይ ግማሹን ወስዶ ተዝናናበት። በጉዳዩ የተናደዱት እናት ምሽት ላይ ልጆቹ ሲመጡ የበፊተኛውን ሌባ ሙልጭ አድርገው ገረፉት።
“አሁንማ አውቄሃለሁ” እያሉ። ቢምል ቢገዘት ሰሚ አላጋኘም።ከዛ በሁዋላም ስርቆቱን እርግፍ አድርጎ ተወ። ወንድምየው እያደባ መመንተፉን ቀጠለ። የሚደበደበው ግን ያልሰረቀው ሆነ። ጎረቤቶቻቸው፡-
“እሱ መሆኑን በምን አወቅሽ?” ብለው ሲጠይቋቸው … ምን እንዳሉ … መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ።
***
ወዳጄ ፡- እንደ ሰው በኑሯችን፣ እንደ አገር በዜግነታችን፣ እንደ ስልጣን በሃላፊነታችን በየጊዜው የሚገጥሙን ፈተናዎች ብዙ ናቸው። እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁመን ወደ ድል አድራጊነት የምንሸጋገረው በጥሞና ማሰብ ስንችል ነው። ማሰብ ማሸነፍ ነው። ቼስ ስንጫወት ባላጋራችንን ለማጥቃት የተለያዩ የመከላከልና የማጥቃት ዘዴዎችን (alternatives)  እናስባለን። በምናወጣው ስትራቴጅም ተጋጣሚያችንን መንቀሳቀሻ አሳጥተን፣ በጥቂት ሃይል ንጉሱን እንማርካለን። በጨዋታው ቋንቋ ይህ የሚሆነው “smart move” ስንወስድ ነው። ታላቁ ቦቢ ራሽር የጨዋታውን ህጎች መሰረት ያደረጉ ብዙ ስማርት ሙቮችን በስዕል ማስረጃ በተደገፈ መጽሐፍ አስነብቧል።
ወዳጄ፡- “ ሁሉም ለበጎ ነው፣ ሁሉም መልካም ይሆናል” ብለን መዘመራችን ጥሩ ነው። ነገር ግን ስኬትና ድል አድራጊነት በምኞት፣ በፀሎትና በተስፋ ብቻ አይገኝም። የተዘጉትን በሮች ማንኳኳት ያስፈልጋል። ካልተከፈቱ ደግሞ በግድ መበርገድ … smart move!
ወዳጄ፡- “ከሾህ የተጠጋ ቁልቋል ዘለዓለም ሲያለቅስ ይኖራል” እንደሚባለው ሁሌ ከመስጋት፣ ሁሌ ከመፈናቀል፣ በገዛ ሃገራችን ስደተኛ ከመሆንና እንደ ከብት እየተጎተትን ከመታረድ በማያዳግም እርምጃ ሰላማችንን ማረጋገጥ የወቅቱ ጥሪ ነው።
የአንባ ገነኖች የራስጌ መጽሐፍ /Bed side reading/ በመባል የሚታወቀውን፣ አርባ ስምንት የሃይልና የስልጣን ህጎች (48 Ru les of power) የተሰኘውን መጽሐፍ የፃፈው ሮበርት ግሪን፡-
“እባብ ስትገድል ድምጥማጡ መጥፋቱን እርግጠኛ መሆን አለብህ፣ አንዲት እንቁላል እንኳ ብትተርፍ ነገ ብዙ ትሆናለች” ይላል። ተፈጥሮን በሚያውክና አምባገነንነትን በሚያበረታታ መጽሐፍ ባንቀሰቀስም፣ ነገሩ እውነትነት ይጠፋዋል ማለት አይደለም።
አንድ ሳይባል አይቆጠርም። የ “smart move” መርህ ከአምባ ገነኖች ቅዠትና ስሜታዊ እርምጃ የሚለየው ከጭቆናና ከበደል ተወልዶ፣ በቀልን መሰረት ሳያደርግ፣ በተነጠለና በተጠና ታርጌት ላይ ማነጣጠሩ ነው። በነገራችን ላይ ስማርት ሙቭ በትልልቅና በተወሳሰቡ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን በትንንሽ ጨዋታዎችም ድል አድራጊነትን ያጎናጽፋል። እንደ ምሳሌ የመጀመሪያውን ዓይነት እውነተኛ የቤተሰብ ውዝግብ ታሪክ ልጨምር።
ወንድና ሴት ህፃናት ናቸው፣ ታላቅና ታናሽ። ረዥም ዓመታት አውሮፓ ኖራ የተመለሰች፣ ስልጡን እናት አላቸው። ታዲያ ትንሿ ልጅ ከወንድሟ ጋር ስትጫወት በራሷ ጥፋት ቀድማ ታለቅሳለች።
“ምን ሆንሽ?” ስትባል
“መታኝ” እያለች ወንድሟን ታሳጣለች።
እናትም … “በል ቶሎ ይቅርታ ጠይቅ፤ ሶሪ በላት” በማለት ትቆጣለች። ልጁ ደግሞ ሳያጠፋ ይቅርታ መጠየቅ አልዋጥ እያለው እልህ ይተናነቀዋል። ይሄኔ እናት በኩርኩም ትገጨዋለች። ልጁ ጭቆናው ሲብስበት ባህሪውን ቀየረ። ሳይነካት አስቀድማ ታለቅስ የነበረው እህቱን ባገኘው አጋጣሚ አስቀድሞ  ያቀምሳት ጀመር። እናት ለቅሶዋን ሰምታ ቱግ ስትል፡-
“ማሚ ያጠፋችው እሷ ናት፣ እኔ ግን ” ‘ ሶሪ’ ብያለሁ”ይላል።
እናትም “ ከዚህ የበለጠ ምን አድርግ ነው የምትይው?” በማለት እህቱን ትቆጣለች። ለቅሶዋን ካላቆመች ደግሞ ትጨምርላታለች።
ልጁ በሆዱ ይስቃል።… ባይበረታታም ስማርት ሙቭ! ነው።ወደኛ አገር ፖለቲካ ስንመለስ፡ አንዳንድ ባለስልጣኖች የተሃድሶ ግስጋሴውን ወይም የለውጡን የነፋስ አቅጣጫ በመገንዘብ ስልጣናቸውን ለቀዋል። አቶ ሃይለማርምና አቶ ሙላቱ እንደ ምሳሌ ሊቆጠሩ በመቻላቸው ይመሰገናሉ። ለአቶ ደመቀና  ለአቶ ለማም ከመቀመጫችን ተነስተን አጨብጭበናል። ቀደም ሲል ደግሞ ለኮ/ል መንግስቱ የዝንባብዌ ጉዞም ኮፍያችንን አንስተናል። ሁሉም ለሰላም የተደረጉ አስተዋጽኦዎች ናቸው። …..smart moves!!
ወዳጄ፡- ስማርት ሙቭ እንዳለ ሁሉ ቀሽም እርምጃዎችም አሉ። ሕወሀትና ተባባሪዎቹ በቀደም እለት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያደረሰው ጥቃት ከብዙ ስህተቶቹና ቀሽም እርምጃዎቹ አንዱ ነው።… የታሪክ ጥቁር ነጥብ!... በዚህ አጋጣሚ መንግስታችን የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅና ህግ ለማስከበር የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ መቁረጡ እንደ ስልጣን የሃላፊነት ግብሩን መወጣቱ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የሰበዓዊ መብት ኮንቬንሽኖችን ለማክበር ያለውን ዝግጁነት ይመሰክራል።
እንደ ሕዝብ ከጎኑ ቆመን አገራችንን ከፀረ ሰላም ሃይሎች መታደግ ደግሞ ለኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ “smart move” ነው!!
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ከሴትየዋ ሁለት ልጆች አንደኛው ያለ አግባብ መቀጣቱ ስላበሳጨው የወሰደባቸውን ገንዘብ ከመሬት ወድቆ እንዳገኘ በማስመሰል እንደ መለሰላቸው ተጨዋውተናል። ከዛ በፊት ገንዘብ ሲጠፋባቸው ሁለቱንም ልጆች ይቀጡ የነበሩት እናት ‘ሌባውን አወቅሁት’ ብለው የሚገርፉት መስረቅ ያቆመውን ልጅ ብቻ ሆነ። ጎረቤቶቻቸው፡-
“እሱ መሆኑን በምን እናውቃለን?” ሲሏቸው
“ይኸ ከይሲ! እሱ ነው የሚሰርቀኝ። ያኛውማ እንኳን ያስቀመጥኩትን ሊወስድ ወድቆ ያገኘውን አንስቶ ይሰጠኛል” ይሏቸዋል።… የተበዳይ smart move እንዲህ እንዲያስቡ አደረጋቸው።
ሠላም!


Read 1260 times