Monday, 23 November 2020 00:00

በታገዱት የጥበቃ አገልግሎት ተቋማት በኩል የተቀጠሩ ሰራተኞች ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

   “ከዚህ በኋላ ለምሰራው ስራ ተገቢ ክፍያዬን እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ
                                
            በታገዱት የጥበቃ አገልግሎት ተቋማት በኩል በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የተቀጠሩ  የጥበቃ ሰራተኞች፣ ስራቸውን ባሉበት ተቋም ውስጥ  እንደሚቀጥሉና ከሚሰሩበት ተቋም ጋር ቀጥተኛ የሥራ ውል ሊፈፅሙ መሆኑን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቆሙ፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ በህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል በሚል  በታገዱ 14 የጥበቃ አገልግሎት ተቋማት በኩል የተቀጠሩና ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ የሚገኙ ሰራተኞች እዚያው  ባሉበት ተቋም ውስጥ ስራቸውን መስራት ይቀጥላሉ፡፡ ከታገዱት የጥበቃ አገልግሎት ድርጅቶች መካከል  አንዳንዶቹ ለሰራተኞቻቸው የጥበቃ ስራቸውን እንዲያቋርጡ ሊደረግ እንደሆነ በማስመሰል የሚያሰራጩት መረጃ ፈጽሞ የተሳሳተና ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል ጀነራል መላኩ፡፡ ሰራተኞቹ በተቀጠሩበት ስፍራ በህጋዊ መንገድ ስራቸውን እንደ ሚቀጥሉ የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ መንግስት የጀመረውን የጥፋት ተልዕኮ  አስፈጻሚ ግለሰቦችን የመያዝና ተቋማቱን የማሸግ እርምጃ ህጋዊ ሰራተኞችን እንደማይመለከት አስታውቀዋል፡፡
 አሁን ካለው የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የጥፋት ተልዕኮ የሚያስፈፅሙና ሽብር ለመፍጠር የሚሰሩ ተቋማትን የማገድና ወንጀለኞቹን ለፍርድ የሚቅረቡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት  ጀነራል መላኩ፤ በእስካሁኑ አሰሳ በርካታ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ የእጅ ቦንቦችና ፈንጂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ካለፈው ዓመት መጀመሪያ እስካሁኑ ባሉት ጊዜያት 169 ያህል በነዚሁ የታገዱ የጥበቃ አገልግሎት  ድርጅቶች የሚጠበቁ  ባንኮችና ሌሎች ተቋማት መዘረፋቸውንም ተናግረዋል ምክትል ኮሚሽነሩ፡፡
ምንጮች ለአድስ አድማስ እንደገለጹት፤ በጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች አማካይነት በተለያዩ ተቋማት የተቀጠሩ የጥበቃ ሰራተኞች ከሚሰሩባቸው ተቋማት ጋር የስራ ውል ለመፈጸም በሂደት ላይ ናቸው፡፡ አሰሪ ተቋማቱ የሰራተኞቻቸውን ሙሉ መረጃ፣ አሻራ፣ ፎቶግራፍና መሰል መረጃዎች እየተቀበሉ እንደሆነም እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
“ስብሐትና ልጆቹ” በተባለው የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በኩል በአንድ ኤምባሲ ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራው ሰለሞን ተስፋዬ እንደሚናገረው፤ ከ8 ዓመታት በፊት በስዊዘርላንድ ኤምባሲ  ስራ ለመጀመር የቅጥር  ውሉን የፈፀመው ከኤምባሲው ከአሰሪው ጋር ሳይሆን “ከስብሐትና ልጆቹ” የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ጋር ነበር። በዚህም ወቅት ድርጅቱ ምንም ዓይነት ጉዳይ ቢኖር መነጋገር የምንችለው ከተቋማቱ  ጋር ሳይሆን ከእነዚህ ኤጀንሲዎች ጋር እንደሆነ በመግለጽ ውል አስፈርመውናል። በውሉ መሰረት አንድ ሰራተኛ ከአሰሪዎቹ  ተቋማት ጋር በምንም ጉዳይ ላይ ቢነጋገር፣ ድርጅቱ ውሉን እንደሚያቋርጥና ከስራ  እንደሚታገድ ይገልጻል፡፡ ስለዚህም ለአመታት ስለሚከፈለን ደመወዝም ሆነ በስራ ላይ ስለሚደርስብን ጫና  ምንም ነገር ሳንተነፍስ ኖረናል፡፡ እነዚህ በእኛ የጥበቃ ሰራተኞች ላብ የተፈጠሩት የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች  የሚከፍሉን ደመወዝ እነሱ ከተቋማቱ ከሚቀበሉት  ከግማሽ በታች ነው በእኛ ጉልበት የሚነግዱ ክፉዎች ናቸው፤ ለአመታት በእኛ ላይ ለሰሩት ወንጀል፤ በፈፀመብን የባሪያ ንግድ በህግ ሊጠየቁልን ይገባል ብለዋል፡፡
በአጋር የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ በኩል ተቀጥሮ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ዓለማየሁ ታዬ እንደሚገልጸው፤ የስራ ውል የፈረምኩት ከአጋር ጋር ነው። አሁን እየሰራሁበት ካለው ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት የሥራ ውል የለኝም፡፡ ድርጅቱ ለጥበቃ ሰራተኞች የሚከፍለው ደሞዝና ለእኔ የሚከፍለኝ ደመወዝ በእጅጉ እንደሚለያይ ባውቅም፣ ለዓመታት ምንም ነገር ማድረግ ሳልችል ቀርቻለሁ። በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ቅሬታ ያሰሙ በርካታ ባልደረቦቻችን ከስራቸው ሲባረሩ አይተናል። ማንም ለምን ብሎ አይጠይቅም፤ የሰራተኛ   ማህበር ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ ወደ ስራ ስቀጠርም ድርጅቱ ምንም ዓይነት ጉዳይን የተመለከተ ነገር መነጋገር የሚቻለው ከእነሱ ጋር እንጂ ከምሰራበት ተቋም ጋር እንዳልሆነ ውል  አስፈርመውኛል፡፡
ስለዚህ ከስራዬ ላለመባረር ሁሉን  እያወቅኩሁ እየሰራሁ ቆይቻለሁ፤ አሁን የተደረገው ነገር ተስፋ አሳድሮብኛል፡፡ ምናልባት ለምሰራው ስራ ተገቢ ክፍያዬን አገኝ ይሆናል፤ የስራ ዋስትናዬ ተጠብቆ የመስራት ዕድሉንም አገኝ ይሆናል፡፡ በዚህም ደስ ብሎኛል፤ “የላቤ ተጠቃሚ የምሆንበት ጊዜ ደርሶ ይሆን?” እላለሁ፡፡ እነዚህ ተቋማት  በእኛ ላይ በፈፀሙብን ወንጀልም በህግ ሊጠየቁ ይገባል ብሏል-ዓለማየሁ፡፡
ከህወሃት አባላት ጋር በተለያዩ መንገዶች ግንኙነት አላቸው የተባሉት 14 የጥበቃ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት መታገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡


Read 2450 times