Sunday, 22 November 2020 00:00

ፔሩ በአንድ ሳምንት 3 ፕሬዚዳንቶችን ቀይራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)


             በኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ የተመታችውና በህዝባዊ ተቃውሞ ስትናጥ የሰነበተችው ፔሩ፤ 1 ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 3 ፕሬዚዳንቶችን መቀያየሯን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በሙስና ወንጀል መዘፈቃቸው የሚነገርላቸውንና ህዝቡ አደባባይ ወጥቶ በተቃውሞ ስልጣን እንዲለቁ የጠየቃቸውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራን ባለፈው ሳምንት ከመንበረ ስልጣናቸው ያነሳው የአገሪቱ  ምክር ቤቱ፣ ከቀናት በኋላ የቀድሞውን አፈ ጉባኤ ኢማኑኤል ሜሪኖን በፕሬዚዳንትነት ቢሾምም ሰውየው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ሌላ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ፣ ለ5 ቀናት ከቆዩበት ስልጣን አንስቶ፣ ባለፈው ሰኞ ደግሞ ፍራንሲስኮ ሳጋስቲን በጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነት ሾሟል፡፡
በሙያቸው መሃንዲስ የሆኑት የ76 አመቱ አዲሱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንሲስኮ ሳጋስቲ ከአምስት ወራት በኋላ እስከሚካሄደው የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ድረስ በስልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ከምክር ቤቱ አባላት መካከል ግማሽ ያህሉ ሙስናና የገንዘብ ማጭበርበርን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኙም ገልጧል፡፡


Read 2717 times