Saturday, 21 November 2020 11:27

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

   ወዳጄ ካሳሁን በነገረኝ ቀልድ ልጀምር፡- “እንደው ምን በድዬህ ነው……እንዲህ የጨከንክብኝ”  ሲል አማረረ አሉ ሰውየው……አምላኩን ውጪ ሲያገኘው፡፡
“ምን አጠፋሁ?”
“ሎተሪ እንዲወጣልኝ አስመስለህ እንኳን መኖሪያዬን ጀባ ብትለኝ ምን ችግር አለው? ላንተ ምን ይሳንሃል?”
“ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ያንተም ጥረት ያስፈልጋል፡፡ አንኳኩ! ይከፈትላችኋል ነው ያልኩት፡፡”
“ማለት?”
“ሎተሪውን እንኳን ቁረጥ! ሌላውን ለኔ ተወው”
“ጌታዬ ሎተሪ ኮ ቅጠል አይደለም፣ ከዛፍ ላይ አልበጥሰውም”
“ገባኝ” አለ ጌታው ….. ትንሽ አሰብ  አደረገናም “ውሳኔዬን እስካሻሽል ታገሰኝ” አለው።
“የምን ውሳኔ?“
ነገረውና መንገዱን ቀጠለ …. ምን ብሎት ይሆን? መጨረሻ ላይ አስታወሱኝ
*  *  *
ወደጄ፡- መከራ ከጀርባችን አልወርድ አለ። “እፎይ” ስንል መልሶ ይፈናጠጥብናል፤ እንደምንም ገፍተን ልንቋቋም ስንሞክር ተመልሶ አናታችን ላይ እንዘጭ ይላል ….. እንደ ሲሲፐስ ቋጥኝ፡፡ መኖር አለመኖር እንደ ገመድ ጉተታ ጥንቃቄ ይፈልጋል።  የህይወት ስፖርት የሚዳኘው በጊዜ ነው። “…ጊዜ አያዳላም። ሁሉም ነገር፣ ሁሉም ጉዳይና ሁሉ ሰው ተጀምሮ የሚያልቅበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ የልቦና ወለምታን በፍቅር ወጌሻ ለማረቅ በቅሬታ የተኮማተረን ጅማት በፈገግታ ለመፍታት ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ለመኖርም ጊዜ! …ለማሞትም ጊዜ!... በትዕግስት ጊዜ ይሸመታል፤ በጊዜም ተስፋ ይገዛል፡፡ በተስፋ ህይወት ይነቃል”
“ከንጹሃን ገና አልተወለዱም” መፅሀፍ የተወሰደ
ወዳጄ፤ ጊዜ መስታወት- ነው ራሳችንንም ሌላውንም ያሳየናል፡፡ ጊዜ ሰባሪን ይሰብራል፣ የተሰበረውንም ይጠግናል፡፡ ሐበሻ፡- “ጊዜ የሰጠው ቅል ደንጋይ ይሰብራል፣ ጊዜ እስኪያልፍ ያባትህ ባሪያ ይግዛህ” ወዘተ… ይላል።… ሁሉም በጊዜው እንደሚሆን ሲሰበክ። ውሃ የሚፈላውም የሚረጋውም በጊዜ ነው። ህጻንንት፣ ልጅነት፣ ወጣትነት ሽምግልና ጊዜ ነው፡፡ አሸናፊነት ተሸናፊነት ጊዜ ነው፡፡ ሰውና ጊዜ አንድ ናቸው። አንዱ ከሌለ ሌላው የለም።…. ወዳጄ፤ ጊዜ አይጣልህ! መባል ትልቅ ምርቃት ነው፡፡ የጊዜ ፍርድ አይቀለበስም፡፡
በአሜሪካን የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት ሽንፈት የደረሰበት የኮንፌዴሬት ሀይል ደጋፊዎች የነበሩ በአትላንታ ከተማ ዙሪያ የሚኖሩ ሀብታሞች፤ ኑሮአቸው ከፎቅ እንደተወረወረ መስታወት ተንኮሽኩሾ ነበር፡፡ ከጦርነቱ ማብቂያ በኋላ የሸፈቱ፣ ለክብራቸው የተራቡና ተጎሳቁለው ያለፉ እንዳሉ ሆነው! “አላማህን ይዘህ አትሙት” እንደሚሉት፤ ከጊዜው ጋር ተመሳስለው ሁኔታዎችን በሰላማዊ ፉክክርና በድምጽ ብልጫ ለመቀየር የታገሉ ብዙ ነበሩ። ከነዚህ ቤተሰቦች የአንዳንዶቹ ሴት ልጆች የአባታቸውን አገልጋዮች አግብተዋል። ወንዶቹም ለበታቾቻቸው ተቀጥረው አገልግለዋል፡፡ ሁኔታዎችን በትእግስት እልህ ውስጥ ባለመግባት ዝቅ ብሎ በመኖር ጊዜን ማሳለፍ እንደ ትልቅ ዘዴ የሚቆጥሩ  ብዙ ጠንካራ  ሰዎችን ፈጥረዋ። ችግሩ በተሳሳተ ዓላማና ዕምነት ስር መሰለፋቸው በመሆኑ ፍሬ አላፈራም።  በምርጫቸው ጊዜም ቢሆን እንዳሰቡት ብዙ ደጋፊዎች አሰባስበው ወድድሩን ሊያሸንፉ አልቻሉም፡፡ ባርነት ጊዜው አልፎበት ነበርና!
የሽማግሌው ዶ/ር ፎንቴይን ባለቤት ግራንድማ ፎንቴይን፤   
“ጊዜውን መስሎ በመኖር ለውጥ ማምጣት ይችላል” ብለው ከሚያምኑት የመኳንንት ቤተሰቦች አንዷ ነበሩ። በወዳጃቸው ጀራልድ ኦሃራ ቀብር ዕለት ለስካርለት ኦሃራ፡-
“ እንደ ምርጥ ስንዴ ዝርያ ወይም እንደ ለስላሳ የዛፍ ቅርንጫፍ ብዙ ጊዜ ወድቀን ተነስተናል። ሃይለኛ ነፋስ ሲነፍስ ቆመን አንሰበርም። ለጥ ብለን እናሳልፈውና ወደ ነበርንበት እንመለሳለን። ያገኘነውን ስራ ሳንንቅ እየሰራን፤ እንዳልተበደለ ሰው መስለን፣ ከማይመጥኑን ሰዎች ጋር እየሳቅን ጊዜውን እንሸኘዋለን” (we bow to inevitable. we are buck wheat. when a storm comes we bend with the wind.  we are not a stiff-naked tribe, we are mighty, limber, because, we know it pays to be limber.  we work, smile and we bide our time. we play along with lesser folks and we take what we can get from hem.  when we are strong enough, we kick the folks whose necks we have climbed over.  My child, that is the secret of survival, I pass it to you” በማለት የህይወት ልምዳቸውን እያጣቀሱ አስተሳሰባቸውን ሊጭኑባት ሞክረዋል። ደግነቱ እንደሷ ላለ ትውልድ፣ እነዚህ ቃላቶች ስሜት የሚሰጡ አልነበሩም።… ጊዜ አልፎባቸዋልና!
ወዳጄ፡- ህይወትን በፎርሙላ ለመኖር የሚወጥኑ ብዙ ናቸው፣ የተሳካላቸው ግን የሉም። ቢኖሩም ጥቂት ለመሆናቸው አያጠራጥርም። ማንም ሆነ ምን በሚቀጥለው ደቂቃ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር አያውቅም። አንድ ነገር ልብል፡- ሳይንስና ጥበብ የሚመዘኑት የሰው ልጅ በእድገቱ ባስመዘገበው የአስተሳሰብ መጠን ወይንም የአእምሮ እድገት ደረጃው ነው።
የአእምሮ እድገት ስለማያቆም አሁን ያለው የሰው ልጅ ከሚያውቀው በላይ ወደ ፊት የሚያውቀ ይበዛል። ሳይንስና ጥበብ በደረሱበት የማይቆሙና ሁሌም ክፍት መሆናቸው ለዚህ ነው። እውቀት ሂደት በመሆኑ ኩነቶችን  እንጂ አስተሳሰብን ወይም ህሊናን  መጨረሻ አድርጎ አይደመድምም።… የኤዲንግተን “ ቲዎሪ ኦቭ አንሰርቴይኒቲ” (Theory of un certainity) ልብ ይሏል!!
ወዳጄ  ከሳሁን በኢትዮጵያውያን ያኔ ካጫወተኝ  የዓረብ ተረቶች አንድ ልጨምር፡-
ሐሰን የሚባል ጎልማሳ ነበር፣ የአካባቢው ሰዎች የሚወዱት። ትንንሽ ስራዎችን እንዲያግዛቸው እያደረጉ የሚፈልገውን ሁሉ አሟልተውለት ይኖራል። ሐሰን ሌላ ቦታ የምትኖር እህት አለችው። ሞልቶ የተረፉት ባለፀጋ። ለወንድሟ መልካም ባለመሆኗ ግን አጅሬ ብቻውን ይኖራል።
ከእለታት አንድ ቀን ሃሰን እህቱ ወዳለችበት ቦታ ተጠራ። ሴትየዋ በመሞቷ ንብረቱን እንዲረከብ ነበር። ተረከበ፡፡ ያልጠበቀው ሲሳይ እጂ ገባ።… እናም፡-ሃሰን
 “ግፋ ቢል ከአሁን በሁዋላ የሚኖረኝ እድሜ ከአስራ አምስት ዓመት አይበልጥም። ይኽንን ንብረት ሸጨ ገንዘቡን ለእያንዳንዱ ቀን አካፍልና (X=15 X 365) ረሃ የሆነ ኑሮ አሳልፌ እሞታለሁ ሲል ቀመር እንዳለውም አደረገ። በአስራ አምስተኛው ዓመት የመጨረሻ ቀን ጀምበር ስትጠልቅ፣ የሃሰን የመጨረሻ ሳንቲምም አብራ ጠለቀች።
ሐሰን ግን ቁልጭ እንዳለ ነበር።
በሚቀጥለው ዕለት ወደ ቀድሞው ጁምአው ሲመለስ፣ በጣም ያማረበት ወጣት ይመስል ነበር። ጁምአው ኪሱ ባዶ መሆኑን ሲያይ ፡-
 “ምነው ሀሰን?” ብሎ ጠየቀው
“ቀለጠ ብል ሂሳብ?” አላቸው በአረብኛ።
(ሃሰን  ሂሳብ ተሳሳተ ማለቱ ነበር።)
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ሰውየው እግዜርን፡-
“የትኛው ውሳኔ?” ብሎ ሲጠይቀው…
“ጥረህ፣ ግረህ ኑር” የሚለውን…… በማለት ነበር የመለሰለት!!…
ሠላም!!

Read 635 times