Saturday, 21 November 2020 12:22

ደበበ ሰይፉ እና ኢትዮጵያዊነት

Written by  ፊደል ችሎ
Rate this item
(1 Vote)

 ግጥም በባህሪው ቁጥብ ነው፤ እዝነ ልቦናን  ጠልቆ የመኮርኮር የተለየ ባህሪም አለው፡፡ በተመረጠ ቋንቋ፣ ስርአቱንና ፍሰቱን በተከተለ አደራደር ማህበረሰባዊ ሁነቶችን፣ የግለሰብ አተያይን ወዘተ… ምጥን  አድርጎ ለመቋጠር አይነተኛ ስልት ነው፡፡
አጭሬ ግጥም ቁመተ ዶሮ
የሚንጠራራ ወደ ሰው ጆሮ
እንዲሉ ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ። ገጣሚው ማህበራዊ ክንውኖቹን ይዋሀዳቸዋል፤ የገበሬውን ውሎ ይውላል፣ እያንዳንዱን የኑሮ ክዋኔ ልብ ይላቸዋል፣ ስለ ታመሙ ይታመማል፤ ህመሙንም ይወደዋል፣ ምጡን ደስ ይሰኝበታል። አንድ ገጣሚ በተፈጥሮ ሲገረም፣ የሰው ልጅ ውሎን ሲያጤን፣ በጎ ስራን ሰርተው ስለ አለፉ ሰዎች ሲመረምር ስራቸው ምን ትቶ አለፈ? ብሎ ሲጠይቅ ያኔ ግጥም ይከሰትለታል፡፡
በኢትዮጵያ የማህበረሰብ ታሪክ ውስጥ ግጥም በሬና ገበሬ መሃል ይገኛል፤ የለቅሶ ስርአት ላይ ዋና አጋፋሪ ሆኖ ይውላል፡፡ ገበሬዎች ስራቸውን ጉልበት የሚሰጡበት፣ የሚያሞቁበት እንዲሁም የኑሮ መረዳታቸውን የሚናገሩበት ብሂል ነው፡፡ በማህበረሰባችን ገበሬው፣ ማሽላ ጠባቂ እረኛው፣ እንጨት ለቃሚ ልጃገረዶች ግጥምን የሚቀባበሉበት፣ የሚሞጋገሱበት፣ የሚመራረቁበት መንገድ ነው፡፡ እስኪ ለምሳሌ ብንባል ከገበሬው አፍ ቀበል ብለን ይቺን ግጥም እንይ፡-
ና ውጣ ና ውረድ ሲል እየሰማሁት፣
የጠመደበትን ስፍራውን አጣሁት
የለቅሶ ላይ ግጥሞች አላማቸው ለቅሶውን ማሞቅ፣ ተጨማሪ እንባን መጋበዝ ቢሆንም የሚጮሁት ሀቅ ሲመረመር ግን ሰፋ ብሎ ይገኛል፡፡ አስለቃሾች (አሟሾች) የለቅሶውን ስርአት በመምራት ትልቅ ሚና አላቸው፤ የሚቋጥሩት ግጥም እንደ ሞተው ሰው ይለያያል። ልጅ የሞተ ለት፣ ወጣት ያረፈ ለት፣ አዛውንት ይቺን ዓለም የተሰናበተ እለት፣ ጀግና አፈር የቀመሰ እለት የሚያውርዱት ግጥም ይለያያል፡፡ ልጅ የሞተ እለት ከሚባሉቱ ውስጥ ለአብነት፡-
ከላይኛው አምላክ ይሻላል ገበሬ
እሸቱን አያጭድም ሳያፈራ ፍሬ
ይህ ግጥም የመለኮት ስራው ይጠየቅበታል፤ አሳይተህ ለምን ትነሳለህ የሚል ፈጣሪን የመገዳደር መንፈስ ይስተዋልበታል፡፡ እንዲህ ያሉትን ተገዳዳሪ ወይም ሰፊ ፍልስፍናዊ ጥልቀት ያላቸውን ስንኞች  ለመቋጠር ምን አልባት አብሮ የሚወለድ ተፈጥሮ ያበረታ ይሆናል፤ ቢሆንም በሚጠይቁት፣ በሚመሰጡት፣ በሚታመሙት መጠን ይሰናኛል። በማህበረሰባችን ውስጥ መሸነፍን፣ ድል ማድረግን፣ መራብን፣ መጥገብን፣ ባይተዋርነትን፣ እንዲሁም የነፍስና ስጋን ትግል የሚናገሩ ግጥሞች እናገኛለን፡፡ ይህንን እውነት ለማለት ይህንን ስንኝ ልብ እንበል፡-
ሰው መሆን ሰው መሆን ሰው መሆን ከበደኝ
ከላይ ቤት አልሰራሁ ከታች አልተመቸኝ፣
እኒህና መሰል ግጥሞች ኢትዮጵያኖች ሲከፋቸው ተበደልን፣ ለፍተን ከሰርን ሲሉ በቃላቸው እንዲሁ የታመሙትን የልባቸውን ሳይሰስቱ የሚቋጥሩት ነው፡፡
ደበበ ሰይፉ፣ በታሪካችን ደመቅ ብለው ከምናገኛቸው ባለቅኔዎቻችን አንዱ ነው፡፡ ደበበ ለግጥም ስስ ነው፤ ግጥሞቹ ልበ ደንዳናውን ያባባሉ፣ ዐይኑ እንባ እንዲያቀር ያደርጋሉ፣ የሀገርን ጉዳይ ያገናሉ፣ የማህበረሰብ ሀቅን ያጎላሉ፣ ፍቅርን ይጨነቁበታል፡፡ ደበበ ሁለት የግጥም መድበሎችን ማለትም  የብርሃን ፍቅር ቅፅ 1 እና ቅፅ 2 አሳትሟል፡፡ በውስጣቸውም፤ እሰይ ብለን የምንደሰትባቸው፣ ህመማችንን ታመምህልን የምንልባቸው ግጥሞች፤ ስለ ሰው፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ህይወት፣ ስለ ሀገር፣ ስለ ተስፋ፣ ስለ አንድነት ወዘተ… ገጥሟል። ግጥሞቹ ያስደስቱናል፣ ያስለቅሱናል፤ ያሳምሙናል ይፈውሱናል፤  ያፈላስፉናል፣ ጭው ያለ ዝምታ ውስጥ ይከቱናል፡፡
ደበበ እጅግ የላቀ ገጣሚ ነው፡፡ የግጥሞቹን ጥልቀት፣ የሀሳባቸውን ልኬት፣ የታሪካቸውን ስፋት፤ የሚያነሱትንና የሚጠይቁትን ስንመረምር ሳናስበው ኮርኮም የሚያደርግ፣ ደርሰን እንባ እንድናወርድ፣ እንድንጠይቅ፣ እንድናፈቅር ያደርገናል፡፡ ስለ ሀገር ሲፅፍ፣ ታሪክን መሰረት አድርጎ፣ የህዝቦችን መስተጋብርና የባህሎችን አይነት ትርጉም ሰጥቶ ውብ ያደርገዋል፡፡ የደበበ ግጥሞች ለየት የሚያደርጋቸው አይደበቁም፣ የቃላት አመራረጡ በቀላሉ እንዲገቡን የተለኩ ናቸው፡፡
ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ ስለ ኢትዮጵያ የኑሮ እውነት፣ በህመም ውስጥ ስለሚያልፍ ታሪክ፣ በችግር ስለ ሚፈተን አንድነት የቋጠረው ነው፡፡ ስንኞቹ የሚናገሩት ችግርን አብሮ ስለ መቸገር፣ ይሉኝታ፣ ተርቦ የመጣን ስለ ማጉረስ፣ ተቸግሮ የመጣን በወጉ መርዳት ምን ያህል ህመም እንደሚሆን፣ ምን ያህል እንደሚያስጨንቅ ይናገርበታል፡፡
ትግራይ ላከ ወሎ ጋ አበድረኝ ብሎ አንድ
ቁና ጤፍ
ወሎም አፈረና የለኝም ማለቱን ባህሉን መዝለፍ ቆሌውን መንቀፍ
በግጥሙ ውስጥ የሚንከራተተው ከትግራይ ተነስቶ ሸዋ እስከ ሐረር የሚደርሰው የኢትዮጵያ ህመም ነው፡፡ የወሎው መታመም ለሐረሬውም ህመሙ፣ የትግራዩ መቸገር ለባሌው መቸገሩ እንደሆነ የሚናገር ግጥም ነው፡፡ ግጥሙ በያንዳንዱ ማህበረሰብ ውስጥ ስላለው ባህል፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ  ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ስለሚገኘው፣ ስለሚያተሳስረው የባህል መንፈስ፣ አለፍ ሲልም  የስነ-ልቦና መገናኘት አልፎም የታሪክና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጮክ ብሎ ይናገራል፡፡  
በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ወደ ጎጃም ብንሄድ፣ በዚህ በኩል ወደ ባሌ ብንዘልቅ፣ ወደ ጋሞም ጎራ ብንል ተቸግሮ የሰው ፊት ማየት ጭንቅ ነው፣ የራበውን ኩርማን መስጠት አለመቻል የሚያስጨንቅ ሀቅ ነው።  ይህንን ሀቅ ደበበ እንዲህ ሲል በስንኝ ገልፆታል፡-
ሸዋም አፈረና የለኝም ማለቱን  ወደ ሐረር ዞረ
ሐረርም መልሶ ባሌን አተኮረ
ባሌም ወደ አርሲ፣ አርሲም ሲዳሞን
ሲዳሞም ተክዞ፣ ግን የለኝም ብልስ ማን
ያምነኛል ብሎ
ወደ ጋሞ ላከ አቁማዳ ጠቅሎ፡፡
በግጥሙ ውስጥ፤ ችግር የማይፈትነው፣ ማጣት መታረዝ የማያላላው መተሳሰብ ይታያል። ግጥሙ፣ ባህልን ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከሰሜን ተነስቶ እስከ ደቡብ፣ በምስራቅም በምዕራብም ኢትዮጵያኖች ያላቸውን የባህል መስተጋብር፣ የልባቸውን፣ እንዲሁም የሚኖሩትን እውነት በስንኞቹ እያንዳንዳቸውን  ያናግራቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ በጎና አስከፊ ታሪኮችን አልፋለች፡፡ ረሀብና የእርስ በእርስ ጦርነት በየጊዜው የሚፈትኗት ነገሮች ናቸው። ታሪክ እንደሚነግረን፤ ኢትዮጵያኖች በተለያየ ዘመን በተለያየ ችግር ተፈትነዋል፡፡ በደበበ ግጥም ውስጥ ያለችው ኢትዮጵያም የሚፈትናት ረሀብ ነው፡፡ በዚያው ልክ የትግሬው ህመም የሸዋውን ሲያመው፣ የባሌው ችግር ሐረሬውን ሲቸግረው፣ የወለጋው ማጣት ጎጃምን እንደሚያስደነግጠው ግጥሙ ይናገራል፡፡
ደበበ፣ በስንኞቹ ከትግራይ ተነስቶ፣ ሸዋ ዘልቆ፣ በባሌ አሳብሮ፣ ሐረር ዘልቆ ይመለሳል። ኢትዮጵያኖች የሚሳሱለትን የመተሳሰብ ባህል፣ የሚያበዙትን አንተ ትብስ ይትበሀል፣ የሚኖሩትን ኑሮ በግጥሙ ይብሰለሰልበታል። ግጥሙ ማእከል ያደረገው በረሀብ መፈተን ቢሆንም ታሪክን፣ ዘመኑ የሚመስለውን፣ በየጥጉ ያሉ የማህበረሰብ ክንዋኔዎችን አቢይ ትኩረት ሰጥቷቸዋል፡፡
የግጥሙ መሠረታዊ ጭብጥ ተፈትኖ ስለሚያልፍ ታሪክ ነው፡፡ ገጣሚውን እጀግ የሚያብሰለስለውም ማህበረሰቡን የሚያንገላታው የዘመን ቅርሻ፣ የሚፈትነው ማጣት እንዲሁም የመንፈስ ትስስራቸው ነው፡፡ ለዚያም ነው እንዲህ ሲል የቋጠረው፡-
እኔና ወንድሞቼ ሁላችን….ሁላችን
ከባዶ አቁማዳ ነው የሚዛቅ ፍቅራችን
ይህ ነው አንድነታችን
ይህ ነው ባህላችን
ዘመን ማዛጋቱ በያንደበታችን፡፡
ጠቅለል ስናደርገው፣ ደበበ በግጥሙ ታሪክን፣ ባህልን፣ ማጣትን፣ መፈተንን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን ውብ በሆነ የቃላት ምርጫና አደራደር ትናንት ኢትዮጵያኖች የተፈተኑትንና ያለፉትን የመከራ ታሪክ የሚዳስስ ነው፡፡  


Read 792 times