Sunday, 29 November 2020 15:11

ምዕራፍ አንድ፡ እንደገና…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 “ቋ..ቋ..ቋ…” ከአለቃዬ ቢሮ እንደወጣሁ፣ ኮሪደሩ ላይ የሂል ጫማ ድምፅ ተቀበለኝ። ድምፁን ወደሰማሁበት ቀና ብዬ ተመለከትኩ። ፈዘዝ ያለ ቢጫ ቦዲ፣ በጥቁር ጨርቅ ሱሪ፣ የሚያምር የሰውነት ቅርፅ፣ በረጅም ሂል ጫማ የተጫማች ልጅ ወደኔ አቅጣጫ እየመጣች ነው። ከአለቃዬ ቢሮ፣ የኔ ቢሮ ሩቅ የሚባል አይደለም። የጎረምሳ ነገር ልጅትዋን በቅርበት ሳያት ወደ ቢሮዬ መግባት አልፈለኩም። እንድትደርስብኝ እንደ ኤሊ ተጎተትኩ። አልተሳካም! ቢሮዬ በር ደረስኩ። ይሄኔ የሚመጣው ሰው ማልፈልገው ሆኖ እንዳላየ ለመግባት ብጣደፍኮ ኖሮ…። መጠበቅ አለብኝ። ከአለቃዬ የተቀበልኩትን ወረቀት፣ የቢሮዬ በር ላይ ቆሜ ማንበብ ጀመርኩ።
“ሄይ! አዲሱ ስታፋችን?” እጇን ዘረጋችልኝ…
“አዎ! ያቤዝ እባላለሁ።” እጇን ጨብጬ፣ ከላይ እስከ ታች በዐይኔ እየዳበስኳት።
“ማሂ ቆንጆ እባላለሁ-”
“እመሰክራለሁ! በጣም ቆንጆ ነሽ!”
“ኪ…ኪ…ኪ…አመሰግናለሁ። እንኳን ደህና መጣህ። በስርዓት አቀባበል እናደርጋለን# ብላ፣ የቆምኩበት ትታኝ፣ ወደ አለቃዬ ቢሮ መሄድ ጀመረች።
“አመሰግናለሁ…!“ እልኩ፣ የጀርባ ውበቷን ለማረጋገጥ ካንገቴ ዞሬ በዐይኔ እየተከተልኳት። ትንሽ እንደተራመደች እያየኋት እንደሆነ ለማረጋገጥ ይመስል፣ ድንገት ዞር ስትል ዐይን ለዐይን ተጋጨን። ወደ ቢሮዬ ተስፈንጥሬ ገባሁ። ሃሳቤ ግን ተከትሏት ሄዷል። ውበቷ ሙጫ ነው፣ ተጣብቆ የሚቀር። ማራኪ ነች። በዛ ላይ በደንብ ተኳኩላለች። ቢሆንም ፣ ሲፈጥራትም ልቅም ያለች ቆንጆ ነች። ሃም…፣ ጥሩ ጥቅማ ጥቅም ያለው አሪፍ መስሪያ ቤት ነው የገባሁት። ይሄንን ቢነግሩኝ ኖሮ፣ መች ደሞዙን እንደዛ እጨቃጨቃቸው ነበር። ምን ክፍል ይሆን እምትሰራው…?
ቢሮዬን ዝም ብዬ ተመለከትኩት። የሰለቸው የወንደ ላጤ ቤት መስሎ ተዝረክርኳል። እዚህ ቢሮ ውስጥ በቀን ስምንት ሰዓት መቆየት በራሱ ያደክማል። የጠረጴዛና ወንበሮቹ አቀማመጥ በዘፈቀደ ነው። ማስተካከል ጀመርኩ። ለስራ በሚመቸኝና ቢሮው የተሻለ እይታ እስኪኖረው መላልሼ አዟዟርኳቸው። እማልፈልጋቸውን ወረቀቶች አስወገድኩ፤ ያስፈልጋሉ የምላቸውን፣ በየዘርፍ በየዘርፍ አድርጌ፣ ፋይል ውስጥ አስቀመጥኳቸው። ስሰራ ሃሳቤ እንዲሰረቅ አልፈልግም። ቢሮ ውስጥ ያሉ ኮተቶችና ምስቅልቅሎች ሃሳብን ያናጥባሉ። በነጻነትና በትኩረት ስራዬን ለመስራት፣ በምችለው መጠን ቢሮዬን ስርዓት ያለውና ነፃ አደረኩት። ይህ በቀደሙት መስሪያ ቤቶቼም የምከውነው የመጀመሪያ ቀን ተግባር ነው። ጎንበስ ቀና ያልኩበት፣ እቃዎቹን የጎተትኩበት ድካም ተሰማኝ። እርጅና ሊመጣ ነው። ትንፋሽ ለመውሰድ ወንበር ላይ አረፍ አልኩ። ሰዓቴን ስመለከት የሻይ ሰዓት ደርሷል። ከሻይ በኋላ የቀረውን አስተካክለዋለሁ ብዬ እያሰብኩ፤
“ጤና ይስጥልኝ!...” ብለው አለቃዬ ወደ ቢሮዬ ገቡ። እጄን ጨብጠው ሰላምታ ተለዋወጥን። አለቃዬ መልከ መልካም፣ እድሜያቸው ጎልማሳነትን የዘለለ ይመስላሉ።
“እንኳን ደህና መጡ!”
“ደግሞ ከመቼው ቢሮውን እንዲህ አሳመርከው…?፣ ይሄ ቢሮ እንዲህ ያምር ነበር እንዴ…?” በፈገግታ ጥርሳቸውን ፈልቀቅ አድርገው።
“እንዲመቸኝ ትንሽ ነው የነካካሁት”
“ሌላ ቢሮ አስመስለህ አሳምረኸዋል እንጂ። አይ ወጣት! መቼም ውበት ትወዳላችሁ! በል ና አሁን ቡና ልጋብዝህ፤ በዛውም ስታፎቻችንን ላስተዋውቅህ፤” ብለውኝ ከቢሮዬ ወጡ።
“እሺ!” ብዬ ቢሮዬን ቆልፌ ተከተልኳቸው።
ካፍቴሪያ ስንደርስ፣ ክብ ሰርተው እየተንጫጩ ሻይ ቡና የሚጠጡ ሰዎች ጋር ወስደው ቀላቀሉኝ። እየጮሁ ያወራሉ፤ እየጮሁ ይሳሳቃሉ። ይህ የግቢው አውራ ቡድን እንደሆነ ሁኔታቸው ይናገራል።  እየተሽቀዳደሙ ያወራሉ፤ ከፍ አድርገው ይስቃሉ፤ ያሽካካሉ፤ ሌላ ሰው ይሰማናል፣ እንረብሻለን፣ ምን ይሉናል የሚሉት ነገሮች እሚያሳስቧቸው አይመስሉም።
“ጎበዝ! አዲሱ አድሚናችንን ትተዋወቁት ዘንድ ይዤው መጥቻለሁ። ያቤዝ ይባላል። እናንተ ደግም እራሳችሁን አስተዋውቁት፤” ብለው ወንበር ስበው ተቀመጡ። ጫጫታቸውን አቁመው፣ ፀጥ ብለው ካዳመጡ በኋላ፣ አንድ ላይ፣
“እንኳን ደህና መጣህ! ዌል ካም!" ብለው አልጎመጎሙ። አራት ሴትና ሶስት ወንድ ናቸው። ሴቶቹ ወጣትና ቆነጃጅት ሲሆኑ፣ ወንዶቹ በእድሜ ከፍ ከፍ ያሉና፣ ሙሉ ሰውነት ያልደረሱ ጎልማሶች ናቸው።
ከሁሉም ወንዶች በእድሜ ወጣት እንደሆንኩ ተሰማኝ። እየዞርኩ እየጨበጥኩ መተዋወቅ ጀመርኩ…።
“ ኤፍሬም ፣ እንኳን ደህና መጣህ!”
“ማሂ ቆንጆ፣ ቅድም ተዋውቀናል!”
“ሳሚ፣ እንኳን ደህና መጣህ!”
“ቤቲ፣ እንኳን ደህና መጣህ!”
“ግርማ፣ እንኳን ደህና መጣህ!”
“ፌቨን፣ እንኳን ደህና መጣህ!”
“ሜሪ፣ እንኳን ደህና መጣህ…!”
ሁሉም በፈገግታና አክብሮት በተሞላ ሁኔታ ሰላምታ ሰጥተው ተዋወቁኝ። ሳምሶን ከጎኑ እንድቀመጥ ወንበር ስበር ጋበዘኝ። አስተናጋጇ ስትመጣ፣ እንደኔ ጠቆር ያለ ማኪያቶ ብዬ አዘዝኩ። ሴቶቹ ዞር ብለው የፊት ቀለሜን ተመለከቱ። እኔም እንደዛ ብዬ ያዘዝኩት ይሄን ፈልጌ ነበር።  ወደ ጫጫታቸው ተመለሱ። እኩል እየጮሁ ያወራሉ። ማንን ማዳመጥ እንዳለብኝ ግራ እስኪገባኝ ይሽቀዳደማሉ፤ ይበሻሸቃሉ፤  በጣም ይስቃሉ፤ ፊታቸው ላይ የሚነበበው ደስታና እርካታ ያስቀናል። ማሂ ቆንጆ በጣም ታወራለች። ትስቃለች። በየመሃሉ በዐይኗ ተጫወት ትለኛለች። አለቃዬ እየተሳሳቁ ትንሽ ከተጫወቱ በኋላ፣ “በሉ አስለምዱት!” ብለው ተነስተው ወደ ቢሮ ሄዱ። አሪፍ መስሪያ ቤት እንደገባሁ ሁለት ማስረጃዎች አገኘሁ፤ ደስ የሚል አለቃና ፍቅርና እርካታ የተሞሉ ሰራተኞች። አለቃማ እንደዚህ ነው፤ ለሰራተኞቹ ያለው ቀረቤታና አክብሮት እሚያስቀና ነው። በውስጤ “ዋ..ው! ፀዴ  መስሪያ ቤት ነው የገባሁት” አልኩኝ። ከቀድሞው መስሪያ ቤቴ ጋር አነጻጽሬ ውስጤ በደስታ ሞቀ። እዚህ ፍቅራቸው የሚያስቀና፣ በመስሪያ ቤታቸው ደስተኛ የሆኑ፣ በመልክ ተመርጠው የተቀጠሩ የሚመስሉ፣ የውብ ሴቶች ጥርቅም!! ያወራሉ፤ ይስቃሉ፣ በየመሃሉ “ተጫወት!” ይሉኛል። ቀስ ብዬ የሴቶቹን የግራ እጆቻቸውን ተመለከትኩ። ጣቶቻቸው ላይ ቀለበት የለም። “ያብ… ከእነዚህ ውስጥ ሚስት ካላገኘህ፣ መቼም አታገኝም! ብዬ ወደ ውስጤ አንሾካሾኩ።
(ከዶ/ር መለሠ ታዬ "የታካሚው ማስታወሻ" አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2636 times