Sunday, 29 November 2020 15:15

የዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

   ‹‹በመንግሥተ ሰማይ አብረን ኳስ እንደምንጫወት ተስፋ አደርጋለሁ።›› ፔሌ
በእግር ኳስ ዘመኑ በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከ500 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል። 311 ጎሎችን በክለቦች ሲጫወት 34 ደግሞ ለአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ከመረብ አዋህዷል ‹‹የአርጀንቲና ደጋፊዎችን ልዩ የሚያደርጋቸው ቡድናቸው ጎል ሲያገባም፤ ሲገባበትም በማልቀሳቸው ነው፡፡››


               በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አርጀንቲናዊው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና በ60 ዓመት ዕድሜው በልብ ችግር የተነሳ በሞት መለየቱ መላውን ዓለም አሳዝኖታል፡፡ በወሩ መግቢያ ላይ በአንጎሉ ውስጥ  የደም መርጋት አጋጥሞት የተሳካ ቀዶ ሕክምና አድርጎ ነበር፡፡ ከአልኮል ሱስ እንዲላቀቅም ተከታታይ ሕክምና ሲደረግለት ቆይቷል፡፡ የአርጀንቲና መንግስት ከሞቱ በኋላ ለ3 ቀናት በመላው አገሪቱ ሃዘን ሆኖ እንዲታሰብ ያወጀ ሲሆን፤ የአገሪቱ እግር ኳስ ማኅበር ባወጣው መግለጫ “በጀግናችን ሞት በጣሙን አዝነናል፤  ሁልጊዜም በልባችን ውስጥ ትኖራለህ” ብሏል።
በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ዘመን የማይሽረውን ስብዕና ተጎናፅፎ የኖረው ማራዶና፤ በኮከብ ተጫወችነት እና በዋና አሰልጣኝነት ስፖርቱን አገልግሏል፡፡ የ21ኛው ክፍለዘመን ምርጥ ስፖርትኛ ተብሎ የመጀመርያውን የክብር ስፍራ ከብራዚላዊው ኤዲሰን አራንተስ ዶናሺሜንቶ ፔሌ ጋር ተጋርቷል፡፡ ከወር በፊት 80ኛ  ዓመቱን የደፈነው  ፔሌ በትዊተር ገፁ ላይ ባሰፈረው የሃዘን መልዕክት “ታላቅ ጓደኛዬን አጣሁ፡፡ ዓለምን ታላቅ ባለታሪክ ተሰናበተ፡፡…  ገና ብዙ የሚነገር ታሪክ አለ፣  ለአሁኑ ግን እግዚአብሔር ለመላው ቤተሰቡ  ብርታቱን ይስጣቸው። አንድ ቀን፣ በመንግሥተ ሰማይ አብረን ኳስ እንደምንጫወት ተስፋ አደርጋለሁ።›› ብሏል፡፡
በዓለም እግር ኳስ የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀሰው ማራዶና ዓመታትን ተጫውቶ ጫማውን ከመስቀሉ በፊት በክለብና በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ከ500 በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በክለቦች ሲጫወት 311 ጎሎችን በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን 34 ግቦችን ከመረብ አዋህዷል፡፡  በመላው ዓለም ስሙ ሊገን የበቃው በተለይ በ1986 እኤአ ላይ ሜክሲኮ ባስተናገደችው የዓለም ዋንጫ ላይ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን የዓለም ዋንጫ ባለቤት እንድትሆን ቡድኑን በአምበልነት እየመራ፤ በድንቅ ችሎታውና  የኳስ ጥበቡ ታሪክ በመስራቱ ነበር፡፡ በተለይ አርጀንቲና ከእንግሊዝ ጋር ባደረጉት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ላይ እሱ “የእግዜር እጅ” ያላትና ዳኞች ሳያዩ በእጁ ያስቆጠራት ግብ ዝንት ዓለም የምትታወስ ይሆናል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስም ለሚታወቁት ለስፔኑ ባርሴሎናና ለጣሊያኑ ናፖሊ ክለቦች በመጫወት በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ላይ በዝውውር ገበያ፤ በስፖንሰርሺፕ እና በሚዲያ ሽፋን በሚያገኛቸው ትኩረቶች በርካታ ፈርቀዳጅ ታሪኮችን የሰራ  ነበር።
በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ማሊያ በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ የተሳተፈው ማራዶና  እግር ኳስን ያቆመው ከ23 ዓመት በፊት በ37 ዓመት ዕድሜው የነበረ ሲሆን ወደ አሰልጣኝነት ሙያው በመግባት በመጀመርያ የአርጀንቲና ክለቦችን ካሰለጠነ በኋላ የአገሩን ብሔራዊ ቡድንንም በዋና አሰልጣኝነት በመምራት በ2010 እኤአ ላይ በተካሄደው የደቡብ አፍሪካው 19ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ተሳትፏል፡፡   በአሰልጣኝነት ሙያው  በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና በሜክሲኮ ሊሰራም ችሏል፡፡
የአርጀንቲና ደጋፊዎች ልዩ ትውስታ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ራሽያ
ከ2 ዓመት በፊት 21ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመዘገብ በአስተናጋጇ አገር ራሽያ ውስጥ ነበርኩኝ።  በወቅቱ በቀጥታ ለመመልከትና ለመዘገብ ከቻልኩባቸው 15 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች መካከል  ሶስቱ አርጀንቲና የተጋጠመችባቸው ናቸው፡፡ በመጀመርያው ከአይስላንድ ጋር በሞስኮው ሉዚሂንኪ ስታድዬም ተካሂዶ 0ለ0  ተለያዩ። በሁለተኛው ደግሞ ከክሮሽያ ጋር በኒዚሂኒ ኖቭጎሮድ ስታድዬም ተጋጥመው 3ለ0 ተሸነፉ።  3ኛውና የመጨረሻው ደግሞ ከናይጄርያ ጋር በሴንትፒተስበርግ ተፋጥጠውበት 2ለ1 በማሸነፍ ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል። በ3ቱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ከአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን፤ ደጋፊዎች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጋር በተደጋጋሚ እየተገናኘን ብዙ ሁኔታዎችን አሳልፈናል፡፡ የማራዶና ወሬ፤ ምስል፤ ታሪክ እና ሌሎች ነገሮች ሳያሰለቹን በተደጋጋሚ በየከተሞቹ አንስተናቸዋል፡፡ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንና ደጋፊዎቹ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ ድምቀት  ነበሩ፡፡ በሶስት የተለያዩ የራሽያ ከተሞች ስዘዋወር በስታድዬም ውስጥ እና ዙርያ ባሻገር፤ በባርና ሬስቶራንቶች፤ በከተማና በአገር አቋራጭ ባቡሮች ወደተለያዩ ከተሞች በባቡር ስጓዝ ያነጋገርኳቸው አርጀንቲናዊያን የዓለም ዋንጫን እንደባህል ያደረጉ ህዝቦች መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ ማራዶና ዋናው ምከንያት ነበር። 20ኛውን የዓለም ዋንጫ ለመታደም 17.4 ሺ ኪሎ ሜትሮች በላይ አትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥና በትራንዚት ከ40 ሰዓታት በላይ በሚወስዱ የአውሮፕላን በራራዎችን በማድረግ ራሽያ የገቡት አርጀንቲናውያን ከ30 ሺ በላይ ይሆናሉ፡፡
በራሽያ ውብ ከተማ ከሴንት ፒተርስበርግ ያገኘሁት ጆርጌ ቦሲ የተባለ አርጀንቲናዊ እንዳወጋኝ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ብሄራዊ ቡድናቸውን እስከ ፍፃሜ እንደሚጓዝ ተስፋ ሰንቀው ከላቲን አሜሪካ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡  የዓለም ዋንጫ ድል ከማራዶና በኋላ እጅግ ናፍቋቸው ስለነበር ቡድናቸውን ተማምነውው  በራሽያው የዓለም ዋንጫ ቢያንስ እስከ 20 ቀናት ለመቆየት  በነፍስ ወከፍ ከ5ሺ እስከ 8ሺ ዶላር በጀት አውጥተዋል። ጆርጌ ቦሲ በምግብ፤ በመጠጥ እና በተለያዩ የሽቶ ምርቶች የሚያገለግሉ መዓዛዎችና ቅመሞችን በሚያመርት የስዊዘርላንድ ኩባንያ የሚሰራ ነው። ከሙያ ባልደረባው ጋር በራሽያ የተገኙት በሜሲ ዘመን የዓለም ዋንጫን ድል ለማጣጣም  ነበር፡፡
የአርጀንቲናን ደጋፊዎች በየስታድዬሙ Vamos Argentina በሚለው ዝማሬያቸው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ በተደጋጋሚ ሳይሰለቸኝ ሰምቻቸዋለሁ። ደጋፊዎቹን ልዩ የሚያደርጋቸው ቡድናቸው ጎል ሲያገባብ ሲገባበትም በማልቀሳቸው ነው፡፡
ክዝማሬያቸው በአንዱ ላይ
"እንደምንወዳችሁ ታውቃላችሁ፤ ለዋንጫው ድል ያለን ሁሉ እንሰጣለን… ማራዶናና ሜሲ የእኛ ናቸው፡፡ ወደራሽያ መጥተናል፤ የምንመለሰው ዋንጫውን ይዘን ነው…. እያሉ ነው የሚዘምሩት። በሌሎች ዝማሬያቸው… ሻምፒዮን መሆን እንፈልጋለን፤ እ ነሜሲ እንደሚያሳኩትም ተስፋ እናደርጋለንም እንደሚሉ በትርጉም ተገልፆልኛል፡፡
አርጀንቲናውያኑ በዝማሬያቸው በስታድዬም ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአውራ ጎዳናዎች፤ በአደባባዮች፤ በባቡር ጣቢያዎች በሌሎች ስፍራዎች የማራዶናን ጀግንነት እና የማይረሳ ጀብዱ ከሚያወጋቸው ጋር ያነሳሉ፤ በዙርያቸው ላለ ሁሉም ይሰብካሉ። ለማራዶና ጤንነትና ለመልካም ደህንነቱ መልካም ምኞታቸውን በህብረት በመዘመር ድጋፋቸውን ሲገልፁ ኖረዋል።
አርጀንቲና በዓለም ዋንጫ ከማራዶና
በፊት እና በኋላ
በ1978 እ.ኤ.አ ላይ 11ኛውን  የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ እድል ያገኘችው አርጀንቲና ነበረች። በ1ኛው ዓለም ዋንጫ ለፍፃሜ ጨዋታ ደርሳ ዋንጫውን በኡራጋይ ከተነጠቀች ከ48 ዓመታት በኋላ መስተንግዶውን ያገኘች ሲሆን፤ ወደ እግር ኳስ ሃያልነቷ ለመመለስ የበቃችበት ነበር፡፡  በዓለም ዋንጫው ዋዜማ አርጀንቲናን ያስተዳድር የነበረው መንግስት በመፈንቅለ መንግስት ተገልብጦ አምባገነኑ መሪ ጄኔራል ቪዴላ ስልጣን መያዛቸው ነበር፡፡ ስለሆነም የዓለም ዋንጫው መሰናዶ በጄኔራል ቪዴላ መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰትና በአምባገነናዊ ስርአቱ ከበርካታ አገራት ተቃውሞ የተሰነዘረበት ነበር፡፡ የዓለም ዋንጫ ድልን ለመጀመርያ ጊዜ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ለፍፃሜ ጨዋታ የቀረቡት አርጀንቲና እና ሆላንድ  ነበሩ። የፈረንሳዩ ለኢክዊፔ ጋዜጣ እና ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃናት አስቀድመው ከተደረጉት 10 የዓለም ዋንጫዎች ምርጡ የፍፃሜ ፍልሚያ ብለውታል፡፡ አርጀንቲና 3ለ1 በሆነ ውጤት ሆላንድን በማሸነፍ  በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ድል አግኝታለች፡፡ በወቅቱ የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሴዛር ሜኖቲ ናቸው፡፡ ከቡድናቸው የ17 ዓመቱን ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና መቀነሳቸው አስተችቷቸው ነበር፡፡ ይሁንና ዓለም ዋንጫው ከተጀመረ በኋላ ቡድናቸው የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የተከተለው ውበትን የተላበሰ አጨዋወት  በዋንጫ መቋጨቱ አድናቆት አትርፎላቸዋል፡፡ለ17 ዓመቱ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶንም ድሉ ከፍተኛ ጉጉት ያሳደረበት ሆነ። ከማራዶና በፊት በነበረው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ከተጨዋቾች የሚጠቀሱት አምበሉ ዳንኤል ፓሳሬላ እና ማርዮ ኬምፐስ የተባለው አጥቂ ነበሩ። የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ማርዮ ኬምፕስ በአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ከነበሩ  ተጨዋቾች መካከል  በፕሮፌሽናልነት በስፔን ላሊጋ ለሚወዳደረው ሻሌንሺያ ክለብ በመጫወት የመጀመርያው ሲሆን አርጀንቲናውያን በአውሮፓ እግር ኳስ ለሚኖራቸው ገበያ ፈር የተቀደደበት ነበር።
13ኛው የዓለም ዋንጫ በ1986 እ.ኤ.አ ላይ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ ዞን የምትገኘው ሜክሲኮ  ያስተናገደችው ነበር፡፡  ይህ ዓለም ዋንጫ በመስተንግዶ ው ማራኪነት፤ በስታድዬሞች በታየው ‹‹ሜክሲኳውያን ማዕበል›› የተባለው ድጋፍ አሰጣጥና በአርጀንቲናዊው ኮከብ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና  የላቀ ችሎታ የማይረሳ ሊሆን በቅቷል፡፡ በፍፃሜ ጨዋታ የተገናኙት አርጀንቲና ከምእራብ ጀርመን ጋር ነበር፡፡ ከ115ሺ በላይ ተመልካች ባስተናገደው ታላቁ አዝቴካ ስታድዬም የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ 2ለ2 በሆነ ውጤት እስከ 83ኛው ደቂቃ ቆየ፡፡  ማራዶና ለቡድን አጋሩ ጆርጌ ቡርቻጋ አመቻችቶ ያቀበለው ምርጥ ኳስ አማካኝነት  የማሸነፊያ ጎል ተመዘገበችና በአርጀንቲና 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ከ30 ሚሊዮን በላይ አርጀንቲናውያንም በድሉ ፌሽታ መላው አገራቸውን በደስታ አጠልቅልቀው ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ፔሌን ያስበልጣሉ
ከዛሬ 34 ዓመታት በፊት ነው፡፡  13ኛው የዓለም ዋንጫ በሜክሲኮ እየተካሄደ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫው በወቅቱ  ከተነተኑት መካከል ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የሚገኙበት ሲሆን ጥያቂያቸውን ለማቅረብ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በሚሰራጭ ፕሮግራም ላይ 10 የስፖርት ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡ ደምሴ ዳምጤ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ግርማ ሰይፉ ከአዲስ ዘመን፤ በሃይሉ አስፋው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ኢብራሂም ሃጂ ከበሪሳ ጋዜጣ፤ ሰለሞን ገብረእግዚአብሕር ከኢቲቪ፤ ይንበርብሩ ምትኬ ከኢትዮጵያ ሬድዮ፤ ሃድጉም መስፍን ከዓልአለም ጋዜጣ፤ ገዛህኝ ፄዮን መስቀል ከኢዜአ እና አዋያዩ ፀጋ ቁምላቸው ነበሩ፡፡
90 ደቂቃዎችን በፈጀው መግለጫ ላይ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ
ከፔሌና ከማራዶና የቱን ያደንቃሉ? የሚል ነበር፡፡ ክቡር ይድነቃቸው ምላሽ ሲሰጡ ‘’አንድ ያልገባችሁ ነገር ፔሌን አናውቀውም ስትሉ እራሳችሁን ልጅ ማድረጋችሁ ነው? ወጣት ነኝ ለማለት ካልፈለጋችሁ በቀር ፔሌ ሲጫወት አይታችሁታል፡፡”
“ማራዶና በአሁኑ ትውልድም እንደምናየው ጥሩ ተጫዋች ነው ግን ግራኝ ነው”
ብለው ማስረዳታቸውን ሲቀጥሉ ማራዶና እና ፔሌን ማወዳደር በእጅጉ እንደሚከብድ አመልክተው ነው፡፡ ፔሌ  በሁለቱም እግሮቹ እንደሚጫወት፤ ሰውነቱም የተደላደለ እንደሆነና ኳስን የመቆጣጠር ብቃቱ በጣም የተሻለ መሆኑን ክቡር ይድነቃቸው አስረድተው፤ማራዶና ብዙ ጊዜ ኳስን በእራሱ እንደማይነካ ፔሌ በአንፃሩ ብዙ ጎሎችን ያስገባው በጭንቅላቱ ገጭቶ እንደሆነና ፍጥነቱም እንደሚያስደንቅ አብራርተዋል፡፡ ማራዶና ሰባት የኢንግሊዝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱ አለምን ማስደነቁን የጠቀሱት ይድነቃቸው ፤ ፔሌ እስከ ዘጠኝ ተጫዋቾችን አብዶ ሰርቶ ማግባቱን  ከ20/30 ጊዜ በላይ እንደደገመው በማንሳትም የፔሌን ብልጫ አስቀምጠዋል፡፡
ሰፊ ሽፋን በዓለም ዙርያ በምስጋና እና አድናቆት
ከማራዶና ሞት በኋላ የዓለም ህዝብ በተለያየ መንገድ ሃዘኑን እየገለፀ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ትልልቅ የሚዲያ አውታሮች፤ ጋዜጦች ፤ መፅሄቶች፤ የኢንተርኔት እና ዲጅታል ህትመቶች  በፊት ሽፋናቸው ላይ አብይ ርእሳቸውን  ለዲያጎ ማራዶና ያደረጉ ሲሆን ሁሉም አድናቆት እና ምስጋና አንፀባርቀዋል፡፡ የእንግሊዙ ታብሎይድ ባጠናከረው ዘገባ በመላው ዓለም ስለማራዶና ከተሰራጩ ዘገባዎች አስገራሚውን ርእስ  የፈረንሳዩ ሌክዊፕ ማድረጉን ጠቅሶ አንጋፋው መፅሄት የፊት ሽፋኑ ላይ ‘God is dead’ ‘ማለቱን አውስቷል፡፡ በመላው አውሮፓ አሜሪካና ኤሽያ አህጉራት፤ ከህንድ እስከ ማሌዥያ ፣ ከናይጄሪያ እስከ ጃፓን ትልልቅ የሚዲያ አውታሮች በማራዶና ምስል እና ስንብታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
የማራዶናን ድርብ ምስል በፊት ገፁ የለጠፈው የስፔኑ ኤልማርካ ከስሩ ያሰፈረው ፅሁፍ ‹‹ዳግም ብወለድ እግር ኳስ ተጨዋች ነው መሆን የምፈልገው፡፡ በድጋሚ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶናን ነው የምሆነው፡፡ ህዝብን ደስተኛ ያደረግኩ ተጨዋች ነኝ ያም ይበቃኛል›› የሚል ነው፡፡ የአርጀንቲናው ላ ናስዮን ጋዜጣ ‹ እናመሰግናለን ሻምፒዮን በሚል ርእስ ዘገባውን ሲያቀርብ የባርሴሎናው ላ ቫንጋርድያ የእግር ኳስ ዓለም አቀፍ ጀግና ብሎ አወድሶታል፡፡ ተወዳጅ ማልያውን 10 ቁጥር  በመጠቀም “ AD10s” በሚል አብይ ርእስ የሰጠው ቱቶስፖርት ሲሆን ኮርዬሮ ዴሌስፖርት በበኩል ዲዬጎ ለዘላለም ይኖራል በሚል አትሟል፡፡ ሌላው የጣሊያን ጋዜጣ  ላጋዜታ ዴሎ ስፖርት በፊት ገፁ ማራዶና የዓለም ዋንጫ ሲስም ከሚታይ ምስል ጋር ‹‹ የእግር ኳሱ አምላክ ሞት›› ብሎ ልዩ ህትመቱን ሲያሰራጭ የፈረንሳዩ ላፓሬስያን በበኩሉ ‹‹ በእግዚአብሄር እጅ›› የሚል ርእስ ተጠቅሟል፡፡
100ሺ ዶላር ብቻ
ማራዶና በ60 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ከእንጡራ ሃብቱ የቀረው 100,000 ዶላር ብቻ መሆኑን የዘገበው ዘኤክስፕረስ ጋዜጣ ነው፡፡በ1984 እና 1991 መካከል ለናፖሊ በተጫወተበት ጊዜ እስከ 37 ሚሊዮን ዶላር ማካበቱንም አውስቷል። በማራዶና ስምና የህይወት ታሪክ ዙርያ በርካታ መፅሃፍት፤ ፊልሞች እና ዘጋቢ ፊልሞች፤ ቪድዮ ጌሞችና ተሰርተዋል፡፡ ከታዋቂ መፅሃፍት መካከል El Diego: The Autobiography Of The World’s Greatest Footballer, Touched by God ; How We won Mexixo ‘ 86 World Cup , Maradona The Hand Of God,  Yo Soy El diego ከፊልሞቹ መካከል ደግሞ hbo የሰራው Diego Maradona እና በተመሳሳይ በብሪታኒያ የተሰራው ዘጋቢ ፊልም ይጠቀሳሉ፡፡

Read 1406 times