Sunday, 29 November 2020 16:13

ሰው፣… መሳይ…. አስመሳይ

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(1 Vote)

 የሰው እውቀቱና ክብሩ፤ በምሳሌና በዘይቤ መናገሩ?
                         
              እምሯችንን የሚያባንኑ፣ በውስጣችን ሃሳብ የሚጭሩ፣ ብርሃን  የሚፈነጥቁ አባባሎች፣ ውድ እንቁ ናቸው፡፡ “የሰው ክብሩ፣ በምሳሌ መናገሩ ነው”  ቢባል  አይገርምም:: “እውን መሳይ” ልብ ወለድ ታሪክ፣ ከእውን የሕይወት ታሪክ በላይ ልቆ ይታየናል -“larger than life” እንዲሉ። የሰውን ሕይወት አጥርቶና አንጥሮ፣ አድምቆና አጉልቶ ማሳየቱ ነው፣ የልብ ወለድ ታሪክ ጥበብነቱ፡፡ የማስመሰል ምትሀቱ፡፡  
ግን፣ “ሰዎች ከሌሎች እንስሳት የሚለያቸው፣ በምሳሌ መናገራቸው ነው” የሚሉም አሉ፡፡” ከምሳሌና ከዘይቤ ውጭ፣ማሰብና መናገር ብሎ ነገር የለም” ብለውም ይሰብካሉ። እንዲህ አይነት ስብከት ፣እርስ በእርስ እየተፋጀ የሚጠፋ፣ አልያም እየተላተመ የሚፍረከረክ ይመስላል፡፡ ነገር ግን፣በችኮላ  ወዲያ ወርውረን፣ እንደዘበት  አጣጥለን ከማለፋችን በፊት፣ለአፍታ፣ አዟዙረን፣ ገልጠን ብናየው አይከፋም፡፡
“ምሰላ” ሞልቶ ተተረፍርፎ! ከጣዕሙ ብዛቱ፡፡ በልብ ወለድ ድርሰት፣በትያትር፣ በቲቪ ድራማና በሌሎች የኪነፅሁፍ ስራዎች የምናጣጥማቸው ምርጥ አገላለጾችን ማስታወስ እንችላለን። አርስቶትል እንዳለው፣ የድርሰት ቋንቋ፣ ከተራ ተርታው አነጋገር የተለየ ማዕረግና ግርማሞገስ የሚጎናፀፈው፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ ነው። ከሁለት ሺ ዓመት በፊት፣ አርስቶተል የተነተናቸው ምሳሌያዊ ዘይቤዎች፣ እስከ ዛሬ ድረስ፣  ምርጥ ማስተማሪያ ሆነው ዘልቀዋል ። ድንቅ ነው። አሁን፣  “ቋንቋ ሁሉ፣ የምሳሌያዊ አነጋገር ነው”  የሚል ፈሊጥ መምጣቱ ነው ችግሩ።
ነገር ሁሉ በምሳሌ ነው?  እንዴት ሊሆን ይችላል? እንየዋ።  እስቲ በዘወትር ወሬና ጽሁፍ ፣ውስጥ ስንት የምሳሌ  ዘይቤ እንደምናገኝ፣  “ለአፍታ እንይ”፡፡
  “ለአፍታ እንይ”? እንይ ስንል፣ ድምጾችንና ቃላትን፣ ሃሳብቦችንን ንግግሮችን፣ በእውን “እንይ” ማለት አይደለም፡፡ መቼም፣ “ለአፍታ” ሲባልም፣ በቀጥታ፣በቃል በቃል፣“ የአንድ ትንፋሽ ጊዜ” ማለት  እንዳልሆነም እናውቃለን ”፡፡
“ለአጭር ጊዜ” ወይም “ለጥቂት ጊዜ ”ለማለት ስንፈልግ …..“ለአፍታ” ብለን እንናገራለን  በምሳሌያዊ  ዘይቤ፡፡ ለነገሩ፣ “አጭር” የሚለው ቃልስ? “አጭር ዛፍ፣ አጭር ገመድ” ስንል፣ ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ከታች እስከ ላይ፣ ወይም ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ፣ “ይበልጣል? ያንሳል?” የሚል ንፅፅርን የሚገልፅ ነው- “አጭር” የሚለው ቃል።
“ጊዜ” ግን፣ ከእንጨትና ከገመድ ይለያል። እንደ ቁስቋስ አይደለም፡፡ በክንድ ወይም በእርምጃ አይለካም። ግን፣ “አጭር ጊዜ”፣ ”ረዥም ጊዜ” በማለት እንናገራለን፡፡  ከቁስቁስ እጥረትና ርዝመት ጋር ማመሳሰል፣ ምሳሌዊ አነጋገር መሆኑ ነው። “ጥቂት ጊዜ”፣ “ብዙ ጊዜ” የሚሉ አባባሎችስ?  “ጊዜ”፣እየተለቀመና በመዳፍ እየተጨበጠ እንደ ጥራጥሬና እንደ ፍራፍሬ  አንድ ሁለት ተብሎ አይቆጠርም። ቢሆንም ግን፣ እንደ ጠጠር የሚቆጠር ይመስል፣  “ጥቂት ጊዜ፣ “ብዙ ጊዜ” እንናለን።
“ጊዜው አይግገፋም!” ይባላል - ጊዜ ጋሪ ይመስል። ጊዜው ይሮጣል! ጊዜ ይመጣል፤ ይሄዳል…. ይባላል፤ ጊዜ- እግር ያበቀለ ይመስል…። “ጊዜው አለፈ፣ ጊዜው ደረሰ” ብለው ሲነግሩን፣… “አለፈ እንዴ? ወዴት በኩል? ደረሰ እንዴ? የታለ?” ብለን አንጠይቅም።
ስራው እንዴት እየሄደልህ ነው? ወይስ ተቋረጠ እየተባለም ይነገራል ስለተንቀሳቃሽ እንስሳና መኪና የምንናገር አይመስልም? በሰይፍ ፍልሚያ ከሁለት ከሶስት የተቆረጠም ይመስላል፡፡
የሠው ቋንቋ  በምሳሌ የተንበሸበሸ ነው ለካ፡፡ “ሃሳብህ የት ደረሰ? ሌላ ሃሳብ መጣልህ? ሃሳብ ብልጭ ይልልሻል? ከሃሳብ አትራቅ። ሃሳብ ሃሳብን ያጭራል። ሕልም ይኑርህ። ግን የሕልም እስረኛ አትሁን።”….. እንላለን፡፡
… ያው … ይሄ ሁሉ ቃል በቃል አይደለም። ስራው ሲውተረተር ሲያዘግም፣ ሃሳብ ሲራመድና ሲተነፍስ፣ ጭረቱና ብልጭታው፣ ርቀቱና ቅርበቱ… በእውን ካላየን ብለን እንነታረክም። ለምን? ምሳሌዊ አባባል እንደሆነ አውቀነዋል ወይም ለምደነዋል።
ሕልም ይኑርህ ሲባልም፣… “የእንቅልፍ ጊዜ ሕልም” ማለት እንዳልሆነ አይጠፋንም። የህልም እስረኛ አለመሆንስ? ከሕልም ማምለጥና መሸሸግ ማለት ነው?  ሕልም ሲባል፣ ማሰሪያ ገመድ ወይም ባለቁልፍ እስር ቤት እንደሌለው ግልጽ ነው። ማብራሪያ አያስፈልገውም።  
እዚህ ላይ ፣ማብራሪያ ሲባል፣ ከአምፖልና ከማብራሪ ማጥፊያ፣ ከሻማና ከክብሪት ጋር ቀጥተኛ  ግንኙነት የለውም- በምሳያዊ ገጽታው እንጂ።
“ግልጽ ነው” ሲለንም፣ የተገለጠ፣ የተገለበ ነገር ለማየት አንጠብቅም። ማወቅንና መገንዘብን፣ በአይን ከማየት ጋር በማስመሰል የተነገረ  ነዋ። “አላማህን አጥብቀህ ያዝ” ስለተባለ፣ በመዳፉ ምንን አጥብቆ ወይም ከምን ጋር አጣብቆ እንደያዘ፣ አክርሮ እንደጨበጠ ለማወቅ፣ እጅ እጁን አንመለከትም።
በእርግጥም፣ የምሳሌ አባባሎች፣ የደራሲዎች ፈጠራ ቢሆኑም እንኳ፣ የአዳሜ ሆነዋል፡፡ በልማድ ወርሷቸዋል። የዘወትር ቋንቋ አድርጓቸዋል። “እርግጥ”፣  “ርግጥ” ሲባል፣ ቃል በቃ የማንተረጉመውም በዚህ ምክንያት ነው። ከመርገጥና ከእርግጫ ጋር ቃል በቃል እናቆራፕውም በምሳያዊ ዘይቤ ነው የምንተረጉመው- የአንድን ሃሳብ እውነተኛነት ለማመልከት። እግር የረገጠው አለት፣ በእውን የሚታይ የሚዳሰስ አለት መሆኑ ያከራክራል?በጭራሽ አያከራክርም፡፡ከዚህ ተጨባጭ ሁኔታ  ጋር ስናመሳስል፣ “የተረጋገጠ እውነት” የሚለውን አባባል እናመጣለን።
አስገራሚ ነው። “የሰዎች ንግግር፣ በምሳሌና በዘይቤ አባባሎች የተጥለቀለቀ ነው” ያስብላል።
“አዲስ አድማስ” የሚለው የዚህ ጋዜጣ “መጠሪያም”፣ ለምሳሌያዊ ትርጉም የተመረጠ እንጂ፣ ከማዶ አማትረን የምንቃኘው ቦታ ለማለት አይደለም። ታዲያ፣ “መጠሪያ” ስንልም፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ መናገራችን  እንጂ፣ ጋዜጣው እንደ ሰው፣ በስሙ ስንጠራው፣ “አቤት” ብሎ እንዲናገር አንጠብቅም። “ተጠርቶ ይምጣ” ብለን ለማዘዝም አንሞክርም።  
“የፖለቲካ  አባባሎች ሳይቀሩ፣  ለምሳሌያዉ ዘይቤ ቤተኛ ናቸው። “ኢትዮጵያና ርምጃዋ” በሚል “ርዕስ” የታተመው የአፄ ኃይለ ሥላሴ መፅሐፍ፣ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ “አረንጓዴ አሻራ” በሚል “የሚካሄደው” የችግኝ ተከላ? “ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ”  “መሪ ቃል” የተከናወነው ስነ-ስርዓት? የ”ገበታ ለአገር”የተሠኘው  የእራት “መስተንግዶ”ስ?…. እነዚህ አራት ማጣቀሻዎችን ተመልከቱ፡፡
ከውስጣቸው ስንት የምሳሌና የዘይቤ አባባሎችን እየመዘዝን ማውጣት እንደምንችል ብናይ፣ ያስደንቃል። “በምሳሌና በዘይቤ አብዝተው ተዋቡ ወይም የተሸቀረቀሩ አባባሎች ናቸው” ማለት ይቻላል።
“አላማ እንደሩቅ አድራሻ ነው፣ የእድገት እቅድ እንደ ጥርጊያ መንገድ ነው። ታሪክ እንደ ጉዞ እንደ  እርምጃ ነው “ ከሚል ምሳሌያዊ ሃሳብ ውስጥ እልፍ አባባሎች ይመነጫሉ። ንጉሱ የመረጡት የመጽሐፍ ርዕስ፣ ይህንን ይመሰክራል። ኢትዮጵያና ርምጃዋ ብለው ሰይመውታል። በዚያ ላይ፣ “አገር እንደ እናት ናት” የሚል ተጨማሪ ምሳሌዊ መልእክትም ያዘለ ነው። “ርምጃዋ” ይላልና ርዕሱ።
ርምጃ፣… ቃል በቃል የእግር እንቅስቃሴን፣ መራመድንና መሄድን የሚያሳይ የድርጊት ትርጉም ይዟል። ነገር ግን፣ ታሪክን እና የታሪክ ክስተቶችን በምሳያዊ ዘይቤ ለመግለጽ ጠቅሟል። ርምጃ፣ አንድ የድርጊት ዓይነት ቢሆንም፣ ሌሎች  ድርቶችንና ውሳኔዎችን ሁሉ ከእርምጃ ጋር በማመሳሰል፣ እንናገራለን። “ሕጋዊ እርምጃ”፣  “የመንግስት እርምጃ” የሚሉ አባባሎችን እንጠቀም የለ?
“መሄድ” የሚለው ቃል፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ፣ ተከታታይ እርምጃን የሚያሳይ ነው- ቀጥተኛ ትርጉሙ። ነገር ግን፣ ሌሎች ተከታታይ ተግባርራትን እንገልጽበታለን። “የአርንጓዴ አሻራ” ዘመቻ “ተካሄደ” እንላለን-  የችግኝ ተኮላ ተግባራትን ለመግለጽ። ምን ይሄ ብቻ? “አረንጓዴ” የሚለውን ቃል፣ ተመልከቱ በቀለም ዓይነት አማካኝነት  ቅጠልን መግለጽ፣ የተክልና የዛፍ በቅጠል አማካኝነት ደግሞ፣ ተክልና ዛፋን በሙሉ  ማመልከት የምንችለው በምሳሌ ዘይቤ ነው።
አሻራ የሚለው ቃልስ? የእጅ መዳፍ ላይ የሚገኝ፣ ከእጅ ንክኪ ም የሚፈጠር ውጤት አይደል? ይሄንንም፣ በምሳሌያዊ ዘይቤ ፣ የእጅን ተግባር፣ የሰዎችን ጥረትና በረከቱን ያመለክታል፡፡
“እቆማለሁ” የሚለው ቃል፣…. በቀጥታ በሁለት እግር ፀንቶ መቆም ከሚል ትርጉም ይነሳል። በምሳሌያዊ ዘይቤስ? በአላማ መነሳትን፣ በሃሳብና በተግባር መፅናናትን ለመግለጽ ይጠቅማል። ፅኑ አቋም እንዲሉ።  
“ገበታ” የሚለው ቃል፣ የእራት መስተንግዶን ሲጠቁም፣ “አገር” የሚለውም፣ በጥቅሉ መላ ሀገርን፣ ከዚህም ጋር የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችንም ያመለክታል።
አራቱ ማጣቀሻዎች፣ በምሳሌና በዘይቤ የተትረፈረፉ አባባሎች እንደሆኑ በዝርዝር ለማየት ሰንሞክር፣ እኛም  “የምሳሌ ዘይቤን” መጠቀማችን አልቀረም… ቢያምርም ባያምርም። የመፅሐፍ “ርዕስ” ሲባል፣… ቃል በቃል፣ መፅሐፉ፣ አንዳች  “ራስ” ኖሮት አይደለም። “መስተንግዶ” ስንልም፣ ጥሬ ትርጉሙ መሰረት፣… ከእንግዳ ወይም ከተጓዥ ከነጋዴ ጋር የተያያዘ፣ መሆኑን ለመናገር አይደለም። “ሄደ ነጎደ” ይባል አልነበር? እንዲህ ከመሄድና ከመጓዝ ጋር የተዛመደ ነው፡፡  ለእንግዳ፣ ጥላና ማረፊያ፣ ምግብና ውሃ፣ ጨዋታና ቡና  ማበርከት ነው መስተንግዶ፡፡ ለደንበኞች በክፍያ፣ ለወዳጅ ጎረቤት በግብዣማብላት ማጠጣትም መስተንግዶ ይባላል በምሳሌያዊ ዘይቤ።   “መሪ ቃል” ሲባልም…. አንድ ነጠላ ቃል ማለት አይደለም፡፡ በምሳሌያዊ ዘይቤ፣ ቃላትንም  ሃሳብንም አካትቷል።  “መሪ” ሲባልም፣ በአካል፣ ከፊት እየተራመደ መንገድ የሚመራ ማለት ብቻ አይደለም። ጥሬና መነሻ ትርጉሙ እንደዚያ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ ዋና ዋና ሃሳቦችንና አውራ የተግባር ውሳኔዎች ለመግለፅም  እንጠቀምበታለን- “መሪ” ሃሳብ በማለት።  
ምናለፋችሁ! የሰው ቋንቋ፣…  ዙሪያ ገባው ሁሉ ፣ የምሳሌና የዘይቤ አባባሎችን አብዝቶ የሚያበቅል ለምለም መስክ ይመስላል። ምሳሌና ዘይቤ፣ የሁልጊዜ እህል ውሃችን ናቸው ማለት ይቻላል።  ንግግራች ሁሉ በምሳሌ ዘይቤ የበለፀገ ነው-ከምር “ነገር በምሳሌ” ነው ለካ፡፡
“ነገር ግን፣ “ቋንቋ ሁሉ፣ ምሳሌና ዘይቤ ነው” የሚለው አስተሳሰብስ? ቀጥተኛ ትርጉም የያዘ፣ ግልጽ መልእክት የሚያስጨብጥ ንግግር የለም?  “የሰው ሃሳብ ሁሉ፣የወዲያ ግድም  ዘወርዋራ ነው?  የሰው ንግግርና ፅሁፍ፣ ያ ሁሉ ሐተታና መረጃ፣….የምር በግላጭ እውነታን አያስገነዝብም? ከግድፍ ተመሳሳይነት የማይሻገር ገልቱ ልፋት ነው?” ይሄ እንዲህ የሰው ሃሳብና ንግግርን  ለማጣጣል መሆኑ ነው።
ነገር ግን፣ በደፈናው፣ የሰውን ሃሳብ በሙሉ፣ በጭፍን የሚያናንቅ ሃሳብ፣… ከቁምነገር ሊቆጠር አይችልም። የራሱንም ሃሳብ የሚያናንቅ ነውና። በዚያ ላይ፣ ስቴቨን ፒንከር እንደገለጹት፣ ሁሉም ቃላትና ሁሉም ንግግር፣ ምሳሌና ዘይቤ ሊሆኑ አይችሉም።
“እርግብ” የሚለው ቃል፣ ቀጥተኛና ግልጽ ትርጉም አለው፡፡ ሰላማዊ ሰው ወይም ቀና ባህርይ ደግሞ በእርግብ ይመሰላል። “መንገድ እንደ እቅድ ነው  ፣ እርምጃ እንደ ተግባር ነው፡፡ ጉዞ እንደ  ታሪክ ነው” በማለት  ለምሳሌያዊ አባባል መጠቀም ይቻላል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን፣ የመንገድና የእርምጃ ቀጥተኛ ትርጉም የሚታወቅ ከሆነ ብቻ ነው።  አንቲገን ከተሰኘው የሶፎክልስ ድንቅ ድራማ ውስጥ  እንድ አባባል ተመልከቱ፡፡ “ ንጉስነት እንጀራዬ ነው” ተብሎ የተተረጎመ አባባል ነው፡፡ይሄ የንጉስ ክርዮን ንግግር፣ አያስገርምም? ማንም ጥሩ አናፂ ፣ምርጥ አንጥረኛ ወይም ጎበዝ ገበሬ፣ ሙያውን እና ስራውን “እንጀራዬ” ብሎ እንደሚሰራ ይገልጻል ንጉሱ። ንጉሥነት ፣ ከሌላ ሙያና ስራ የተለየ ነገር እንዳልሆነ ለማስረዳትም ፣ “ንጉስነት እንጀራዬ ነው” ይላል። ምሳሌያዊ ንግግር ነው፡፡ ምሳሌያዊ ትርጉሙን መገንዘብ የቻል ነው፣ “እንጀራ “ የሚለው ቃል፣ ቀጥተኛና ግልጽ ትርጉም ስላለው ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።
በምሳሌያዊ አተረጓጎም የምንጠቀምባቸው ብዙ ቃላት፣ በትርጉም እየበለፀጉ ይሄዳሉ። ምሳሌያዊ ትርጉማቸው ወደ መደበኛ ትርጉም ይለወጣሉ።
“ጥሩ” የሚለው ቃል፣ ከመፅዳት ከመጥራት ጋር ተያያዘ ነው- መነሻ ትርጉሙ። በምሳሌያዊ ዘይቤ ደግሞ ፣ ለሰው ሃሳብ፣ ለሰው ድርጊትና ለባህሪ  እንጠቀምበታለን፡፡ የፀዳ ስራ፣የጠራ ሃሳብ፣ንጹህ ሰው እንል የለ፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ምሳሌያዊ አነጋገር መደበኛ አነጋገር ሆኗል፡፡  ጥሩ የሚለው ቃል፤ ስነ-ምግባርን የሚገልፅ መደበኛ ትርጉም ወደ መያዝ ተሸጋግሯል። ቀጥተኛ ትርጉም ሆኖም፣ ወደ መዝገበ ቃላት ገብቷል።
መንግስት ስንል፣ ቀጥተኛ ትርጉም እንጂ ምሳሌያዊ ዘይቤነቱ ይታወሰናል? ንጉስ የሚለው ቃል፣ በአካል አንድ የበላይ ባለስልጣንን የሚገልፅ  ቃል ነው። በምሳሌያዊ ዘይቤስ? ሌሎች ባለስልጣናትን፣እንዲሁም  የህግና ስርኣት ተቋማትን ሁሉ የሚያካትት ምሳሌያዊ ፣ ትርጉም ተሰጥቶታል። ከጊዜ በኋላ ግን መደበኛ ትርጉም ሆኗል።
 እንዲያውም፣ መነሻውንና አመጣጡን  ልንረሳው እንችላለን። “መንግስት” የሚለውን ቃል፣ ከንጉስ ጋር አናቆራኘውም። ለምን? ከጊዜ በኅላ፣ ራሱን የቻለ መደበኛና  ቀጥተኛ ትርጉም ስለያዘ ነው።  



Read 2093 times