Sunday, 29 November 2020 16:36

በናፍቆትና በትዝታ ዳና የታጀቡ ግጥሞች

Written by  ኤማንዳ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ኪናዊ ስሱነት (aesthetic  sensitivity) “የኑሮ ጥራት መገለጫ፣ የስሜትና የነፍስ ዕድገት መታያ ክሂል ነው” ይላል-የስነጽሁፍ ምሁር ብርሃኑ ገበየሁ፣ ‘የአማርኛ ሥነግጥም’ በተሰኘው የንድፈ-ሃሳብ ትንታኔ መጽሐፉ። እንደ ግጥም ያሉ ኪናዊ የፈጠራ ስራዎች የልቡናን ዝማሬ ለመስማት መፍቀድ፣ የሌሎችን ቃል ለመስማትና ለማድነቅ መፈለጉ ላይ ነው፤ የኪናዊ ስሱነት ዋንኛ ምንጨቱ”… ለመደነቅ፣ ለመደመም ፈቃደኛ መሆን፣ ዓለምንና ህይወትን በምልዓትና በጥራት ለመኖር መሻት፤ አንድም፣ ገጣሚው የሰጠውን ቃላዊ ገጠመኝ የመተርጎም፤ እርሱንም ደግሞ ደጋግሞ የመኖር፣ የማሰላሰል፣ የማፍታታት፣ የመለጠጥ ችሎታ ነው” ሲል የኪናዊ መማለል ገፊ ምክንያቶችን ምሁሩ ዘርዝሯል፡፡
ከያኒው በልቡናውና በህውስቱ ያገኛቸውን፣ በኑረቱ ያስተዋላቸውን፣ በሰርካዊ እንቅስቃሴው የታዘበውን ነው ከምናቡ አፍልቆ የሚያቀርበው። ከያኒው እንደ ማንኛውም ሰው የማህበረሰቡ አባል እንደመሆኑ፤ ከማህበረሰቡ ጋር የሚጋራቸው አያሌ ነገሮች ይኖሩታል፡፡ አስተውሎቱና ተሃዝቦቱ፤ ንባቡና አሰላሳይነቱ ላይ ተተግኖ ቀድሞ ከማህበረሰቡ የተቀበላቸው ነገሮችን አንድም ያጸናል፤ አንድም ነባሩን ስምምነት ሽሮ አዲስ እውነታ ያንጻል፡፡ ከያኒው የማህበረሰቡን የተዛነፈ አስተሳሰብ በብዕሩ ይሄሳል፡፡ የሚሄስበት መንገድ ቀጥተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ አንድም በምጸት አንድም በኩሸት፤ አንድም በእንጉርጉሮና በሙሾ ሊሆን ይችላልና።
ኪናዊ ተውህቦ (aesthetic experience) ራስን ከማወቅ ይጀምራል፡፡ እኔ ማነኝ? ከየት ነው የመጣሁት? የህይወት ትርጉምስ ምንድን ነው? የሚለው የህላዌ (existence) ጥያቄዎች ከያኒውን ይመዘምዙታል፡፡ ከያኒው ስለነዚህ ጥያቄዎች ሲያሰላስል፣ ስለ ሰው ልጆች እያሰላሰለ ነው፡፡ ስለ ማህበረሰቡ እያሰበ ነው፡፡ አጠቃላይ ስለ ዩኒቨርስ እያሰበ ነው፡፡ እንግሊዛዊው የነገረ-ኪን (Aesthetics) ተመራማሪና ፈላስፋ ኮሊንግዉድ፤ ‘The Principles of Art’ በተሰኘው መጽሐፉ፤ “The aesthetic experience is knowing of oneself and of one’s world, these two knows and Knowing’s being not yet distinguished.” እንዲል፡፡
የየሱፍ ግዛው ዓለምጉድ ‘ናፍቆት’ የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞችም ሰርካዊ የሰው ልጆች ጥያቄ ሌላኛው ጎናቸውን እንድንመለከት ይገፋፋናል፡፡ በግጥሞቹ እንደ ማህበረሰብ ጉድፋችንን በመንቀስ ይሄሳል፡፡ ዘለልማዳዊ አረዳዳችንን ቆም ብለን እንድናይ ይወተውተናል፡፡ ገጣሚው በትውልዱ እጣ ፈንታ ላይ ሙሾ አውርዷል፡፡ የገጣሚው የናፍቆትና የትዝታ ዳናዎቹንም በተዋቡ ቃላት ይሞሽራል፡፡   
‘ናፍቆት’ የተሰኘው የግጥም መድበል በ2012 ዓ.ም የህትመት ብርሃን ማየት ከቻሉ ኪናዊ ስራዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ መድበሉ 91 ግጥሞችን በውስጡ አካትቷል። በገጽ ብዛት ከታየ ደግሞ የመፍትሄ ቃላትን (Glossary) ጨምሮ 160 ገጾችን ይሸፍናል፡፡ እኔም በገጣሚው የግጥም ስብስቦች ውስጥ ልህቀትና ኪናዊ ረብ አላቸው ያልኳቸውን ጥቂት ግጥሞች፣ በዚህ ውስን አምድ ላይ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
ገጣሚው ያሰበውንና ያሳሰበውን የህይወት ተሃዝቦቱን በቃላት አስውቦ፤ በቅርጽ ደርዝ አሲዞ ግጥምን ይወልዳል። ገጣሚው በግጥሞቹ ውስጥ ደስታና ሃዘኑን፤ ማግኘትና ማጣቱን፤ መረዳቱንና ግራ መጋባቱን፤…ያስተጋባበታል፡፡ ግጥሞቹ ከጥልቅ አስተውሎት ወይም መረዳት የመነጩ ሲሆኑ ሰውኛ ስሜት ያረብባቸዋል። ይኸ በግጥሞቹ ውስጥ የረበቡት የገጣሚው ስሜቶች መልሰው ተደራሲው ላይ ይጋባሉ። ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን "እሳት ወይ አበባ" በተሰኘው የግጥም መጽሐፉ መግቢያ ላይ፣ “ዘለቄታ የሚኖረው ሥነ-ግጥም የሰውን ልጅ ዘላለማዊ የሃቅ እውነታ ሊያቅፍና ሊያበስር ይሻዋልና” ሲል ያስገነዘበው ይህንኑ ጉዳይ ይመስላል፡፡
በ’ናፍቆት’ ውስጥም ገጣሚው፤
የኖርሁት እውነቴን
ያልኖርሁት ጉምዠቴን
ባ’ንድ አንቀልባ አዘልሁ፥ ኹለቱም ናፍቆቴ፤
ትዝታን በጀርባ፥ ተስፋን በደረቴ --ይለናል፤ ገጣሚው የኖረው ‘እውነት’ ብቻ ሳይሆን በምናቡ የሚጎመዥበት ተስፋውም የግጥሞቹ አንድ አካል መሆናቸውን ለመግለጽ፡፡
ትዝታ የሃገራችን ኪናዊ ስራዎች ዕምብርት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ለነገሩ የሰው ልጅ አንድም በትዝታ ትላንትናውን እያውጠነጠነ፤ አንድም በተስፋው ነገውን እያማተረ የሚኖር ፍጥረት እንደ መሆኑ የኪናዊ ስራዎች ማሟሻ ቢሆን አያስገርምም። ትዝታ የሃገራችን ሙዚቃ ውስጥ አንድ መታወቂያ ዘውግ (genre) መሆኑ እሙን ነው፡፡ በተለያዩ የግጥም ስራዎች ውስጥም ገጣሚዎች የትዝታን መልኮች ገልጠው ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡
በእርግጥ ትዝታችን አንድና ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን የተቃየጠ ነው፡፡ አንድም ያለፈውን ውብ ጊዜ እናይበታለን፡፡ ወድቀን ዳግም የተነሳንበትን በልዩ ሁኔታ እናስበዋለን። የህይወታችንን ክሬም የላስንበትን ወቅት በደስታ አጅበን እንዘክራለን። በሌላ በኩል፤ ትዝታችን በህይወት ጉዞ የተሰናከልንበት ሊሆንም ይችላል፡፡ ያፈቀርነውን ያጣንበት፤ ባመንነው ሰው የተከዳንበት ወቅት የትዝታችን መዘውር ሆኖ ግዙፍ ቦታ ሊይዝም ይችላል፡፡  ገጣሚው ‘እወድሽ ነበረ’ በሚለው ግጥሙ፣ ትዝታን እጥር ምጥን ባለ መልኩ እንደዚህ ገልጾታል፤
ትዝታ ምንድነው?
‘ማይጎነጩት ጣዕም፥ የኋልዮሽ ተስፋ
በተዘጋ ዶሴ፥ ዛሬን የሚገፋ፤
ገጣሚ ዜመኛ ነው፡፡ በግጥሞቹ ያዜማል። ግጥሞቹም ዜማ ያወጣሉ፡፡ ዜማቸው ጎልተው የሚሰሙ ግጥሞች ደግሞ የተደራሲውን ቀልብ መግዛት ይችላሉ። ገጣሚው ይህንን ተገንዝቦ ግጥሙን በዜማ ሲያጅበው ለግጥሙ ኪናዊ ልህቀት ያጎናጽፈዋል፡፡ "ዜማ ተለጣጣቂነት ያላቸው የቃላት ቅንብሮች የሚያስገኙት ስርዓታዊ የድምጽ አወራረድ ነው” በ"ናፍቆት" ውስጥም አልፎ አልፎ ዜማቸው የሚጥሙ የግጥም ስንኞች ይገኛሉ፡፡ ገጣሚው የዜማ አስፈላጊነትን አምኖበት ወይም ባጋጣሚ ሊሆን ይችላል፤የዜማ ቅመራው። እስኪ ከገጣሚው ዜመኛ ግጥሞች ውስጥ እንቀንጭብ፤
ናፍቆቴ
አንቺ የመጣሽ’ለት
ነፋስ አልነፈሰም፥ ዛፎችም ቀጥ አሉ
አዕዋፍ ባ’ርምሞ፥ አደብ ገዝተው ዋሉ፤
ዝምታ ሰፈነ፥ ፍጥረታት ‘ረገቡ
ለኔና ላንቺ ፍቅር፥ ድምጻቸው ታቀበ፤
በእነዚህ የግጥም ስንኞች ውስጥ ዜማ ብቻ አይደለም የምንሰማው፡፡ ስዕልም በምናባችን ይከስታሉ፡፡ ስንኞቹ በዘይቤ የታጀቡ በመሆናቸው ለምዕስል ክሰታው ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ፍቅረኛሞቹ ሲገናኙ ነፋስ፣ ዛፎች፣ አዕዋፍና ሌሎችም ፍጥረታት ድምጻቸውን አርግበው፤ ፍቅረኞቹን በአርምሞ ሲመለከቱ እንሰማለን፣ እናያለን፡፡
‘ከቅድ ሸሚዜ ሥር’ በተሰኘው ግጥም ውስጥም በዜማ የተሽቀረቀሩ ስንኞች እነሆ፤
ሴትነቷን ልስል፥ ማንጋጠጡን ትቼ
ከቁጫጩ ልማር፤ ከረምሁ ተደፍቼ
በራሴ ዘንቤ፥ በራሴ አባራሁ
ሌላ እኔነት ሰራሁ፤…  
ገጣሚው ‘የትውልዴ ዕጣ’ በተሰኘው ግጥሙ፣ በትውልዱ ዕጣ ዕዝነቱን ይገልጻል። የትውልዱን ዕጣ ከዘመኑ መንፈስ ጋራ አቆራኝቶ ቁጭቱንና ንዴቱን ያጋራናል፡፡ በዚህም ትውልዳችንን በሰላ ሂስ ሸንቁጦታል፡፡ እንዲያው ጠንከር ተደርጎ ይገለጽ ከተባለ ትውልዳችን ላይ አንካሴ ሳይሆን አፎቄ የሚያህል የሰላ ሂስ ወርውሮበታል፡፡ እንዲህ በማለት፤
እንዳያልፍ ካ’ባት ደጅ፥ አያት ከዋለበት
በጠዋት ቢነቃም፥ ፀሃይ ዘገየበት፤…
የኔ ዘመን ትውልድ፥ ከማር የወጣ ዕቃ
የትም ዓሳ ልሶት፥ ላገሩ ማይበቃ፤…
ጊዜ አደናግሮ፥ አደረገው ሰብይ
አንጋጦ በተስፋ፥ ይጠብቃል ነቢይ
ሲያጣ ሲመክን፥ የጠበቀው ከላይ
ጥያቄ በመውለድ፥ ይጨብጣል ድንጋይ
ደሙም እንደገና፥ ተከዜን ያስንቃል
ጥያቄ አስቀርቶ፥ የሱ ጀምበር ያልቃል፡፡
-
‘የኔ ነገር’
እሳትና ውሃ፥ ሰጥቶኝ የምርጫ ቁር
ገጼ ወየበብኝ፥ ላይነጣ ላይጠቁር፤
እኔ ፈንደላላ፥ በመሻት ታንቄ
መምረጥ ቢቸግረኝ፥ የነፍስ ጥያቄ
በመሃል ተጣድሁኝ፥ በግራጫ ስቃይ
ሕይወት በሚል ዕዳ፥ በሞት በሚሉት ሲሳይ፡፡
የህይወት ተቃርኖዋ….የሰው ልጆች ዕጣ በ”መሆንና ባለመሆን” መሃል የሚመላለስ ሸምቀቆ ውስጥ የገቡ ናቸው ይለናል። በእነዚህ የህይወት ተቃርኖ ውስጥ እንድንባዝን ተፈርዶብናል ነው በግጥሙ ውስጥ ድምጽ አውጥቶ የሚጮኸው፡፡ ገጣሚው ግጥሙን የዘጋበት ስንኝ ደግሞ ከለመድነው የህይወት ዘይቤ ወጣ ያለ ነው። “ሕይወት በሚል ዕዳ፥ በሞት በሚሉት ሲሳይ” ሲል፣ ህይወትን በዕዳነት፣ ሞትን በሲሳይነት ፈርጆታል፡፡ ይኸ የገጣሚው ‘ዕውነት’ ቢሆንም ቅሉ፣ የሰው ልጆች ከሞት ይልቅ ህይወትን ያፈቅራሉ፡፡ ሞትን በዕዳነት ፈርጀው፣ የቱንም ያህል ስቃይ ቢበዛበት፣ “ከመሞት መሰንበት”ን ይመርጣሉ። ይህንን የሰው ልጅ የሞት ፍርሃትና የህይወት ጥልቅ መሻቱን ‘ግን ምን ልልሽ ነበር?’ በተሰኘው ግጥሙ፣ ግሩም በሆኑ ስንኞች ገልጧቸዋል፤
በጊዜ ምህዋር ውስጥ
መንከልከሉ ላይቀር፥ ለመስከን ይጥራል
ሰው ማለት ምንም ነው
ከምንም ተስማምቶ፥ እውነትን ይፈጥራል፤
ምድርና ሰማይ
ፈጥረሃል እያለ፥ ጌታው ይለምናል
ከፈጣሪው በላይ፥ ግን መሬትን ያምናል፤…
የሱፍ ግዛው ኢትዮጵያንም በቃላት ኩሏታል፡፡ ‘ፀሐይና ኢትዮጵያ’ በሚለው ግጥሙ ልጅነቱን አስታውሶበታል፡፡ ‘ሀገሬ እወድሻለሁ’ ሲል ወደ ኋላ ሄዶ ከታሪክ መዛግብት አስረጆችን በመምዘዝ ትውልዱን ሞግቶበታል፡፡ የዘመኑን ስሁት ትርክት ወደ ጎን ገፍቶ ‘ሀገሬ እወድሻለሁ’ ይላል፡፡
ሀገሬ እወድሻለሁ፥ ልዋጭ ምትክ የለኝ
እማማ
ሳልርቅ በፍቅርሽ እየራድሁ፥ በናፍቆትሽ
እስክደማ፤
ዕሳቤው ቢከረፋ፥ ሕዝብሽ መርዝ ቢጋት
እንቆቆ
ከዚህ ጭቅቂት ወሌት መኻል፥ ይታየኛል
ፍቅርሽ ደምቆ፤
መጨካከን መተራረድ፥ እየኾነም ያንቺ  እጣ
ግምድ ቁርኝቱን ፈ’ቶ፥ ሊጠላሽ ልቤ
ዐቅም አጣ…
በ"ናፍቆት" ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች እንደ ሸንኮራ አገዳ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሸንኮራ አገዳ መለለት ብቻ ሳይሆን አንጓም አለው፡፡ የመለለቱን ጣፋጭ ውሃ ለመምጠጥ የምንጓጓውን ያህል፣ ለአንጓው የምናሳየው ፍላጎት በጣም ውስን ነው፡፡
በየሱፍ ግጥሞች ውስጥም ብዙ የግጥም መለለቶች እንዳሉ ሁሉ የተወሰኑ የግጥም አንጓዎችም አሉ። አልፎ አልፎ የተልገዘገዙ (ነገርን በቶሎ የማይቋጩ) ግጥሞች ማስተዋላችን አይቀሬ ነው፡፡ የተወሰኑ ግጥሞች መልገዝገዝ፣ ከመርዘማቸው አሊያም ከማጠራቸው ታይተው ሳይሆን የግጥሙን ፈር በመልቀቅና ዙሪያ ጥምጥም በመሽከርከራቸው ምክንያት ነው፡፡ ይሄም ሆኖ እነዚህ ጥቂት ለዛዛ ግጥሞች መኖራቸው ተጠባቂ ነው፡፡ ገጣሚው ሰው እንደመሆኑ በስራዎቹ ውስጥ ኪናዊ ፍጽምና (aesthetic perfection) መጠበቅ አይገባምና፡፡
በተወሰኑ ግጥሞች ለዛዛነት ሳይጎመዝዘን፣ በግጥም ስብስቦቹ ውስጥ በተካተቱት አረግራጊ ግጥሞች መመሰጥ እንችላለን፡፡ በሃሳብ የሚያረገርጉ እነዚህ ግጥሞች አንድም እያሰብን እንድናነብ፤ አንድም እያነበብን እንድናስብ ይገፋፉናል፡፡


Read 1117 times