Print this page
Sunday, 29 November 2020 16:40

የአንለይ ጥላሁን ትችት ሲተች! (“ከመደነጋገር መነጋገር”)

Written by  አሌክስ ዘጸአት
Rate this item
(3 votes)

 "ከራሱ ጋር ያልተስማማ፣ አስተሳሰብና አመለካከቱን ያላቀና፣ ስሜቱን ገርቶ በምክንያታዊነትና ልዩነቶችን ተነጋገሮ ለመፍታት ራሱን በአዎንታዊ መልኩ ዝግጁ ያላደረገ ሰው፣ የቱንም ያህል የተማረ፣ የቱንም ያህል የሰለጠነ ቢሆን፣ ምንም ያህል የሕይወት ልምድ ቢኖረው፣ ሁለት ጸጉር ያበቀለ እድሜ ጠገብ ቢሆን፣ ለመደነጋገርና ለማደናገር ካልሆነ በቀር - ለመነጋገር ዝግጁ አይደለም።"
               

              ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለንባብ በበቃው የአዲስ አድማስ እትም፣ የጥበብ አምድ ላይ ‘ከመደነጋገር መነጋገር’ን እንዳነበብኩት” በሚል ርዕስ አንለይ ጥላሁን ምትኩ፣ በሳሙኤል ወልዴ የተጻፈው መጽሐፍ ላይ ያቀረበውን ትችት አነበብኩት፡፡ አንለይ “ስለ መጽሐፉ የተሰማኝን አስተያየት በጥቂቱ ለመግለጽ ያህል እንጂ ጥልቅና ሙያዊ ሂስ ለማቅረብ እንዳልሆነ አንባቢ እንዲረዳልኝ” በሚል ያቀረበው "ሂስ ወ አስተያየት"፤ ከመጽሐፉ አንድ ዐውድ ቀንጭቦ ካቀረበ በኋላ ወዲያውኑ  ወደ ትችት ተሸጋግሯል፡፡
ከመደነጋገር መነጋገር በ216 ገጽ የተቀነበበች ብትሆንም፣ አንለይ ጥላሁን መርጦና ነቅሶ  ያቀረበው  ትችት፤ ከገጽ 35፣36፣ እና 45 ላይ የተቀነጨቡ ዐውዶች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሳያንስ “በአጠቃላይ መጽሐፉ በስምንት ምእራፎች የተዋቀረ ቢሆንም አቀማመጣቸው ምክንያታዊ አይመስለኝም” በሚል ምክንያት አልባ ድምዳሜ ትችቱን መቋጨቱ፣ ግለሰቡ መጽሐፉን ጨርሶ አለማንበቡን እንድጠረጥር አድርጎኛል፡፡
ከ“መደነጋገር መነጋገር”ን  ከአንዴም ሁለቴ እንዳነበበ ሰው ሆኜ የአንለይ ጥላሁን ምትኩን “ጥልቅና ሙያዊ  ሂስ አይደለም” ተብሎ ወደ ትችት የተሸጋገረውን ጽሑፍ ሳነብ፣ “የተግባቦትንና የንግግርን እንዲሁም የሃሳብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን በግልጽና በማያሻማ መንገድ ማስፈር አልቻሉም” በማለት  የደራሲውን የአቅም ውስንነት ለመግለጽ የጨከኑበት ድፍረት፣ እርባና ያለው የሙግት ነጥብ ሳያስቀምጡ፣ “ለስሜት ያላቸውን የመረረ ጥላቻ ከመጽሐፉ መግቢያ እስከ መደምደሚያው (ማጠናቀቂያ) ምእራፎች ሁሉ በመረረ መንገድ ገልጸውታል። በእኔ እምነት ጽንፈኛ አቋማቸውን እንዲያንጸባርቁ ያደረጓቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም” እያለ ደራሲውን “ጽንፈኛ” ብሎ የፈረጀበትን ጉዳይ አንለይ ጥላሁን “ስለ መጽሐፉ የተሰማኝን አስተያየት በጥቂቱ ለመግለጽ” በማለት የጀመረው #ሂስ ወ አስተያየት;፤ በጥቂቱ ለዚህ ፍረጃ ካበቃው በሰፊው ለመግለጽ ቢነሳ ምን ይል እንደነበር የሚያውቀው ጸሃፊው  ብቻ ነው፡፡
አንለይ ጥላሁን “‘ከመደነጋገር መነጋገር’ን እንዳነበብኩት” በማለት የጀመረውን መልእክት ሲቋጭ፣ ከመጽሐፉ ምንም አይነት ገንቢ ነገር ያላገኘበት መሆኑን በገደምዳሜ ነግሮናል። ግን እንዴት?
እኔ ግን፣ “ከመደነጋገር መነጋገር”ን  እንዳነበብኩት ከአንለይ ጥላሁን፣  ከ"ሂስ  ወ አስተያየት" ተፋትቶ በፍረጃና ትችት የተሞላውን የኦንላይን  እይታውን እዚህ ላይ ልቋጨውና፣ ከመጽሐፉ ወቅታዊና አስፈላጊነት አንጻር ቀደም ብለው ያነበቡት [መጽሐፉን] ሃሳቡን ደግመው እንዲያብላሉት፣ ያላነበቡትም መጽሐፉን አግኝተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማበረታታት ያህል መጽሐፉ ላይ ያደረኩትን ዳሰሳ እነሆ።
እንደ መነሻ፤
የመጽሐፉን ጠንሳሽ ሰበብ በተመለከተ ፀሐፊው አንድ አስደንጋጭ የሕይወት ገጠመኛቸውን ያወጉናል። በእርግጥ ገጠመኙ የእሳቸው የግላቸው ብቻ ሳይሆን የጠቅላላ ቤተሰብ ገጠመኝ ነው። ይኼንን ገጠመኝ በተመለከተ፥ እንደ ዜጋ፣ እንደ ማኅበረሰቡ አባል፣ እንደ ምሁር ችግሩን የፈቱበት  መንገድ መጽሐፉ ለሚያነሳው ጠቅላላ መልእክት ተግባራዊ ዐቢይ ምሳሌ ሆኖ ያገለግላል።
በተለይም እኔነት፣ ዘረኝነት፣ ብሔርተኝነት፣ አትንኩኝ ባይነት፣ በነገሠበት በዚህ ዘመን፣ ሰዎች እንደ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣  ኅብረተሰብና ብሔረሰብ ቂምና ቁርሾ ቋጥረው፣ ለበቀል በእልህ አድብተው ቢላዋ በሚስሉበት በዚህ መሰሪ ዘመን፤ ታላቅ ራዕይ፣ የማደግ ጉጉትና የላቀ ተስፋ ያላትን ውዷን የቤተሰባቸውን አባል የሆነች እህት [አበቢ] በሐኪም ቸልተኝነት በሞት ከተነጠቁ  በኋላ፣ ሌሎችን አማራጮች በሞላ እርግፍ አድርጎ ትቶ ስሜትን በመግራት፣  ነገሩን በሰከነ መልኩ በውይይት ለመፍታት መቀመጥን የመሰለ ተግባራዊ ምሳሌ የት ይገኛል? ፀሐፊው ሰፊ ገጽ ሰጥተው ይኼንን ክስተት ካሰፈሩ በኋላ በቤተሰብ፣ በቡድን፣ በማኅበረሰብ፣ በኅብረተሰብና ብሔር ደረጃ ያሉ ያለመግባባቶችና ችግሮችን ተደነጋግሮ - ከመወዛገብ ተነጋግሮ መፍታት ይቻል ዘንድ ጥሪ ያቀርባሉ። “አድርጉ” እያሉ አይደለም፤ ማድረግ እንደሚቻል አሳይተው ለተመሳሳይ ተግባር ጥሪ እያቀረቡ ነው።  
ወደ ውስጥ ስንዘልቅ፤
ቋንቋ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በሞላ ተለይቶ ከታደለባቸው መሳሪያዎች አንዱና ዋናው ነው። ቋንቋ ልዩ  ጸጋ የሆነው፣  ስሜቶቻችንን በመግለጽ፣ እንደ ሰው ያለንን ኅብረት፣ ፍቅርና አንድነት ማጎልበቻ መሳሪያ በመሆኑ ነው። ሌሎች እንደ እንስሳት ያሉ ፍጥረታት - በመሳሳም፣ በመተቃቀፍና ትርጉም የሌለው ድምፅ በማውጣት በውስጣቸው የታመቀውን ፍልቅ የወዳጅነት ስሜት መግለጥ ሲችሉ፤ የሰው ልጅ ግን ውስጡ የታመቀውን ስሜት በንግግር  የመግለጥ ጸጋ ተችሮታል። ሌላው  ቋንቋ  ልዩ የሆነ ጸጋ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ተነጋግረን በመግባባት ማኅበራዊ እሴቶቻችንን ለማስፋትና ልዩነቶቻችንን በማጥበብ እንደ ማኅበረሰብ ተያይዘን ለመኖር፣ ለማደግና፣ ለመለወጥ ነው። በእርግጥ ቋንቋን በመስማት ብቻ መግባባት፣ ችግሮችን መፍታትና እንደ ማኅበረሰብ ተያይዞ ማደግ አይመጣም።  ቋንቋ ለጠብ፣ ለመለያየትና ማኅበራዊ ትሥሥርን በጣጥሶ ጥላቻ ለመዝራት፣ ተበጣጥሶ ለመበታተን መጠቀም እንደሚቻል የሰው ልጅ በታሪክ እልፍ ጊዜ መስክሯል። ቋንቋ ተነጋግሮ መግባቢያ ከመሆንም አልፎ ተነጣጥሎ መደነጋገሪያም ሊሆን ይችላል።
“ከመደነጋገር መነጋገር” መጽሐፍ ደራሲ - ተደነጋግሮ የተደነባበረ፣ የተበታተነና ተያይዞ መቆም ያልቻለ ማኅበረሰብን እንዴት ከአምላኩ በተቸረው ጸጋ (ቋንቋ)፤ ተነጋግሮ በሚያግባቡ ነገሮች በመግባባት፣ ባልተግባባቸውም ነገሮች ላይ ባለመግባባት ለመለያየት፣ መነጋገር እንዳለበት ሙያዊ ምክርና መፍትሔ ያቀርባል። መጽሐፉ ለአገራችን አንገብጋቢና ወቅታዊ ጉዳይ መፍትሔ ነው። ሕዝቦችና ብሔሮች በቀዬ ተለያይተው፣ ያደረና የቆየ ቂም ቋጥረው፤ የሆነም ያልሆነም ትርክት ገልጠው፣ ጥቂቷንም ብዙውንም ሰበብ ልዩነትና ጠብ ለማስፋት ፍጆታ ሆኖ እየዋለ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ለጸብና ለኩርፊያ የማያበቃ ተልካሻ አጀንዳ ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል፣ በቢሊዮን  ብሮች ለሚገመት ንብረት ውድመት ሰበብ እየሆነ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ሕዝብ ከስሜት ጡዘት ሰረገላ ወርዶ መሬት ላይ በመነጋገር ልዩነቶችን የመፍታት፣ እልፍ ነፍሳትን ከሞትና ስደት የመታደግ፣ ንብረትን ከውድመት የማዳን  መላና  ጥበብ ይለግሰናል።
በሀገር  ብቻ ሳይሆን በቡድኖች ፣ በትዳር/ቤተሰብ፣ ወዘተረፈ መካከል የሚፈጠር ያለመግባባትን በሰከነ መልኩ መፍቻ ቁልፍ-ነው- መጽሐፉ። ለዚህም መሰለኝ ደራሲው የመጽሐፉን ንዑስ ርዕስ “ለቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ፣ ብሔረሰባዊና ኢ-ኅብረተሰባዊ ዙሪያ-ገጠም ውጤታማነት መክፈቻ” ያሉት።
ከየት እንጀምር?
ከራሱ ጋር ያልተስማማ፣ አስተሳሰብና አመለካከቱን ያላቀና፣ ስሜቱን ገርቶ በምክንያታዊነትና ልዩነቶችን ተነጋገሮ ለመፍታት ራሱን በአዎንታዊ መልኩ ዝግጁ ያላደረገ ሰው፣ የቱንም ያህል የተማረ፣ የቱንም ያህል የሰለጠነ ቢሆን፣ ምንም ያህል የሕይወት ልምድ ቢኖረው፣ ሁለት ጸጉር ያበቀለ እድሜ ጠገብ ቢሆን፣ ለመደነጋገርና ለማደናገር ካልሆነ በቀር - ለመነጋገር ዝግጁ አይደለም። በመሆኑም ፀሐፊው ይኼንን እውነት በመጽሐፉ ምዕራፍ ሁለት “መነጋገር ማለት ምንድን ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር “ንግግር ከራስ ጋር” እና “ከራሴ ጋር ያለኝ ምክክር ምንድን ነው?” በሚሉ ንዑስ ርዕሶች ሥር ዳስሰዋል (ገጽ 41-68)።
ከቤተሰብ፣ ወዳጅ፣ ዘመድ  አዝማድ ሆነ ማኅበረሰብ ጋር ከመነጋገሩ በፊት አንድ ሰው ከራሱ ጋር ጊዜ ወስዶ መነጋገር ግድ ይላል። ሰው በራሱ ለራሱ ነጻ ፍጡር ነው። አስቦ አሰላስሎ፣ መዝኖ  አመዛዝኖ፣ እውነትን ከሐሰት በማንጠር በግሉ ከራሱ ጋር በሚያደርገው ተመስጦ ወይንም ንግግር አመለካከቱን ማጥራት ይችላል። በቡድናዊ አስተሳሰብ በስሜት ከመነዳት፣ ከስሜታዊ ፍርደ ገምድልነት ነጻ ሆኖ የሌሎችን አሳብ ከመደፍጠጥ የሚታደገው በተረጋጋ መልኩ ከራስ ጋር በሚደረግ ውይይት ነው። ይኼም ከግለሰቦች፣ ከቤተሰብ፣ ከቡድኖች፣ ከማኅበረሰብ ጋር በሚኖረን  ውይይት ውጤታማ ለመሆን የሚያስችለንን አቋም ለመያዝ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ በግላችን በሰከነ መንፈስ በምናደርገው “የራስ ንግግር” ወደ ሆነ ድምዳሜ መምጣት ግድ ይለናል።
ለዚህም ደግሞ በውስጣችን እያውጠነጠነ ባለው አሮጌ ክር ውስጥ ያለውን ሙዚቃ ደምስሰን፣ አዲስ መቅዳት ግድ ይለናል። በመሆኑም “አእምሮው በአሉታዊ ቃላት የተሞላ ሰው ፈጥኖ ወደ እሳቤው የሚሰርገው ምክር አሉታዊ ነው። በተቃርኖ መዝገበ ቃላት የተደናቆረ አንጎል የተቃና ምክር ያፈልቃል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው” ይላሉ ፀሐፊው(ገጽ55)። ለመግባባት  በግለሰብ ደረጃ ቀናና ተማሪ ልብ ይዞ መዘጋጀት እጅግ ወሳኝ ነው። በ“አውቃለሁ” ባይነትና “እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ” ግትርነት የሚጸና ሰው፤ ለለውጥም ሆነ ለመግባባት ዝግጁ አይሆንም። ስለዚህም አክሳሪ የሆነውን የውስጥ ለውስጥ የተንሻፈፈ እይታ በአዎንታ ለመቀየር፣ ከሌሎች ለመማር የሚያስችል የተማሪነት ልብ ያስፈልጋል። “እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ፣ እኔ ያሰብኩት ብቻ ካልጸደቀ”  የሚል ግትር ሰው ወደ ተሻለ አሳብ የመምጣት እድሉ እጅግ የጠበበ ነው። የተማሪነት  መንፈስ ያለው ሰው የተሻለ አሳብ ያላቸውን ሰዎች ፈልጎ ለማግኘት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሁሉ በደስታ ይከፍላል። የራሱን የውስጥ ንግግሩን በአዋቂዎች ምክር ለመቃኘት ያዘጋጃል። አሉታዊውንና ሳያቋርጥ የሚዘፍነውን ክር በመደምሰስ አዲሱንና የተሻለውን እውቀት ለመገብየት ወደ እውቀት ገበያ ይወጣል” ይላሉ ጸሐፊው (ገጽ 57)። በመሆኑም የመነጋገር ጅማሮው ከግለሰብ “ከራስ ጋር ንግግር” ይጀምራል  ማለት ነው። ራሱን በዚህ መልኩ ያዘጋጀ ሰው ብቻ ነው እምነቱን ፣ አመለካከቱንና አቋሙን ከሌሎች አሳብ አቋምና እምነት ጋር አፋጭቶ ለማጎልበትና ለመስማማት ወደ ውይይት መድረክ የሚመጣው።
ማን ወደ ጠረጴዛው ዙሪያ ይጋበዝ?
አልባሌም ሆኑ ያልሆኑ ምክንያቶችን በመዘርዘር ቁልፍ የጉዳዩ ባለቤቶችን ከውይይት መድረክ ማግለል እጅግ የተለመደ ተግባር ነው። ሰዎች በርቱዕ አንደበታቸውም ሆነ በምልክት ቋንቋ የታመቀውን ውስጣዊ ብሶታቸውን ገልጠው፣ ችግሮቻቸውን ይፈቱ ዘንድ ባለቤቶቹን ራሳቸውን በውይይት መድረክ ማሳተፍ የትም የሌለ ትርፍ ያለው ነው። በተለይም በአፍሪካ የቡድኖች፣ ብሔሮችና ኅብረተሰቦች ግጭት በተመሳሳይ አዙሪት ከሚሽከረከርባቸው ሰበቦች አንዱና ዋናው ለፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ሲባል የጉዳዩ ባለቤቶች ወይም ትክክለኛ የጉዳዩ ተወካይ ተሳታፊዎች በሌሉበት ተወስኖ የሚተላለፍ የሰላም እርቅ ሂደት ነው።
የጉዳዩን ዋና ባለቤቶች ከውይይት መድረክ ለማግለልና እነርሱ በሌሉበት በጉዳዩ ላይ ለመወሰን የትኛውም አይነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሳይንሳዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ሰበብ በቂ አይደለም። ደራሲው ይኼንን ርዕሰ ጉዳይ በምእራፍ ሦስት ከገጽ 68-82 አትተዋል። እንደ ፀሐፊው እምነት ከሆነ፣ እውነተኞቹን የችግሩ ባለቤቶች ወደ ጠረጴዛ ላለማምጣት የሚዘረዘሩ ሰበቦች አያሌ ናቸው። አንደኛው የማኅበረሰብ ክፍል ስለሌላው ያለው የተዛባ አመለካከት ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የአንዱን ቡድን/ወገን የኑሮና የኢኮኖሚ ደረጃ ዝቅተኝነት ጠቅሰው አስተሳሰብን ከኑሮ ደረጃ ጋር በማስተሳሰር፣ በኅብረተሰብና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ አናሳ ድምፅ እንዳለው ለማሳመን መጣርን ፀሐፊው እንደ አንድ ሰበብ አቅርበዋል። ይኼ እውነት ሊከሰት የሚችልና የሚጠበቅ እንደሆነም አትተዋል። “ይኼ ራስን ጠብቆ የማኖር ዝንባሌ(Self – Preservation)  ክፋት የለውም። ችግር የሚሆነው ይኼ ብዙውን ጊዜ ያለ አሳብ በፍጥነት የሚካሄደው ግለሰቦችን በመደብ ሆነ በአይነት የመፈረጅ ተግባር ያለ ፍተሻ ዝም ብሎ እያለፈ እየሄደ፣ በኅብረሰቡ ዘንድ እውነት ተብሎ ተደላድሎ ሲቀመጥ ነው” ይላሉ ደራሲው (ገጽ 71)። ደራሲው ሙያቸውንና ልምዳቸውን ተጠቅመውና ሌሎች ምሁራንን  ዋቢ ጠቅሰው “ራስ ተኮርነት ወይም ውስጣዊ ባለቤትነት” እና “ውጫዊ ወይም ሁኔታዊ ማመካኛ” ሰዎችን ለውይይት ወደ መድረኩ ላለማምጣት ጥቅም ላይ የሚውሉ ሰበቦች መሆናቸውን ከገጽ 75-82 ባለው ክፍል አትተዋል። ደራሲው እኔ “የመጽሐፉ ልብ ነው” ብዬ የማምንበትን አሳብ፤ በምእራፍ አራት “አዎንታዊ ግጭትን መቅረፊያ አቀራረብ” በሚል ርዕስ ከገጽ 83-98 በሰፊው አትተዋል። ቡድኖች፣ ብሔሮችና ኅብረተሰቦች በተለያዩ የቅድመ ውይይት መማለጃ ዘዴዎች ከግትር አቋማቸው ተለሳልሰውና ከአሉታዊ አመለካከታቸው ተቃንተው ለውይይት ፈቃደኛ በመሆን ወደ መድረኩ ከታደሙ በኋላ በአቀራረብ የጥበብ ጉድለት ብቻ ታላላቅ ውጤቶችን ሊያስከትሉ የሚችሉ የሰላምና እርቅ መድረኮች ያለ ውይይትና ስምምነት ተቋጭተው በተገላቢጦሽ  ለከፋ ጥፋት፣ ለነፍስ መጥፋትና የንብረት ውድመት ምክንያት ሆነዋል።
ፀሐፊው በዚህ ክፍል አሁንም ከሙያቸውና  ልምዳቸው ተጠቅመው እንዲሁም ሌሎች ምሁራንን  ዋቢ ጠርተው “ችግርን ወይንም ግጭትን አስቀድሞ መረዳት”፣ “ለግጭቱ መንስኤ የሆኑትን ጭብጥ ነጥቦችን ማንሳት”፣  “የግጭቱ መንስኤ ላይ ማተኮር”፣ “ከእርቅ ንግግሩ የሚጠበቀውን ውጤት በግልጽ ማስቀመጥ” እና “ግጭትን የሚያርቅ ግልጽ የሆነ መፍትሔ ይዞ መጓዝ” በሚሉ ንዑስ ርዕሶች ሥር አዎንታዊና ውጤታማ የሆኑ የግጭት መቅረፊያ ሳይንሳዊ አቀራረቦችን በጥልቀት ተንትነው አስቀምጠዋል። በዚህ ምእራፍ የመጨረሻ ገጽ ላይ ያስቀመጧቸው “የግብታዊነት መዘዝ ትውልድ ነቅሎ የማይጨርሰው አረም ዘርቶ ማለፍ ነው”፣ “ሰው ሁሉ የትናንትና ኑሮ ተሞክሮ ውጤት ነው”፣ አሳብን በጭፍን ሳይሆን በእሳት ነጥሮ በመጣ የተሻለ ምክር መቀየር ወላዋይነት ሳይሆን አዋቂነት ነው”፣ “ጥበብ በየዕለቱ የሰው ኑሮ ውስጥ የሚመነዘር የስኬት ፍራንክ ነው” እና “አምባገነንነት የሚጠናወታቸው መሪዎች የሚናገሩት እንጂ የሚያደምጡ አይደሉም” የሚሉ ሃሳቦች ለክፍሉ እንደ መሪ አሳቦች የሚወሰዱ ታላላቅ ኃይለ ቃላት ናቸው።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የግጭት ጡዘት ውስጥ ላለች አገር ለመነጋገርና ችግሮችን ለመፍታት እጅግ ዝቅተኛ ፍላጎት እያሳዩ ያሉ የብሔር የፖለቲካ መሪዎችና ስሜታዊ ወጣቶች ልዩነቶችን እየጎተቱ ወደ ተለያዩ ጦሶች እየወሰዱ ባለበት ወቅት፣ የብሔርና የቋንቋ መሰረት ያደረጉ ግጭቶች፣ ሞትና መፈናቀል በተባባሰበት በዚህ ወቅት በሰከነ መልኩ በውይይት ልዩነቶችን አጥብቦ ከችግሩ መውጫ ሳይንሳዊ መንገድን የሚጠቁም ነው መጽሐፉ።
የመጽሐፉ ጠንካራ ጎኖች፤
የቃላት አመራረጡ፤ የአሳብ አወቃቀሩ፤ የሙግት አቀራረቡ፣ የሥነ ጽሑፍ ውበቱ እጅግ ጠንካራና በየትኛውም ደረጃ ላለ ሰው በሚገባ መልኩ ሙያዊ ደረጃን ጠብቆ በጨዋ ደንብ የቀረበ፣ ሳይጎረብጥ እየጣፈጠ የሚነበብ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ በሁሉም የማኅበረሰብ ደረጃ፣ ማለትም በግለሰቦች፣ በቤተሰብ፣ ብሔረሰብና ኅበረተሰብ ደረጃ ያሉ ችግሮችን ዓለም ለደረሰበት፣ ለዘመኑ የሚመጥን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በሰለጠነ ደንብ ተነጋግረን እንዴት መፍታት እንዳለብን ሙያዊና ሳይንሳዊ መንገዶችን ያቀርብልናል። በይሉኝታ፣ በእብሪተኝነት፣ በማን አለብኝነት፣ በድንቁርና ያለማወቅ ወዘተረፈ ችግሮች ተጠርንፈን በቂም በቀልና የታሪክ ቁርሾ ግጭት እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ አገር በአዙሪቱ እንዳንከራተት መውጫ መንገድ የሚሰጠን፣ በተለይም አሁን አገሪቱና ሕዝቦቿ ላሉበት ውጥንቅጥ የመፍትሔ መንገድ የሚጠቁም ማለፊያ መጽሐፍ ነው።
የመጽሐፉ ዕጥረቶች፤  
መጽሐፉ በርካታ ጠንካራ ጎኖች ቢኖሩትም፣ መጽሐፉን በማነብበት ወቅት  ያስተዋልኳቸው ዕጥረቶች ማስፈር ግድ ይለኛል። የመጀመሪያውና ዋናው አስተውሎቴ በተለይም በምእራፍ ሰባት ላይ በተጠቀሰውና “የመሪዎች ኃላፊነት” በሚል ክፍል ውስጥ አገር በእልቂት፣ መበታተንና ፍጅት ቋፍ ላይ በምትሆንበት ወቅት መሪዎች ሊወስዷቸው የተገቡ ለውይይት፣ ለሰላም፣ ለዕርቅ ፣ ትውልድ ለመታደግ የሚጠቅሙ ቆራጥ እርምጃዎችን ያካተተ ቢሆን ጥሩ ነበር የሚል እምነት አለኝ። በተለይም እንደ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ፣ ናይጀሪያ የመሳሰሉት አገሮች መሪዎች የወሰዷቸውን አይነት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በመወሰን በሕዝባችን መካከል ያለን ያደረ ቂምና ቁርሾ አስወግዶ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት፣ አብሮ ለማደግ መጣርን ያካተተ ቢሆን የመጽሐፉ ፋይዳ እጅግ ጎልቶ ይወጣል እላለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የማኅበረሰብ ግጭት ውስጥ ያለፉ ፣ በኋላም ግጭቶቹን በውይይት ፈትተው በሰላምና አብሮነት የበለጸጉ አገሮችን  ልምድና ተሞክሮ፣ ብሎም በአገራችን በተለያዩ ብሔረሰቦች ውስጥ ያለውን የውይይት፣ ዕርቅና ችግሮችን ፈትቶ በሰላም የመኖር ባሕላዊ ዘዴዎች ያካተተ ቢሆን፣ አሁንም የመጽሐፉ ሁለተናዊነት ሙሉ ይሆናል ነበር ብዬ አምናለሁ የሚል እምነት አለኝ።
ከአዘጋጁ፡- ፀሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1087 times