Sunday, 29 November 2020 16:45

"ያቺ ሴት"

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(8 votes)

ጠንጋራ ነው። መሬትን ሲመለከት እንደ መብረቅ ዓይኖቹ ሰማይ ’ሚያርሱ የሚመስል፤ ሰማዩን ሲመለከት የአይኖቹ ጨረር ምድር ግርጌ ላይ ይተከላሉ። ታዲያ እሱ ማነው ካላችሁ፣ የመሳለሚያው ጀግና አሸብር ነው። እዚያ አህዮች የሚበዙባት፣ ውሪ የታክሲ ሹፌሮች የሚርመሰመሱባት ... እህል ሽቃዎች ሰኞ ሰኞ መንገድ ዳር እንደ ብቅል የሚሰጡባት የጥንት የጠዋቷ እህል በረንዳ ላይ ሆኖ አሸብር ይፎልላል። ቀረርቶውን ያንቸለችላል። ወጉን ከማንም መንገደኛ ጋር ይጠርቃል። ተራ የመንደር ወሬ እንደ ባልቴት ያወራል። ከዚያ ጠባብ ፍኖት ላይ ደረቱን ነፍቶ ይመላለሳል።
ሲሉት ወግ አጥባቂ ነው። ሲሉት ግድ የሌለው አለሌ ነው። ደስ ሲለው ደግሞ ጥሩ ሌባ ነው። ሲመጣበት  እንደ እናት አዛኝ ነው። አሸብር ይጠጣል። አሸብር እንደ ስሙ አሸባሪ ነው። ሚስቱን ያሸብራል። እነዚያን ነፍስ የማያውቁ ልጆቹን ያሸብራል። ጎረቤት ያሸብራል። ዓለምን ያሸብራል።
"ኧረ፣ እንደው ምከሩልኝ። ይሄን መጠጥ አልተው ብሎ ሲያንቋርርብኝ ነው የሚያድረው"
[ቂቂቂቂቂቂቂ ] ያስተከላት የወርቅ ጥርስ ብልጭታዋ የቤቱን ከባቢ ትሞላለች።
"ተው እንጂ ልጄ" የነብስ አባቱ፣ ይመክራሉ።
«አንቺም ታገሺ። ’ወንሕነኒ ይደልወነ ንትፋቀር በበይናቲነ’ ብሏል፤ ምን ለማለት ፈልጎ ነው’ እኛም ከትዕግስት ጋር እንፋቀር’ ማለቱ ነው። .. አንቺም ታጋሽ ሁኚ እንደ እዮብ» አሏት።
አንድ ዕለት እንደ ልማዱ ሲስቅ፣ ያቺ የወርቅ ጥርስ በቦታዋ እንዳልነበረች ታያለች - ባለ ቤቱ።
«የት ወሰድካት አንተ?»
«ሽጥኳት»
«በስማም! ያንተስ ምን መዓት ነው»
ጥርሱን አውልቆ ሲሸጥ ትንሽ የመሳሳት ወይም የመፀፀት አሊያም በራሱ ባህሪ የመናደድ ነገር ፈፅሞ አያሳይም። ደስ እያለው ይሸጣል። ደስ እያለው ይጠጣበታል። ግንባሩ ሰፊ ነው። ጥቁር መልክ አለው፤ ሰልካካ አፍንጫውና ሰፊ ትከሻው ወንዳ ወንድ ያስመስለዋል። አሸብር ወዛደር ነው። እህል በረንዳ ብዙ ነገር ይሸከማል። አንዳንዴ በደህና ጊዜ የገዛቸውን የቤቱን እቃ እያወጣ ይሸጣል። አባቱን ሊጠይቅ ገብቶ፣ የቲቪ ሪሞት ይሰርቃል። ቅጥ አንባሩ የተበላሸ...ሞራል የሚባል ነገር ያልፈጠረበት እኩይ ሰው ነው -- አንዳንዴ። አሸብርን በተሻለ ሁኔታ የሚገልፀው ካለ፣ እሱ ሰው አክባሪነቱንና አዛኝነቱን ያነሳሳሉ። አንዳንዴ የሚያደርጋት ሱፍ፣ የሸሚዟ ክሳድ የአገር መሬት የሚመስል...ከዘመኑ የራቀ ሰፊ ሙሉ ልብስ አድርጎ፣ በመሳለሚያ መንገድ ላይ ሽር ብትን ይላል። የሚያውቁት ሰዎች እየጠሩት ይጋብዙታል። ከሁሉም በላይ የሚወደው ጂን ነው። ጂን በሎሚ። ታዲያ ሳይሰክር ቤቱ ገብቶ የማያውቅ ሰው ነው። አንዳንዴ የጨረቃን ብርሃን ተተግኖ፣ የሴት ቂጥ እንደ አታሞ እየመታ ይሄዳል። በዚህ ደስ ይለዋል። አንዳች ልዩ ስሜት ይሰጠዋል። ሲናደድ እንኳን ሚስቱን ከፊቷ ይልቅ ቂጧን በጥፊ ማጋል ይመርጣል። ይሄ ልዩ ባህሪ ከሆነ የእሱ መለያው ነው።
ሲለው ደሞ ጠጅ ቤት ይመርጣል። እዚያ መሳለሚያ ጫፍ ላይ ካለው ጠጅ ቤት ገብቶ ብዙ ይጠጣል። ጠጅ ሲጠጣ ሴት ያምረዋል። የሚስቱ ገላ ፊቱ ላይ ይላገዳል። ይሄኔ በጊዜ ቤት ይገባል። ሌላ ጊዜ አውቶቢስ ተራ የሚቆሙ ሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ  ጎራ ይላል።
እዚያ ጥግ ላይ ሄዶ ተቀመጠ። አሳላፊው ትልቅ ማንቆርቆሪያውን ተሸክሞ ጠጅ ሊቀዳለት መጣ። አሸብር አይኖቹን ቡዝዝ አድርጎ አንዲት ሴት ያያል። ያውቃታል። እንደውም ቅርብ ጊዜ አብሯት አድሯል። ፈገግ ብሎ አያት። እሷም አየችው። ብርሌዋን ይዛ አጠገቡ ቁጭ አለች። የሰው ሳቅ ስለናፈቃት፣ የሰው ፍቅር ስለጠማት... ሆዷ ሰው ሰው እያለ እውነተኛ ሰው ተርቧል።
“ሴት ብቻዋን ጠጅ ቤት ምን ትሰራለች?” አላት፤ ሳቅ እያለ።
“ሴት እህ አይ ሴትነት... የሴት ወጉ ቀርቶብኝ...”
“ስራ የለም እንዴ?”
“ስራ! ከወንድ ጋር መተኛቱን ነው ስራ ያልከው?! እንዴት ተሰራና ተሞተ አሉ”
ጭኖቿን መታ አድርጎ፣ አይዞሽ በሚል ዓይን አያት።
“ምርር ብሎኛል-- ታውቃለህ። የተባዕት እድፍ ተሸክሞ መሄድ ታክቶኛል! ስምህ ማን ነበር? ማንም ይሁን ብቻ ተጨንቄያለሁ ነው የምልህ። የስራ መጥፋት ከእድሜዬ መሄድ ጋር የተያያዘ ነው አየህ። አሁን አሁን አየት አድርገውኝ የሚሄዱ ወንዶች በዝተዋል። አንዳንዶች ቢመጡም የእኔ ቢጤዎች ምናምን ናቸው። የሰው ልጅ አያሳዝንህም ግን... ምፀቱ ከባድ ነው። ጉያችን ስር የሸጎጠልን ተዓምር ነው መቼም። ይሄም ስራ ሆኖ ገበያ ጠፋ ይባላል። ይሄም ስራ ነው አየህ”
“አይዞሽ ! ለምን ሌላ ነገር አትሞክሪም?”
“አዪ ሌላ ነገር። ይሄው ልጄ እርቦት የማደርገው ቢጠፋኝ እዚህ ጠጅ ቤት መጥቼ ያለኝን እጠጣበት ጀመር። ምን ላድርገው? ልዋጠው? ልጅህ እርቦት ማየት ስሜቱ ገባህ አይደል? ልጅ ተርቦ ማየት ግማሽ ሞት እንደሆነ ይገባሃል አይደል? “ እንባዋ መጣ። ዓይኖቿን እየጠራረገች ቀጠለች። “እሱስ ይሁን ከማንም ሰካራም ጋር ገንዘቤን አምጣ እያልኩ ስታገል የምውለውስ ነገር በናትህ...እናትህ እንዲህ ናት እያሉ ሲያሸማቅቁትስ ... ይሄ ከርሃብ አይበልጥም ወይ! ከጥማት አይልቅም ወይ! ይሄም ልጅ አድጎ ሰው ይሆናል”
ብርሌውን ይዛ በአፏ በኩል ያን ብጫጭ ጠጅ አንደቀደቀችው።
“አንድ የተረገመ ዕለት ነው” ዞር ብላ አየችው፤ ትሰማኛለህ አይነት “ገንዘብ ሳልቀበል አድሬ ጠዋት ላይ ገንዘብ ብጠይቅ አልሰጥም አለኝ። ሰውየው ሲታይ ጥሩ የለበሰ ነው። ውድ ጫማ ተጫምቷል። ይከለክለኛል ብዬ አላሰብኩም። እንደውም ጨምሮ ይሰጠኛል ብዬ አስቤያለሁ። እሱ ግን ከለከለኝ። ልጄ ጓዳ ተኝቶ ንግግራችንን ይሰማል። ከወገቤ በታች እርቃኔን ነኝ። ሰውየው ሊወጣ ሲል ተከትዬው ወጣሁ... አደባባይ መሳቅያ ሆንኩኝ። አላፊ አግዳሚው አየኝ። ክናዱን ይዤ ስጠኝ ገንዘቤን ብዬ አለቀስኩ። ጭንቅ ሲለው ሶስት አስር ብሮች ወረወረልኝ። ታዲያ እንደዚያ የተዋረድኩት ለማን ብዬ ይመስልሃል? ለልጄ ብዬ ነው። ጠዋት ቁርስ መብላት አለበት። ዳቦና ሻይ። አየህልኝ አይደል? “ ሳግ ተናንቋት የድምጿ ቃና ተለወጠ።
ዝም ብሎ አዳመጣት። እንባው አይኑ ላይ ግጥም አለ። “አየህልኝ አይደል? ምን ላርግ። ሸርሙጣም ብሆን እናት ነኝ። ሁለት መንገዶች ተዘርግተዋል። አንደኛው ወደ ሲኦል፣ ሌላኛው ወደ ገነት ነው ብትባል የትኛውን ትመርጣለህ? ወደ ገነት ነው አይደል? አዎ! አየህ ምርጫችን ተመሳሳይ ነው። ህይወት ግን አንደኛችንን ወደ ሲኦል፣ ሌላኛችንን ወደ ገነት ትልከናለች። አዎ! አየህልኝ አይደል?”
“የአርባ ቀን እድሌ ይሄ ህይወት ነው። ልጅነቴስ ብትል...” እንባዋን ስትጠራርግ፣ ጭንቅላቷን ወደ ደረቱ አስጠጋት።
“ለምን ታለቅሽያለሽ? ተይ...እንረዳዳለን በቃ”
“ወድጄ መሰለህ የማለቅሰው? ወድጄ አይደለም። ችግሬ ነው የሚያስለቅሰኝ። እንድታዝንልኝ ይመስልሃል የማለቅሰው? ወይ እንድትረዳኝ? አይደለም! አየህልኝ አይደል? ብሶቴ ሰፊ ሃገር ነው። የአገሬ ሰው ብቻ በድሎኛል። የወደድኩት ባይከዳኝ እኔ እማወራ ነበርኩ። ታውቃለህ አይደል? በጣም በጣም ነድጃለሁ! መተንፈስ እፈልጋለሁ። መፍሰስ እፈልጋለሁ። የኑሮ ስቃይ በአፍ በአፌ እየገባ አስመለስኩት። አዎ! ችግሬን አስመለስኩት። ብሶቴን አስመለስኩት። ሲርበኝ ታዲያ ያስመለስኩትን እበላለሁ። አየህልኝ አይደል? ህይወት እንዲህ ነው። ልጄ ብርድ ላይ ሆና ይሄን ጊዜ እየጠበቀኝ ነው። እማዬ ምግብ ይዛ ትመጣለች ብሎ ይጠብቀኛል፤ እኔ ግን....ባዶ የእናት ፍቅር ምን ያደርጋል? ውጪዎች እንውሰደው ብለው መጡ። በምን አንጀቴ ለሌላ ሰው አሳልፌ ልስጠው። አልችል አልኩኝ!? ገባህ አይደል? የእናት ፍቅር ይገባሃል አይደል? ባዶ ፍቅር ታዲያ ምን ይሰራል። ባዶ ፍቅር ችግር ነው። ጠኔ ነው። ምን ላድርገው ታዲያ? ለፈረንጅ ሰጥቼው እንደ ራበው ፈረስ እህህ--ስል ልኑር ነው የምትለው? አልችልም። እራስ ወዳድ ነኝ አየህ ... ይሄንንም የሚያይ አምላክ አለ ግን? የድሮ አምላክ አሁን ያለ አይመስለኝም። ታውቃለህ? ስድስት አመት በዚህ ስራ ውስጥ ኖርኩኝ። ይሄ ያለ ስሙ አለ የምትሉት አምላክ ሳይጠብቀኝ አይቀርም--- በሽታ የለብኝም። ታዲያ የውስጤ ሃዘን ከኤችአይቪ አይብስም ትላለህ? ማን ነው ስምህ ግን? አስጨነኩህ አይደል?;
“አሸብር” አላት፤ ሃዘኗ ውስጡ እየገባ።
“ይሁን! ሁሉም ነገር ይደረግ ግድ የለም። እንዲህም ሆኜ ልኑር። እስቲ የቤት ሰራተኝነት እንኳን ፈልግልኝ አሸብር ? ልጄንና እኔን ከቀለቡ ይበቃል። ገንዘብም አልፈልግም! የሚበሉትን በልቼ ልኑር ነው የምልህ...አዎ! ከዚህስ በላይ አልችልም። ከዚህስ በላይ ይበቃኛል”
አሁንም አቅፎ ወደ ደረቱ አስጠጋት።
“ይሄን እስቲ ያዢ” ብሎ ከኪሱ ውስጥ ሁለት መቶ ብር አወጥቶ ሰጣት።
“አይ! አይ! እንድትረዳኝ አይደለም! ችግሬ ነው ያስለፈለፈኝ!”
“ግድ የለም ያዢው”
ምንተፍረቷን  ተቀበለችው።
“አሁን ለልጄ ልድረስለት አይደል!? ይሄኔ እርቦታል”
ተነስታ ስትወጣ ጀርባዋን አያት። እንዲህም አይነት ህይወት አለ ሲል አሰበ። አሁን የሰጣት የቀን ገቢውን ነው። አሁን የሰጣት ለልጁ ወተት መግዢያው ነበር። እንባውን እየጠራረገ ተነሳ። ለሚስቱ ምን እንደሚላት እያሰበ ተነሳ። አየሩ ነፋሻማ ነው። ግማሽ ጨረቃ አድማስ ላይ ማጭድ መስላ አጎንብሳለች። በዝግታ የመሳለሚያን ቁልቁለት መውረድ ጀመረ። ከዚህ በኋላ ውስጡ የቀረው ጥልቅ ዝምታ ብቻ ነው፡፡



Read 2486 times