Print this page
Sunday, 29 November 2020 16:49

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

   ዋና ዋና ባለስልጣናት ወደ ውጭ አገር ለጉብኝት ለመሄድ ኦፊሻል ቪዛ ማስመታት ነበረባቸው… በማለት ይጀምራል፤ አንድ የድሮ ቀልድ። ሰዎቹ ኢሚግሬሽን ሲደርሱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ተሰልፏል።
“ሁሌም እንደዚህ ነው?... ወይስ…” በማለት ጠየቀ አንደኛው።
“አዎን ጌታዬ” አለ ተራ አስጠባቂው።
“ይኸ ሁሉ ህዝብ አገሩን ትቶ የት ነው እሚሄደው?”
ዝም።
“ንገረኝ እጂ” ሲሉ ተራ አስጠባቂው ላይ አፈጠጡበት… ሌላኛው።
“እኔ ምን አውቃለሁ… ባለ ጉዳዮቹን ይጠይቁ”
“መልካም፤ ስንወጣ እንጠይቃለን” በማለት ባለስልጣናቱ ወደ ውስጥ ገቡ። ከጥቂት ደቂቃዎች በሁዋላ ጉዳያቸውን ጨርሰው ተመለሱ። የተገረሙበትን ሰልፍ ምክንያት ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮባቸዋል። ነገር ግን የሚጠይቁት አንድም ባለ ጉዳይ በቦታው አልጠበቃቸውም። ግራ ገባቸው። ወደ ተራ አስጠባቂው ተጠግተው፡-
“ያ ሁሉ ሰልፈኛ የት ገባ?” አሉት።… እውነቱን ነገራቸው። ጭንቅላታቸውን ነቀነቁ።… ምን ብሏቸው ይሆን?
*   *   *
በምሽት ሰማይ ላይ
ሲደምቁ ክዋክብት
በጨለማው ጉድጓድ
አሮጌው ቀን ሲሞት
አዲሱ ሲወለድ…እዩት።
(Thomas Cole Twilight)
ወዳጄ፡- “ከአሁን በሁዋላ ይኸ ጉዳይ አያሳስበኝም፣ ሃሳብ ደህና ሰንብት” ስንል እያሰብን መሆናችን አይታወቀንም። አለማሰብም እንደ ማሰብ ሂደቱ አይቋረጥም። አለማመን በራሱ እምነት እንደሆነ….. አለማሰብም በራሱ ሃሳብ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍት እየገዛሁ ባቃጥል ወይ ሌላ ተገቢ ያልሆነ ነገር ባደርግ አለማሰብ አይደለም። ያን ዕኩይ ድርጊት ለመፈፀም የተነሳሳሁበት ሃሳብ ውስጤ ነበር ወይም ቀደም ሲል ምክንያት ፈጥሬለታለሁ። ድርጊቱ ወይም የተፈጸመው ስህተት  በኑሮ አስገዳጅነት፣ በጥቅም ፍላጎት፣ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በስካር ወይም በፖለቲካ ቅዠት ግፊት  ሊሆን ይችላል።
ወዳጄ፡ ከእያንዳንዱ ድርጊት በሁዋላ ደስታና ሀዘን ወይ እርካታና ፀፀት መከተሉ አይቀርም። በጎም ሆነ ክፉ ሃሳብ በድርጊት ካልተተረጎመ ይመክናል (Mere thought) ወይም “ሃሳብ” ሆኖ ይቀራል። በርግጥ በፅንሰ ሃሳብ ግንባታ ወይም ግንዛቤ (Conception) የሚቀድም ነገር አለ ካልን በዓይናችን የምናየው፣ በጆሮአችን የምንሰማው፣ በአፍንጫችን የምናሸተው፣ በእጃችን የምንነካውና በምላሳችን የምንቀምሰውን ነገር ይለናል። እነዚህ በስሜት ህዋሳቶቻችን በኩል ወደ አእምሮአችን የምናስገባቸው (Sensation, Perception) ነገሮች ከሌሉ “ሃሳብ” የሚባል ነገር የለም።… በአጭር አማርኛ ሞተናል።
ሰዎችን ለማስደሰት፣ ሠናይ ምግባር ለማከናወን ወይ ግፍና ጭካኔ በማንም ላይ ለመፈፀም የሚያበቃ ምክንያት ወይም ተከራክረው የሚረቱበት፣ ተናግረው የሚያሳምኑበት እውነት የሚገኘው ወይም የሚመነጨው መጀመሪያ ከሰው አእምሮ ውጭ ያለ የተጨበጠ ነገር ሲኖር ነው። በዚህ ሃቅ ወይም ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ያልተመሰረተ ድምዳሜ ውሸት ወይም ቅዠት ሊባል ይችላል።
ወዳጄ፡- ስለ ወቅታዊ ጉዳያችን ሳስብ፣ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ደቡብነት፣ ትግራዋይነት፣ ሶማሌነት፣ ቤንሻንጉልነት፣ ሃረሬነትና ሌሎችም ማንነቶች ተመሳሳይ የኑሮ ዘይቤ ወይ የአካባቢ ባህል ጥቅል መጠሪያ እንጂ ወያኔ /ኢህአዴግና/ መሰሎቹ እንደሚያስቡት፤ ከሰው ዘር አመጣጥና ከዘር ግንድ ጋር የተያያዘ እውነት አይደለም።
እየደጋገሙ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን “አማራ” እያሉ ጥቃት የሚፈጽሙ ጠባብ ብሔረተኞች የቃሉን ፅንሰ ሃሳብ ወይም ስራ ነገሩን በትክክል መግለፅ አልቻሉም። ለምሳሌ ቀደም ሲል የሻቢያ ሰዎች መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ “አማራ” እያሉ ነበር የሚጠሩት። አቶ መለስ ዜናዊ ከዳቪድሺን ጋር ሲነጋገሩ፡
“ማንን ነው አማራ የምትሉት?” ተብለው ሲጠየቁ
“የሸዋ ሰዎችን “ በማለት ነበር የመለሱት። አማራነት እንደ  “ጎሳ” ለነሱ ቅዠት ነው።
አንድ ጊዜ ደግሞ ኮሎኔል መንግስቱ፤ በብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው “አምሃራ” ማለት በተራራ ላይ የሚኖር ህዝብ ማለት ነው የሚል ገለጻ አድርገዋል። ከሞላ ጎደል፣ ቢጣፍጥም ቢመርም …. የሳቸው ይሻላል። ምክንያቱም በማጣቀሻ መፃሕፍት ላይ ከሰፈረው እውነት ጋር ይዛመዳል። ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1643 ገደማ የተጻፈውና “Paradise lost” በተሰኘው የጆን ሚልተን መጽሃፍ ውስጥ፡-
“The Amara Mountains under the Abssinian sky…” የሚል የግጥም `Epic` መስመሮች ተመልክቻለሁ።
ወዳጄ፡ በዚህ ዘመን በተጨበጠና ማስረጃ ባለው እውነት ላይ ሃሳብ መገንባት አለመቻል (Mis-Conception) አገራችንን ወደ ኋላ የሚመልስ፣ ስልጣኔያችንን የሚጎትት ከመሆኑም በላይ የጎሳ ፖለቲከኞች መናኸሪያ፣ የጠመንጃ ነካሾች መፈንጫ ማድረጉ ያሳዝናል።
ወዳጄ፡-  የዐድዋና የሌሎች አገርን ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል በተደረጉ ዘመቻዎች  ሰበብ በተፈጠሩ ሴትልመንቶች ተወልደው ያደጉ ማንነቶችን ወደ ጎን ትተን ፣በቀደም እለት ያሉት በወንጀል ተጠርጥረው በፌደራል መንግስት  የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው ስማቸው ከተዘረዘረው ባለስልጣኖች ውስጥ የአባታቸው ስም የኦሮምኛ ቃል የሆነ አጋጥሞኛል። ይህ የሚያሳየው “ማንነት” የቤተሰብ ባህል ነፀብራቅ እንጂ ከዘር ጋር ወይ ከደም ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ነው።
ባለፈው ሰሞን በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ቀበሌ ውስጥ  የተጨፈጨፉት ዜጎች በኦሮሞ ባህል ያደጉ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን እንጂ ህወሃትና ግብረ አበሮቹ፤ እንደሚሉት፤ አማሮች አይደሉም። ለምሳሌ የኤፌዲሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ሳዕረ መኮንን ይመር፤ በትግሬ ባህል ውስጥ ተወልደው አድገው፣ በዛው ባህል ውስጥ ያለፉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ትግሬነት ባህል መሆኑ ቀርቶ ዘር ቢሆን ኖሮ፣ ሰውየው ወሎዬ ነበር መባል የነበረባቸው። የህወሃት ካድሬዎች የሆኑት እነ አቶ ሴኩቱሬም እንደዛ ናቸው።
አቶ በረከትም ቀላል ምሳሌ አይደሉም። አማራነት ባህል ሳይሆን ዘር ቢሆን እሳቸው ተከሰው የተፈረደባቸው በሙስና መሆኑ ቀርቶ በዘር ማጥፋት ይሆን ነበር።
ወዳጄ፡- “አማራነት” እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ህወሃትና ቢጤዎቹ የተጠናወታቸው ፀረ አገርና ፀረ አንድነት ቅዠት ነው። ቅዠት ዕውን ሊሆን እንደማይችል ሲታወቅ እብደትን ይወልዳል።  እብደት ደግሞ ጭካኔን የስከትላል። በማይካድራ በሚኖሩ ንፁሃን ዜጎችን ህወሃት ያፈሰሰው…… ንፁህ ደም፤ ከዚሁ ቅዠት የመነጨ የእብደት ወንጀል ነው።
ወዳጄ፡ ሊሆን የማይችልን ነገር፣ እውን ለማድረግ ሲባል ንፁሃን ዜጎች ላይ መዝመት መጨረሻው የናዚና የሩዋንዳ አራጆችን ፅዋ መጎንጨት ይሆናል።… ታላቁ ገተ፡-
“To put a wrong throught in to action is the most difficult thing in the world” ይሆናል።
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- ባለስልጣናቱ ተራ አስጠባቂውን፤
“ያ ሁሉ ሰልፈኛ የት ገባ?” በማለት ሲጠይቁት “እነሱ ከሄዱ እኛ ለምን እንሰደዳለን? ብለው ተመለሱ” ነበር ያላቸው።
ሠላም!


Read 940 times