Saturday, 05 December 2020 18:30

"ጎበዝ፤ ወደ ቤታችሁ አትሄዱም!!!"

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  ደምበጫ ከአዲስ አበባ በ346 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት። በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ የደምበጫ የገበያ ቀን ነው፡፡ አሁን ተለውጦ ይሆናል፡፡ እዚህ ከተማ ውስጥ ትኖር የነበረች የአዕምሮ ሕመምተኛ፣ በዚያ ዘመን አጠራር ‹‹እብድ›› ነበረች ይባላል፡፡ በተከታታይ ለሳምንታት ገበያውን እየዞረች፣ ‹‹ሰኞ ቀን ደምበጫ ይቃጠላል›› እያለች ለፈፈች፡፡ ማንም ቁብ አላላትም፡፡ እሷ ግን አንድ ሰኞ ጠብቃ ሰው ወደ ገበያ ሲወጣ፣ መንደሩን እየዞረች በእሳት ለኮሰችው፡፡ በዚያን ዘመን መንደሩ ሁሉ ስር ቤት ነበርና በአንድ ጊዜ ተያያዘ፡፡ ገበያተኛው ግር ብሎ እሳት ለማጥፋት ሲሮጥ፤ ‹‹ሰኞ ቀን ደምበጫ ይቃጠላል ብዬ ነግሬያችሁ ነበር፤ አልሰማኝ ብላችሁ ነው›› አለች ይባላል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በተረከቡበት ዕለት፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ ለተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ያላቸውን አተያይ የገለጡት ‹‹ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መንጽር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ፣ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሐሳብ አለኝ ብሎ እንደ መጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው›› በማለት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ተስፋ ሰጭ ንግግር ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ከተቃዋሚ በእሳቸው አማርኛ፣ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ጋር በነበራቸው ግንኙነትና ስለ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች በአሜሪካና በሀገር ውስጥም ሀሳባቸውን በሰነዘሩባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ፣ አሁን ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ብዛታቸው ቀላል ባለመሆኑ፣ መንግሥት ማገዝ የሚከብደው መሆኑን፣ ለዜጎች የኮንዶሚኒየም ቤት ከመስጠት እኩል አስቸጋሪ እንደሆነ ወዘተ-- በመግለጽ፣ ‹‹ሰብሰብ›› ብላችሁ ሶስት አራት ሆናችሁ ብትመጡ፣ ለእኛም ለመርዳት የተመቸ ይሆንልናል›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ምክሩንም ማሳሰቢያውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደባባይ ከገለጡ አንድ ዓመት ከሶስት ወር ቢሆነውም፣ በተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ የታዩ ለውጦች እምብዛም ነው፡፡ ከውጭ የመጡት ራሳቸውን ሕጋዊ ለማድረግ አዝጋሚ የሆኑትን ያህል፣ በአገር ውስጥ የቆዩትም ለመሰብሰብና ራሳቸውን ለማጠናከር ያደረጉት እንቅስቃሴም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ሊዋሃዱ ነው ወይም የጋራ ግንባር ለመፍጠር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ እየተባለ የተነገረላቸውም የውሃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል። ከኢዜማ፣ ህብር ኢትዮጵያና በቅርቡ በጋራ ለመስራት ከተስማሙት የኦሮሞ ድርጅቶች በስተቀር፡፡
ገዥ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ በሁሉም ዘንድ የሚታየው ሁኔታ ‹‹እነዚህ ሰዎች ለምርጫ እየተዘጋጁ ነው? ወይስ ትተውታል?›› በማለት ለመጠየቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ የ1977 የምርጫ ዝግጅትና ቅስቀሳን ያስታወሰ ሰው፤ የዘንድሮዎቹን የፖለቲካ ድርጅቶች ጥልቅ እንቅልፍ ላይ እንዳሉ አድርጐ ቢረዳ ተሳስቷል ማለት ይከብዳል፡፡   
የምርጫው ጊዜ ቀስ በቀስ እየተሳበ እየመጣና እየተጠጋ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ወደ ሰባ የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ አዲሱ የምርጫ ሕግ ለአገር አቀፍ ፓርቲነት ሃያ ሺህ፣ ለክልል ፓርቲነት አስር ሺህ ፈራሚና መሥራች አባላት አቅርበው እንዲመዘገቡ መጠየቁ፣ አዲሶቹንም ነባሮቹንም በአዲስ መልክ መመዝገብ እንዳለባቸው የጣለባቸው ግዴታ የከበዳቸው መሆኑን ገልጠዋል፡፡ ይህን ውሳኔ ለማስለወጥና ሕጉን እንዲሻሻል ለማድረግ በዚህ ወር ማለቂያ የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡ ከረሃብ አድመኞቹ ፓርቲዎች መካከልም፣ የምርጫ ቦርዷ አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ፤ ‹‹ስምንት አባላት ይዞ፣ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂጃለሁ ብሎ የቀረበ የፖለቲካ ፓርቲ አለ›› ሲሉ የገለጹት ፓርቲ እንደሚኖር አልጠራጠርም፡፡ ብዙዎቹ ግን ቢከፍቷቸው ተልባ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡
አሁን ያለንበት ዘመን 1967 ዓ.ም ወይም 1983 ዓ.ም አይደለም፡፡ እቃወማለሁ በማለት ብቻ እንደ ተቃዋሚ ተደርጐ የሚያስቆጥር ጊዜ አይደለም፡፡ ለመቃወም ነገሮችን ማጥናት መመርመር፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ነገሮችን የሚተነትን፣ ህፀፆችን ፈልፍሎ በማስረጃ አስደግፎ ማውጣት የሚችል፣ ያንን በልዩ ልዩ የመገናኛ ዘዴዎች ለሕዝብ ለማድረስ አቅም ያለው አባላትን መያዝን ይጠይቃል። ስንቱ ፓርቲዎች አጥኚና ተመራማሪ የሰው ኃይል አላቸው? ስንቶቹ በምን ያህል ጊዜ ራሳቸውን ለማሳወቅ ወደ ሕዝብ ሐሳባቸውን ያደርሳሉ? ፈልፍለው ያወጡት እውነት አለ ወይ? ብለን ብንጠይቅ፣ የምናገኘው መልስ የሉም፡፡ በአጭሩም ያሉን ፓርቲዎች፣ ዘመኑን የማይመጥኑ ናቸው ቢባል እንደ ድፍረት አይቆጠርም፡፡
እንደ እኔ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶችን አቅመ ቢስነትና ከጊዜው ጋር መራመድ አለመቻል በግልጽ ተረድተውታል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመትም፣ እንደ ወገን አስበው የሰጧቸውን ምክር እንዳልተቀበሏቸው፣ እንዳልሠሩበትም አይተዋል፡፡ አንጀታቸው እርር ድብን ሳይል የቀረ አይመስልም፡፡
በሌላው በኩል፤ ሰባ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በረሃብ አድማ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ መዘጋጀታቸውን ሰሞኑን በጋዜጣዊ መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡ በረሃብ አድማው ባይኖርበትም፣ ነፍስ አላቸው ብዬ ከማስባቸው ፓርቲዎች አንዱ የሆነው “መድረክ”፣ በዚህ ሳምንት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ.፤ እንደ አዲስ ተመዝገቡ መባሉ እንዳልጣመው ጠቁሟል፡፡  
በተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀ ከወር በላይ የሆነው የምርጫ ሕግ፣ እስከ ዛሬም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ወጥቶ አስገዳጅ ሕግ ሊሆን አልቻለም፡፡ መንግሥት እየቀረቡ ያሉትን ቅሬታዎች የመቀበልና ጉዳዩን እንደገና የማየት፣ ሕጉን የማሻሻል ፍላጎት አለው ይሆን? ከሌለውም ፈጥኖ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንኳን በምክንያት ያለ ምክንያትም፣ የሕጎች መሻሻል አዲስ ሊሆንበት አይችልም።
ሕጉ ሲታረም ቢውል ዋጋ ቢስ ፓርቲዎችን ከሜዳው ለማስወጣት መንግሥት ያለውን ፍላጎት ግን ይለውጠዋል፤ ወደ ጎን ይገፋዋል የሚል እምነት ግን የለኝም፡፡ ይህ ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ደጋግመው አጠንክረው የተናገሩበት ጉዳይ መሆኑ በአፅንኦት መታወስ አለበት፡፡ ‹‹ለሥልጣን የመወዳደር አቅም የሌለው ፓርቲ ወትሮም ፓርቲ አይደለም›› የሚለው የጥቅምት 11 ቀን 2012 የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር፤ የቀደመውን ማጠናከሪያ፣ መደምደሚያም ነው ባይ ነኝ፡፡ እስከሚገባኝ ድረስ በዚህ አቅጣጫ የሚሻሻል ነገር የለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተናገሩት፣ ግን በተግባር ያሉት ደግሞ፡- ‹‹ጎበዝ፤ ወደ ቤታችሁ አትሄዱም!!!›› ነው፤ ሰሚ ከተገኘ፡፡
አቦ እግዜር ይስጥዎ! ጠ/ሚኒስትር!!
(ከሰሞኑ  ፓርቲዎች ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉትን ውይይት መነሻ በማድረግ በድጋሚ የወጣ ጽሁፍ)


Read 2652 times