Tuesday, 08 December 2020 00:00

በጦርነት ውስጥ - የልጆች ሥነልቦና (ለወላጆች ምክረ ሀሳብ)

Written by  ብርሃኑ በላቸው አሰፋ (ከሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲ)
Rate this item
(0 votes)

 እ.ኤ.አ በ2016 የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት፤ በመላው ዓለም 60 ሚሊዮን ሰዎች በጦርነት ሳቢያ የሚፈናቀሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከግማሽ የሚበልጡት እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ልጆች ናቸው፡፡
በግጭትና በጦርነት አካባቢ የሚኖሩ ልጆች በአንፃራዊ ሰላም አካባቢ ከሚኖሩ ልጆች በበለጠ ለአእምሮ ጤና መቃወስ ይጋለጣሉ፡፡ በተለይም ልጆች የሚኖርባቸውን የስነልቦና ጫና በግልፅና በቀጥታ ስለማይናገሩ ችግሩን ለብቻቸው እንዲሸከሙት ይገደዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ለከፋ ችግር ያጋልጣቸዋል፡፡
ከጦርነት ጋር ተያይዞ ልጆች ለስነልቦናዊ ችግር የሚጋለጡት በሁለት መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ልጆች በግጭትና በጦርነት ቀጠና አካባቢ በመሆናቸው በቀጥታ ለችግሩ ሲጋለጡ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ልጆች ከጦርነት ቀጠና ውጭ ሆነው በተዘዋዋሪ በመገናኛ ብዙኃን ሁነቱን ሲከታታሉ ይጠቀሣል፡፡
የልጆች አእምሮ ገና በእድገት ደረጃ ላይ በመገኘቱ ግጭትና ጦርነት በስነልቦናቸውና በስሜቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ያሣድራሉ፡፡ ጦርነትን ተከትሎ የሚስተዋለው ስነልቦናዊ ጫና የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ በዋናነት ከሚታዩት ምልክቶች መካከል ድበታ፣ ቁጣ፣ ፍርሃት፣ ግራ መጋባት፣ ጭንቀት፣ ፀፀት፣ መነጫነጭ፣ ትኩረት ማጣትና ተስፋቢስነት ይጠቀሣሉ፡፡
በአካላቸው ላይ ደግሞ ራስ ምታት፣ ዝለት (ድካም)፣ የልብ ምት መጨመርና ላብ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል በፍላጎት ያደርጉት የነበረው የእለት ተእለት ልማዳቸው ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ፣ ብቸኝነት መምረጥ፣ ሌሊት ላይ  መባነንና መቃዠት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ወላጆችም /አሣዲጊዎችም ታዲያ በዚህ ፈታኝ ወቅት የችግሩን አሣሳቢነት በመረዳት ልጆቻቸው ላይ የሚስተዋለውን እንግዳ ባህሪና ልምምድ በንቃት ሊከታተሉ ይገባል፡፡ ግጭትና ጦርነት በልጆች ስነልቦና ላይ ያደረሰውን ስብራት ለመጠገን በተለይም የወላጆችና አሣዳጊዎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በጦርነት ወቅት በወላጆች/አሣዳጊዎችና ልጆች መካከል የሚኖረው ውይይት ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ግጭቱንና ጦርነቱን ተከትሎ ልጆች ለሚያነሡት ጥያቄ በተቻለ መጠን ልጆች ሊገባቸው በሚችል ቃላት መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ውይይቱ ልጆች ለብቻቸው ከአቅማቸው በላይ የሆነውን አሊያም የሚያብሰለስሉትን ጉዳይ እንዲተነፍሡ ዕድል ይሠጣል፡፡
ሌላው የወላጆች /አሣዳጊዎች የአብሮነት ማረጋገጫ ቃላት፣ ለልጆች ከባድ ጊዜ እፎይታን ይሠጣቸዋል፡፡ ለምሳሌ ‘’ሁልጊዜ አንተን/ቺን ልጄን እንከባከባለሁ’’ ፣‘’ሁሌም ከጎንህ/ሽኝ ነኝ’’ የሚሉ ማረጋገጫ ቃላት ሥነልቦናዊ ፈዋሽነት አላቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቤት ውስጥ ያለው ከባቢ ሁኔታ የልጆችን የስሜት ደህንነት ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡ ወላጆች/አሣዳጊዎች በጦርነትና በግጭት ወቅት ከልጆች ጋር የሚያሣልፉትን ጊዜ ሠፊ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ የልጆችን የስነልቦና ጤና ለመጠበቅ በተለይም በጦርነት ወቅት የመገናኛ ብዙኃን አጠቃቀም ገደብ ሊኖረው ይገባል፡፡
ምንም እንኳን  የጦርነት ወቅት ለወላጆች /አሣዳጊዎችም ጭምር ከባድ ጊዜ ቢሆንም፣ ወላጆች /አሣዳጊዎች ራሳቸውን በተቻለ መጠን በማረጋጋት ለልጆች ተምሣሌት ሊሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወላጆች /አሣዲጊዎች በልጆቻቸው አእምሮ ላይ ተስፋን የሚያነቃቃና የሚያበረታታ ገንቢ ሀሳብ ሊዘሩ ይገባል፡፡ ሠላማችሁ ይብዛ!
(Resilience In Children Exposed To Trauma, Disaster And War Global Perspective From University Of Minnesota.)

Read 1707 times