Tuesday, 08 December 2020 13:41

“የአንለይ ጥላሁን ትችትን” ሲተች!

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)


            “ከመደነጋገር መነጋገር”ን እንዳነበብኩት በሚል ርዕስ  ባለፈው ህዳር 12  በተወዳጇ አዲስ አድማስ ጋዜጣ የ”ጥበብ” አምድ ስር የታተመ ነፃ አስተያየት ፅሁፌ ላይ ተመስርተው “አሌክስ ዘጸአት” የተባሉ ፀሐፊ “የአንለይ ጥላሁን ትችት ሲተች!” በሚል ርዕስ በህዳር 19 ዕትም፣ በጥበብ አምድ ስር  ያቀረቡት ለቅሶ የበዛበት ትችት ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ሆነኝ፡፡
በእርግጥ ባለፈው ፅሁፌ ላይ በዝርዝር ያልዘለቅሁባቸውን የመፅሐፉ ክፍሎችንም አካትቻለሁ፤ አስረጅ ይሆነኝ ዘንድ፡፡
ፀሐፊው “አሌክስ ዘጸአት” በፅሑፋቸው ሁለተኛ አንቀፅ ላይ “በአጠቃላይ መጽሐፉ በስምንት ምእራፎች የተዋቀረ ቢሆንም አቀማመጣቸው ምክንያታዊ አይመስለኝም” በሚል ምክንያት አልባ ድምዳሜ ትችቱን መቋጨቱ፣ ግለሰቡ መፅሐፉን ጨርሶ አለማንበቡን እንድጠረጥር አድርጎኛል።” በማለት የገለፁትና በሶስተኛው አንቀፅ መጨረሻ ላይ ደግሞ “ደራሲውን “ፅንፈኛ” ብሎ የፈረጀበትን ጉዳይ አንለይ ጥላሁን ...በማለት የጀመረው ሂስ ወ አስተያየት፤ በጥቂቱ ለዚህ ፍረጃ ካበቃው በሰፊው ለመግለፅ ቢነሳ ምን ይል እንደነበር የሚያውቀው ፀሐፊው ብቻ ነው።” እንዲሁም ቀጥሎ ባለው አንቀፅ ላይ “...የጀመረውን መልዕክት ሲቋጭ፣ ከመፅሐፉ ምንም ዓይነት ገንቢ ነገር ያላገኘበት መሆኑን በገደምዳሜ ነግሮናል።...” በማለት የጥንቆላ ባህሪ አሳይተዋል፡፡ ግን እንዴት ፅሁፉን መረዳት አልቻሉም? ምክንያቱም የተሰማኝን ከመረጥኩት የመፅሐፉ ክፍል የመጥቀስ መብት አለኝ፡፡
እነኝህንና ሌሎች የተችውን ነጥቦች እንደ አስፈላጊነቱ በመጥቀስ ስለ መፅሐፉ ተጨማሪ  አስተያየቶች አክያለሁ፡፡
መናገር ወይም ንግግር ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሠብዓዊና አንደበታዊ የመግባቢያ ክህሎት ነው፡፡ ይህ ክህሎት በህልውናችንና በኑሯችን ላይ ያለው ሚና ወደር የለሽ ነው፡፡የህልውናችን መስፈሪያዎች ወይም ሚዛኖች ሁሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ የሚመሰረቱት በንግግር ችሎታችን ላይ ነው፡፡ ለዚህም ነው፤ ዶ/ር ሳሙኤል ወልዴ “...ንግግርም የማያቋርጥ የሕያውነት ምልክትና የማይታየው የምናቡ ዓለም ነጸብራቅ ነው” የሚሉን (ገፅ 45)። እዚህ ላይ ንግግር ለሠብዓዊ ፍጡር ሁሉ የተሰጠ መለያ ባህሪው ነው፡፡
“ባህሪ ሁሉ ቋንቋ ነው! ...ሐሳብ የሚተረጎመው በቋንቋ ነው፡፡ የሚቀዳውና የሚንሸራሸረው በቃላት፣ በዝምታ፣ በድርጊትና ባለማድረግ ነው፡፡ የስውሩ ዓለም ጠሊቅ ምክር በአንደበት ቃል፣ በአቋቋም፣ በአቀማመጥ፣ በአካሔድ፣ በአስተያየት፣ በአይን አከፋፈት፣ አዘጋግ  ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፋል፡፡ እንዲሁም በአብዛኛው እጅ፣ አንዱ ከአንዱ ጋር የሚነጋገረውና ሐሳቡን ለመግለጽ የሚወናጨፈው፣ ቃላት አልባ በሆኑ የሰውነት ውዝዋዜዎችና የፊት ገጽታ ነው፡፡
ምንም እንኳ በዚህ መንገድ የሚተላለፈው መልእክት፣ በቃላት ተቀርጾ በድምፅ ወይም በብዕር ቀለም ከሚፈሰው ንግግር፣ መጠኑ የበዛ ቢሆንም፣ በተቀባዩ ወይም በተመልካቹ ዘንድ የሚፈጥረው ግንዛቤ ያወዛግባል። መልዕክተኞች በገፅታቸውና በቃላቸው ሁለት ተፃራሪ መልእክቶችን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም እንደ ፀሐይ በፈካው ፈገግታ ጥላቻን መሰወር ይቻላል፡፡ አቅፈው እየሳሙ ለገዳይ አሳልፎ መስጠት አያቅትምና። የሚገፋተር የፊት ገፅታ ተላብሰው “እንኳን ደህና መጣህ!” ሊሉ ይችላሉ፡፡” (ገፅ 45)
የሐሳብና የስሜት ተራክቦ የሚከናወንባቸውን ስልቶችና መንገዶችን ዘርዘር ባለ ሁኔታ ያሰፈሩት የተግባቦትን ሂደትና አስቸጋሪነት ለማመልከትም ጭምር ይመስላል፡፡ በእርግጥ ጥያቄ የሚያስነሳ አሻሚ ጉዳይንም የያዘ አገላለፅ ነው፡፡ ምክንያቱም የተግባቦትንና የንግግርን እንዲሁም የሃሳብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን በግልፅና በማያሻማ መንገድ ማስፈር አልተቻለምና፤ ነው፡፡ ተድበስብሷል፡፡ ለእንደዚህ አይነት አሻሚ አገላለፆች (መድበስበስ) ተጨማሪ ምሳሌዎችን ከመፅሐፉ ላይ ልጥቀስ (ከበርካታዎቹ ጥቂቱን)፡፡
““መነጋገር ማለት ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ ከመዳሰሳቻን በፊት ንግግር ለምን አስፈለገ የሚለውን ቁም ነገር እናንሳ፡፡ መነጋገር ለምን?" (ገፅ 41)
ይህ አገላለፅ ከሰዋስው ስህተቱ ባሻገር እርስ በርሱ የሚጋጭ (የተድበሰበሰ) ነው፡፡ መነጋገርንና ንግግርን አንድ አድርጎ ያቀረበ ነው፡፡ ማለትም “...በቅድሚያ (በፊት) ንግግር ለምን አስፈለገ...”? (ጥያቄ ምልክቱ የእኔ ነው፤ ለአፅንኦት)  የሚለውን ቁም ነገር እናንሳ ካለ በኋላ  ተመልሶ “መነጋገር ለምን?”  ይልና ምሳሌ ማቅረቡን ይቀጥላል፡፡ ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ ስለሆነም ሊተላለፍ የተፈለገው ጉዳይ ስለ ንግግር ወይስ ስለመነጋገር ? የሚል ብዥታ ውስጥ ይከታል። የተዋጣለት ፅሁፍ ደግሞ የተነሳበትን ነጥብ በትክክል ማስገንዘብ አለበት፡፡
ሌላ እርስበርሱ የሚጋጭ ሀሳብን የያዙ አገላለፆች እናንሳ፡፡
“ማን ይናገር? ሲባል ውስጡ ያልተመቸው፣ የመረረው ሁሉ ይናገር፤ ንግግር የነፍስ መስኮት ስለሆነ፡፡...” (ገፅ 116) ይህ አገላለፅ ለአንባቢ የሚሰጠው መልዕክት የተዛባ ይመስለኛል፡፡ መናገር ያለበት ያልተመቸው ነው?.. .የንግግር መነሻው የትኛውም ማህበራዊና  ተፈጥሯዊ ጉዳይ ነው፡፡ የመረረው፣ ያልተመቸው ...ሲባልስ በምን ጉዳይ ላይ?... መቼም ሁሉም ሰው ለመናገር እስኪቸገር እስኪመረው መጠበቅ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ንግግር ለሁሉም ሰው እኩል የተቸረ ፀጋ ነውና፡፡
እንዲሁም በመፅሐፉ “ስለ ስሜት” ሠፋ ያለ ትንታኔ ተሰጥቷል፤ማለትም ስሜታዊነት የሚያስከትለውን ቀውሶች። ያም ሆኖ በአብዛኛው የሚያመዝኑት ወደ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነው፡፡
“..ስሜታዊነት ኅብረተሰብን ለተግባር “ሆ!” ብሎ በጅምላ ለማነሳሳት የማነቃቂያ ሞተር ቢሆንም፣ በአግባቡ፣ በቅን ምክር ካልተቃኘ ግን የሚያስከትለው ጉዳት በደረሰ መስክ ላይ ከዘመተ የአንበጣ መንጋ አይተናነስም፡፡ የስሜት ፍንዳታ አይሎባቸው ፣ለመሰንበቻቸው የሚያዛልቅ ምክር አልሰማ ብለው ከትልቅነት ግባቸው የታቀቡ፣ የሌሎችን ተሞክሮ፣ ግራና ቀኝ በመቃኘት ትምህርት ሊቀስሙበት ይገባል። በስሜታዊነት ብቻ ሰክረው፣ በአየር ላይ ሲንሳፈፉ የከረሙ ግለሰቦች ዛሬ መሬት ላይ መውረድ ብቻ ሳይሆን አመድ ነስንሰው በቁጭት መነፍረቃቸው እሙን ነው” (ገፅ 35)
ፀሃፊው “ስሜት” እና “ስሜታዊነት”ን ቀላቅለው የገለፁባቸው በአንድ ከጨፈለቁባቸው አገላለፆች ውስጥ ከላይ ያሠፈርኩት “ጥቅስ” አንድ ማሳያ ነው። ለስሜት ያላቸውን የመረረ ጥላቻ፣ ከመፅሐፉ መግቢያ እስከ መደምደሚያ (ማጠናቀቂያ) ምዕራፎች ሁሉ በመረረ መንገድ ገልፀውታል። በእኔ እምነት ፅንፈኛ (የምሬት አገላለፆች) አቋማቸውን እንዲያንፀባርቁ ያደረጓቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም በዋናነት ግን የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ወቅታዊው የሐገራችን ፖለቲካ ምስቅልቅልና ለውጡን ተከትሎ የመጡ አመፆች ቅጥ ማጣት ከስሜታዊነት የመነጩ በመሆናቸውና ስሜታዊነትን መግሪያው ብቸኛ መንገድ ምክንያታዊ ንግግር (ምክክር) ነው ፤ ብለው ማመናቸው ነው፡፡
በእርግጥ “የመደነጋገር ዋናው ምክንያት አለመነጋገር ነው” የሚለው ሐሳብ ስለሚጎላ ለአጠቃላይ የተግባቦት ችግሮች መሠረታዊ የመፍትሔ ሐሳብ የሚጠቁሙ በርካታ ጭብጦችን መፅሐፉ አካቷል፡፡
እዚህ ላይ “አሌክስ ዘጸአት”፣ ደራሲውን “ጽንፈኛ” ብሎ የፈረጀበትን ጉዳይ አንለይ ጥላሁን “ስለ መፅሐፉ የተሰማኝን አስተያየት በጥቂቱ ለመግለፅ በማለት የጀመረው ሂስ ወ አስተያየት፤ በጥቂቱ ለዚህ ፍረጃ ካበቃው...” በማለት ላሰፈረው የጥንቆላ ሐሳብ ተጨማሪ ማሳያ ይሆነኝ ዘንድ የሚከተለውን ልጥቀስ።
“በልጅነት ዕድሜዬ የማውቀው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭምት፣ ከመናገር ይልቅ ማድመጥን የሚያስቀድም እንደ ሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ከቤተሰብ አንስቶ፣ ማኅበረሰቡንም አካቶ፣ በጥቂቱ የታዘብኩት ጉዳይ አብዛኛው ሰው፣ በሁሉም ጊዜና በሚነሱ ጉዳዮች ሁሉ ላይ ሳይታቀብ የመናገር ልምድ ወይንም በቂ እውቀት እንዳለው እንደሚገምት ተረድቻለሁ፡፡
ማህበረሰቡ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ሳይመርጥና ሳይታቀብ እንደ ምሁር ወይንም እንደ ሙያው ባለቤት የመናገር ንቃቱና ነጻነቱ ግራ አጋብቶኝ ነበር፡፡” ካለ በሗላ፣ ፅሁፉ በርካታ ምሬቶችንና ሽሙጦችን አስፍሯል፡፡ ቀጥሎም እንዲህ ይላል፤ “ይሄ በሁሉም ጉዳይ ላይ ሳይቆጠቡ አስተያየት የመስጠት ባህል ከማይምነት ውስጥ የፈለቀ ድፍረት እንደ ሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡” (ገፅ 119)  ጉዳዩ የለቅሶ ያክል በምሬት ቢገለፅም፣ ጣትን ከመቀሰር የዘለለ አይደለም፡፡ እንደ ማህበረሰብ (እንደ ሐገር) ሁሉም ዜጋ ቁጥብ እንዲሆን መጠበቅ የማይቻልና የህብረተሰብንና የግለሰብን መልከ ብዙነት መካድ ይመስለኛል፤ ሆደ ሰፊ መሆን ይገባል፡፡
ሌላው ደግሞ “ሁሉም ነገር” የሚለው የጅምላ አገላለፅ በራሱ ከጠቅላይነት የሚመነጭ  በመሆኑ  የግለሰብ  ነፃነት  (ፍላጎት)ን የሚጨፈልቅ ነው፡፡ ሀገር የፈታውም በፖለቲካችን ውስጥ ያለው ጅምላ ፍረጃ ነው፡፡ በእርግጥ መፅሐፉ “ለጁንታው ሐይል” የተፃፈ ከሆነም መልኩን ይለይ፤ በግልፅ ይስፈር፡፡ ይህንም እንድል እድል ከሰጡኝ ነጥቦች መካከል (በርከት ያለ ነጥብ እንዳለ ልብ ይባልልኝ) ለማሳያ ያክል ልጥቀስ፦
«...ምናልባትም ለእነርሱ የጊዜ እንቅስቃሴ ቆሞአል፡፡ ወደ ጫካ ሲገቡ ወደ ኋላ የተውት ኅብረተሰብ እይታና አመለካከት፣ በጊዜ ሂደት እየተለወጠ መሄዱን ግን አይተውም፡፡ ከተለዩት ህዝብ ጋር የሚያቆራኛቸው፣ አልፎ አልፎ በስሚ ስሚ የሚኖራቸው የቤተሰብና የዘመድ ንክኪ ካልሆነ በስተቀር፣ በእነርሱና “ነፃ” ሊያወጡት ጫካ በገቡለት ማኅበረሰብ መካከል፣ የአመለካከት ክፍተትና የተዘበራረቀ የአደራረግ ቅደም ተከተል ሊኖር እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ስለሆነም ያኔ ከ25--40 ዓመታት በፊት አንገብጋቢ የነበረው  ጉዳይ፣ ዛሬም ትኩስነቱን እንደያዘ አለ ማለት ከተቻለ፣ በውጭ ያሉትም ሰዎች ባለፉት ከ25--40 ዓመታት ይኖሩ ነበር ብሎ በድፍረት ለመናገር ያዳግታል፡፡” (ገፅ 194)
ከዚህም አንፃር መፅሐፉ ከተግባቦት ይልቅ ለፖለቲካ ያደላ በመሆኑ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ (የአብይን መንግስት) በሁለት እግሩ እንዲቆም ታስቦ የተሰነዘረ የግለሰብ ማስታወሻ ነው፤ ማለት እችላለሁ። ማስታወሻ ነው ያልኩትም “አፃፃፉ ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ...” ወግ የመጠረቅ አይነት  አቀራረብ ስላለው ነው፤ ለንግግር ያደላል፡፡
በምዕራፍ አምስት ስር በርካታ ነጥቦች ቢካተቱም፣ ሁሉም ትርጉም የሚያገኙት ዓብይ ርዕስ ሆኖ የቀረበው አገላለፅ ትክክል ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ማለትም ርዕሱ “ሐሳብ የሚገለጥባቸው የንግግር ዓይነቶች” የሚል ነው፡፡ በዚህም ስር ንዑስ ርዕስ ሆነው የገቡት የሚከተሉት ናቸው፡፡
ሀ. ማን አህሎኝነት (Aggressiveness)፣
ለ. ቁጡ ተግብሮ /passive Aggressive/  የሐሳብ አገላለጥ፣
ሐ. የጉልት ወይም ተከራይ የሆነ (passive) የስሜት አስተሳሰብ አገላለፅ እና
መ.የራስን ፍላጎትና ሐሳብ በግልፅ መግለጥ (Assertive) የዶግማቲዝም የንግግር ዘዴ ናቸው፡፡
እዚህ ላይ የተዘረዘሩት ነገሮች “የንግግር ዓይነቶች” ተብሎ መቅረቡ ስህተት ነው። መባል የነበረበት “ስልቶች” ወይም “ዘዴዎች” ነበር (ድምፀቱን ለማመልከት መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ በዚህም ስህተት የምዕራፉ ሐሳቦች “በርዕሱ” ምክንያት አሻሚ ሆነዋል፤ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ፡፡ አልተገናኝቶም እንተው!
የዚህ አይነት ስህተት በምዕራፍ አራት ላይም የተደገመ ይመስለኛል፡፡ ማለትም ዓብይ ርዕሱ “አዎንታዊ ግጭትን የመቅረፊያ አቀራረብ” የሚል ሲሆን በስሩ የተካተቱ ነጥቦች ግን “አሉታዊ ግጭትን” የመቅረፊያ መንገዶች ናቸው። አይ” አዎንታዊ ግጭትን” የሚመለከት ነው ከተባለም ለአንባቢ በቂና ግልፅ ፈር ማስያዣ ትንተና ሊሰጥበት ይገባ ነበር፡፡
አለመነጋገር የሚያስከትላቸው ጉዳቶችም በዝርዝር ተጠቁመዋል፡፡ ለማሳያ ያክል የሚከተለውን እንመልከት፡፡
“አለመነጋገር መደነጋገርን ይፈጥራል። በቤተሰብ በኅብረተሰብ እንዲሁም በዜጎች መካከል ጥርጣሬን ያረባል ያራባል፡፡ በግልፅነት ካለመነጋገር የተነሳ በቤተሰብ በማህበረሰብ እንዲሁም በዜጎች ዘንድ ክፍተት ሲፈጠር፣ በሒደት ጥርጣሬ ይንሰራፋል። የአመለካከትና የአስተሳሰብ ክፍተቶች፣ ትክክለኛው የመረጃ መንሸራሸሪያው እንዲስተካከል  ካልተደረገ፣ የማህበረሰቡ አባላት እንደገባቸው፣ ክፍተቱን ለማጥበብ መላምት እንዲመቱ ይገደዳሉ” (ገፅ 36)::
የትኛውም ግለሰብ ለሚገጥመው ችግር ስነልቦናዊና አካላዊ ቀውሱን ለመቋቋም በራሱ መንገድ መፍትሔ ይፈልግለታል። ሆኖም ግን እንደ ህብረተሰብ የጋራ ችግር በጋራ ለማስወገድ ወሳኙ መንገድ የጋራ ግንዛቤ መያዝ መሆኑም አጠያያቂ አይደለም። ስለሆነም እንደ ህብረተሰብ በርጋታ የመነጋገር ባህል ማዳበር የሚከተሉት ጥቅሞች እንዳሉት በመፅሐፉ ተጠቅሷል፡፡ እነሱም፦
1.“በመነጋገር የጋራ አላማን ማስጠበቅ ይቻላል”፣
የህብረተሰብ መሠረቱ የጋራ ጉዳይ በመቅረፅ ሲሆን የጋራ ዓላማ ደግሞ ከነቃ ተሳትፎ ይመነጫል፡፡ ስለሆነም በግልፅ የተመከረበት ሀሳብ ፣በጋራ የዳበረ ጉዳይ ሩቅ ለመራመድ ጉልበት አለው፡፡
2. በመነጋገር የጋራ ግንዛቤ ይፈጠራል እና
3. በመነጋገር ጥርጣሬና ሐሜት ይጠፋል የሚሉት ናቸው፡፡
ስለ መፅሐፉ ተጨማሪ ነጥብ ከማንሳቴ በፊት “አሌክስ ዘጸአት” የተባሉ ተቺ  "ከገፅ 35፣ 36 እና 45 ላይ የተቀነጨቡ አውዶች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሳያንስ ...ግለሰቡ መጽሐፉን ጨርሶ አለማንበቡን እንድጠረጥር አድርጎኛል፡፡”  ላሉት መልሴ ምነው እርስዎስ ገፅ 98 ላይ ቆሙ?...የሚል ይሆናል፡፡ የመፅሐፍ ዳሰሳዎን ከአስተያየት ከፍ ካደረጉት አይቀር የመፅሐፉን ዘውግ፣ የጭብጥ አደረጃጀቱን ኪናዊ ፋይዳ (ስነፅሁፉዊ ውበቱን) ከቅርፃዊ መመዘኛ ጋር አስተሳስረው ብልጭ የምትል እውነት ነፈጉንሳ? “ወደ ውስጥ ስንዘልቅ” በሚል ርዕስ ያሰፈሩት ረጅም ሐተታ ሙሉ በሙሉ የእርስዎ እንጂ የመፅሐፉ ስለመሆኑ የጠቀሱልን አንድም ማስረጃ የለም። በተጨማሪም “የመፅሐፉ ጠንካራ ጎን”  በሚል ካሰፈሯቸው ነጥቦች መካከል የቃላት አመራረጡና የስነፅሁፍ ውበቱን ለማሳያ የሚሆን ነጥብ አልጠቀሱም፡፡
በአጠቃላይ መፅሐፉ በርካታ ጭብጦች የተዋቀሩበት ሲሆን ለሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች መፍትሔ የሚሆኑ የተባሉ  ጠቃሚ  ነጥቦችን አካቷል፡፡ ለግለሰብ ሰብዓዊ ልማት አስተዋፅኦ ያላቸው ዝርዝር ነጥቦችም ተካተውበታል፡፡ ደራሲው እጅግ የተማሩና በህይወት ልምድ የዳበሩ ስለመሆናቸው በመፅሐፉ መግቢያዎች ተደጋጋሚ ምስክርነት ተሰጥቷል፡፡ ይህም በጣም የሚያኮራና ለደራሲ ስንቁ ነው፡፡ ነገር ግን የመፅሐፉን አወቃቀር፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ሥነፅሁፉዊ ፋይዳና የጭብጥ አመራረጥ ወዘተ...በሚመለከት በቂ ሙያዊ (የአርትኦት) ድጋፍ አለማግኘታቸው የሐሳባቸውን እንቁነት ዋጋ ዝቅ አድርጎታል፡፡ ይህን ጉዳይ በቀጣይ እትሙ የሚመለከተው አካል ቢያስብበት ለሐሳብ ልዕልና የሚያበረክተው  አስተዋፅኦ የላቀ ይሆናል፡፡
ቸር እንሰንብት! አገራችን ሰላሟ ይብዛ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡Read 1055 times