Tuesday, 08 December 2020 13:47

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(6 votes)


                  ጥንቸል መጠጥ ጠጥታ፣ ድብን ብላ ትሰክራለች:: እንቅልፏን ስትለጥጥ አዳኞቹ ደርሰው ከሷ ጋር የነበሩትን እነ አንበሶን፣እነ ዝሆንና ነብርን ገድለው ይሄዳሉ አሉ- እሷ የሞተች መስሏቸው ትተዋት። ከእንቅልፏ እንደነቃች ከሩቅ የመጣ መንገደኛ በአጠገቧ ሲያልፍ መተከዟን አይቶ፡-
“ጤና ይስጥልኝ እትዬ ጥንቸል!” በማለት ሰላምታ አቀረበላት፡፡
“ጤና ይስጥልኝ ወዳጄ!”
“ምነው ተክዘሻል? ይኸ የማየው ጉድስ ምንድን ነው?”
“እባክህ… ተወኝ…… እንዴት አልተክዝ?”
“ምን ተፈጠረ ?”
ጥንቸል እራሷን እያወዛወዘች……..
የሆነውን ነገረችው፡፡ መንገደኛው ማዘን ሲገባው፤ እየተንከተከተ መሳቅ ጀመረ……ምን ብላው ይሆን?
*   *   *  
በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣነት ወደ ሳውዲ አረቢያ በማቅናት፣ አቻዎቸው ከሆኑት ሼኮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ የኢራኑ የኒዩክለር ሳይንቲስትም በርቀት የቴክኖሎጂ መሳሪያ ሕይወታቸው ያለፈው በዚሁ ሰሞን ነው፡፡ የኢራን ባለስልጣናት ግድያው የተፈፀመው በእስራኤል የስለላ ድርጅት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ቴል አቪብ ግን እንግዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ከማለት ተቆጥባለች፡፡ በቀደም ማክሰኞ ዕለት ደግሞ ትውለደ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ሴት ሚኒስትር የሚመራ የእስራኤል ልዑካን አዲስ አበባ ገብቷል፡፡ ሚኒስትሯ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳያቸውን ሲጨርሱ እግረ መንገዳቸውን 500 ቤተ እስራኤላውያንን  ይዘው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሰምቻለሁ፡፡ ምን አለፋችሁ……. በዚህ ሳምንት ሁሉ ነገር እስራኤል፣ እስራኤል ይሸታል፡፡ ... ለምን ይሆን?
በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 10 ቁጥር 1 እና ከቁጥር 22 እስከ 32 እንዲሁም በክሮኒክለስ ምዕራፍ 1 ቁጥር ከ17-28 ድረስ እንደ ተፃፈው፤ ከክርስቶስ ልደት 4000 ዓመተ ዓለም  ቀደም ብሎ የሦስት ታላለቅ እምነቶች አባት የሚባለው አብርሃም (Abram) ከሚኖርባት ሰሜናዊ ግዛት ከሚገኘው ሱርያ አካባቢ ከነበረችው የዑር ቀበሌ (Ur of the chaldians)  ተነስቶ ወደ ሱዳን ከነዓን ምድር አቀና፡፡ አብርሃም ወደዚህ ቦታ የመጣው አምላኩ (እግዜር) ”የከነዓንን ምድር ልጆችህ ሰጥቻለሁ” (ዘፍጥረት 11፡31/.12.37.)”በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈፀም ዘንድ ነበር፡፡
ትንቢቱን ወደ ጎን ከገፋነው የአብርሃም ታሪክ እንደ ማንኛውም ሰው ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖርና የመዋለድ ታሪክ የተለየ አይሆንም ነበር። የሆነው ሆኖ….. ታላቁ አባት ከተስፋይቱ ምድር ደርሶ ሳራን አግብቶ ይስሃቅን ወለደ። ይስሃቅ ደግሞ “ እስራኤል” ተብሎ የተሰየመው ያዕቆብን ወለደ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 32፡ 27-29)… ያዕቆብም የአስራ ሁለት ልጆች አባት ሲሆን ልጆቹ የአስራ ሁለት ነገደ እስራኤል መነሻ መሆናቸው በቅዱሳን መፃህፍት ላይ ሰፍሯል። በዚያው ዘመንም ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል ልጆች አንደኛው “ይሁዳ” በሚባለው ስም የአይሁድ ሃይማኖት  “Judaism” መጠራት እንደ ጀመረ ተፅፏል።
ወዳጄ፡-  “ሁሉም እስራኤላዊ የያዕቆብ ዝርያ ነው፣ ንጉስ ዳዊትና ታላቁን ቤተመቅደስ የገነባውን የልጁ የሰለሞንም መስመር ከዛ የቀጠለ ነው” የሚለውን ትርክት ብዙ የታሪክ አጥኚዎች አይቀበሉትም። ይህ እግዜርን የግል (Personal) የሚያደርገው ትርክት፤ ተቀባይነቱ የዘለቀው ከክርስቶስ ልደት ሰባ ዓመታት ቀድም ብሎ በተደረገው የሮማውያን ወረራ ብዙ የዕምነትና የታሪክ ድርሳናት በመቃጠላቸውና ማመሳከሪያ በመጥፋቱ ምክንያት እንደሆነም ሊቃውንቱ ይናገራሉ። የአይሁድ እምነት መሪዎች  ግን አሁንም አንድ ቀን ከዚሁ የአይሁድ ነገድ የሚመዘዝ መሲህ ይመጣል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።
ይሁዳውያን በግብር ተፈፀመ በማለት ማስረጃ ከሚያቀርቡባቸው ትንቢቶች ውስጥ አንደኛው “ቤተ መቅደሴን መልሼ እሰራዋለሁ፣ እናንተም ወደ ነበራችሁበት ትመለሳላችሁ” የሚለው ሲሆን እንደተባለውም በ539 ዓ.ዓ ፐርሺያኖች ባቢሎናውያንን ወግተው ሲያባርሩ፣ ቤተ መቅደሱ እንደገና ተገንብቷል። እንደዚሁም ሜቅዶኒያዊው እስክንድር ወደ አገረ እስራኤል ሲመጣ የአይሁድ አባቶች የኢየሩሳሌምን በሮች ከፍተው በመቀበል፣ ከ200 ዓመታት በፊት የሱ ንግስናና ታላቅነትን ነቢያቸው ዳንኤል ተንብዮ እንደነበረ ከቅዱሳን መጽሃፍቶቻቸው ላይ እንዳስነበቡት የሚገልፀው ታሪክ ይገኝበታል። በነገራችን ላይ መጽሃፈ ዳንኤል፣ የእስራኤላዊ ማንነት የተቀረፀበው “ከግሪክ አእምሮና ከሮማውያን ሰይፍ” እንደሆነ የሚያትቱ መስመሮች እንደሚገኙበት ታሪክ ፀሃፊዎቻቸው ዮሴፍ ቤንማቲ ያሁና ማክስ ዴሞንት  “Jewish antiquities” በሚለው መጽሐፍ፤ በአስራ አንደኛ ቅፅ ምዕራፍ አስራ ሶስት ላይ አስፍረዋል።
ወዳጄ፡- የአይሁድ ሃይማኖት ለሌሎች ብዙ እምነቶችና ሴክቶች መሰረት እንደሆነ አያጠራጥርም። ታላላቅ ባህላዊ እምነቶች ለሆኑት ክርስትናና እስልምና ግን በእጅጉ ተወራራሽ የሆኑ ጉዳዮች አሉት። (ቅዱስ ቁርዓን ሱራህ 2፡49-57፣ ሱራህ 32፡23-24 መመልከት ይቻላል።)
አይሁዳዊነት ለምሳሌ ከባህላዊው ኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር በሰንበት አከባበርና በመስዋዕት አቀራረብ ፍፁም የሆነ ተመሳሳይ  ልማድ ነበረው። አሁን  አሁን ግን በብዙ የክርስቲያን ማህበረሰብ እነዚህ ልምዶችና ህጎቻቸው እየተሸረሸሩ፤ እየተሻሩና በአዲስ ኪዳን ትምህርቶች እየተተኩ መጥተዋል።
በኛ አገር ዐውድ ደግሞ በተለይ በቀድሞ ስርዓተ ነገስታት ዘመን ሰለሞናዊው የዘር ሃረግ  ቆጠራ፣ የታቦተ ፅዮን መምጣትና የፈላሻነት ባህሪ ታይታ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ቤተሰባዊ አድርጎታል።  ለምሳሌ እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም እስራኤላውያን የራሳቸውን ነፃ መንግስት ለማቋቋም ደፉ ቀና በሚሉበት ወቅት አገራችን ለፍልስጢኤማውያን በመወገን ከእስራኤል መንግስት ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጣ እንደነበር ይታወቃል። ሆኖም በዲቪድ ሞንጎርዮን ይመራ ለነበረው ንቅናቄ  ከአውሮፓ ሃገራት የጦር መሳሪያዎችን በራሷ ስም በመግዛት ከጣሊያን ወደብ በሚስጢር እንዳስጫነች ዶሚኒክ ላፒየርና ፍሬዴሪክ የሚባሉ ሁለት ፈረንሳውያን ፀሃፍት “… Is Paris burning?” በሚለው  መጽሃፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። ይህም ጉዳይ ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነታቸው በተቋረጠበት ወቅት እንኳ ታሪካዊ ቁርኝታቸው በዋዛ የሚላላ እንዳልሆነ ያመለክታል።
በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን የBBC ዓለማቀፍ ሬዲዮ ባወጣው ዘገባ ላይ በወንጀል የሚፈለጉትን የህወሃት መሪ የዶ/ር ደብረፅዮንን ስም  “Mount Zion” ማለት ነው ብሎ እንደ ፃፈ ተመልክቻለሁ።
ወዳጄ፡ እስራኤል ትልቅ ስም ያላት ሃያልና የሰለጠነች ግን ደግሞ ኩርማን የምታክል ሃገር ናት።… ለምን?... ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- መንገደኛው ሰው የሞቱትን አራዊት አይቶ ጥንቸሏን…
“ምን ተፈጠረ?” ብሎ ሲጠይቃት
“ስጠጣ የማደርገውን አላውቅም” በማለት ነበር በሃዘኔታ የመለሰችለት።
ሠላም!

Read 1137 times