Print this page
Tuesday, 08 December 2020 13:50

"ውጊያው ቀጥሏል፤ የኢትዮጵያን ሠራዊት ፈጅተነዋል"

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

   ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቀድሞው የህወኃት ቡድን፣ "ጁንታው" የሚል ስያሜ የሰጡት በሰሜን ዕዝ ላይ ዓለም ያወገዘውን አሰቃቂ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ነው፡፡ ብዙዎችም ከቀድሞው ስሙ ይልቅ አዲሱን ስሙን ወደውለታል፡፡ ሁሉም "ጁንታው! ጁንታው!" ሲል ነው የሰነበተው፡፡
የጁንታው ቡድን በተለይ ካለፉት 3 ሳምንታት ወዲህ "ነጫጭ" ውሸቶችን እንደ ጉድ እየፈበረከ ነው፡፡ ሰሞኑን የትግራይ "መከላከያ ሃይሎች" ቃል አቀባይ የሆነው ታጋይ (ኮሜዲያን) ከተሸሸገበት ዋሻ ወጥቶ ቦንብ የሆነ ውሸት አዝንቦብናል፡፡ "ጦርነቱን በመቀሌ ዙሪያ እያካሄድን ነው፤ የብልጽግናን ሰራዊት ከፈጀን በኋላ ከኤርትራ ወታደሮች ጋር እየተዋጋን ነው" በማለት፡፡ "ባለፉት ሁለት ሦስት ቀናት 11 ታንኮችን አቃጥለናል" ሲልም ሌላ ውሸት አክሏል፤ ቃል አቀባዩ፡፡  ልብ በሉልኝ፤ ታጋዩ ይሄን ያለው የፌደራል መንግስቱ የህግ ማስከበር ዘመቻውን ማጠናቀቁን ያፋ ካደረገ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው፡፡ ጠፍተው የሰነበቱት አቶ ጌታቸው ረዳም ዝም አላሉም፡፡ ድንገት ብቅ ብለው የቆመ ጦርነት የለም አሉን፡፡ "የዐቢይና የኢሳያስ ወታደሮች ትግራይን ለማጥፋት በትጋት  እየሰሩ ነው" ሲሉም ከሰዋል፤ አቶ ጌታቸው፡፡ ("ነጫጭ ውሸቶች"!)
የመከላከያ ሰራዊት መቀሌን በቁጥጥሩ ስር ከማድረጉ በፊት የጁንታው ቡድን አመራሮች  ለመንግስት እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጥሪ ቢቀርብላቸውም እነሱ ግን የመረጡት ከተማዋን ጥሎ መሸሽ ነበር። ("ጠላቶቻችን ይቀበሩበታል” የሚለው ፉከራ የት ገባ?)  ባለፈው ሰኞ የህወኃቱ ተሳዳጅ ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ “ትግሉን በመቀሌ ዙሪያ ቀጥለንበታል” ብለዋል፤ ከተሸሸጉበት ሃገረ ሰላም ሆነው፡፡
ደብረጽዮን ባለፈው ቅዳሜ ለሮይተርስ በአጭር የፅሁፍ መልዕክት (ቲቪ ማማረጡ ቀርቷል?!) በሰጡት መግለጫ፤ “የእነዚህ ወራሪዎች ጭካኔ እስከ መጨረሻው ድረስ ለመዋጋት ያበረታታናል፤ ይኼ ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችንን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማትና ሚዲያዎች፣ ጽንፈኛው የህወኃት ቡድን፣ በማይካድራ አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈፀሙን ቢያረጋግጡም፣ ቡድኑ ግን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብሏል፡፡ በእርግጥ ከዚህ ቀደም የጁንታው ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ በትግራይ ቲቪ ብቅ ብለው፣ ጭፍጨፋውን የፈፀመው የፌደራል መንግስቱ ነው ብለው ነበር - ባይደግሙትም!
ባለፈው ሰኞ መቀሌ አቅራቢያ እየተዋጉ አንደሆነ በፅሁፍ መልዕክት ለሮይተርስ የገለፁት ዶ/ር ደብረፅዮን፤ አክሱምን መልሰው እንደተቆጣጠሩና አንድ የመንግስት ሚግ-23 ተዋጊ አውሮፕላን እንደጣሉም በድፍረት ተናግረዋል፤ በሽሽት ላይ ሆነው። የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ዛይድ አብርሃ ግን “ነጭ ውሸት" ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ “የህወኃት የመጨረሻ ይዞታ የነበረችው መቀሌ ናት፤ ይህንን ሊያደርጉ አይችሉም” ብለዋል፤ አቶ ዛዲግ ለቢቢሲ፡፡  ለህወኃት ግን “ነጭ ውሸት” አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ጥርሱን የነቀለበት ነው፡፡ የህወኃት መሪዎች ባለፉት ሶስት ሳምንታት፣ በትንሹ ሶስት ጀቶችን ጥለናል ብለዋል - ዓለም አንዱንም ባያምነውም፡፡
ገራገር መሳዩ ዶ/ር ደብረጽዮን፤ መንግስት መቀሌን ከተቆጣጠረ ከቀናት በኋላ ለአሶሼትድ ፕሬስ ሰጡት የተባለው ቃለ ምልልስ “ወይ ግሩም!” ያሰኛል፡፡ (ካልሞትኩ አላምንም ይሆን?!) እናም ደብረጽዮን “እብደቱን አቁምና ወታደሮችህን ከትግራይ ክልል አስወጣ” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል - ለጠ/ሚኒስትሩ፡፡ አክለውም፤ "ውጊያው በሁሉም ግንባሮች ቀጥሏል" ብለዋል፤ አዲስ ጦርነት ፈብርከው፡፡ ልብ አድርጉ! እሳቸው ለአሶሼትድ ፕሬስ ይሄን በተናገሩ ዕለት፤ ጠ/ሚኒስትሩ ፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፤ የህወኃት አመራሮች በሃገረ ሰላም ዋሻ መሸሸጋቸውንና ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ "ትላንት ማታ አራት ሰዓትና አምስት ሰዓት ገደማ ከsituation room በቪዲዮ ላይቭ አይተናቸዋል፤ ሀገረ ሰላም ላይ ህዝቡ ውስጥ መተረማመስ ተፈጥሯል" ብለዋል፡፡  
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ "የጁንታው ቡድን ላይ እርምጃ ያልተወሰደው ሚስቶቻቸውን፣ ህፃናትንና ወታደሮችን ስለያዙ ነው፤ ነገ ግን ይሄ አይደገምም" ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፌዴሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ባለፈው ማክሰኞ እጃቸውን ለመንግስት የሰጡ ሲሆን የህወሃት ጓዶቻቸው፣ "እጅ እንስጥ፤ አንስጥ" በሚል ውዝግብ መፍጠራቸውን አልሸሸጉም፡፡ (ጦርነት ያሉት ውዝግቡን ይሆን?!)
መከላከያ መቀሌ ከመግባቱ በፊት ጁንታው እጅ እንዲሰጥ በተቀመጠለት የ72 ሰዓት ገደብ እጅ ከመስጠት ይልቅ የጅምላ ውሸቶችን መፈብረክ ነው የመረጠው። የፓርቲው አፈ ቀላጤ አቶ ጌታቸው ረዳ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው፣ የውሸት ቦንብ አዝንበውብን ሄደዋል። "21ኛውን ክፍለ ጦር  ዶግ አመድ አድርገነዋል፤ አንድ ሄሊኮፕተር መተን ጥለናል” ብለዋል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ "ትንታጉ" ሲሉ ያሞገሷቸውን ጀነራል አበባውን "ገድለነዋል” ብለው ፎከሩ። ጀነራሉም "እነሱ ሞተውም መዋሸታቸው አይቀርም!" ሲሉ መለሱ፡፡ አልተሳሳቱም!!
የጁንታው ቀንደኛ አመራሮች በቲቪ መስኮት እንደ ዘበት ብቅ እያሉ ጣል የሚያደርጓቸው አንዳንድ ውሸቶች “ቦንብ” ናቸው - አያወድሙም እንጂ። ለውጡን የተቀበሉ መስለው የሸወዱን አዛውንቱ የህወሃት ሊቀ መንበር፣ በተለይ አንድ ሌሊት በቲቪ መስኮት ብቅ ብለው በተናገሩት በእጅጉ ነው የተቀየምኳቸው፡፡ “ከዐቢይ ሰራዊት ጋር ተባብረው እየወጉን ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወታደሮች በዛሬው ዕለት ማርከናቸዋል፤ በቅርቡ ለህዝብ እናቀርባቸዋለን” ሲሉ አልጠረጠርኳቸውም ነበር፡፡ በቀትር ሌሊት ቤቴ ድረስ በቲቪ መስኮት ዘው ብለው ይዋሹኛል ብዬ አልጠረጠርኩም፡፡ በዚህም እስካሁን ድረስ ተፀጽቻለሁ፡፡ ባይገርማችሁ የዚያ ዕለት ሌሊት ብቻዬን ነበር ደብረፅዮንን በቲቪ ያየኋቸው፡፡ እናም እኔን ብቻ የዋሹኝ እየመሰለኝ አሁንም ድረስ  ብሽቀቱ አለቀቀኝም፡፡ ለነገሩ እሳቸው የዋሹት ዓለሙን ሁሉ ነው፡፡   
እናላችሁ…. እሳቸውና የጁንታው አባላት ከመቀሌ የሸሹት “ማርከናል” ያሉትን የኤርትራ ወታደሮች ሳያሳዩን ነው። (ከየት ያምጧቸው?!) ስም ማጠልሸት ሙያው የሆነው የጁንታው ቡድን፤ የመከላከያ ሰራዊት ከኤርትራ ወታደሮች ጋራ በማበር የትግራይን ወጣት እያሰቃዩና የህዝቡን ንብረት እየዘረፉ ነው ሲሉም ወንጅለዋቸዋል። ደግነቱ ግን ጨዋው የትግራይ ህዝብ የመከላከያ ሰራዊቱን ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ገና የትግራይ ልዩ ሃይል ሳይጸነስ ነው ከትግራይ ህዝብ ጋር መኖር የጀመረው፡፡
በነገራችን ላይ ውሸት ካልደባለቁ መንቀሳቀስ የማይችሉት የጁንታው አባላት፤ ውሸትን እንደ ሃሺሽ የሚጠቀሙበት ይመስላል፡፡ በውሸት ሳይጦዙ አይቀርም፡፡ ካናቢሱንም ቢሆን አይተውትም፡፡ በሰሞኑ የህግ ማስከበር ዘመቻ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለው አደንዛዥ ዕጽ መገኘቱን ፖሊስ ነግሮናል፡፡ በርካታ የጦር መሳሪያ፣ ገጀራና የወንድ ማኮላሻ መገኘቱንም ሰምተናል፡፡ ያስደነግጣል። ሁለት ሦስት ቦታ ደግሞ የጅምላ መቃብር ተገኝቷል። ሌላ ብዙ ጉድ እንዳለ ጠቋሚ ነው፡፡ አንዳንዶች ብዙ ያልተገኙ ማይካድራዎች እንዳሉ ይጠረጥራሉ፡፡ ይህን ፍሩልኝ፡፡  (ኢትዮጵያችን ፈርዶባታል!)
የጁንታው ቡድን መሪዎች እኛን ብቻ አይደለም ሲዋሹን የኖሩት፡፡ ምንም የማያውቁ የትግራይ እናቶችና  ህፃናትንም  ዋሽተዋል፡፡ ከማን ጋር እንደሚዋጉ በትክክል ሳይነግሯቸው ነው፣ ጠመንጃ አሸክመው ወደ ሞት የላኳቸው፡፡ የመቀሌ ነዋሪዎች "መከላከያው ያጠፋችኋል፤ ይዘርፋችኋል" ስለተባሉ ቤታቸውን ቆላልፈው በየዋሻውና ምሽጉ ውስጥ  ተደብቀው ነበር፡፡  ጁንታው "ወራሪው ሃይል ይዘርፋችኋል" ብሎ ስላስፈራራቸው አንድ ገበሬ፣ ያመረቱትን ሽንብራ መሬት ቆፍረው መቅበራቸውን ተናግረዋል፡፡ "የአማራ ልዩ ሃይል ያርዳል” የሚል ፕሮፓጋንዳ የተጋተች አንዲት ታዳጊ የትግራይ ታጣቂ፤ የአማራ ልዩ ሃይል  ሊማርካት ሲሞክር ሸሽታ ነው የሮጠችው፡፡ ከተያዘችም በኋላ እንደ ህፃን ልጅ ስታለቅስ ነበር - አማራ  እንዳያርዳት  በመፍራት፡፡  ይሄ ሁሉ የጁንታው ቡድን የውሸትና የቅጥፈት ፍሬ ነው። የሆነ ሆኖ ግን የትግራይ ህዝብ የማታ ማታ ማን ገዳይ፤ ማን ጨፍጫፊ፤ ማን  ዘራፊ፤ ማን አራጅ -- ወዘተ እንደሆነ  እውነቱን ተገንዝቧል። የመከላከያ ሰራዊቱ የሚያወቁት፣ የጥንቱ የጠዋቱ እንደሆነ በዓይናቸው አይተው አረጋግጠዋል። ከሁሉም ግን ጁንታው በለውጡ ማግስት ፈብርኮ ለትግራይ ህዝብ የነዛው ወደር የለውም፡፡ ለራሱ ደህንነት ሲል ቦንብ የሆነ ውሸት ለመላው የትግራይ ህዝብ ነዝቷል፡፡ “ከየአቅጣጫው  ተከበሃል፣ ተወረሃል፤" እያሉ ነው ላለፉት 2 ዓመታት በሥልጣን ላይ የከረሙት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ለማስጠላት ያልፈጠሩት ውሸት የለም፡፡ አሃዳዊ ሥርዓት እየገነባ ነው ብለዋል፡፡ ከመንግስቱ ሃይለማርያም የባሰ አምባገነን ነው ብለው ስም አጥፍተዋል፡፡ "ዐቢይ በአንበጣና በኮቪድ እያጠቃን ነው፤ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ሸጦታል" ወዘተ-- በጁንታው ያልተፈበረከ ውሸት የለም!!  


Read 4673 times