Tuesday, 08 December 2020 13:51

መኪና አስመጪዎች መንግስት እንዲደርስላቸው ተማፀኑ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   “መኪኖቻችን በወደብ ላይ እያሉ ጨረታ ወጥቶባቸዋል”
                       
             ኮቪድ 19 መከሰቱን ተከትሎ በተፈጠረ የመጓጓዣ ችግር ከውጭ ግዢ የፈፀምንባቸው መኪኖቻችን እጃችን ሳይገቡ በጨረታ ሊሸጡብን ነው ሲሉ መኪና አስመጪዎች መንግስት እንዲደርስላቸው ተማፀኑ።
አዳማ ጉምሩክ ከህግ አግባብ ውጪ በመኪኖቻችን ላይ ጨረታ አውጥቶ ባዶ እጃችንን ሊያስቀረን ነው ያሉት አስመጪዎቹ፤ መኪኖቹ ግዢ የተፈፀመባቸው ኮቪድ 19 የተከሰተ ሰሞን ቢሆንም ውቅቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት  መኪኖቹን በጊዜ አጓጉዘን መረከብ አልቻልንም ይላሉ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከውጭ ተገዝተው ለሚገቡ ዕቃዎች አዋጅ ጠቅሶ  የማጓጓዣ ጊዜው ለ6 ወር እንዲራዘም የፈቀደ ቢሆንም ጊዜ እንዲራዘምላቸው ከተጠቀሱት ውስጥ የመኪና አስመጪዎች ጉዳይ  አልተካተተም በሚል አዳማ ጉምሩክ በመኪኖቻችን ላይ ጨረታ አውጥቶ ሊሸጥብን ነው ሲሉ አማርረዋል። አስመጪዎቹ አክለውም፤ የቅንጦት እቃ ለሚባሉት ለውስኪና ቼኮሌት አስመጪዎች የስድስት ወር ማራዘሚያ፤ተጠቃሚ ሲሆኑ ከ60 በመቶ በላይ ለስራ የሚውሉ መኪኖቻችን ግን  በጨረታ ሊሸጡብን ነው ሲሉ አማርረዋል።
ኮቪድ 19 ቀነሰ ተብሎ ወደብ ስራ በጀመረበት ጊዜ መኪኖቻችንን ለማጓጓዝ ጥረት ብናደርግም በቅርቡ አገራችን ላይ በተከሰተው ችግር ምክንያት መከላከያ የራሱን መኪኖች ቅድሚያ ሰጥቶ ማጓጓዝ በመጀመሩና የእኛ ወደ ኋላ በመቅረቱ አሁን ለተጋረጠብን ችግር ተዳርገናል ብለዋል። እስካሁንም በውጭ፣ በወደብ ላይና በአገር ውስጥ የሚገኙ ከ7ቢ.ብር በላይ የወጣባቸው ከ5 ሺህ መኪኖች በላይ እንዳሉ የገለፁት አስመጪዎቹ፣ መንግስት እነዚህ መኪኖች በሰላም ለአስመጪዎቹ ቢገቡ ቀረጥና የስራ ግብርን ጨምሮ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያገኝ ቢሆንም አሁን በደረሰው ችግርና መጉላላት መንግስትም ከላይ የተገለፀውን ገንዘብ ያጣል፤ እኛም ከእነ ልጆቻችን ጎዳና ላይ መውደቃችን ነው ሲሉ መንግስት እንዲደርስላቸው ተማፅነዋል፡፡
የኛ ጉዳይ የሚመለከተው ገንዘብ ሚኒስቴር በመሆኑ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴን አነጋገረናል በማለት የገለፁት አስመጪዎቹ፣ እሳቸው ጉዳዩን በአስተዳደር በኩል እናየዋለን የሚል ቀና ምላሽና ተስፋ ቢሰጡንም አዳማ ጉምሩክ ግን ሰኞ ጨረታውን የሚከፍት በመሆኑ መኪኖቻችንን መዘረፋችን ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ የበላይ ስልጣ ባቤት የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ6 ወር ይራዘም  ብሎ የሰጠው ትዕዛዝ እንዲፈፀምልንና ግዢ የፈፀምንባቸው መኪኖቻችንን እንድንረከብ መንግስትን እንጠይቃለን ሲሉ ተማፅነዋል።Read 2033 times