Saturday, 12 December 2020 00:00

የ20ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች 12 ሺህ 500 ናቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 20 ተሳታፊዎች ባዶ እግራቸውን ይሮጣሉ


            የ20ኛው ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባው ትናንት የተጀመረ ሲሆን፤ በ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ላይ የተሳታፊዎቹ ብዛት 12550 እንደሚሆንና ምዝገባው ሰኞ ላይ እንደሚያበቃ ታውቋል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቢሮ እንዳስታወቀው የኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄዎችን ተቀዳሚ ባደረገው  ምዝገባ  በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ አሞሌን በመጠቀም መመዝገብ ይችላሉ።
የመጀመርያዎቹ 200 ተመዝጋቢዎች የመለማመጃ ቲ-ሸርት በነጻ እንደሚሰጣቸውም የተገለፀ ሲሆን የመመዝገቢያ ዋጋ 450 ብር እንደሆነና ለመመዝገብ በቴሌግራም @greatethrun መጠቀም እንደሚቻልም ተጠቁሟል፡፡ ከዓመት በፊት  45ሺ ተሳታፊዎች የነበሩት የጎዳና ላይ ሩጫው 20ኛ ዓመቱን ለማክበር ተሳታፊዎችን 50ሺ ለማድረግ እቅድ ነበረው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ መሰረት ግን በዘንድሮው ሂደት 25 በመቶውን ብቻ እንዲያሳትፍ ተፈቅዶለታል፡፡
ከኮቪድ 19 ጋር በተገናኘ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የገቢ መቀነስ፤ የውድድሮች መሰረዝ እና እቅዶችን ያለመተግበር ችግሮች ገጥመውታል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ  ኤርምያስ እንደሚናገረው በኮቪድ 19  ሳቢያ ስመገናናው ተቋም ከዓመታዊ ገቢው ግማሹን አጥቷል፡፡ ይህም የተሳታፊዎች ብዛት 75 በመቶ ቀንሶ ከምዝገባ የሚገኘውን ገቢ ስላስቀረው፤ ከስፖንሰሮች ጋር የሚገባው ውል በመከለሱ የተፈጠረ ነው፡፡  
ተቋሙ  በኢትዮጵያ የኮሮና አዋጅ ከመነገሩ በፊት የ5ኪሜ  የሴቶች ሩጫን ባለፈው ዓመት ማርች 8 ላይ አካሂዷል፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በአውሮፓ ህብረት የሚዘጋጅ የህፃናት ውድድር፤ የጎዳና ሪሌ ሌሎችንም የውድድር እቅዶች ሰርዟል፡፡ የውድድር መርሃ ግብሮችን መሰረዝ ግን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አልወሰነውም፡፡ ቨርችዋል ሩጫዎችን በማዘጋጀት ተሳታፊዎች ሳይገናኙ በያሉበት ሆነው ውድድር የሚያደርጉበትን አሰራር  ፈጥረዋል፡፡  በመጀመርያ ደህና እንሁን ከዚያም ተስፋን መርህ ባደረጉ የቨርቹዋል ሩጫዎች ሺዎችን አሳትፈዋል፡፡
የ20ኛውን አመት ክብረ በዓሉን በተለያዩ መርሃግብሮች ለማድመቅ ጥረቱን ቀጥሏል። ስለዚህም ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች ተሳታፊዎችን ለማካተና በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ ለመስራት ማቀዱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዋናው የ10 ኪሜ ውድድር ጋር በተገናኘ በየዓመቱ በዋዜማው ቀን ይደርግ የነበረው የህፃናት ሩጫ ዘንድሮ አይካሄድም፡፡ "1000 ህፃናትን በቨርቹዋል ቴክኖሎጂ በያሉበት ሆነው ከቤተሰቦቻው ጋር ሆነው በመወዳደደር ሜዳልያ ልንሸልማቸው ወስነናል" ሲልም ኤርምያስ አየለ ለስፖርት አድማስ ገልጿል፡፡ ቨርቹዋል ሩጫ  ሰው ሳይገናኝ በራሱ ቦታ ሆኖ አዘጋጆች በሚገልፁት የውድድር ርቀት የሚሮጥበት ሲሆን በስልኩ ላይ በሚገኝ የአፕሊኬሽን በመመዝገብ እና ውጤቱን ለአዋዳዳሪው አካል በማስገባት ተሳትፎ የሚያደርግበት ነው፡፡ በአካል ሳትገናኝ በሚመች ቦታ በመሮጥ መወዳደር የሚቻልበት ነው፡፡ በኮቪድ ምክንያት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለውድድሩ የሚመጡት በጣት የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡
ዋና ስራ አስኪያጁ ኤርምያስ አየለ ለስፖርት አድማስ ሲናገር "በኮቪድ 19 ምክንያት  ለ20ኛው ዓመት ልዩ ክብረ በዓል  እንዳሰብነው 50ሺ ተሳታፊዎችን ለማስሮጥ አልቻልንም። 2ኛውን ስናዘጋጅ የነበረን ተሳታፊ ብዛት አሁን በ20ኛው ላይ እናስሮጣለን ማለትነው። የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ያደረጉ በርካታ ዝግጅቶችን ማድረግ አልቻልንም። ዋናው ውድድር በሚካሄድበት መደበኛው የህዳር 6 ቀን ላይ በእንጦጦ ፓርክ ላይ የሩጫ እና የሳይክል ኢቨንት አድርገናል፡፡  በ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ላይ ከያዝናቸው እቅዶች ዋንኛው 20ኛ ዓመቱን በማሰብ 20 ሰዎች በባዶ እግር ሩጫቸውን እንዲሳተፉ ነው። የአበበ ቢቂላን ታሪክም መዘከር እንፈልጋለን፡፡" ብሏል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለስፖርት አድማስ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የውድድሩ መነሻ መስቀል አደባባይ ሆኖ መድረሻው አትላስ አከባቢ መሆኑ ነው፡፡ ተሳታፊዎች ውድድሩ ሊካሄድ 10ቀናት ሲቀሩት የመወዳደሪያ ቲ-ሸርት፤ የመሮጫ የደረት ቁጥር ፊደል እና ጭምብል ምዝገባ ሲያደርጉ በመረጡዋቸው የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በመሄድ መቀበል ይኖርባቸዋል። በመግለፃው በተጨማሪ እንደተገለፀው ውድድሩ የሚጀመረው በሶስት የተለያዩ ማዕበሎች (አረንጓዴ፤ ቢጫ፤ ቀይ) ይሆናል። ሶስቱ ማዕበሎች ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡበት አቅጣጫ በየቲ--ሸርት ቀለሙ ተለያይቶ የተሰየመ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማዕበልም ማህበራዊ ርቀትን ለማስጠበቅ ሲባል በ3 እና በ4 ቡድን ይከፈላል፡፡ ሩጫው በሶስት የተለያዩ መነሻ ሰዓታት የሚደረግ ሲሆን ተሳታፊዎች የሚጀምሩበትን ሰዓት እና አብረው የሚሮጡትን ቡድን ለመለየት ከሩጫ ቲ-ሸርታቸው ጋር አብረው የሚወስዱት የደረት የመሮጫ ፊደል ጠቋሚ ይሆናል፡፡ ተሳታፊዎች የመሮጫ ቲ-ሸርታቸውን ሲወስዱ አብሮ የሚሰጣቸውን የአፍና አፍንጫ ጭንብል የውድድሩ መነሻ፤ የመሰበሰቢያ ቦታና ውድድሩን ከጨረሱ በኋላ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ተሳታፊዎች መወዳደሪያ ቦታው ላይ እንደደረሱ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሰውነት ሙቀት ልኬት ይደረግለታል፡፡ እንዲሁም በውድድ መነሻና መድረሻ የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር ይቀርባል፡፡ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ‹‹ወፎችን ታሳቢ ያደረገ የሀይል መሰረተ ልማት›› bሚል መርህ ሲሆን በርድ ላይፍ አፍሪካ- የነጩ ጆፌ አሞራ ፕሮጀክት የዚህ መልዕክት አስተላላፊና አጋር ድርጅት ሆኖ እንደሚሰራም በመግለጫው ተገልጿል፡፡


Read 1076 times