Saturday, 12 December 2020 00:00

90 በመቶ የአለማችን ድሆች ለ1 አመት የኮሮና ክትባት ላያገኙ ይችላሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ክትባቱን ለማግኘት አመታት ሊፈጅባቸው ይችላል

            ሃብታም አገራት አጠቃላይ ህዝባቸውን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከ3 ጊዜ በላይ ሊከትቡበት የሚችል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ገዝተው ቢያጠናቅቁም፣ በመላው አለም ከሚገኙ 10 የድሃ አገራት ዜጎች ውስጥ 9ኙ ወይም 90 በመቶ ያህሉ እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2021 ድረስ ክትባቱን ላያገኙ እንደሚችሉ ኦክስፋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ክትባትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ታስቦ የተቋቋመውና አገራትንና አለማቀፍ ተቋማትን በአባልነት ያካተተው አለማቀፉ የክትባት ጥምረት አባል የሆነው ግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ አነስተኛና ዝቅ ያለ መካከለኛ ገቢ ያላቸው 67 የአለማችን አገራት በመጪው የፈረንጆች አመት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ማዳረስ የሚችሉት ለ10 በመቶ ዜጎቻቸው ብቻ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
አገራት የኮሮና ክትባትን ፈጥነው ለማግኘት እሽቅድምድም ሲያደርጉ እንደቆዩ የጠቆመው ዘገባው፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገራትና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠና እጅግ ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ከተመሰከረላቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መካከል 53 በመቶ የሚሆኑትን ቀደም ብለው የገዟቸው ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 14 በመቶ ያህሉ ብቻ የሚገኝባቸው ጥቂት አገራት መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
ሃብታም አገራት የጀመሩት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽሚያ አንዳች ሁነኛ መላ በፍጥነት ካልተበጀለት በአለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአመታት ያህል ክትባት ላያገኙ እንደሚችሉ ስጋቱን የጠቆመው ኦክስፋም፣ ለአብነትም ከውጤታማዎቹ የኮሮና ክትባቶች አንዱ የሆነው ፋይዘር ክትባት 96 በመቶ ያህሉ በሃብታም አገራት ቀደም ብሎ መገዛቱን ጠቅሷል፡፡
ያደጉ አገራት ክትባቱን በፍትሃዊነት ለማዳረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የገቡትን ቃል በመጣስ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በመግዛት ላይ እንደሚገኙና እስካሁንም 7.3 ቢሊዮን ያህል ክትባቶች መሸጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ክትባቱን በብዛት ከገዙ አገራት መካከል በምሳሌነት ያቀረባት ካናዳ አጠቃላይ ህዝቧን ከአምስት ዙር በላይ ደጋግማ ለመከተብ የሚያስችላትን ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በገፍ መግዛቷን አብራርቷል፡፡
ስትሬት ታይምስ በበኩሉ፣ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመግዛት ህንድ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና አገሪቱ እስካሁን አስትራዜንካ፣ ኖቫቫክስና ስፑትኒክ 5ን ጨምሮ በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ክትባቶችን መግዛቷን ዘግቧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዜና ደግሞ፣ ፋይዘር የተሰኘውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት በመግዛት ከአለማችን አገራት ቀዳሚዋ በሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱ ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ባለፈው ማክሰኞ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን፣ በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩት የ90 አመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ማርግሬት ኪናን ክትባቱን ከምርምር ውጭ በመደበኛነት የተከተቡ የመጀመሪያዋ የአለማችን ሰው ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፤ አስተማማኝነቱ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውንና 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ አረጋግጫለሁ ያለችውን ስፑትኒክ 5 የተሰኘ የራሷ ምርምር ውጤት የሆነ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በመዲናዋ ሞስኮ ለዜጎች መስጠት መጀመሯንም ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከሳምንታት በኋላ ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚገቡ የሚጠበቁት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በመጀመሪያዎቹ 100 የስልጣን ቀናት ውስጥ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 100 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ክትባት እንዲያገኙ ለማስቻል ማቀዳቸውን ከሰሞኑ ማስታወቃቸውን ያስነበበው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡ የኮሮና ክትባትን በአገልግሎት ላይ ለማዋል ዝግጅቷን እያጠናቀቀች በምትገኘው አሜሪካ፤ ህዝቡ ለክትባቱ በጎ አመለካከት እንዲኖረውና ለመከተብ እንዲነሳሳ ለማበረታታት በማሰብ የቀድሞዎቹ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ቡሽ፣ ክሊንተንና ኦባማ በቴሌቪዥን እየታዩ ክትባቱን ለመውሰድ ቃል መግባታቸውም ተነግሯል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከ2.29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና በተጠቁባትና 55 ሺህ የሚሆኑም ለሞት በተዳረጉባት አፍሪካ በድምሩ 54 ሺህ ያህል የጤና ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸውንና አብዛኞቹም ነርሶች መሆናቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡


Read 920 times