Print this page
Monday, 14 December 2020 19:40

አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ የአራት ኪሎውን ግዙፍ ማዕከል ስራ አስጀመረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በማዕከሉ የኮቪድ 19 ምርመራ ጀምሯል
                            ናፍቆት ዮሴፍ


             48 ዓመታትን  በላብራቶሪ ቴክኖሎጂ አገልግሎት በመሰጠትና አሰራሩን በማዘመን የቆየው አርሾ ላብራሮሪ ቴክኖሎጂ በመሀል አራት ኪሎ ያስገነባው ባለ 6 ወለል ሪፈራል ላብራቶሪ ማዕከል ከትላንት በስቲያ አስመርቆ ስራ ጀመረ።
ለአዲስ አበባ ዘጠነኛ ቅርንጫፍ የሜዲካል ላብራቶሪ የሆነው ይሄው ግዙፍ ማዕከል የውጪ አገር ጉዞ ለሚያደርጉ ተጓዦች በ24  ሰዓት ውጤት ማሳወቅ የሚችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኮቪድ 19 ምርመራ በዚሁ አዲስ ማዕከሉ ግልጋሎት ጀምሯል።
ባሻ ወልዴ ችሎት በሚባለው ቦታ በሊዝ በተገዛ ቦታ ላይ የተገነባው ይሄው ሪፈራል የሜዲካል ላብራቶሪ ማዕከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚደራጅና እንደ እስከዛሬው ሁሉ ለህብረተሰቡ፣ ለሆስፒታሎች፣ ለክሊኒኮች፣ ለጤና ተቋማትና ለግለሰቦች ከፍተኛ ግልጋሎት ይሰጣል የተባለ ሲሆን በቅርብ የጀመረውን የኮቪድ 19 ምርመራ በመስጠትም ሆነ ኮቪድን ለመከላከልና ለማስወገድ እንደ አገር በሚደረገው ጥረት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የአርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘላለም ፍስሀ ለመገናኛ ብዙሃን ባሙያዎች ገልፀዋል።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ደቂቃ 32 ናሙናዎችን የማዘጋጀት አቅም ያለው ቴክኖሎጂ ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ ያለምንም ጥድፊያ በ24 ሰዓት ከ700 እስከ 1ሺህ ምርመራዎችን  እንደሚደርስም የላብራቶሪ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎቹ ገልፀዋል። ባለ ስድስት ወለሉ ይሄው ግዙፍ ማዕከል በምን መልኩ እንደተደራጀ ተጎብኝቷል።
አርሾ መስቀል ፍላወር አካባቢ በሚገኘው አድቫንስድ ላብራቶሪ ማዕከሉ በአራት የህክምና ምርመራ ዘርፎች ማለትም በኬሚስትሪ፣ በሄማቶሎጂ፣ በኢንዶክትሪኖሎጂና በሴሮሎጂ የISO 151:2012  ከኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ፅ/ቤት (ENAO) ሰርትፍኬት ማግኘቱን የገለፁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፣ አርሾ በአሁኑ ወቅት ለሶስት ሀኪመች፣ ለሁለት ማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ ለ29 ሜዲካል ላብራቶሪ ቴክኖሎጂስቶች ፣ ለ31 ሜዲካል ላብራቶሪ ቴክኒሽያኖች፣ ለ11 ነርሶች፣ ለ2 ራዲዮግራፈሮች፣ ለ7 ልዩ ልዩ የጤና ባለሙያዎችና 122 ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠሩም በዕለቱ ተገልጿል።

Read 3741 times