Monday, 14 December 2020 19:48

የአፍቃሪው ደብዳቤ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 "አንቺ ማለት የልቤ እረፍት፣ የመንፈሴ ወሰን፣ የሰላሜ ሰረገላ፣ ብቻ ምን አለፋሽ ዋስትናዬ ጭምር ነሽ፡፡ ማሬ… አንቺ ማለት ያሰብሁትን ሳይሆን እማይታሰበውን መጠን አልባው ግዛቴ… የኔ ሐምራዊ ግምጃ… ያሰብሁትን ሳይሆን ለማሰብ እያሰብሁ ነውና ያኛውን ነሽ መሰል…"


            ይሄ ሰው ሁለት መልክ አለው፡፡ ልክ ነጭ ሉክ ሁለት ገጽ እንዳለው አይነት፡፡ የውስጥ ሙግት እና ከውስጥ ባሻገር፡፡ የወጣት ጉልበት ያልማል፡፡ በፀሐይ የሚበገር፣ በዝናብ የሚቆረፍድ፣ በነፋስ የሚዝለፈለፍ ስላይደለ፤ ርቀቱ ወሰን አልባ ነው፡፡ ሁለት ገጽ ድርጊቱ መስፈሪያ የለውም፡፡
“…ለአፈቀረው ገጽ የመጠነ ጸሐፊ፣ ድንበር ከልሎ እንደሚጃጃል አገር አልባ አገርኛ ይቆጠራል፡፡ አንቺ አገሬ ስለሆንሽ በድንበር አልመጥንሽም፤ አንቺ የልቤ የመዐዘን ድንጋይ ነሽና፣ የትም ስፍራ ብንቀሳቀስ አንቺን እና አንቺን ከማሰብ እሚያግደኝ አንዳች ሀይል የለም! ከላይ የተቀባሽ ልዩ ሀይሌ ስለሆንሽ (ልዩ ሀይሌ አስምሪበት) የትኛውም የሰውነት ክፍሌ ደቦ ፈጥረው ይወዱሻል፡፡ የትኛውም መጠን ያለው (አስፈሪም ቢሆን) ከትሮ የገዛ ግዛቴ ናት ማለት አይችልም፡፡ ውዴ… ማሬ… አንቺ ማለት የልቤ እረፍት፣ የመንፈሴ ወሰን፣ የሰላሜ ሰረገላ፣ ብቻ ምን አለፋሽ ዋስትናዬ ጭምር ነሽ፡፡ ማሬ… አንቺ ማለት ያሰብሁትን ሳይሆን እማይታሰበውን መጠን አልባው ግዛቴ… የኔ ሐምራዊ ግምጃ… ያሰብሁትን ሳይሆን ለማሰብ እያሰብሁ ነውና ያኛውን ነሽ መሰል…
ውዴ ከእውነቴ በላይ ያለው እምነቴ ማለት ነሽ፣ ይሄ ያልገባቸው ቤተሰቦችሽ የእኔን ካንቺ ደጅ መመላለስ እንደ ድፍረትም እንደ ጅልነትም ይቆጥሩታል፡፡ አንች ማለት ለኔ እኔ ነኝ ያለ ጀግና… አልጨርሰውም ብቻ ጀግናዬም ጀግናቸውም ነሽ፡፡ ይግረማቸው ገና ያልተሰራው ታሪኬ ነሽ፣ ምንም ማይሽርሽ ዘመን ማይረሳሽ… እግዜር በቃሉ ያተመሽ ምስክሬ ነሽ ለኔ!...
ሌተ ቀን አንቺን እያልሁ ከደጅሽ እየተመላለስሁ ርግማን ባተስናግድ፣ እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ ብወገር፣ መናፈቄን የገደበው የለም፡፡
እያንዳንዷ ንጋቴ በጀምበር ልክ የተሰፋች ውበቴ ነሽ፡፡”
ይሄ 17ኛው ደብዳቤ ነበር፡፡ እያንዳንዷን ደብዳቤ ጠዋት ጠዋት ወፎች ማዜም ሳይጀምሩ የወንዝ ውሃ ሳይቀንስ፣ ለማኝ ወገቡን ሳይፈታ እንቆጳ እንደተኛች ይደርሳታል፡፡ ድንገት ካልደረሳት እያለ ከራስጌው አጠገብ ካለው መደርደሪያ ላይ ቅጅአቸው አለ፡፡ ቅደም ተከተል ያላቸውን ደብዳቤዎች በቀይ ቀለም ምልክት ያደርግባቸዋል፡፡
27ኛው…
“…ትዝ ይልሻል ሳትወድ የተሸኘች በጊዜ ዳኛነት ትመለሳለች ያልሁሽ…? ጊዜን ሚያህል ዳኛ ህሊናን ያህል ፈራጅ የትም የለም፡፡
ጊዜ ጉልበተኛን ያደልባል…
ማታ ወንድምሽ ከምዝናናበት ቦታ መጥቶ እንደዛ እስኪያስነጥሰኝ ድረስ በቦክስ አራግፎኝ ሲሄድ “ኧረ በገላጋይ” ያለው አልነበረም፡፡ አንችን መውደዴ ብቻ ጋሻ ጎኖልኝ ነበር፡፡ እማልዋሽሽ የመጀመሪያው ቦክስ ግራ ፊቴ ላይ ሲያርፍ አስር ብሎኬት የወደቀብኝ ያህል ያየሁትን ቀለም፤ እግዜር እራሱ አያውቀውም፡፡ ዞረብኝ ሳይሆን ለምድር ዞርሁባት፡፡ በቴስታ ሲደግመኝ የቦክሱን ቀለም አጣጥሜ ሳልጨርስ ሌላ የቀለም ትርክት በርከክ ብዬ ማየት ጀመርሁ፡፡ በጫማው ያጓነኝ ጊዜ ወደ ኋላ በጀርባዬ ተዘርሬ ከዛ በኋላ`ንኳ የሆነውን እርሱ ይንገርሽ፡፡ ግን ደምቼም ተደፍቼም አንቺ አንቺ ነሽ፡፡ ለወንድምሽ ግን ይሄን ሁሉ ጉልበት ለአንድ ምስኪን አፍቃሪ ከሚያውለው ብቻውን ተደራጅቶ ለሀገር ሐይል ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ የሆነው ሁሉ ሆኖ አፍንጫዬ ላይ ያለው ቁስልም እየጠዘጠዘኝ አፈቅርሻለሁ፡፡ (አፈቅርሻለሁ ላይ አስምሪበት፡፡)”
ይሄን ደብዳቤ እያነበበ የወንድሟ ሁኔታ ትዝ ብሎት ከጣሪያ በላይ ሳቀ… ሌላኛው ክፍል እናቱ ሰምተው ከሰሞኑ ሁኔታው ጋር እያያያዙት ተጨነቁ… ብቻውን እያወራ ይገባል፣ ክፍሉን ከቆለፈ ማንም ቢጠራው መልስ አይሰጥም፣ የገዛ ቆዳው እላዩ ላይ ተዝረክርኳል ሰፍቶታል ማለት ይቻላል። ለቁመተ ስጋ ያህል እህል ከቀመሰ ዞርም ብሎ አያያቸውም፡፡ ይሄ ደግሞ ለወላጅ እናት…
32ኛው
“…ሐሳብሽ እንደዚች አገር ፖለቲካ ተመሰቃቅሎብኛል፡፡” የኔ” ባይሽ በበዛበት (ይሄ እንኳን ውስጤ የፈጠረው ቅናት እንጅ የተጨበጠ አይደለም) “የኔ” አይደለሽም ለማለት ድፍረት አጥቻለሁ። ያጣሁትን ድፍረት አንቺን አግኝቼ መሙላት ስለምሻ ትዕግስቴን ከፍርሃት አትደምሪው፡፡ እሚቀየም ሊበዛ ይችላል አንቺን ማለቴን ግን አላቆምም፡፡ አራት ነጥብ… የዛሬ ጠዋቷ ፀሐይ አንቺን አይታ የምታውቅ አልመሰለኝም፡፡ ውዴ በናትሽ ለዛሬ ብቻ ውበትሽን አበድሪያት… ስሞትልሽ ለአንድ ቀን ብቻ ፈገግታ ለግሻት… መሳቅ አስተምሪያት፣ መራመድ አሳያት… ሙቀት ጽደቂባትና ልግስናሽን ታድንቅ፤ በፍንጭትሽ ማማር፣ በጉንጭሽ ስርጉድ ውበት ተደምማ መድረሻ ትጣ…? ከቤት ስትወጭ ለማየት የተለመደችው ቦታዬ ሆኜ አንቺን ስጠብቅ የጠዋት ተብዬዋ ፀሐይ እንደኔ አንቺን ለማየት ከፊት ለፊቴ በደብዛዛ ፈገግታ ትገተራለች። ምናለ ፊቷን እንኳን ብትታጠብ…? በገንኩባት ደግሞ ከፊቴ ሆና ጥርስ በሌለው አፏ ስትስቅ የጃጀች አሮጊት ትመስላለች፡፡ ድድ ብቻ፣ በሷ ተናድጄ እያለሁ ያ ወንድምሽ እንደ ገዳይ ግራና ቀኝ እየተገላመጠ ወጣ፤ ልቤ ስትከዳኝ ይታወቀኛል፡፡ የትናንትናው ደብዳቤዬ ላይ ጽፌልሽ የለ፤ በጉልበቱ እንትኔ ላይ ያለ ርህራሄ ከመታኝ በኋላ ከስልክ እንጨቱ ላይ እንደ ጃኬት አንጠልጥሎኝ ሄደ። ሰው ነበር ያወረደኝ፡፡ ላንቺ ስል ምስማር ላይም ቢሆን ተሰቅያለሁ፡፡ ይሄን መንገላታት ያዢልኝ። አሁንም ሳየው ራድሁ፤ሽንቴ አመለጠኝ አልሁሽ እንዴ? ለመፈለግ ወጥቶ የጠፋ ታውቂያለሽ፤ እኔ ነኝ፡፡ እፎይ! ሳያየኝ ወንድምሽ ሄዷል፡፡ ፊቴን እንደዚህ ጠፈጠፍ የሸረሸረው የጭቃ ቤት አስመስሎት፣ የገዛ ገጼን በመስታወት ስመለከተው እየፈራሁት ነው፡፡


Read 4089 times