Saturday, 19 December 2020 10:08

ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ - የቻይናዎች አባባል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    የተረት - አባት የሆነው ኤዞፕ እንዲህ ይለናል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ተኩላዎች ተመካከሩና መልዕክተኞች ወደ በጐች ላኩ፡፡
የተኩላዎቹ ልዑካን እበጐች መንደር ደረሱ፡፡ በጐች ተኩሎች መጡብን ብለው ተሸሸጉ፡፡
አድፍጠው ጋጣቸው ውስጥ አድብተው ተቀመጡ፡፡ ተኩሎቹ ግን ረጋ ብለው፣ አደብ ገዝተው፤
“በጐች አትደናገጡ” “እንደምና ዋላችሁ” አሉ፡፡
“ለድርድር ነው የመጣነው” አሉ ተኩሎቹ፡፡
በጐቹ ቀስ በቀስ ከተደበቁበት ወጡ፡፡
“እኛ በድርድር እናምናለን፡፡ እህስ? ምን እግር ጥሏችሁ መጣችሁ? ምን የድርድር ሃሳብ ይዛችሁ መጣችሁ?” አሉ በጐች፡፡
“አንድ የቸገረ ነገር ገጥሞን ነበርና ልናዋያችሁ ፈልገን ነው”
“ምንድነው? ከተመካከርን የማይፈታ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ዋናው ተቀራርቦ መነጋገር ነው
ንገሩን፡፡”
ተኩሎችም፤
“እግዚአብሔር ይስጥልን፡፡ የቸገረን ነገር ምን መሰላችሁ? ይኸው ከተፈጠርን ጀምሮ ከውሾች
ጋር ነጋ - ጠባ እንታገላለን፡፡ የችግራችን መነሻም መድረሻም ውሾች ናቸው፡፡ እርኩስ ውሾች እኛን ባዩ ቁጥር ይጮሃሉ፡፡ ይተነኩሱናል፡፡ ሠፈር ይረበሻል! ለእኛና ለእናንተ ወዳጅነትና ሰላም ዋናዎቹ እንቅፋቶች ውሾች ናቸው፡፡”
በጐችም፤
“ታዲያ ምን እናድርግ? ምን ዘዴ ብንፈጥር እንቅፋቶቹን ማስወገድ እንችላለን?”
ተኩሎችም፤
“እናንተ እሺ ካላችሁማ ዘዴ አይጠፋም ነበር”
“እኮ ዘዴ ካለ ንገሩና?”
“ለጌታችሁ ንገሩ፡፡ ውሾች እንዳልተመቿችሁ፣ ሰላምም እንደነሷችሁ አስረዱ፡፡ ይባረሩልን
በሉ!”
“ይሄማ ቀላል ነው፡፡ እንነግረዋለን፡፡”
በዚህ ተስማሙና ተኩሎቹ ሄዱ፡፡
በጐቹ፤ ውሾቹ እንዲባረሩ ለጌታቸው አመለከቱ፡፡ ጌታቸውም ስንት ዘመን ቤት - ደጁን ይጠብቁ የነበሩትን ውሾች ከቤት አስወጥቶ አባረራቸው፡፡
ከዚያን ቀን በኋላ፣ የዋሆቹ በጐች የዘመናት ጠባቂዎቻቸውን አጡ፡፡ ተንኮለኞቹ ተኩሎች እየተዝናኑና በጐቹን አንድ በአንድ እየለቀሙ፤ በሏቸው፡፡
* * *
የድርድርን ትርጉም አለማወቅ እርግማን ነው፡፡ ከማን ጋር ነው የምደራደረው? ተደራዳሪዬስ ሊደራደረኝ ያሰበው ምን አስቦ ነው? ጠላቴ እንኳ ቢሆን ድርድሩ ያዋጣኛል ወይ? ከቅርብ ጊዜ ግቤ አንፃር ምን እጠቀማለሁ? ከዘለቄታ ግቤ አንፃርስ ምን እጠቀማለሁ? ትላንትና ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ዛሬስ? ዛሬን በዛሬው ክስተት መዳኘት እንዴት እችላለሁ? ብሎ ማሰብ የአባት ነው፡፡
በሁለኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአሜሪካው ጄኔራል ማካርተር በፊሊፒንስ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ተደርጐ ሲሾም አንድ ረዳት መኰንን አንድ መጽሐፍ ይሰጠዋል፡፡ መጽሐፉ ከዚህ ቀደም የነበሩት አዛዦች የዋሉባቸውን ጦርነቶች ዝርዝር የያዘ ነው፡፡ ማካርተር “የዚህ መጽሐፍ ስንት ቅጂ አለ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ረዳቱም “ስድስት አሉ” አለው፡፡ ጄኔራሉም “መልካም፡፡ በል ስድስቱንም መጽሐፍት ሰብስበህ አቃጥልልኝ፡፡ እኔ የትላንትና ውሎዎች ባሪያ መሆን አልፈልግም፡፡
ችግር ሲከሰት እዛው ወዲያውኑ መፍትሔ እሰጠዋለሁ፡፡ መጽሐፍቱን በሙሉ አቃጥልና ሁኔታዎች በተከሰቱ ሰዓት እንደ ሁኔታው ግዳጅህን ፈጽም” አለው፡፡ ታሪክ የራሱ ዋጋ አለው፤ያንን እንደ ተመክሮ መውሰድ ተገቢም፣ ደንብም ነው፡፡ በትላንት ለመመካት ከሆነ ግን የግብዝ አመድ - አፋሽ መሆን ነው!
“ነበርን ማለት ግን ከንቱ ነው፣ ተውነው መጀነኑ በቅቶን
ጉራ መንዛት መዘባነን፣ የሚያዛልቅ ዘዴ ባይሆን!” ይለናል ኦቴሎ የሼክስፒሩ፤ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሣን! ስለታሪክ፣ ስለትላንት ማውራት ሳይሆን ዛሬን ማሸነፍ ነው የፖለቲካ ፋይዳው! ይሄን ያወቁ ላቁ! ይሄን የናቁ ወደቁ! እንደማለት ነው፡፡
ከ1966 ጀምሮ የተከሰቱ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች አበሳዎች፤ እከሌ ከእከሌ ሳይባል በትንሹ አሥር መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የተንተራሱ ይመስላሉ፡፡ ከአበሳዎቹ፤ አንደኛው/ በትንሽ በትልቁ መከፋፈል፣ ያለመስዋዕትነት ድል መመኘት፣ ውሎ አድሮ ጧት የማሉበትን ማታ መካድ፡፡
“ዕምነት ሲታመም፣ ሺ ወረቀት መፈራረም” ነው፡፡ 2ኛው/ ለባላንጣቸው ሠርጐ - ገብነት መጋለጥ ነው፡፡ 3ኛው/ እርስ በርስ አለመከባበር፣ አለመተሳሰብ 4ኛው/ የመስመር ጥራት አለመኖር ርዕዮተ - ዓለማዊ ብስለት ማጣት 5ኛው/ በትንሽ ድል መወጣጠርና በትንሽ ሽንፈት መፍረክረክ 6ኛው/ ተጋጣሚን መናቅና ወሬን/አሉባልታን እንደ አቋም መውሰድ 7ኛ/ የጊዜን ፋይዳ በትክክል መረዳት፣ ባልፈውስ? አለማለትና የኃይል ሚዛን የማን ነው አለማለት፣ ከተፈፀመም አለመመዘን፣ ይሄ ዓላማ ባይሳካ ምን ሁለተኛ ዘዴ ቀይሻለሁ? ብሎ አለመዘጋጀት፡፡ 8ኛው/ ባለፈው ያረግነው የት አደረሰን? ታሪኩ ተተንትኖ ተገምግሞ ሳያልቅ በነዚያው ተዋንያን ተውኔቱ መቀጠሉ 9ኛው/ እምቢ አላረጅም ማለት ነው፡፡ አዲሱ ያሸንፈኛል አለማለት The new is invincible የሚለውን መርሳት “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለት፡፡ 10ኛው/ እኔ ባልሆንስ መፍትሔው? ሌላ ቢኖርስ ከኔ የተሻለ አለ ብሎ ፈጽሞ አለማሰብ…
ከነዚህ ሁሉ ይሰውረን፡፡ እነዚህን ሁሉ ከልብ ከመረመርን ፓርቲዎቹ ሁሉ የቆሙት በአንድ ወይም በጥቂት ቡድን ሐብለ ሠረሠር (Spinal cord) ዙሪያ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሚሆነው፤
“ከተኳሾቹም - አሉ በልዩ
ማህል - አገዳ የሚለያዩ”
በምንልበት አገር ነው፡፡ ከፖለቲካ ንቃተ - ባህሉ (ትምክህቱ ጥበቱ፣ ዕምነቱ፣ የፖለቲካ
ጥንቆላው፣ ሟርቱ ወዘተ) ባለበት አገር ልማድን አለመመርመር ጦሱ ብዙ ነው፡፡ አጠቃላይ
የፖለቲካ ተመክሮአችን ገና አልተፈተሸም፡፡ “ዳሩ ሲነካ መሀከሉ ዳር ይሆናል” ይላል ያበሻ አባባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ግንዱ ሲመታ ቅርንጫፉና ቅጠሉ መርገፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቻይናዎቹ “ዛፉ ሲወድቅ ዝንጀሮዎቹ ይበተናሉ” የሚሉን መሠረታዊ ነገር የሚሆነው ለዚህ ነው! “ቁልቋል የወደቀው ቅርንጫፍ ስላበዛ ነው” የሚለውም የትግሪኛ ተረት አዙረን ስናየው እንደቻይናዎቹ ነው!!

Read 13823 times