Saturday, 19 December 2020 10:57

የዘመኑ ቴክኖሎጂና አዲሱ ጦርነት (የድሮን ጦርነት)

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)


            ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ሰው አልባ አውሮፕላንን (ድሮንን) ያየው፣ ከልዩ ኃይል ወታደሮች ጋር፣ለዘመቻ የተሰማራ ጊዜ ነው፡፡ ወታደሮቹ እንደስማቸው፣ ለልዩ ተልዕኮ የሚሰለጥኑና በላቀ ብቃታቸው የሚመረጡ ናቸው፡፡ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም፤ በፍጥነት ግዳጃቸውን ፈፅመው ይመለሳሉ፡፡ በከባድ፣ ስልጠና ያገኙት እውቀትና  በተግባር ያዳበሩት ልምድ ቀላል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ፣ የረቀቁ መሳሪያዎችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማሉ፡፡
ዛሬ፣ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን)፣ ለልዩ ሀይል ወታደሮች መደበኛ ትጥቅ ሆኗል፡፡ ያለ “ድሮን” የሚካሄድ ዘመቻ የለም፡፡ ታዲያ፣ ድሮን ሁሉ እኩል አይደለም፡፡ ዓይነታቸው ይለያያል፡፡ ከትልልቅ እስከ ትንሽ፣ …..ዋጋቸውና አገልግሎታቸው ብዙ ዓይነት ነው፡፡
በልዩ ሃይል ቡድን ለተልዕኮ የሚሰማሩ ወታደሮች፣ ከደርዘን አይበልጡም፡፡ ግን፣ አይምሬ ናቸው፡፡ ድጋፍ ሰጪ የመረጃ ባለሙያ ቢመደብላቸው፣ ለእያንዳንዱ ቡድን፣ ሰው አልባ አውሮፕላን ቢመደብላቸው አይገርምም፡፡
ቡድን መሪው “ማየት ትፈልጋለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ወጣቱ የመረጃ ባለሙያ ወታደራዊ “ድሮን” አያውቅም፡፡ ለማየት ጓጉቷል፡፡
ቡድን መሪው፣ ሰው አልባዋን አውሮፕላን፣ ሽቀብ ካመጠቃት በኋላ፣ ከርቀት አቅጣጫዋን እየተቆጣጠረ፣ በግራ በኩል አዙሮ፣ በቀኝ በኩል እየመለሰ እያበረራት ነው፡፡ ያን ያህልም የተለየ ነገር የለውም፡፡ የጌም መጫወቻ ይመስላል፣ መቆጣጠሪያ መሳሪያው፡፡
ቀላል ነው፡፡ “መሞከር ትፈልጋለህ?”አለ ቡድን መሪው፡ አዲሱ የመረጃ ባለሙያ፣ ጆሮውን ለማመን አልቻለም፡፡ አለቃው ግን፣ አበረታው። “ችግር የለውም፤ ያዝ፤ ሞክር” በሚል ስሜት የበረራ መቆጣጠሪያውን አስጨበጠው፡፡ አዲሱ የመረጃ ባለሙያ፣ በጉጉት ተቀበለ፡፡ በእርግጥም ከባድ አይደለም፡፡ አንጋጦ እያየማተረ፣ እንደገና ወደ ቪዲዮው አቀርቅሮ እያየ፣ አውሮፕላኗን ያከንፋታል፡፡ የእረፍት ቀን ስለነበረ፣ ወታደሮቹ በጋራ የጥብስ ምሳ እያሰናዱ ነበር፡፡
አዲሱ የመረጃ ባለሙያ ግን፣ ሰው አልባዋን አውሮፕላን በማብረር ተመስጧል፡፡ ቡድን መሪው፣ ”ለጊዜ ይበቃል” አለ፡፡ የጥብስ ምሳ ደርሷል፡፡ ”በል”፤ አውሮፕላኗን አሳረፋት” አለ ቡድን መሪው፡፡
ወጣቱ የመረጃ ወታደር፣ የርቀት መቆጣጠሪያውን እንደያዘ ነው፡፡ በቀስታ የአውሮፕላኗን ከፍታ  ለመቀነስ አልከበደውም፡፡ አውሮፕላኗ ዝቅ እያለች፣ በዝግታ መሬት ልትነካ ተቃረበች፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ለማመን ያቸግራል። ትንሽ እንደቀራት፣ ቁልቁል እየተምዘገዘገች ከመሬት ጋር ተላትማ ተከሰከሰች፡፡ ብትንትኗ ወጣ፡፡ አዲሱ የመረጃ ወታደር፣ ተቁለጨለጨ፡፡ አዎ፤ ተከስክሳለች ደንዝዞ ቀረ፡፡ አይኑ ፈጠጠ፡፡ አለቃው፣ከግራ በኩል እጁን አጣምሮ ያየዋል፡፡
“ከሰከስካት?” በሚል መንፈስ፡፡ ወጣቱ የመረጃ ወታደር፣ መናገር አቃተው….የመንግስትን ንብረት ሰባብሮ ማን ዝም ይለዋል? በስንት ዓመት፣ እዳውን ከፍሎ እንደሚጨርስ እንጃ? መፈጠሩን የጠላ፣ ህይወት ያቅለሸለሸው ይመስላል፡፡ በዝግታ ሊያሳርፋት ነበር፡፡ ድንገት ተፈጠፈጠች፡፡ ክንፎቿ ተገነጣጥለው፣ ጭራዋና አፍንጫዋ ተሰባብረው፣ አስፋልት ላይ ተበታትነዋል፡፡ ቡድን መሪው መሳቅ ጀመረ፡፡ “ሰራሁልህ” እያለ ተንከተከተ፡፡ ….. መሬት ላይ የተበታተነውን መለቃቀም ጀምሯል ወደ ምሳው ለመሄድ፡፡
በቃ?
በቃ፡፡ ችግር የለውም፡፡ ገጣጥመው ይጠግኗታል፡፡ ስሪቷ እንደዚሁ ነው፡፡ ማረፍ አትችልም፡፡ ትከስክሳ ትበታተናለች፡፡ ተገጣጥማ ትጠገናለች….
አውሮፕላኗ ትንሽ ነች፡፡ ጥሩነትዋ ግን፣ በማንኛውም ቦታ ታገለግላለች፡፡ መንደርደሪያ አስፋልት አያስፈልጋትም፡፡ መንደርደሪያ ጎማ የላትም፡፡ በእጅ ወደ ሰማይ ሽቅብ ይወረውሯታል፡፡ በአንድ መቶ፤ ሜትር በሁለት መቶ ሜትር ከፍታ፣  ቪዲዮ እየቀረፀች ታስቃኛለች፡፡ በ10 ኪ.ሜትር ርቀት ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማን ሁለቴ መዞር ትችላለች። ከዚህ አልፋ፣ ድንገት ርቃ ከሄደች ግን፣ የርቀት መቆጣጠሪያው አይሰራም፡፡ በዚያው ጠፍታ ትቀራለች፡፡ በጠላት እጅም ልትገባ ትችላለች።  ኪሳራ ነገር ግን፣ ተከስክሳ ብትንትኗ ስለሚወጣ፣ ለጠላት አታገለግልም፡፡ ያለ ትክክለኛ የጥገና መሳሪያና ያለ ትክክለኛ የመለዋወጫ እቃ፣መልሰው ሊገጣጥሟት አይችሉም፡፡
ታዲያ፣ “ስሪታቸው ነው” እያላችሁ፣ ሌሎች ድሮኖችን ብትከሰክሱ ችግር የለውም ማለት አይደለም፡፡ ችግር አለው፡፡ “ድሮኖች”፣ በዋጋም በስሪትም ይለያያሉ፡፡
ትንሿ ተገጣጣሚ ወታደራዊ ድሮን፣ ዋጋዋ ከ30 ሺህ ዶላር ብዙም ላይበልጥ ይችላል። መጠኗም ትንሽ ነው በእጅ የምትወነጨፍ፡፡ ጉዞዋም ከጥቂት ኪሎ ሜትር አያልፍም፣ አየር ላይ ቆይታዋም ከአንድ ሰዓት ብዙ አይበልጥም።
ግን ደግሞ፣ ሁለት ሚሳየል ታጥቀው የሚበርሩ  ድሮኖች አሉ፡፡ የክንፋቸው ርዝመት 20 ሜትር ይደርሳል፡፡ ኢላማ የማይስቱና (በድምር 12 ኩንታል የሚመዝኑ ሚሳየሎችን የሚታጠቁ ድሮኖችም በብዛት ተመርተዋል፡፡ አየር ላይ፣ 16 ሰዓት መቆየት ይችላሉ፡፡ ከ700 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው የመጓዝና የመመለስ አቅም አላቸው- “ሪፐር” የተሰኙት የአሜሪካ ወታደራዊ ድሮኖች፡፡ ዋጋቸው ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው (ከግማሽ በሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው)፡፡
`The dron war` በሚል ርዕስ ዘንድሮ ከታተመው መፅሐፍ የተወሰደ የአንድ ወታደር ገጠመኝ ነው፡፡ መነሻ እንጂ ማሰረጊያ አይደለም። ሺ ኪሎ ሜትር የሚጓዙ፣ አየር ላይ ቀኑን ውለው ሌሊቱን የሚያድሩ፣ በብርሃንና በጨለማ ቪዲዮ የሚቀርፁ፣ በሌዘርና በጂፒኤስ ኢላማቸውን አነጣጥረው በሚሳየል የሚመቱ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አይቷል። ምን ማየት ብቻ? እነዚህን ማሰማራትና መከታተል፣ ኢላማዎች በሚሳየል ማጋየት፣ ውሳኔና ትዕዛዝ መስጠት፣ ስራው ሆኗል፡፡ ዋና ስራ ሌላ ነው ይላል ፀሐፊው፡፡
አዎ፤ ሚሳየል እንጠቀማለን፡፡ ኢላማችንን በትክክል እንመታለን፡፡ ጠላት ላይ ከባድ ጉዳት እናደርሳለን፡፡ ነገር ግን፣ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ዋና አገልግሎትና ትልቁ ጥቅም፣ ሚሳየል መተኮስ አይደለም፡፡ ሌሎች አውሮፕላኖችም ይህንን ይችላሉ፡፡
አየር ላይ ቀን ከሌት የሚያዣብብ ሰው አልባ አውሮፕላን ግን፣ አካባቢውን ሁሉ ለመቃኘት፣ የጦር እንቅስቃሴን ለመሰለል፣ ወይም የአንድ ሰውን መውጫና መግቢያውን ለመከታተል፤ ውሎና አዳሩን፣ የግንኙነት መረቡን ለማጥናት ያገለግላል፡፡ በማናቸውም ሰዓት ያገለግላል- ቀንም ማታም፣ ያለፋታ፣ ደቂቃ በደቂቃ። በማንኛውም ቦታ ይሰራል - በገጠርም በከተማም፡፡ በቃ ማምለጫ የለም፡፡ እፎይታም መፈናፈኛም አይሰጡም፡፡ ከሰማይ ላይ የሚያንዣብቡ አይኖች፣ አያንቀላፉም። ሁሌም ያያሉ፡፡ ኢላማቸው አይዛነፍም፡፡ ሁሌም ባለ “ሌዘር” የሚሳየላቸው ኢላማ ሁሌም በጠላት ላይ  እንደተነጣጠረ ነው፡፡ ምናለፋችሁ። ዛሬ የጦርነት ባህሪይ ተቀይሯል፡፡ አዲስ ገጽታ ተጨምሮበታል- በድሮን አማካኝነት፡፡Read 1672 times