Sunday, 20 December 2020 00:00

"የወያኔዎች መሳደድ የትግል ግብ ሊሆን አይችልም"

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   • ለልጆቼ በመትረፌና እኔን ማየት በመቻላቸው እንኳን አልሞትኩ ብያለሁ
            • እዚህ አገር “ዘውጌ ብሔርተኝነት” እንጂ ያደገ ብሔርተኝነት የለም
            • የእኔ መታሰር “የግንቦት 7”ን ትግል አግዟል ብዬ አስባለሁ

       የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሌላ ክስ  ደግሞ የዕድሜ ልክ እስራት የተበየነባቸው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ የነፃነት ታጋዩና አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፤ የ#ግንቦት 7; ከፍተኛ አመራር በነበሩበት ወቅት ከየመን ሰንአ አየር ማረፊያ ታፍነው ወደ ኢትዮጵያ የተወሰዱ ሲሆን ለ4 ዓመታትም  በእስር ላይ ቆይተዋል።  እንደመታደል ሆኖ፣ የዛሬ 2 ዓመት ተኩል ገደማ፣ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ትግልና ጥረት ከእስር ሊፈቱ ችለዋል፡፡
በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው አዲሱ መጽሐፋቸው፣ “የታፋኙ ማስታወሻ”፤ በደህንነት ሰዎች ከታፈኑበት ጊዜ አንስቶ ለ4 ዓመታት ያሳለፉት እስር በጥልቀትና በዝርዝር ይተርካል - እንደ ፊልም ታሪክ፡፡ አቶ አንዳርጋቸው “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” እና “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር” የተሰኙ ሁለት መፃህፍትን ቀደም ብለው ለአንባቢያን ማቅረባቸውም ይታወቃል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ “የታፋኙ ማስታወሻ” በሚለው መፅሐፋቸው መነሻነት ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጋለች። እነሆ፡-

          ጋሽ አንዳርጋቸው -- በእጣ ፈንታ ያምናሉ?
እጣ ፈንታ በሚባለው ነገር ብዙም እምነት የለኝም። ሰዎች ካሰቡ በጥንቃቄ ከተራመዱ ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮች አስቀድመው ማየት ይችላሉ፣ አደጋውን ማስወገድና  መቀነስ ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው። ስለዚህ ከሰው …ቁጥጥር ውጪ የሆነና በሌላ ሀይል የሚደረግ ነገር አለ ብዬ አላምንም። ለምን ጠየቅሽኝ ግን…?
እርስዎ በየመን አየር መንገድ ለመብረር የፈለጉት 400 ዶላር ተጨማሪ ክፍያ ከፍለው ወደ ኤርትራ ላለመጓዝና “የግንቦት 7ን” ገንዘብ ላለማባከን ብለው ነው አይደል?
አዎ!
የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወደ ኤርትራም ብበር ልታሰር እችል ነበር ብለው ያምናሉ ወይ ለማለት ነው?
 እውነት ለመናገር 400 ዶላሩን ለማትረፍ ብቻም ሳይሆን ወደ ኤርትራም ብበር አደጋ ሊመጣ ይችላል ብዬ ስለሰጋሁ ነው። ብዙ ዝግጅትም ለማድረግ ሞክሬ ነበር። አንደኛው የኤርትራ አምባሳደር ትራንዚት እስከ ማደርግ ድረስ፣ የመን ኤርፖርት እንዲጠብቀኝ አድርጉልኝ ብያለሁ። ሌላው ፀጉሬን ቀለም ለመቀባት ሁሉ ገዝቼ ነበር። ነገር ግን ቀለም መቀባት እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። መመሪያውን ሳነበው ቀላል ነገር አይደለም። እንደው ዝም ብሎ ቀለሙን ጭንቅላት ላይ ቅብት አይደረግም። ያንን ቀለም ቆሻሻ ውስጥ ነው የጣልኩት። ይህንን ሁሉ ለማድረግ የገፋፋኝ ጉዞውን በየመን በኩል ማድረግ አደጋ አለው በሚል ነው። ስለዚህ የመታሰሬ ጉዳይ የእጣ ፋንታ ጉዳይ ሳይሆን አደጋውን በአግባቡ ያለመመዘን ዝርክርክነት ነው። ያለኝ ሰዓት አጭር በመሆኑ እንጂ በግብፅ አየር መንገድ መሄድ እችል ነበር። ነገር ግን  እዛ አንድ ቀን ይባክንብኛል ብዬ ነው ቶሎ ሊያደርሰኝ ይችላል ባልኩት በየመን አየር መንገድ የበረርኩትና ይሄ ሁሉ ችግር የተከሰተው።
ከየመን ታፍነው እንደመጡ የእጅዎ ወደ ኋላ መታሰር፣ የታሰሩበት ክፍልና ፍራሽ ቆሻሻነት ተዳምሮ፤ ከስቃይዎ ብዛት በክፍሉ ካለ የቧንቧ ብረት ጋር ተጋጭተው ለመሞት ሙከራ አድርገው፣ ብረቱን በመሳትዎ እንደተረፉ ገልፀዋል። አሁን ላይ ሆነው ሁኔታውን ሲያስቡት ምን ይሰማዎታል?
እኔ ከሁሉም ከሁሉም አሁን ላይ ሆኜ የሚሰቀጥጠኝ፣ የ7 ዓመት ዕድሜ የነበራቸው ህፃናት ልጆቼ፣ ከአሁን በኋላ አታዩትም የሚል መልዕክት ሲሰሙ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሳስብ ነው። ሁልጊዜም አንድ ቦታ ለመሄድ በተነሳሁ ቁጥር መቼ ነው የምትመጣው? መቼ ነው የምትመለሰው? እያሉ ጥያቄ የሚያቀርቡ ልጆች፤ ጭራሹኑ “አይመጣም” የሚለውን ከእናታቸው ሲሰሙ ምን ይሆናሉ የሚለው ነው። ለእነሱ በመትረፌና እኔን ማየት በመቻላቸው እንኳን ያልሞትኩኝ እላለሁ። ለራሴ ግን ይህ ዓለም ነው ብዬ፣ በተለይ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያሉበትን ሁኔታ ሳይ፤ መኖር የሚያጓጓ አይደለም። የሰው ልጅ ከመሞት አያመልጥም። አሁን አባቴን እያየሁት ነው። እኔ ስፈታ በስነ-ስርዓት ሰው ማናገር ይችል ነበር። ለሚዲያ ኢንተርቪው ሁሉ ይሰጥ ነበር። አሁን ግን እኔንም አያውቀኝም። በሁለት ዓመት ውስጥ ጠቅላላ ትውስታውን አጥቷል። 96 ዓመቱ ነው። በሰው ድጋፍ ነው የሚነሳው፤ ሰው ነው የሚያበላው፣ መፀዳጃ ቤት የሚወስደው ሰው ነው። የሰው ልጅ እጣ ፈንታይሄ መሆኑን እያየሁ ለመኖር አልጓጓም። እኔ በልጅነትም ይሁን በመካከለኛ እድሜዬ፣ ሞትና ከሞት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ሳስብ ስለኖርኩ፣ መትረፌ ይህን ያህል ተዓምር አይሆንብኝም። ነገር ግን እንዳልኩሽ ለቤተሰቤ ለሚወዱኝ ሰዎች፣ ለአባቴ መትረፌ ትልቅ ነገር ነው። የአባቴ ትልቁ ስቃዩ እኔ ነኝ። በፊትም ልጆች ሞተውበታል፤ በቤት ውስጥም ትራጄዲው ብዙ ነው። ወንድሞቹ በልጅነቱ ነው በጣሊያን ጊዜ፣ ከእናቱ እግር ስር  እየተጎተቱ የታረዱበት። እና እኔም አንድ ነገር ሆኜ ቢሆን ኖሮ፣ በጣም ትልቅ መሳቀቅ ውስጥ ይወድቅ ነበር። ለእሱም መትረፌ እፎይታ ነው። የቅርብም የሩቅም ዘመድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብም፣ መቼም ለኔ ያለው ነገር ቀላል አይደለምና፣ ይህን ይህን ሳስብ መትረፌ የተሻለ ነው። ህዝቡ ከስለት አንስቶ እስከ ፀሎት ድረስ እኔ እንድፈታ ያደርግ የነበረውን ስሰማ፣ በጣም ይገርመኛል።
በእስር ቆይታዎ በጣም መጥፎ ሰዎች እንደገጠምዎ ሁሉ ሩህሩህም ገጥምዎታል። በተለይ አጭሩና ቀዩ ጠባቂዎ እንዲሁም የውስጥ ሱሪ ገዝታ ያመጣችልዎ ሀኪም አይረሱም። ከእስር ከተፈቱ በኋላ እነዚህን ሰዎች ለማግኘትና ለማመስገን ሞክረዋል?
ምንም ያደረግኩት ጥረት የለም። ለምን? ወዲያው በስራ ነው የተጠመድኩት። ከዚያ ወደ ቤተሰቤ ነው የሄድኩት። ነገር ግን መፅሐፉን ካገኙትና ካነበቡት አለዚያም ይሄንን ጋዜጣ ካነበቡት፣ እኔን ለማግኘት አይቸግራቸውም። ከደህንነት መስሪያ ቤቱ ጋር በጥብቅ አብረው ይሰሩ ስለነበረ በስጋት ብቻ  ከከተማው ተወስደው ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ብዙዎቹ ተጠቃለው ወደዚያው ነው የገቡት። ይህንን መፅሐፍም አርፍጄ ነው መፃፍ የጀመርኩት። አገር ሰላም ከሆነ አንድ ቀን እንገናኛለን። አስፈልጋቸዋለሁ። ይህንን ጋዜጣም ካነበቡ፣ ስልኬን ከእናንተ ወስደው ሊያገኙኝ ይችላሉ። ይህንን መልዕክት አስተላልፉልኝ፤ ላገኛቸው እፈልጋለሁ።
ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን አጠገብ መታሰረዎን ካወቁ በኋላ "የቅድመ አያቴ የይፍቱ ስራ ሚካኤል፣ ከልጆቼ ከቀላቀልከኝ ሰንጋ በሬ ለንግስህ አስገባለሁ" ብለው ተስለው ነበር፡፡ ስለቱን አስገቡ?
ስለቱን በእህቴ በኩል አስገብቻለሁ፣ ለሚካኤል ብቻ ሳይሆን ለእናቴ ገብርኤልም አስገብቻለሁ። ሁለት ሰንጋ ነው ያስገባሁት። በዚያኛው መፅሐፌ ላይ እንደገለጽኩት፤ እናቴ በጣም የምታምነው ገብርኤል አለ። “ልጄ ከተረፈ ያለ ልብስ እርቃኔን እዞራለሁ” ብላ ቁልቢ ገብርኤል ያለ ልብስ ሶስት ጊዜ የዞረችበት ሁኔታ ነበር። እናም ጭንቀት ውስጥ ስትገቢ ብዙ ነገር ታስቢያለሽ። እኔ ቤተ ክርስቲያን የምሄድ ሰው አይደለሁም፤ ግን…
ያው ኮሙኒስት ነዎት… አይደል?
አዎ ኮሙኒስቶች ነን፤ ኮሙኒዝሙም ቢቀር በተደራጀ እምነት አካባቢ የሚሰራው ስራ ቅር ስለሚያሰኝ እንጂ የእምነት አስፈላጊነት ይገባኛል። ሆኖም ወደ እምነት የማይስቡ በተለይ የእምነት መሪዎች ድርጊት፣ ጠቅላላ አኗኗርና ደግሞም እምነቱን በተመለከተ ካለው አስተምሮት ጋር የማይሄዱ ተግባራቶቻቸው እንድርቅ ያደርጉኛል። ነገር ግን አሁንም እናትሽ፣ አባትሽ፣ አያት ቅድመ አያቶችሽ ሁሉ አማኝ መሆናቸው ጭንቀት ውስጥ በምትገቢበት ጊዜ ብዙ እንድታስቢ ያደርግሻል። እኔም ያልኩትኮ ካልጠፋ ቤተ-ክርስቲያን እንዴት ነው ታፍኜ የመጣሁበት ቤት፣ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገቤ የሆነው? አንድ ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ ቅድመ አያቴ ፀልየው ይሆን? እስር ቤቱ እዚህ የሆነው፣ ሚካኤል እንዲጠብቀኝ ይሆን እንዴ? …እላለሁ። ያንን ሳስብ የእሳቸው እምነትና የሞቱበት መንገድ ነው የታየኝ።
እንዴት ነበር ቅድመ አያትዎ የሞቱት?
እምነታቸው በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ፣ እናቴን ጠርተው “ዛሬ ሚካኤል ፈረሱን ይዞ እደጅ ቆሟል፤ ሊወስደኝ መጥቷል፤ ቤትሽን አዘጋጂ” ባሉ በአንድ ሰዓት ልዩነት ውስጥ ነው የሞቱት። አሁን ይሄንን በምንም መንገድ መግለፅ አይቻልም። እንዲህ ብሎ ሰው እንዴት ይሞታል። እርሳቸው የሚያምኑበት እምነት ሀይለኛ መሆኑንና በልጅነቴ አጠገባቸው ሆኜ ተናግረው ሲሞቱ በተጨባጭ ያየሁ በመሆኔ፣ ለእሳቸው በደንብ የሚሰራ ሚካኤል አላቸው ብዬ ወደ ማመን ሄጃለሁ። ለሌላው ይስራ አይስራ አላውቅም። ብቻ በእርሳቸው በኩል የሚያደርገው እርዳታ ካለ፣ እርሳቸው እንደ አማላጅ እንዲሆኑ ነው። ሚካኤል ይህንን ካደረገ፣ እኔ ይህንን አደርጋለሁ ያልኩት።
በጣም ይገርማል! “ዝብርቅርቅ ህልምና ቅዠት” በተሰኘው የመፅሐፉ ክፍል፣ በጣም ረጅምና በተለያዩ ቀናት ያዩትን ህልምና ቅዠት አስፍረዋል። ሲያዩ አድረው ጠዋት ይፅፉታል ወይስ እንዴት ነው ያንን ሁሉ ሊያስታውሱ የቻሉት? ካዩት ህልም ውስጥ እውን የሆነና የተከሰተ ነገርስ ይኖር ይሆን?
እንዳልሽው ብዙ ጊዜ ብዙ ህልሞች ጠዋት ተነስተሸ ወይ ጥቂት ቀናት ቆይተሽ ለማስታወስ ይቸግራል፡፡ ነገር ግን እኔ የመፃፍ ፍላጎት ሁሌም ስላለኝ ሁሉንም ነገር እንደሚጻፍ አድርጌ ነው የምመለከተው። ከእንቅልፌ ልክ ስነቃ ህልሙ ወይም ቅዠቱ ገና ትኩስ ነው። ነቅቼ ወዲያው ተመልሼ አይደለም የምተኛው። እንደነቃሁ ያንን ያየሁትንና የሄድኩበትን ሁሉ ዝም ብዬ አየዋለሁ፤ አስበዋለሁ። አንድ ቀን ሊጻፍ ይችላል በሚል ያንን ሳደርግ፣ የጭንቅላቴ ማስታወሻ ክፍል ውስጥ ይቀራል። ሌሎችንም ነገሮች በእውን የሆኑትንም ቢሆን፣ ማለቴ ነው። ሰው እንዴት ነው የምታስታውሰው ይለኛል። እኔ ያንን ነገር በውስጤ እንዳይረሳ አድርጌ ነው የማስቀምጠው። ለምሳሌ አንዱ ህልም፣ ከዚህ መከራ በህይወት እንደምተርፍ ነው የሚያሳየው።  ለስቅላት ተወስጄ በስህተት ነው የመጣው ተብዬ የተመለስኩበትን ቦታ ማሰብ ትችያለሽ። በኢሜይል ስህተት ነው የመጣው ተብዬ ተመለስኩኝ።
ነገር ግን የዚህ ሁሉ እንግልትና መከራ መነሻ የሆነውም ለንደን ሳሉ ወደ ዱባይ የላኩት የኢሜይል ስህተት ነው። ማለቴ በስህተት ወደ ኤርትራ የሚበሩበትን ቀን በአንድ ወር አራዝመው ነው ዱባይ ለሚገኘው የኤርትራ ቲኬት ቢሮ የላኩለት። ለዛም ነው 400 ዶላር ጨምረው ከፍለው በአንደኛ ደረጃ እንዲበሩ የተጠየቁት:: “አልከፍልም” ብለው ነው በየመን አየር መንገድ በረራ አድርገው፣ ለመታፈንና ለእስራት የበቁት። ትክክል ነኝ?
ትክክል ነሽ።  እውነት ለመናገር እኔኮ ህልሜ ከምን ከምን ተጋጭቶ እንደተፈጠረ አውቀዋለሁ። ቀን ሳስበው ከዋልኩት ነገር ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰ መሆኑንም አውቀዋለሁ። ቀን ስለ አፍጋኒስታን ሳስብ የነበረበት ምሽት ነው፣ እነ ክሊንተን አፍጋኒስታን ላይ የሰደዱት ክሩዝ ሚሳኤል፣ ቢን ላደንን ለማጥፋት ከረን ላይ ሲያርፍ ያየሁት። ሁለተኛ፤ ያ ክሩዝ ሚሳኤል ከረን ላይ ባረፈበት ጊዜ ነው፤ ከረን ከተማ ለጸሀይ እንደተጋለጠ ቅቤ ስትቀልጥ ያየኋት። በአንድ እጁ ክላሽ በአንድ እጁ ከዘራ ይዞ፣ ወደ ተራራ ሲወጣ ያየሁት የኢሳያስ ምስል እኮ ራሱ ቢን ላደን ልክ እንደዛ አይነት ልብስ ለብሶ፣. ዳገቱን ሲወጣ ያየሁት ስዕል ነው፣ ወደዛ የተቀየረው። ይገርመኛል።
“ጆሮ የሚያስደፍን ነገር መብዛቱ” በሚለው የመፅሐፉ ክፍል፣ የዚህን አገር የቤተ-ክርስቲያን ከልክ ያለፈ በድምፅ ማጉያ የሚለቀቅ ድምጽ፣ የመስጊዱም ተመሳሳይ ድምጽ፣ በሌሊት የሚነሳና የሚያርፈውን የጀትና የአውሮፕላን ረብሻና ከሰላም እንቅልፍ የሚቀሰቅስ ድምጽ በመኮነን፤ እርስዎ በሚኖሩበት እንግሊዝ በቀን ሩብ ሚሊዮን ህዝብ የሚያመላልሰው ሂትሮ አየር ማረፊያ፣ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ዝግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእኛ አገር በሌሊት ዝግ የማይሆነው ድሃ ስለሆንን ነው? ወይስ ደንታ ቢስ መንግስት ስለሚመራን? ...ብለው ይጠይቃሉ።  ለእርስዎ መልሱ የትኛው ነው?
መልሱ ድህነታችን ይመስለኛል። ከሌላ አገር ሌሊት መነሳት ስለሚከለከሉ ሀብታሞቹ አገራት ሌሊት ከመሆኑ በፊት ነው የሚነሱት። ስለዚህ እዚህ  ሊነጋጋ ሲል ከሌሊቱ 10 እና 11 ሰዓት አካባቢ ነው መግባት የሚጀምሩት። እነዛ ሰላማቸውን ለመጠበቅ ያገዱት ሰዓት፣ እኛ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። ለዚህ ዋነኛው  ነገር ድህነታችን ነው። ሀብታም አገር ብንሆን፣ በዚህ ሰዓት ማረፍ ክልክል ነው ብለን ማስቆም እንችል ነበር። አውሮፕላኖቹ የግድ ስለሆነ ይስሩ ልንል እንችላለን። የቤተ-ክርስቲያንና የመስጊድ ድምጽና ጩኸት ግን ግዴለሽነት ነው።
ነገር ግን የእኛ አገር ሰው ከሃይማኖቱ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝትና ትስስር ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። እና ይህንን ነገር ሲጽፉ ምዕመናንን ያስቆጣል ብለው አላሰቡም?
ሰው ከሃይማኖቱ ጋር ያለውን ጥብቅ ትስስር አውቃለሁኮ። ለምንድን ነው ምዕመናኑ የሚቆጡት? መስጊድም ቤተ-ክርስቲያንም ድምጽ ጨርሶ አይጠቀሙ አላልኩም። ቤተ-ክርስቲያን በዙሪያው ላሉት በሚበቃ መጠን መጠቀም ይቻላል። ምክንያቱም ምዕመናኑ ያሉት እዚያው ግቢ ውስጥና ዙሪያውን ነው። ስለዚህ በቤተ-ክርስቲያንና በዙሪያው ላሉት ቢጠቀሙ ችግሩ ምንድን ነው? እንኳን ቤተ- እምነቶች ተልካሻ ሙዚቃ ቤቶች ሳይቀሩ በስፒከር ከተማውን ሲበጠብጡ አይደለም እንዴ የሚውሉት። የእምነት ተቋማት ከሙዚቃ ቤቶቹ በላይ ናቸው ማለቴም አይደለም።  ነገር ግን ሁሉም ከልክ በላይ ድምጽ አቁሞ በልኩ ቢደረግ ምንድን ነው ችግሩ? እኔ የሚመስለኝ ፉክክር ነው። የስፒከር ውድድር የተያዘ ነው የሚመስለኝ። ይህ ትክክል አይደለም። አምሽቶ የሚሰራ አለ፣ ህፃናት ጥሩ እንቅልፍ መተኛት አለባቸው። በፀጥታ ውስጥ መተኛት ለጠቅላላ ጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው። እንግሊዝ አገር እንደዚህ አይደለም፡፡ “የቤተ ክርስቲያን ደውል ከተገቢው በላይ አስጩኸዋል” ብሎ አንድ ዜጋ ፍርድ ቤት የሚገትርበት አሰራር አለ። እኔ የሀገሬ ህዝብ ለእምነቱ ያለውን ነገር አውቃለሁ፤ ሁሉንም ማድረግ ይቻላል፤ ግን ጩኸቱና ረብሻው አስፈላጊ አይደለም ነው እያልኩ ያለሁት። ቃሊቲ  ወህኒ ቤት የሰው ጩኸት፤ የሴቶች እስር ቤት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ሆኖ ቀን ፀሀይ፣ ማታ ብርድ የሚያሰቃያቸው ነገር ሲያማቸው፣ ያለው የህመም ጣር፣ መርዶ ሲረዱ የምሰማው ነገር፣ አብረውኝ የታሰሩት ሰዎች ክፋትና ረብሻ፤ በጣም በጣም የሚረብሽ፤ ሲያስጨንቀኝ የቆየ፣ ፍፁም እረፍትና ፀጥታ የሌለበት ነው። በነገራችን ላይ የቤተ-ክርስቲያን ድምጽ በቀስታ እስከመጣ ድረስ ስሰማው የሚሰጠኝ ስሜት አለ። ካደግሁበትና በየቦታው ከምሰማው ነገር ተነስቼ ዝም ብዬ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ሄጄ፣ ዛፍ ተደግፌ፣ ቄሶቹ ሲቀድሱ ሲዘምሩ የምሰማባቸው ሁኔታዎች፣ የራሱ የሆነ የሚያረጋጋ ነገር አለው። ከእምነት ጋር የተያያዘ ይሁንም አይሁንም…የሆነ የማላውቀው ነገር ይፈጥራል። ይህንን የመንፈስ መረጋጋት የሚፈጥረውን ነገር፣ ሌላውን በሚረብሽ መልኩ፣ በስፒከር መልቀቅ በመብት ደረጃም አያስኬድም።
በብሔርና በዘር መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ያብራሩበት መንገድም አለ፡፡ ለእኔ አዲስ ሃሳብ ነው፤ከዚህ በፊት ሰምቼው አላውቅም፡፡ በዚህ ጉዳይ እስቲ ትንሽ ማብራሪያ ይስጡኝ?
በሀገሪቱ ምሁር የሚባሉትም ጋ የብሔር አስተሳሰብ አልደረሰም። ምክንያቱም “ብሔር” የሚለው ቃል መሰረታዊ በሆነ መልኩ ከማህበረሰብ እድገት ጋር የመጣ ነው። ዘብሄረ እንግሊዝ፣ ዘብሄረ አሜሪካ፣ ዘብሄረ ጀርመን፣ ዘብሄረ ኢትዮጵያ አይነት ነው። ብሄር “ኔሽን” ከሚለው ነገር ጋር የሚመጣ ነው፤ በትርጉም ደረጃም ቢሆን። አገር ደግሞ ሰውን በዘር አትለይም፤ በዜግነት ትሰበስባለች እንጂ። ዜጎችም እርስ በእርስ የሚገናኙት በስራም፣ በጉርብትናም ቢሆን የሚኖሩት፤ በሰውነታቸውና በሚስማማቸው ነገር ላይ ተመስርተው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ብሄር ስንመጣ፤ ብሄር የሚለውን አገር ከሚለው ነጥለን ለጠበበ ነገር መጠቀም ጀመርን፤ የጠበበው ነገር በብሄር ደረጃ እንድናየው ከተፈለገ፣ የአንድ ብሄር ክልል በሚባል ቦታ የሚኖሩ ሰዎችን  በሙሉ እንደ ክልሉ ነዋሪ አድርጎም አይወስድም። ልክ አገር ሁሉንም በዜግነት እንደምትወስደው ማለት ነው። በክልል ደረጃ ስትመጪ ግን ሰዎች እዚህ ይኖራሉ፤የፈለጉትን ቋንቋ ይናገሩ፤ የፈለጉትን ባህል ይልበሱ፣ የፈለጉት እምነት ይኑራቸው፤ እነዚህ ሰዎች በእነዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም ሰው እኩል የሚታዩና የሚስተናገዱ ናቸው የሚል አመለካከት የለም። ይህ የሚመነጨው በብሄር ደረጃ ሳታድጊና ሳትደርሺ ስትቀሪ ነው። እኛ አገር ያላደገ ነገር ነው ብሄር የሚባል ስም የተሰጠው። ስለዚህ “ዘውጌ ብሄርተኝነት” ወይም “ኤትኒክ ናሽናሊዝም” እንጂ በደንብ ያደገ ብሄርተኝነት የለም ብዬ ነው “ነጻነት የማያውቅ ነጻ አውጪ” መፅሐፍ ላይ ያሰፈርኩት፡፡ ሰው ወደ ጐሳ እየተሳበ በሚሄድበት ጊዜ ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በደምና በአጥንቱ እየመዘዘ ወደ ዘር ፍተሻ የሚሄድበት ምክንያት፣ በጎሳና በብሄር መካከል ያለ፣ ያላለቀ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ማህበረሰብ ስላለን ነው፡፡ ስለዚህ ብሄር የሚለው ቃል ለአማራውም፣ ለኦሮሞውም፣ ለትግሬውም፣ ለአፋሩም …ለሁሉም አይሰራም። ምክንያቱም የነዚህ አካባቢ የፖለቲካ ሰዎች ምሁራንና ሌላውም ህዝብ ስለ ብሄር ሲያስረዳ፤ የዚህ ሰውዬ አባትና እናት ማናቸው ብለው ነው የሚጠይቁት። የአንድን ማህበረሰብ አባልነት በደም መመንዘር ስትጀምሪ፣ ከብሄር መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳብ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ሌላ ስም ነው መፈለግ ያለበት። በአገራችንም የብሄር ፖለቲካ ድርጅቶች ሳይሆኑ ያሉት  የዘር ፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው። ሰውን በዘር እየመነዘሩ ነው አባል የሚያደርጉትም፤ ሰውን በዘር እየመነዘሩ ነው ከተሳታፊነት የሚያገልሉትም።
የእርስዎ መታሰር የ“ግንቦት ሰባትን”ትግል አጠናከረው ወይስ አዳከመው ይላሉ?
ይህን ጥያቄ ለመመለስ እኔ እስር ቤት ሆኜ ምን እየተካሄደ እንደነበር አላውቅም። እንደው  አልፎ አልፎ መረጃ ሳገኝ “እንደዚህም አለ እንዴ፤ እንዲህ እያደረጉ ነው እንዴ” ከማለት በስተቀር ቤተሰቦቼም እኔን ለመጠየቅ ከተፈቀደላቸው ጊዜ ጀምሮ ስለ ውጭው ነገር ምንም እንዳይናገሩ፣ የእንግሊዝ አምባሳደሩም ወደ እንደነዚህ አይነት ነገሮች መግባት እንዳልተፈቀደለት ነው የታዘብኩት። እነዚህ ነገሮች ተደምረው ጨለማ ውስጥ ነበር የነበርኩት፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ያ የደህንነቱ ሰውዬ፤ “በውጪ የተያዘው  “Free Mandela” የሚል ነው” ብሎ ተናግሯል። “ኦ እንደዚህ እየተደረገ ነው እንዴ?!" አልኩኝ። አንድ ጊዜ ደግሞ ያ ክፉው ሰውዬ፤ “ታማኝ እየተነፋረቀልህ ነው” አለኝ። ስለዚህ የት እንዳለሁ ያውቃሉ ብዬ አሰብኩት እንጂ ስወጣ የሰማሁትን አይነት በውጭም በሀገርም የነበረውን ጠቅላላ ተቃውሞ፤ በኔ መያዝ የተፈጠረውን እንቅስቃሴ፣ ግንቦት ሰባት አባላት መመዝገብ እስኪያቅተው ድረስ የተፈጠረውን ንቅናቄ፣ “እኔም አንዳርጋቸው ነኝ” የተባለውን ዘመቻ፣ በገንዘብም ቢሆን ለንቅናቄው የሚሆን ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉ፣ እዚህ አገር ውስጥም በኔ ጉዳይ ያዘነ የተናደደ ያለ መሆኑንና ሥርአቱንም የበለጠ እንዲጠመድ ያደረገበት ሁኔታ መኖሩን እስክወጣ ድረስ አልሰማሁም። ዶ/ር አቢይ ሲናገር እንደሰማሁትም፤ በአንዳርጋቸው መታሰር የእንግሊዝ መንግስት ያስቀረብን ገንዘብ አለ ብሏል። ስለዚህ ስርዐቱ በፖለቲካም በኢኮኖሚም ተጎድቷል። እኔ ከተያዝኩ በኋላ ነው የዲሲ ግብረ ሃይልም የተቋቋመው። በዚህ ግብረ ሃይል አማካኝነት የትኛውም የወያኔ አባል ዲሲ ውስጥ መጥቶ እንደፈለገ እንዳይንቀሳቀስ መግቢያ መውጫ ያሳጧቸውም ነበር። ስለዚህ የኔ መታሰር ትግሉን አግዟል ብዬ አምናለሁ።
የህወኃት በአጭር ጊዜ ውስጥ ታሪክ መሆን ምን ስሜት ፈጠረብዎ?
መጀመሪያ እነዚህ ሰዎች በእኔ እይታ አሁን የገቡበትን፣ የፈፀሙትን ባያደርጉና  ወደተረጋጋ ሁኔታ ቢመጡ፣ ሰዎች የማይሞቱበት የማይሰደዱበት እንዲሁም በየጉድጓዱ የተወሸቁበት ሁኔታ ባይፈጠር የመጀመሪያ ምርጫዬ ነበር፡፡ እኔን አሰሩም አላሰሩም፣ አፍነው አመጡም አሰቃዩም ለኔ ትርጉም የሌለው ነገር ነው። ህዝብ እስካለፈለት፣ አገር እስከተለወጠ ድረስ ይህንን ለአንድ ደቂቃም እንኳን፣ ከቁም ነገር አልቆጥረውም፤ እንደዛም አይሰማኝም።
ለደረሰብዎ አፈናና ስቃይ ይቅርታ አድርገዋል ማለት ነው?
ይቅርታ የማድረግ ጉዳይ አይደለም። ይቅርታ የሚያደርግላቸው ህዝብ እንጂ እኔ አይደለሁም። ምክንያቱም በእኔ ላይ ካደረጉት በላይ በአገር ላይ የፈጸሙት በደል በጣም በጣም የከፋ ነው። ስለሆነም ይቅርታ መጠየቅ ያለባቸው ህዝብን ነው። ዋናው ነገር፤ ከእንዲህ አይነት ማለቂያ ከሌለው ትርምስ፣ ግጭትና ህይወት መጥፋት ብንወጣ ነው ምኞቴ። የታገልነው እኛንና ህዝብን ሲበድሉ የነበሩ ሰዎች እንዲሳደዱ አይደለም።
ወያኔ በመንግስቱ ሃይለማርያም ላይ የሞት ፍርድ የፈረደ ቀን፣ እንግሊዝ አገር ያሉ ጋዜጠኞች በደርግ  ስርዓት ወንድም እንደተገደለብኝና የት እንደተቀበረ ስለሚያውቁ፣ ደውለው ቢቢሲ ላይ አስተያየት እንድሰጥ ፈለጉና፤ “አሁን በመንግስቱ ላይ በተፈረደው ፍርድ ደስተኛ ነህ ወይ?” ብለው ጠየቁኝ። የእኔ መልስ “ደስተኛ አይደለሁም” የሚል ነው። ወንድሜ የሞተው፣ ሌሎችም የሞቱት ገዳዮቻቸው ፍርድ ቤት እንዲቆሙላቸው አይደለም። እኔም የታገልኩትና ቤተሰቦቻቸውን በወያኔ ያጡት፣ ገዳዮቻችው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡላቸው አይደለም የታገሉት። የፍትህ ስርዓት እንዲስተካከል፣ ብልጽግና እንዲመጣ፣ የተረጋጋ ህይወት እንዲፈጠር… የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ነው። ገዳዮቻችን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ማድረግማ፣ የትግል አላማ ሊሆን አይችልም። ከዚህ አኳያ የእነዚህ ሰዎች መሳደድ የኔ የትግል ግብ አልነበረም። የኔ የትግል ግብ ከላይ የጠቀስኳቸው ነገሮች እንዲፈጠሩ ነው። ያ እስካልተሳካ ድረስ የተከፈለው መስዋዕትነትም፣ እነዚህን ሰዎች ለማሳደድ የተከፈለው ዋጋም ትርጉም ያጣል። ስለዚህ ከዋናው ቁምነገር ላይ አይናችንን ማንሳት የለብንም። የፍትህ ስርዓቱን ማስተካከል አለብን፣ ዘረፋን ማስቆም አለብን፣ በዘረፋ የተነሳ ህይወት ሲኦል የሆነበት ህዝብ ህይወት መለወጥ አለበት። ተስፋ እንዲቆርጥ የተደረገ ወጣት፣ ተስፋ እንዲያይና የስራም ሆነ የትምህርት እድል እንዲኖረው ማድረግ አለብን፡፡ እነዚህን ሁሉ ለማሳካት ብዙ ፈተና ይጠብቀናል። ይሄንን ፈተና በትጋት ለመወጣት፣ የሀገሪቱ ምሁራን እስከ ዛሬ ሲሄዱበት ከነበረው የተሳሳተ መንገድ መመለስና ለሀገር መስራት አለባቸው። ጉዳዩ የሁላችንንም ጥረት  የሚጠይቅ ነው።
ከዚህ ቀደም ቃል የገቡት “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር” ቅፅ ሁለት መቼ ይወጣል?
እስካሁን 10 ምዕራፍ ያህል ፅፌያለሁ፤ ቢያንስ ይህን መፅሀፍ እስከ ቅፅ አምስት ጠብቁ።  1970 ላይ ነው የቆምኩት፤ ገና የ42 ዓመታት ታሪክ አልተነካም። ይሄው ነው።

Read 3017 times