Monday, 21 December 2020 00:00

በምሁራን እየተገመገመ የሚገኘው የኢዜማ ፖሊሲዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 • የኛ ቀዳሚ ፍላጎት ድህነትን በቤተሰብ ደረጃ መዋጋት ነው
        • ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ባሪያ የሚሆኑበትን ስርዓት አንታገስም
        • ግብርናውን ጠፍንጎ የያዘው አንዱ የመሬት ፖሊሲው ነው
        • ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ እንፈልጋለን

             ኢዜማ በምርጫ አሸንፎ መንግስት ቢሆን አገሪቱን የሚመራበት 45 ዋና ዋና ፖሊሲዎችን እያዘጋጀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሰባት ያህሉን ከሳምንት በፊት በምሁራን አስገምግሟል፡፡ በቀጣይም ፖሊሲዎቹን በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አቅርቦ እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡
የሌሎች ፖሊሲዎች ስራም በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ እስከአሁን ፓርቲው ይፋ ያደረጋቸው የኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ ኢንዱስትሪ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ማህበራዊ ከለላና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹ ናቸው፡፡
በእነዚህ ፖሊሲዎችና የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስልቶቹ እንዲሁም ኢዜማ በፖሊሲቹ ሊያሳካው ስላለመው ጉዳይ የፓርቲው የፖሊሲ ጉዳዮች አስተባባሪ አማን ይኹን ረዳ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ  ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡             ኢዜማ ፖሊሲዎቹን ያዘጋጃቸው በምን መነሻ ነው?
ፖሊሲዎቹ ፓርቲው በኢትዮጵያ ውስጥ ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸው ለውጦች ምንድን ናቸው? የሚለውን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ፓርቲያችን ኢዜማ ዴሞክራሲ በፅኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአት መገንባት አንዱ ልናሳካው የምንፈልገው አላማ ነው፡፡ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነበት ሃገር እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ በተለይ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነበት ስንል፤ብዙሃኑ ዜጋ የበይ ተመልካች በሆነበት ሃገር፣ ድህነት እጅግ የከፋና ስር የሰደደ ሆኖ ሰዎች መሰረታዊ ፍላጎታቸውን (ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት) ማሟላት የሚችሉበት ሁኔታ በሌለበት የተረጋጋ ማህበረሰብ ይኖራል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የተረጋጋ  ማህበረሰብ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር የዜጋ ፖለቲካ ብለን ስንነሳ፤ እያንዳንዱን ዜጋ ያከበረ፣ እውቅና የሰጠ የፖለቲካ ስርዓት ያለበት ዴሞክራሲ  እንዲፀና፤ ዜግነት ከነሙሉ ክብሩ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍንና የምናልማቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ነው፡፡ ፖሊሲዎቹን ሰፊ ጊዜ ወስደን፣ ምሁራንን ከሃገር ውስጥና ከውጪ አሳትፈን ያዘጋጀነው፡፡
የተዘጋጁት ፖሊሲዎች ምን መልክ አላቸው?
ፖሊሲዎቹ የተዘጋጁትና እየተዘጋጁ ያሉት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ ነው፡፡ በማህበራዊ ዘርፍ ከአስራ አምስት በላይ ፖሊሲዎች ነው እየተቀረጹ ያለው፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች ጥቅል አላማቸው፣ የድህነትና ያለ እኩልነት ሰው ሰራሹ ተፈጥሮአዊ ምክንያቶችን በውል በመለየት፤ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው፡፡ ለዚህም ደግሞ ዜጎች  እኩል እድል፣እኩል መብትና እኩል አያያዝና እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ እዚሁ ሃገር ላይ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ሁሉም ዜጋ እኩል አይደለም። ልጅና እንጀራ ልጅ፣ባለሃገርና መጤ እየተባለ ትውልዱ የሚከፋፈልበት የፖለቲካ ስርዓት ነው ያለን፡፡ ይሄን ማስተካከል እንፈልጋለን። ከእስረኛ አያያዝ ጀምሮ እኩል አያያዝ የለም። እኩል የሥራ እድል፣ እኩል ጥበቃ የማግኘት እድል የለም፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በፊትም አሁንም ዜጎችን በስራ እድል እኩል አያስተናገዱም፡፡ በቋንቋ፣ በፖለቲካ ወዘተ ውግንና  ዜጎች እኩል ዕድል የላቸውም፡፡ የእኩልነት ፅንሰ ሃሳብ ተፋልሶ ነው ያለው፡፡ ይሄን ማስቀረት እንፈልጋለን፡፡
የእኩልነት እጦት ምንጩ ምንድን ነው?  
የዘውግ ፖለቲካ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ይዘናቸው የመጣናቸው ዘልማዳዊ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ በዝምድና በጓደኝነት ሰዎችን አበላልጦ እድል የመስጠት ልማድና አስተሳሰብ በፊትም የነበረ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የዘውግ ፖለቲካው ተጨምሮበት ነገሩን ወደ ሌላ ከፍታ ነው የወሰደው፡፡ ስለዚህ ይሄን ተፈጥሮአዊ ምንጩን ማድረቅ አለብን፡፡ ይሄን ስንል እያንዳንዱ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ያሉ አሰራሮች መፈተሽ መቻል አለባቸው፡፡ እዚህ ሃገር ፍትህን ጠይቀን በትክክል የከለከለው አይጠየቅም፡፡ እኛ ይሄን በእርግጠኛነት እናስቀራለን፡፡ ፖሊሲያችንም፣ እዚህ ላይ የራሱ አቅጣጫ አለው፡፡
ድህነት የአለም ባንክ እንደሚያምነው የፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ የኛ ሀገር ድህነትም የፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ እኛ እያንዳንዱን ችግር በውል በመለየት ነው ፖሊሲያችንን ያዘጋጀነው። የትምህርት የጤና የመሳሰሉ  15 የማህበራዊ ዘርፍ ፖሊሲዎችን ነው እያዘጋጀን ያለው፡፡ ለምሳሌ የትምህርት  ፖሊሲ ስንል ሁሉም፤ ኢትዮጵያውያን ልጆች እኩል ጥራት ያለው ትምህርት የሚያገኙበት ስርዓት መገንባት ነው፡፡ ትምህርት የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍሪያ መንገድ ሲሆን በሌላ በኩል፤ የድህነት አዙሪት የመበጣጠሻ ፍቱህን መድሃኒት ነው። በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ  ቤተሰቦች፤ ልጆቻቸው ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ማግኘት ሲችሉ፣ ድህነትን ከቤተሰብ አይወርሱም ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ጥራት ያለው ትምህርት፤ የሃብታም ልጅ ልዩ እድል ብቻ ሳይሆን የድሃም ልጅ መብት እንዲሆን እንሰራለን፡፡ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት የሃብታም ልጅ ልዩ ጥቅም ሳይሆን የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት እንዲሆን ነው የምንሰራው፡፡ ኢዜማ ትምህርትና ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በእውቀት የበለፀገ፣ በስራ ፍቅርና፣በሙያ ስነ ምግባር እንዲሆን የሚያስችል ፖሊሲ ነው ያዘጋጀነው፡፡
ሌላው እዚህ ሀገር ላይ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ተግባራዊ እንዲደረግ እንፈልጋለን። መንግስት በርካታ ባለ ሃብቶች የተለያዩ ጥቅሞች እንዲያገኙ እያደረገ ከውጭ ይጋብዛል። ርካሽ ኤሌክትሪክ፣ ርካሽ የሰው ጉልበት እያለ ብዙ ኢንቨስተሮች ይስባል። ኢንቨስተሮቹ እዚህ መጥተው ደግሞ ለዜጎች ከ25 ዶላር ያልበለጠ ወርሃዊ ደመወዝ እየከፈሉ ይበዘብዟቸዋል። አያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ ነጻነቷን ያስከበሩላትን ሃገራችንን በጠራራ ፀሃይ፣ በአደባባይ ለኢኮኖሚ ባርነት ዜጎችን የሚዳረጉበትን ሁኔታ ኢዜማ አይታገስም። ለእነዚህ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያን ያበጃል ማለት ነው። የውጭ ባለሃብት እንፈልጋለን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ባሪያ የሚሆኑበትን ስርዓት አንታገስም። ዜጎቻችን የተሻለ ደመወዝ እንዲያገኙ እውቀት፣ ትጋትና የተሻለ የስራ እድል እንዲኖራቸው ተገቢውን ስልጠና እንሰጣለን፣ ምርታማነታቸው በጣም እንዲጨምር መንግስት የራሱን ስራ ይሰራል። እንደ ኢትዮጵያዊ ከእነ ሙሉ ክብሩ እንዲኖር እናደርጋለን። ዜጋው ክብር ያለው ኑሮ ለመኖር በወቅቱ ስንት ብር ያስፈልገዋል የሚለው ይጠናል። በየጊዜው የኑሮ ውድነትን ከግምት ውስጥ እያስገባን ቀመሩ ይከለሳል። በዚህ መንገድ ነው ድህነትን በቤተሰብ ደረጃ መዋጋት የሚቻለው። የኛም ቀዳሚ ፍላጎት ድህነትን በቤተሰብ ደረጃ መዋጋት ነው። ሰራተኞች ወደ ቤታቸው ይዘውት የሚሄዱት ገንዘብ እንዲጨምር ነው የምንፈልገው።
እስቲ ስለ ኢኮኖሚ  ፖሊሲያችሁ ማብራሪያ ይስጡን?
የኢኮኖሚ ዘርፍ ፖሊሲዎች አምስት አላማ አላቸው። በመጀመሪያ መሰረታዊ ፍላጎታችንን ማሟላት የሚያስችል የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት ነው። ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት ወዘተ…. ማሟላት የሚያስችል የኢኮኖሚ ስርዓት መግባት ነው አላማችን። ለዚህ ደግሞ የግብርና ስርዓታችን መለወጥ አለበት። ዛሬ እኮ እዚሁ ማምረት የሚቻሉ እንደ ነጭ ሽንኩርት ከቻይና፣ ብርቱካን ከግብፅ፣ ኪዊ የሚባል አትክልት ከኒውዚላንድ፣ ቀይ ሽንኩርት ከሱዳን…ወዘተ ከውጭ ነው የምናስገባው። የኢንዱስትሪው ይቅርና በቀላሉ በሃገር ውስጥ ልናመርታቸው የምንችላቸውን የግብርና ውጤቶች ከውጭ ነው የምናስገባው። የከተማችን ህፃናት በአብዛኛው ከአየርላንድና ከኒውዝላንድ የሚመጣ ወተት ነው የሚጠጡት፡፡ በርበሬ ሳይቀር ከቻይና ነው የምናስገበው። ድንጋይ ፣ ሴራሚክ፣ እምነ በረድ…… በርካታ ሃገር ውስጥ በቀላሉ ልናመርታቸው የምንችላቸውን ነው ከውጭ እያስገባን ያለነው። እነዚህ ሁሉ ባሉበት ደግሞ የምግብ ዋስትና ጥያቄ አለብን። የኛ የምግብ ዋስትና ፖሊሲያችን በሁለት አቅጣጫ የሚተገበር ነው። የመጀመሪያው መሰረታዊ የምግብ ዋስትና ነው፣ በልቶ የማደር ጥያቄ ማለት ነው። ሁለተኛው ደግሞ የተመጣጠነ ምግብ ጥያቄ ነው። ዜጎች ለአካላዊና አዕምሮአዊ እድገት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባቸው። እነዚህ አልሚ ምግቦች እንደ ልብ እንዲመረቱና ለብዙኃኑ በቀላሉ እንዲቀርቡ ለማድረግ ነው የምንሰራው። ከዚህ አንፃር የምግብ ምርት በእጅጉ እንዲበዛ ስለምንፈልግ በድጎማም ቢሆን ኢንቨስትመንቶች ምግብ ነክ ላይ እንዲሆኑ እንፈልጋለን። ጤፍ በጣም ተትረፍርፎ መመረት አለበት። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በዓመት የ100 ሚሊዮን ኩንታል የጤፍ ፍላጎት አለ፡፡ አሁን የሚመረተው ግን ከ60 ሚሊዮን  ኩንታል አይበልጥም:: የጤፍ መወደድ የመጣው ከእጥረት የተነሳ ነው። ስንዴም እንደዚያው። ሸገር ዳቦ እኮ ከውጭ የመጣ ስንዴ ነው የሚጠቀመው። ያም ሆኖ ችግሩን መቅረፍ አልቻለም። ችግሩን ከምንጩ መቅረፍ የሚለው የኢዜማ መርህ፤ ምርቱ ስለሌለ ነው እጥረት የተፈጠረው ብሎ ማመን ያስፈልጋል እንጂ “አሻጥረኛ ነጋዴዎች” እያሉ ሲወቅሱ መዋል የራስን የፖሊሲ ድክመት ለአጭር ጊዜ ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ነው። ስለዚህ በሌላ በኩል፣ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ እንሰራለን ብለን ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎች ነው የሚያዘጋጀው። እነዚህ ሁለት ዘርፎች ሲስፋፉ የሰው ሃይል ይቀጥራሉ። በሌላ በኩል፤ በምግብና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ትልልቅ ካፒታል አይፈልግም። ግብርናን ማዘመን የሚችሉ በቀላሉ ሊመረቱ ወይም ሊገዙ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡ ግብርና ብዙ ዜጎችን የቀጠረ፣ ለሃገሪቱ ጥቅል ኢኮኖሚ ብዙ ያበረክተ ዘርፍ፤ ቢሆንም፤ ለዚህ ዘርፍ የሚያዘው አመታዊ በጀት ከአጠቃላዩ ከ10 በመቶ የዘለለ አይደለም። ባንኮቻችን ለግብርና ዘርፍ የሚመድቡት ገንዘብ ከ5 በመቶ በታች ነው። የመሬት ፖሊሲው ዋነኛው ችግር ያለበት ነው። ግብርናውን ጠፍንጎ የያዘው አንዱ የመሬት ፖሊሲው ነው። አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ሆኖ በሚገባ እንዳያለማ እንቅፋት ነው የሆነው። የመሬቱ ስሪት የተበጣጠሰ መሆኑ ደግሞ ቴክኖሎጂን በስፋት ለመጠቀም አስቻይ አልሆነም።
ኢዜማ በጣም የዳበረ የግብርና ፖሊሲን ነው የሚከተለው። በመጀመሪያ ገበሬውን የመሬቱ ባለቤት ነው የምናደርገው። ሲፈልግ መሸጥ መለወጥና ሲፈልግ ማከራየት ይፈቀድለታል ማለት ነው። ይሄ በገጠርም በከተማም የምናደርገው ነው። ህገ-መንግስቱንም እናስተካክለዋለን። በአሁኑ ሰዓት እኛ ሃገር መሬት ትልቁ ሃብት ሆኗል። አስተሳሰቡም በዚህ የተቃኘ ነው። ኢዜማ ደግሞ ትልቁ ሃብት መሬት ሳይሆን ሰው ነው ብሎ ነው የሚያምነው። ዜጎቻችንን በእውቀት የዳበሩ፣ በዓለም ተወዳዳሪ የሆኑ ካደረግናቸው ትልቁ ሃብት ምን እንደሆነ እንገነዘባለን ማለት ነው። አለም በአሁኑ ወቅት እየፈጠረቻቸው ያሉ ቢሊየነሮች ከመሬት ጋር የተጣበቁ አይደሉም። በዓለም ላይ ሃብት እየተፈጠረ ያለው በቴክኖሎጂና በእውቀት ነው፤ ለዚህም የትምህርት ፖሊሲ እጅግ ወሳኝ ነው።
የኢኮኖሚ ፖሊሲያችሁ በምን በምን ዘርፍ ላይ ነው የሚያተኩረው?
እኛ በአጠቃላይ ግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ምክንያቱም እነዚህ ዘርፎች ለእያንዳንዱ ዜጋ ሃብት መፍጠር ያስችላሉ። ብዙ ሰው ይቀጥሩልናል። በኛ ሃገር ሁኔታ ደግሞ በየዓመቱ 2.5 ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወጣቶች ይፈጠራሉ። 2.9 ሚሊዮን ህዝብ ደግሞ በየዓመቱ ይፈጠራሉ። አፍሪካ ውስጥ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሃገሮች፣ የህዝብ ቁጥራቸው ከ3 ሚሊዮን በታች ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከቦትስዋና ህዝብ የሚበልጥ ህዝብ ወይም ከጅቡቲ ህዝብ 3 እጥፍ የሆነ ህዝብ  ይጨመርበታል፡፡ ስለዚህ ይሄን ህዝብ በየአመቱ እንዴት ነው የምንቀልበው? ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ 70 በመቶ የሚሆነው ወጣት ስራ ፈላጊ ነው፡፡ እኛ እድሜው ለስራ የደረሰ ሁሉ ስራ የሚያገኝበትን፣ ድህነትን በቤተሰብ ደረጃ የሚዋጋ ፖሊሲ ነው ያዘጋጀነው፡፡ ይህ ሲተገበር ያለ እኩልነት መሆኑ ይቀርና እኩልነት እየሰፈነ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ተወዳዳሪ የውጭ ንግድ መገንባት አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ምርት በዓመት ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ምርት ከውጭ ታስገባለች፡፡ እኛ ግን ወደ ውጭ የምንልከው ከ3.ቢ ዶላር አልፎ አያውቅም፤ ልዩነቱ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ይሔ ተወዳዳሪ አለመሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው። በቂ ኢንቨስትመንት  በግብርናና ኢንዱስትሪ  ዘርፍ እንዳላፈሰስን የሚያሳይ ነው፡፡ ይሄን ማስተካከል እንፈልጋለን፡፡
እንዴት ነው ይሄን የምታስተካክሉት?  
በሃገራችን ላይ ወደ ውጭም የሚላክ ምርት በመጀመሪያ በሃገር ውስጥ የተትረፈረፈ መሆን አለበት እንጂ ዜጋው የሚበላውን ቀምቶ መሆን የለበትም። ስለዚህ በመጀመሪያ ምርት በደንብ እንዲስፋፋ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል፤ ዘመናዊ የገበያ ስርዓት የመገንባት አላማ ነው በፖሊሲያችን የያዝነው። ከዋጋ ንረትም ሆነ ከዋጋ ማሽቆልቆል የፀዳ ስርዓት መገንባት ነው ዓላማችን። ጥብቅ የሞኒተርና ፊሲካል ፖሊሲን እንከተላለን። በኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነት የሚከሰተው በምርት እጥረት ስለሆነ ምርታማነትን የሚያሳድጉ አካሄዶችን እንከተላለን። ለቤቶች ፖሊሲም ትኩረት እንሰጣለን። ዜጎች አምስትና ስድስት  አመት ብቻ ቆጥበው የቤት ባለቤት የሚሆኑባቸውን ፖሊሲዎች ቀርፀናል። አሁን ኢኮኖሚው የሚዘወረው በመንግስት ነው። ትልቁ ግብር ከፋይ የመንግስት ተቋማት ናቸው። ለምሳሌ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ንግድ ባንክን፣ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የመሳሰሉት ከ10 ትልልቅ ግብር ከፋዮች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ትልቁ ቀጣሪ መንግስት ነው። ትልቁ ገዥም መንግስት ነው። ይህ የሶሻሊዝም ስርዓትን አሁንም እንዳልተላቀቅነው የሚያመላክት ነው። የመንግስት ነፍስ አሁንም ሶሻሊስታዊ እንደሆነች ያሳያል። የግሉ ባለሃብት አቅም የሌለውና የቀጨጨ ነው። ይህ የሆነው ግን በፖሊሲ ውጤት ነው። የግሉ ዘርፍ እጣ ፈንታ ያለው በመንግስት እጅ ነው። አሁን መንግስት ይሄን የግሉን ዘርፍ “ጨብጬ ልግደለው ወይስ ለቅቄው በነጻነት ይብረር” የሚል ማመንታት ውስጥ ነው ያለው። ኢዜማ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንደ ልቡ እንዲበር ያደርጋል። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ማህበራዊ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው። ግብር፣ ታክስ በአግባቡ መክፈል አለበት፡፡ በዚህ ላይ ምህረት አይኖረውም።  ኢኮኖሚው በመንግስት ብርቱ ክንድ የሚዘወር ሳይሆን ከመንግስት ወጥቶ  በግሉ ዘርፍ ሲመራ ውጤታማ የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት እንችላለን። ዛሬ ባንኮች አቅመ ቢስ የሆኑት በመንግስት ፖሊሲ የተነሳ ነው። አንድ ትልቅ የሚባል የግል ባንክ እኮ ከ2 መቶ ሚሊዮን ዶላር በታች ነው ካፒታሉ። በተቃራኒው 1 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ያደረገ የቢራ ፋብሪካ ያለበት ሃገር ነው። ይሄን ስናይ ትልልቆቹ 5 ባንኮች ካፒታላቸው የአንድ ሃገር ውስጥ ያለ የቢራ ፋብሪካን አያክልም ማለት ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ መዝለቅ አንችልም። ባንኮቻችንን ከፍ የሚያደርግ ፖሊሲ ነው ያዘጋጀነው፡፡ በሌላ በኩል፤በመኖሪያ ቤት ረገድ “ቤት ለሁሉም” የሚል ፖሊሲን ነው የምናራምደው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሁሉም ነገር የተሟላለት መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆን አለበት ብለን እናምናለን፤በቂ መሬት፣ የግንባታ ግብዓት አለ፤ ነገር ግን እጅግ ኋላ ቀር የሆነውን የፋይናንስ ስርዓት ማስተካከል ብቻ ነው ያስፈልጋል፡፡
የኢዜማ የፖለቲካ ዘርፉ ፖሊሲዎች ምን ይመስላሉ?
የፖለቲካ ዘርፉ ፖሊሲዎች በዋናነት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና ዜጎች በነፃነት በፖለቲካ የመሳተፍ፣ የመወከል መብታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአለማቀፍ መድረክ የነቃ ተሳታፊ እንድትሆን ነው የምንፈልገው። በአህጉር አቀፍና አለማቀፍ ጉዳይ ኢትዮጵያ ክብሯንና ጥቅሟን ሁልጊዜ አስከብራ እንድትወጣ እንሻለን፡፡ መንግስታዊ ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት እንዲፈጠር እንፈልጋለን፡፡ ይሄ  ማለት እያንዳንዱ ባለስልጣን ለስራው ብቻ ሳይሆን መስራት ሲጠበቅበት ባልሰራውም በህግ መጠየቅ  መቻል አለበት ብለን እናምናለን። እንደውም ኢዜማ፤ የመንግስት ቢሮክራሲው፤ ከፖለቲካ አባል መስፈርት የፀዳ፣ ሙያና ሙያተኛ የተገናኙበትና የተከበረበት፣ በእውቀት በክህሎት የላቁ ሰዎች ብቻ የሚሰሩበትን ስርዓት ለመፍጠር ነው ቃል የሚገባው፡፡
በሚዲያው ፖሊሲያችን ደግሞ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት አለበት፡፡ የመንግስት ሹመኞችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሚዲያዎች በፋይናንስ የሚደገፉበትን  ስርዓት እንገነባለን፡፡ ለጋዜጠኞች አስተማማኝ ከለላ እንሰጣለን፡፡ ለሲቪክ ማህበረሰቡም በተመሳሳይ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ፖሊሲ ነው ያዘጋጀነው፡፡ በአለት ላይ የተመሰረተ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ነው መዘርጋት የምንፈልገው፡፡
ኢዜማ በእነዚህ ፖሊሲዎቹ  ምን ዓላማዎችን ነው የሚያሳካው?
አንደኛ ዜጎች የሉአላዊነት ስልጣን ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዜጎች በክብርና በነፃነት የሚኖሩበትን ስርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ዜጎች ዛሬ በሃገራቸው ስደተኛ የሆኑበትን ስርዓት መቀየር ነው አላማችን። ፖለቲካዊ ነፃነት፤ ኢኮኖሚያዊ ክብር ለዜጎች ይገባል፡፡ በልማት በኩልም  አካባቢን የማይበክል፣ የመጪውን ትውልድ ጥቅም ታሳቢ ያደረገ፣ ዘላቂ ውጤት ያለውን ስርዓት ነው የምንዘረጋው፡፡    

Read 527 times