Saturday, 19 December 2020 11:47

አንዱን እሳት ሳናጠፋ፣ በየአቅጣጫው አዳዲስ እሳት መለኮስ ለምን?

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)


            “እንዳትነግረው ብዬ ብነግረው፤ እንዳትነግረው ብሎ ነገረው”፡፡
አስገራሚ አባባል ነው፡፡ በእርግጥ ተመሳሳይ መልዕክት የሚያስተላልፉ ሌሎች አባባሎችም አሉ፡፡
“ሰው ሲያማ፣ ለኔ ብለህ ስማ” የሚል አባባል፣ በብዙዎች ይታወቃል፡፡
“ነግ በኔ” የሚል ሀረግም አለላችሁ፡፡ በእርግጥ፣ “ትናንት፣ የማናውቀው እንግዳ፣ አላፊ መንደገኛ ነው የተደፈረው። ዛሬ፤ወዲያ ማዶ  አዲስ ተከራይ ነው የተዘረፈው።”… እያልን ራሳችንን ማታለል እንችላለን። ግን፣ ምን ዋጋ አለው?   
ይልቅስ፣ “ነግ በኔ” ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ሌላ ሰው ላይ የተፈፀመ ጥቃትና በደል፣ ዛሬ በዝምታ ከታለፈ፤ ነገ አንተ እና አንቺ ላይ ይደርሳል። “ነግ በኔ” ብሎ ማሰብ ይሻላል። ለምን? የሌሎች ሰዎችን ንግግር፤ተግባርና ባህሪይ በትክክል ለመዳኘት ይረዳል። ከወዲሁ ለመጠንቀቅና ጥቃትን አስቀድሞ ለመግታት ይጠቅማል፡፡ እውነት ነው፡፡ “ነግ በኔ” የሚለው አባባል፤ በትክክለኛ መንገድ  እየዳኘን ክፋትን ለመከላከል ያግዘናል። ነገር ግን፤ የየራሳችንንም መንገድ ልብ እንድንል ይመክረናል፡፡
ዛሬ፣ እከሌን መስደብና ማብሸቅ፣ እከሊትን መተንኮስና በሀሰት መወንጀል እንችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ስድብና የሀሰት ውንጀላ፣ በኮፒራይት ለኛ ብቻ የተፈቀደና ለሌላ ሰው የተከለከለ ነገር አይደለም። “ነግ በኔ” ነው ነገሩ፡፡
ዛሬ፣ እከሊትን መሸንገልና መሸወድ፣ እከሌን መሸፈጥና መዝረፍ ላያቅተን ይችላል፡፡ ሌሎች ሰዎችንና ንብረታቸውን እንደ ማገዶ የማንደድና እሳት የመሞቅ ክፉ ተግባርስ?  ዛሬ፤ እንትና ላይ ማሳደም፣ እንቶኔ ላይ በጥላቻና በጭፍን ስሜት ብዙ ሰዎችን መቀስቀስ ማነሳሳት፣ ብዙ ሰዎችን በመንጋ ማቧደንና ለጥፋት ማዝመት አይከብድ ይሆናል፡፡ ግን፣ ለሌሎችስ ይከብዳል?
የዚህና የዚያ ሃይማኖት፤የዚህና የዚያ ሰባኪ ተከታይ፣ የእከሌ ብሔርና የእከሊት ብሔረሰብ፣ ነባርና መጤ፣ የላይ ሰፈርና የታች ሰፈር፣ ሀብታምና ደሃ እያሉ በጭፍን ማቧደን፣ እንደ መንጋ ለጥፋት ማንጋጋት ተለምዷል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ሰዎችን በጭፍን እምነትና በዘረኝነት ማቧደን፣ ላንተ ወይም ላንቺ ብቻ የተፈቀደ ዘዴ፣ ”በፓተንት” ተመዝግቦ፣ ሌሎች ሰዎች የማይጠቀሙበት መሳሪያ አይደለም፡፡
ዛሬ የታጠቅሽው ክፉ መሳሪያ፣ ዛሬ የዘመትክበት ጠማማ መንገድ፤ ነገ ሌሎች ክፉና ጠማማ ሰዎች ይታጠቁታል፤ ይዘምቱበታል፡፡ ”ነግ በኔ” የተባለው በከንቱ አይደለም፡፡
አዎ፤ብዙ ሰበብ እንደረድራለን፡፡ ለስድብና ለብሽሽቅ፣ ለትንኮሳና ለሀሰት ውንጀላ፣ እልፍ ሰበብ  ለማዥጎድጎድ፣ ጊዜ አይፈጅብንም፡፡ በጣም ከመለማመዳችን የተነሳ፣ በእንቅልፍ ልብም ሆነን የማምከኛ መዓት በእሩምታ መልቀቅ እንችላለን።
“እሱ ነው የጀመረው፤ እሱ እየዋሸ፣ ዝም በል ትለኛለህ!?”
“የሷ ስድብ ለክፋት ነው፤ የዚያች ግን ለበጎ አላማ ነው”
“የእከሌ እንጂ የእገሌ ዘረኝነት፣ ጊዜያዊ ነው”
“እሾህን በእሾህ ነው”፡፡ “ውሸትን በውሸት”፣ “ዘረኝነትን በዘረኝነት”
“የእከሌ አመፅ፣ ለትግል ነው፡፡ የእገሌ ግን፣ ስርዓት አልበኝነት ነው”
“እንቶኔ፣ ጨካኝ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ እንቶኔ ግን፣ብዙ ሰው ቢገድል፣ ቆራጥ ነው”
“አንድም ሰው መገደል የለበትም፡፡ የዚህ ሀገር ህዝብ ሰው አይደለም፡፡ ሰብስቦ መጨረስ ነበር”፡፡
“የህዝብ ጥያቄ ካልተመለሰ ሰላም አይኖርም፡፡ ከዚህ ህዝብ ጋር አገሪቱ ሰላም አታገኝም”፡፡
“ህግ፣ ከህዝብ በታች ነው፡፡ የመንግስት እርምጃ አፈና ነው” ሲል ይቆይና፤ ”ሁሉም ነገር ከህግ በታች ነው፡፡ የመንግስት እርምጃ፣ የህግ እርምጃ ነው፡፡ ደግሞ፣ ለእነዚህ ምን ህግ ያስፈልጋል? ልክ ማስገባት፣ አፈር ማስበላት ነው፡፡”
“ይሄን አትመነው፡፡ ውሸታም ሁሉ፡፡ ወስዶ ቢያሳይሽም እንዳታምኚው፡፡ ምንም ቢናገር አትመኑ፡፡ ተንኮል ነው፡፡”፤ "ይሄኛው ሰውዬስ? ምንም ቢናገር አምነዋለሁ፡፡ መቼም ቢሆን እንደማይዋሽ እርግጠኛ ነኝ”
“ይህችኛዋ ተወነጀለች? ሺ ጊዜ ቢወነጅሏት ያንሳታል፡፡ ምንም ማስረጃ አያስፈልግም፡፡ ወንጀለኛ አይደለችም የሚል አለ? ....ያቺኛዋስ? ምን አደረገች? የምን ወንጀል? የታለ ማስረጃ? አንተ ላይ ወንጀል ፈፅማለች? ሌላ ላይስ እንደሰራች በዓይንህ አይተሃል? እሷን የሚወነጅሉ፣ ……መታሰር አለባቸው”….     
“አትንገረው ብዬ ብነግረው”።
ሲያሰኘን፣ በሐሰት እንመሰክርለታለን። ሲያሰኘን በሐሰት እንመሰክርበታለን። ስንፈልግ እናነሳዋለን። ስንፈልግ እንጥለዋለን። ለሆነ ጊዜ፣ ለሆነ ጉዳይ፣ ለሆነ ሰውና ፓርቲ፣…. ሁሉም ነገር ይፈቀዳል፤ መዋሸት፣ በሃሰት መወንጀል፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ፣ በዘር ወይ በብሔር ብሔረሰብ ማቧደን፣ በጭፍን ስሜት ጥላቻን ማዛመት፣ ለጥፋት አነሳስቶ ማዝመት… ችግር የለውም ማለት ነው?  ችግር ቢኖረው እንኳ፣ ሰበብና ማመካኛ ይዘጋጅለታል? ታይቶ እንዳልታየ ይታለፋል? ሀላል ነው? ለሆነ ሰውና ፓርቲ፣ ለሆነ ጉዳይ፣ ለሆነ ጊዜና ቦታ፣ ሃላል እንዲሆን እንመኛለን።  ለሌላ ሰው በሌላ ጉዳይ ላይና በሌላ ቦታና ጊዜስ … ሃላል ነው? አይደለም። ሐራም ነው ብለን አክርረን እናወግዛለን፡፡  
ለአቤ ሁሉም ነገር ሃላል  ነው። መናገርም መስማትም፣ የሰውን ሚስጥር መዘርገፍም፣ ከሰው ጀርባ በድብቅ ስም ማጥፋትና በሃሰት መወንጀልም፣ አሉባልታ ማዛመትም ችግር የለውም። ባሰኘው ጊዜ ሁሉም ነገር ሃላል እንዲሆንለት ይፈልጋል አቤ።
ነገር ግን፣ ለሱ ብቻ እንጂ ለሌሎች ሐራም ነው። የአቤ ምኞት እንደዚያ ነው። “አትንገረው” ሌሎችን ሁሉ መቆጣጠር የሚችል ይመስለዋል። ብልጣ ብልጥ ጥበበኛ ነኝ ብሎ ያስባል።
አሉባልታና የሐሰት ውንጀላን፣ በዘረኝነትና በጭፍን እምነት ማቧደንን፣ የዝርፊያና  የውድመት ቅስቀሳን፣ የጥላቻና የግድያ ዘመቻን፣… እሱ ሲያሰኘው ማቀጣጠል፣ ሲያሻው ማቀዝቀዝ፤ በፈቀደው ቦታና ጊዜ መለኮስና  ማዳፈን፣ …እንደ ማብሪያ ማጥፊያ፣ እንዳሻኝ እቆጣጠራለሁ ብሎ ስለሚያምን፣ ከምኞቱ ውጭ የሆነ ነገር ሲገጥመው፣ ለማመን ይከብደዋል። ይናደዳል። ይማረራል። ክህደት የተፈጸመበት ያህል ይንገበገባል።
“አትንገረው ብዬ ብነግረው” እያለ ይንጨረጨራል። አቤ ከቤን ያወግዛል። ለምን? ለካ፣ የከቤ አስተሳሰብም እንደ አቤ ነው። ከአቤ የሰማውን ነገር ይናገራል፤ ያየውንም ዘዴ ደገመ። የተለየ ነገር አላደረገም ከቤ። አቤ ግን እንደ ወንጀል ቆጥሮታል፤ ተፀይፎታል። አውግዞታል።
“አትንገረው ብዬ ብነግረው አትንገር ብሎ ነገረው”። በማለትም ነው፤ አቤ በምሬት ከቤን የሚወነጅለው፤ ግን አሰቡት። አቤ ለከቤ ተናገረ፤ “ለከቤ አትንገረው” በማለት።
ከቤ በተራው፤ ለከቤ ተናገረ “ለአቤ አትንገረው” በማለት።
አቤ ይህን ሲያውቅ፣ በከቤ ክህደት ተናደደ። ግን፣ እንዴት አወቀ? ዞሮ ደረሰዋ! እሱ የጀመረውን ጠማማ መንገድ፣ ከቤ ደገመው። ወደ ከቤ አደረሰው። ከቤ ዝም አላለም። ወደ አቤ መጣ።
አቤ ለከቤ አንሾካሾከ፤ ከቤ ደግሞ ለደቤ ሹክ፤ደቤ ደግሞ ለአቤ፡፡”አትንገረው ብሎ ቢነግረው፤ አትንገረው ብሎ ነገረኝ” ይላል አቤ። በዚህም የቀድሞ ሚስጥረኛውን (ከቤን) ያወግዛል። አዙሪት ነው፡፡ የቀድሞ ባላንጣውን (ደቤን) ደግሞ በምስጋና ያደንቃል፡፡ እንዲህ አይነት አዙሪት ነው፣ የአገራችን ፋታ የለሽ የፖለቲካ ቀውስ።
የሶስቱም መጥፎ ሃሳብና ክፉ ዘዴ፣ አንድ አይነት ነው። ግን፤ የሆነ ሰው ላይ ሲሆን ያወግዙታል፤ ሌላ ሰው ላይ ሲሆን ደግሞ፣አስፀያፊ ወንጀል ነው በማለት ይኮንኑታል። የሆነ ሰው ላይ ሲሆን፣ እንደጥፋት አይቆጥሩትም። የብልጥነት ጥበብ፣ በፖለቲካ የመራቀቅ ምጥቀት ሆኖ ይታያቸዋል። በአድናቆት ያጨበጭቡለታል።
የጠላነውን ፖለቲከኛ ወይም የጠመድነውን ፓርቲ ለማውገዝ እስካገለገለ ድረስ፤ የእውነት ተቆርቋሪ፣ የግል ንብረት ጠበቃ፣ የግል ማንነት አክባሪ መስለን ለመታየት እንሟሟታለን። ሸንጋይ፣ ውሸታም፣ አውዳሚ፣ ዘራፊ፣ ዘረኛ፣ ነፍሰ ገዳይ እያልን እናወግዛለን። በሃሰትም ይሁን በእውነት እናወግዛለን።
በተቃራኒው ጠቃሚ መስሎ ሲታየን፣ አቋራጭ መፍትሄ እንደሚሆን ስናምን ደግሞ፣ ሽንገላንና ውሸትን እንደ ጥበብ እናደንቃለን- “ሰራችላቸው” በማለት። ዝርፊያውንና ውድመቱን የለውጥ ሃይል ብለን እንሰይመዋለን። በዘርና በሃይማኖት የማቧደን ክፋትስ? የብዝሃነት ንቅናቄ፣ የመብት ጥያቄ፣ የማንነትና የፌደራሊዝም ትግል ብለን እንክበዋለን። ሲያሻን ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያስውብ ህብር፣ አንድነትን የሚያበለጽግ ብዝሃነት፣ የአገራዊነት ጠንካራ መሰረት” እያል እናወድሰዋለን።  ለምን? ዘረኝነትን እንዳሻን የምንዘውረው ይመስለናል። ለመረጥነው ጉዳይ ብቻ፣ ለዛሬና ለጊዜው ብቻ፣ እዚህች ውስጥና እዚያ ሩቅ ቦታ ብቻ፣ ለእገሌና ለእከሌ ብቻ… እያልን አጥር የምንሰራለት፣ በማብሪያና ማጥፊያ፣ እንዳሰኘን ማጋጋልና ማብረድ የምንችል ይመስለናል።
“አትንገረው  ብሎ መናገር”… የሚያዋጣ ሆኖ ይታየናል። ተነስ ስንለው ብቻ እንዲነሳ፣ በቃ ስንለው በቅፅበት እንዲያበቃ እንጠብቃለን። ግን የአዙሪት ቁልቁለትን ነው የምንጋብዘው።
"አትንገረው ብዬ ብነግረው፣አትንገር ብሎ ነገረው፡፡" ይህን አባባል እናስታውስ፡፡ ከአዙሪት ለመውጣት ሊያገለግለን ይችላል።Read 4748 times