Print this page
Tuesday, 22 December 2020 00:00

የህውሓት ሰዎች፤ ከፊደል “ሀ” ወይም ከመከራ “ዋ” ብላችሁ ተማሩ

Written by  ሳህሉ ቦኩ
Rate this item
(3 votes)

 በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ አገሮች፣ ወዘተ የምትኖሩና የተማራችሁ የህውሓት አባላት፣ ልጆችና ዘመዶች፣ የዝርፊያ የጥቅም ተጋሪዎችና  በብሔር ፕሮፓጋንዳ የተታለላችሁ የትግራይ አካባቢ ተወላጆች፣ ከማህበራዊ ሚዲያዎች ፅሁፎቻችሁ እንደሚታየው፤ የትጥቅ ትግል የሚባለውን ነገር እንደገና ለመጀመርና ትግራይን ገንጥሎ አገር ለመመስረት በመነጋገር ላይ ናችሁ፡፡
እንደ ሁሉን ቻይ ፈጣሪ ያያችሁት ህውሓት፤ ማንም ሳይነካው ራሱ በከፈተው ጦርነት በአጭር ቀናት ውስጥ ውሃ የነካው የጥጥ-ከረሜላ (cotton candy) ይመስል፣ ያ ማንነቱ ሙሽሽ ብሎ ጠፍቷል። የከባድ ሽንፈት ስሜት አእምሮን ሊዘጋ የሚችል ነገር ቢሆንም፣ እስኪ ስሜታችሁን ለጊዜው ረገብ አድርጉትና የሆነው ነገር ምንድነው ብላችሁ አስቡ፡፡
“ሀ” ብሎ መማር የተማራችሁት ዘመናዊ ትምህርትም ሆነ የምትኖሩባቸው የሰለጠኑ አገራት፣ ፖለቲካን የሚመሩት በውይይትና በድርድር፣ በሰላማዊ  መንገድ፣ የህግ የበላይነትን ያለ ማወላወል በመተግበር፣ መብትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሰፈነበት ስርአትን በመፍጠር፣ ወዘተ ነው፡፡ የ21ኛው ክፍለ-ዘመን የሰለጠነ ፖለቲካ ማለት ይሄ መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡
በሃይል፣ በጦርነት፣ በግጭት፣ ወዘተ--ዘላቂ ሰላምና እድገት ሊመጣ እንደማይችል ብዙ ዋጋ ከፍለው አልፈውበት ስለገባቸው፣ የሰለጠኑት አገራት ይህን አካሄድ “ኋላ ቀርነት ነው” በማለት ወደ ኋላቸው ጥለውታል፡፡ እነዚህ አገሮች አሁን የሚጠቀሙት ኋላ ቀሩን የሴራና የግጭት ፖለቲካን ቢሆን ኖሮ፣ እናንተ አሁን እዚያ በሰላምና በተመቻቸ ሁኔታ ባልኖራችሁ ነበር፡፡ ስለዚህ ካጠናችሁት ፊደልና ከምትኖሩባቸው አገሮች የፖለቲካ አመራር ልምድ “ሀ” ብላችሁ ተማሩ፡፡ በትክክል የተማረ ደግሞ  የተማረው ነገር ይቀርፀዋል እንጂ ቀድሞ እንደነበረው ሆኖ አይቀጥልም። ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ቢኖራችሁ ወይም ፕሮፌሰሮች ብትሆኑ፣ አስተሳሰባችሁንና የፖለቲካ አመራር አቅማችሁን ለበጎና ለሰለጠነው አካሄድ ካልቀየረውና “ህዝባችን” የምትሉትን ለመቀየር ካልዋለ፣ የናንተ መማር ጥቅሙ ምንድነው? የተማረ ፊደል የቆጠረ ብቻ ሳይሆን፣ ፊደል ለበጎ የለወጠው ነው፡፡ እናንተ የተማራችሁት ካልተለወጣችሁና ሌላውን ለበጎ ለመለወጥ ካልሆናችሁ፣ ሳያውቅ ከፍተኛ ጥፋት ከሚያደርሰው የባሰ ተጠያቂዎች  ናችሁ - በህግም፣ በታሪክም፣ በህሊናም፡፡
“ዋ” ብሎ መማር ህውሓት ከ30 አመታት በላይ እንደ መንግስት ተጉዞ ዘላቂ ሰላም፣ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርአት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የአገር አንድነት፣ ወዘተ አላመጣም፡፡ አገሪቱ ላይ ያመጣው ክፍፍልን፣ እርስ በእርስ መጠራጠርን፣ የከባድ ሙስና መስፋፋትን፣ በብዙ ቁልፍ ቦታዎች ላይ የትግራይ ብሄር የበላይነትን ማንገስ፣ እርስ-በእርስ መጫረስን፣ ወዘተ ነው፡፡ የተከተለውም ስልት የተቃወሙትን በማሰርና በማሰቃየት፣ በስውር ገድሎ በስውር በመቅበር፣ በመፈረጅ (ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ኪራይ ሰብሳቢ ወዘተ እያሉ)፣ ከእኛ
ወዲያ አዋቂና ጀግና ላሳር ብሎ ሌላውን በመናቅ፣ ለደሃው ህዝብ ፍርፋሪ እየጣሉለት ለራስ ቢሊየን ብሮችን ያለ ገደብ በማከማቸት፣ ወዘተ ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥፋቶች፣ ራሱ ህውሓት መለስ ዜናዊ እያለ “በስብሰናል፣ ስህተት ሰርተናል” ብሎ ያመናቸው ናቸው - የህውሓትን የግምገማ ሪፖርቶችና ቪዲዮዎች ተመልከቱ፡፡
ህውሃት ለህዝብ ዘላቂና ፍትሃዊ ውጤቶችን አምጥቶ ቢሆን ኖሮ ለሌላ 30 አመት ኑርልን፣ ቀጥልልን፣ ምራን የሚለው ህዝብ ራሱ ነበር፤ በከባድ የህዝብ ምሬትና ትግልም ከፌደራል ስልጣን አይባረርም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ከማንም በላይ እቆረቆርለታለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ እንኳ ከ30 አመት በላይ በብቸኝነት አስተዳድሮት የሚረባ ልማት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን አላመጣለትም፡፡ ባለስልጣኖቹ ግን ለራሳቸውና ለፖለቲካ አጋሮቻቸው በቢሊየኖች ዶላር የሚቆጠር ገንዘብና ሃብት ሲሰበስቡ ኖረዋል፡፡
ይህም አልበቃ ብሎት፣ ህውሓት ላለፈው ሁለት አመት ተኩል፣ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪነቱን በብቸኝነት ይዞ ፌደራል መንግስትም ለስለስ ያለ አቋም እያሳየው እያለ፣ የራሱን የሴራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ስሌቶች ሲሰራ ቆይቶ ከድጡ ወደ ማጡ የሆነ ጉዞ ውስጥ ገባ፡፡ ፌደራል ፖሊስ ክስ ሊመሰርትባቸው የሚፈልጋቸውን ጥቂት ወንጀለኞች ስጠኝ ሲል፣ ህውሓት ከህገ-መንግስታዊ ስርአቱ አፈንግጦ፣
ወንጀለኞችን አልሰጥም አለ፤ ፌደራል መንግስቱን የሚያብጠለጥል ማቆሚያ የሌለው ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ኖረ፣ የፖለቲካ ድርድር ካላደረግን ኢትዮጵያ ትበተናለች ሲል በተደጋጋሚ አስፈራራ፤ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በትጥቅ ትግል ለማሳካት የሚፈልጉ ጥቂት የነውጥ ሃይሎችን በመቀሌ በማሰባሰብና ሁሉንም አይነት ድጋፍ በማድረግ፣ የተለያዩ አሰቃቂ ግድያዎችና የንብረት ውድመቶች እንዲደርሱ አደረገ፡፡
በዚህም አላበቃም፣ ሚሊሽያና ልዩ ሃይል በሚል ከ200 ሺ በላይ ወታደራዊ ሃይል ሲያሰለጥን ቆየ፣ በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች የጦር ምሽጎችን ሲቆፍር ቆየ፤ የጦር መሳሪያዎችን በድብቅ ሲያከማች ኖረ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኮቪድ 19 ምክንያት ምርጫ እንዲራዘም ሲወስን፣ ህውሓት ግን ከህግ ውጪ የራሱን ምርጫ አደረገ፣ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ጀምሮ ከፌደራል መንግስት የሚሰጠኝን ትእዛዝ አልቀበልም አለ፤ ትግራይ ለሚገኘው የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት መሪ ከፌደራል መንግስት ሲላክ
አላስገባም አለ፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተሞች ከፍተኛ የሽብር ጥቃት የሚፈፅሙ ሰዎች አሰማራ፣ ወዘተ፡፡
እናንተ በብዙ ሺ የምትቆጠሩ የተማራችሁና ፖለቲካ በሰለጠነው አለም እንዴት እንደሚካሄድ ቀንና ማታ የምታዩ ሰዎች፣ ህውሓት ይህን ሁሉ ሲያደርግ እያያችሁ ነገሩ ስርአት እንዲይዝና እንዲስተካከል ማድረግ ሲገባችሁ፣ ህውሓት ልክ ነው እያላችሁ በተለያዩ ሚዲያዎች ስትደግፉ ከረማችሁ፡፡ ይባስ ብላችሁ፣ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው በማለት ጦርነት ፈላጊ እንደሆናችሁ በተጨባጭ አስመሰከራችሁ። ራሳችሁ ለራሳችሁ እየነገራችሁ የገነባችሁት እብሪት፣ እንደ ፈርኦን ልባችሁን አደንድኖት ማንንም የማትሰሙ
ሆናችሁ፡፡ የምትሆኑትና የምታደርጉት ነገር ሁሉ ለዛሬው ውርደት፣ ለቅሶ፣ “አለም አቀፍ ማህበረሰቡን አድኑን” ብሎ ኡኡ ለማለት፣ ወዘተ ሊዳርጋችሁ እንደሚችል ግልፅ ነበር፡፡
የናፈቃችሁትን ጦርነት፣ ጥቅምት 24 ቀን ህውሓት ለኮሰው - የትግራይ ሚሊሽያና ልዩ ሃይል ተብዬዎችን አሰልፎ አገር ለመጠበቅ የተሰማራውንና የትግራይን ህዝብ ሲረዳ የኖረው የሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ በእኩለ-ለሊት፣ በተኛበት ከውስጥም ከውጪም ወታደራዊ ጥቃት ፈፀመ፣ ብዙዎችን ገደለ፣ በርካታ መሳሪያ ነጥቆ ወሰደ፣ አንዳንዶችንም ማርኮ ወሰደ። ህውሓት - አንድ የፖለቲካ ፓርቲና ቡድን - ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተ። የጦርነቱ አላማና ግብ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ከተሞችና ቁልፍ ቦታዎች ላይ (በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ) ከፍተኛ የሽብር ጥቃቶች በመፈፀም፣ አገሪቱ የለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ማድረግና በዚህ ወቅት አንድ ወሳኝ ጊዜ ጠብቆ፣ ከአጎራባች አስተዳደራዊ ክልሎች ለትግራይ ተጨማሪ መሬት በሃይል ይዞ፣ ነፃ የትግራይ መንግስትን መስርተናል ለማለት ነበር፡፡ ፌደራል መንግስትም ፈጣን አገርን የማዳንና ህግን የማስከበር የአፀፋ ወታደራዊ ዘመቻ ጀመረ፡፡ የአፀፋ ወታደራዊ ዘመቻው ፍፃሜ ምን ሊሆን እንደሚችል በጥቂት ቀናት ውስጥ ግልፅ መሆን ጀመረ - ህውሓት ከባድ ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ፖለቲካዊ ኪሳራዎች ደረሰበት፤ የህውሓት አላማም ከሸፈ፡፡
ሰፊ የሆነውን ዝርዝር ለታሪክ ፀሃፊዎች ልተወውና፣ ህውሓት በከባድ እብሪት ተወጥሮ ራሱ በጫረው ጦርነት ለ30 አመታት ያህል የገነባውን ከፍተኛ የፖለቲካ ቁመና፣ ተፅእኖ ፈጣሪነትና በቢሊየን ብሮች የሚቆጠር የተዘረፈ ሃብት 30 ባልሞሉ ቀናት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አጣው። ይህ በምስራቅ አፍሪካ የክፍለ-ዘመኑ ታላቅ የፖለቲካ ኪሳራ ሊባል ይችላል፡፡
ፖለቲካ የገራገሮችና የቅዱሳን አለም አለመሆኑ ቢታወቅም፣ አንድ ቡድን  በሃይል፣ በተንኮል፣ በዝርፊያ፣ በግፍ፣ በአፈና፣ ወዘተ ላይ ተመስርቶ ሊዘልቅ የሚችል ፖለቲካም አስተዳደርም ሊኖረው እንደማይችል የህውሓት የኪሳራ ታሪክ በቂ ምስክር ነው። ህውሓት ራሱንም በብዙ መቶ ሺ ሊቆጠሩ የሚችሉ ደጋፊዎቹንና የጥቅም አጋሮቹንም አዋርዷል፡፡ እናንተ ማውገዝ ወይም መጥላት ካለባችሁ፣ በደርግ ጊዜ የነፃነት ምሳሌያችሁ የነበረው፣ ነገር ግን ለ30 አመታት ያህል መንግስት ሆኖ ቆይቶ ራሱን መለወጥና ማዘመን ያቃተው ህውሓትንና ቀንና ሌሊት በትጋት ስታጨበጭቡለት የነበራችሁትን ራሳችሁን እንጂ ፌደራል መንግስትን ወይም አገርን የማዳንና ህግን የማስከበር ትልቅ ሃላፊነት ያለበትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን አይደለም፡፡
ታላላቆቻችሁ ከፊደል “ሀ” ብለው መማር አቃታቸው፡፡ አሁን እናንተ እልሁን ተዉትና ከወደቀባችሁ ታላቅ ውርደትና መከራ “ዋ” ብላችሁ ተማሩ - ህውሓትን ለመድገም አትሞክሩ፤ በሰለጠነው መንገድ ኑ፡፡
መቶ አመትም ይፍጅብን ነፃ ትግራይን እንመሰርታለን ለምትሉት ነገር ደግሞ፣ ይህን የትግራይ ህዝብ አይፈልገውም እንጂ፣ ቢቻል እንኳ የጥቂቶቻችሁን ከንቱ የታላቅነት ስሜት ለወራት በጭፈራ ከማርካት ያለፈ ትግራይን የትም አያደርሳትም፡፡ በዚህ በ21ኛው የኒዮ-ኮሎኒያሊዝም ዘመን፣ ሚጢጢ የመሬት ስፋት፣ በቁጥር ትንሽ ህዝብ፣ ድሃና የባህር በር የሌለው መሬት ይዞ ከእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ነፃ የሆነ ታላቅ አገር መገንባት አይቻልም፡፡ እንኳን እንደ ትግራይ ያለ፣ እንደ እነ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት
አረብ ኢምሬትስ የመሳሰሉት ሃብታም አገሮች እንኳ፣ ከምእራቡ አለም የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ማምለጥ አልቻሉም። እንደሚታወቀው፣ የሁለቱም አገሮች ጉዳይና ገንዘብ ያለው በአሜሪካ፣ እንግሊዝና እስራኤል እጅ ነው፡፡
ከ50 እና 60 አመታት በፊት፣ ትንሽ መሬት ይዘህም ቢሆን በመጠኑ ያደገ አገር ለመፍጠር ሰፊ እድል ነበረ፤ አሁን ግን ያ እድል የለም። ባለፉት 50 አመታት ውስጥ በአለም በርካታ አለም አቀፋዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ቴክኖሎጂያዊና የኢንቨስትመንት አማራጭ ነገሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተቀያይረዋል፡፡ ሚጢጢ አገር ይዘህ፣ በእልህ፣ በወኔና በ “ታላቅ ነበርን ታላቅ እንሆናለን” ቀረርቶ ታላቅ አገር መፍጠር አይቻልም - ያ ጊዜ ካለፈ ቆይቷል፡፡ እውነተኛ ነፃነት ያላትና ታላቅ አገር መገንባት የሚቻለው ብዙ ህዝብና ሰፊ መሬት ይዘህ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላምና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እየኖርክ፣ ከምዕራቡ አለም ያለማቋረጥ የሚፈጽሙብህን የዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ድብደባዎች እንደ አንድ ህዝብ መክተህ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቢሊየኖች ሳይሆን በትሪሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ኢንቨስትመንት፣ በታላቅ ጥረትና አመቺ ሁኔታዎችን
በመፍጠር ስበህ፣ የውስጥ ፖለቲካህን በትክክለኛና መጣኝ ዴሞክራሲያዊ መሰረቶች ላይ ተክለህ፣ ህዝብ በእኩልነት እንዲኖርና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ስርአት እንዲኖር አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥረህ፣ እና የሁለት ትውልዶች ያህል እድሜ ፈጅተህ ነው፡፡ የዚህ ዝርዝሩ ብዙ ስለሆነ በዚች አጭር ፅሁፍ ወደዚያ መግባት አልችልም፡፡ የሚያውቅ በደንብ ይገባዋል፤ የማያውቅ ግን የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ፡፡
ስለዚህ፣ እናንተ ተማርን፣ አወቅን፣ ሰለጠንን፣ የበቃን ነን የምትሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች፡- ለትግራይ ህዝብ የምታስቡ ከሆነ፣ እንደ ህውሓት ባረጀና ባፈጀ የጥፋት መንገድ ሳይሆን ለ21ኛ ክፍለ-ዘመን በሚመጥን በሰለጠነው መንገድና አቅም ኑለት፡፡ ህውሓት ላይ ከተከሰተው፣ በምስራቅ አፍሪካ የክፍለ-ዘመኑ ታላቅ የፖለቲካ ውድቀት “ዋ” ብላችሁ ተማሩ፡፡ በድጋሚ በህውሓት መንገድ ብትመጡ፣ ያለፈውን የከፍታና የውርደት ቀለበት ትደግሙታላችሁ እንጂ ትውልድን እየተሻገረ ወደፊትና ወደ ላይ የሚሄድ ዘላቂ ውጤት አታመጡም። አለን እንደምትሉት ጭንቅላቱ ካላችሁ፣ እልሁን ተውትና፣ ህውሓት ያመጣባችሁን
ውርደት ዋጥ አድርጉትና፣ ከእውነት ጋር ታረቁና፣ በሰለጠነው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለትግራይ ህዝብ ኑለትና ከድህነት አውጡት፡፡
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ የተንጸባረቀው አቋምና አመለካከት ጸሃፊውን ብቻ እንደሚወክል እንገልጻለን። ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-contactmerosah1@gma ማግኘት ይቻላል።

Read 8390 times