Print this page
Saturday, 19 December 2020 12:31

የድንቁርና ጌቶች ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርሲቲ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ከመነሻው ጀምሮ ትምህርት ፖሊሲው ብዙ ትችቶችን ያስተናገደ ነበር፡፡ ዋናው ትችት ፖሊሲው በረጂ ሀገራት መራሽነት መመንጨቱና ከሀገር ይልቅ የድርጅቱን ህልውና ታሳቢ ማድረጉ ላይ ነበር፡፡ ይህም በአብዮታዊ ዲሞክራሲ (የብዙሐን ወገኝተኝነት) ስም ትምህርትን ለብዙኃኑ አድርሺአለሁ ለሚል ልፈፋው እንዲበጀው የሰራው ስራ ጥራቱን እጅግ አሽቆልቁሏል፡፡ በተሳሳተ ፖሊሲ “እንዳይማር ተደርጎ የሚመራው” ወደፊት ለመማር የሚኖረውን ዕድል እንኳን ያጠፋ ነበር። ነገሩ ለሌላ አውድ የተፃፈ ቢሆንም፤ ብርጊት ብሮክ “whose education for all? The recolonization of the African mind” በሚል በፈረንጆቹ ሚሊኒየም መጀመሪያ ላይ የፃፈችው መጽሐፍ ትርጉም፣ በኢትዮጵያ አውድ እንድናስብ ያደርገናል፡፡ የእርሷ ጥያቄ ትምህርት ለሁሉም (ይስፋፋ) ሲባል “ምን ዓይነት ትምህርት” የሚል ነው፡፡ እኛ ጋ ደግሞ ትምህርት ለሁሉም (ይስፋፋ) ሲባል “ምን ዓይነት ትምህርት” ተብሎ መጠየቅ ነበረበት፡፡ የጥራቱ ችግር በተመሳሳይ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፤ በላዕላይ ገልብጦ ለህዝብ ተብሎ እንደተሰራና እንደ ስኬት መቆጠሩ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን አበሳጪም ጭምር ነበር፡፡
ህወሃት ኢህአዴግ በሁሉም ደረጃ ስለታየው የጥራት ችግር፣ ብዙዎቹ እየጮሁ በማን አለብኝነት “ጆሮ ዳባ ልበስ” ማለቱ ትውልዱን ለማኮላሸት የረቀቀ ስትራቴጂኩ በመሆኑ ነው መባሉ አግባብ ነበር፡፡ የዚህም መልስ ነው ህወኃት ኢህአዴግን የድንቁርና ጌታ የሚያሰኘው፡፡ ከዓመታት በኋላ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ውጤቱን፤ "ህወሃት ቀጪ ስርዓት ፈጥሮ የተቀናጣና “የተረገመ” የሚመስል ትውልድ አምርቷል። ህወሃት ወጣቱን ትውልድ ሽባ ለማድረግ በአገሩ ጉዳይ ላይ ከመነጋገር ፋንታ የእንግሊዞችን ፉት ቦል ማየት፣ የአረቦችን ሺሻ  ማዘውተር፣ ሽሙጥን እንደቁም ነገር መቀበል፣ የትምህርት ውጤትና ዲግሪ በማጭበርበርና በገንዘብ ሲገዛ እንደ ተራ ነገር መቀበልን እንዲመርጥ አሳምኖታል። ሆነ ተብሎ ወጣቱን ትውልድ ሽባ የማድረግ ዘዴ…።; በማለት መግለፃቸው የድርጅቱን የትምህርት አዝማሚያ በትክክል ያሳየ ነው ሊባል ይችላል።
ዩኒቨርሲቲዎችን ማብዛት ዩኒቨርሲቲውን ለመቅጣት ነው ሲባል፤ ብሽሽቅ ቢመስልም፤ ከህወሃት  አናሳ ተፈጥሮ አንጻር ትርጉም የሚሰጥ ዕይታ ነው። የህወሓትን መሰረተ ሰናናነት በልፈፋ ለማፋፋት በወጣው የትምህርት ፖሊሲ፣ ቀዳሚ ተጎጂው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ስለዚህ የህወሓት ኢህአዴግ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም/ ዩኒቨርሲቲ አቋም መነሻ፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የገባው ፀብ ነበር ማለት ይቻላል። የዩኒቨርሲቲውን ብሔራዊነት የማጥፋት የቅርብ ዓላማውን አሳክቷል። የ1985ቱን ተቃውሞ ተከትሎ በፍጥነት ሰልፋቸውን ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያደረጉትን የሌሎች ኮሌጆች እንቅስቃሴ መነጠል ከሞላ ጎደል ተችሏል። ስለዚህ እነርሱ ስለ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምንም አያገባቸውም፤ ወይ ዩኒቨርሲቲው ስለ እነርሱ አያገባውም ማለት ነው ጀመሩ።
በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉም፤ ዩኒቨርሲቲዎችን ማብዛቱን ለትምህርት መስፋፋት እንደሰራው ማስመሰል ችሏል። ለዚህም ዓላማ በትምህርት ሚኒስቴርና አቅም ግንባታ ሚኒስቴር አማካኝነት ዩኒቨርሲቲዎችን መልሶ  ለማዋቀር በስሩ የሚተዳደር የዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ ፕሮግራም ጀምሯል። የመጀመሪያ ስራውም 13 ዩኒቨርሲቲዎችን ግንባታና የዩኒቨርሲዎችን አስተዳደርን እንደገና ማዋቀር ነበር። ዩኒቨርሲቲዎቹን ከ1993-1995 ዓ.ም በሁለት ዓመት ብቻ ከሁለት ወደ ስድስት አሳድጓል። አስተሳሰቡ  ከላይ እንዳልኩት ያለ እድሜዋ ተድራ ከምትወልደው ህጻን ጋር አብራ ያለ አቅሟ የእናትነትን ሸክም ተሸክማ የምታድገውን ልጅ የጫጨ ዕድገት ይመስላል። ሂደቱን የሚመራው ደግሞ ለራሱ አቅም የሌለው፣ በተፈራ ዋልዋ የሚመራው የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ነበር።
ከዚህ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲውን እንደሌሎች ተቋማት በስሩ አድርጎ በዕለት ተዕለት ስራው ሳይቀር ጣልቃ እየገባ ማዘዝ ጀመረ። ከዚያም አልፎ ወደፊት ዩኒቨርሲቲውን ራሱን እንደ እፉኝት የሚበሉትን ሰዎች ዩኒቨርሲቲው አሰልጥኖ እንዲያስመርቅ ማዘዝ ጀመረ። የመጀመሪያዎቹ በክረምት ለሁለተኛ ዲግሪ ያለ ምንም ፈተና ተቀብሎ አስተምሮ እንዲያስመርቅ መደረጉ ነበር። ኋላ ከእነርሱ መካከል የክልሎች የትምህርት ቢሮዎችን ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲውን  ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንዲመሩ ተሹመዋል።
("የድንቁርና ጌቶች ሞገሱን የገፈፉት ዩኒቨርሲቲ" ከሚለው አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)


Read 1659 times
Administrator

Latest from Administrator