Saturday, 19 December 2020 13:39

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(2 votes)

"እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ እየተገፉና እየተገለሉ የኖሩ ህዝቦች ነበሩ፡፡ በሮማውያን፤ በስፓንያርድስ፣ በቱርኮችና በሌሎች ባለ ጊዜ ወራሪዎች ሰበብ፣ መፈናቀልና መጋዝን ጨምሮ፣ ብዙ በደል ደርሶባቸዋል፡፡ የናዚው ሆለከስት ደግሞ የቅርብ ጊዜ ጥቁር ታሪክ ነው፡፡"
             
      አንድ ቀልድ ላስታውሳችሁና ባለፈው ሳምንት ስለጀመርነው የአይሁድ እምነት (Judaism) ታሪክ ጥቂት ነጥቦችን እያነሳን ንጫወታለን።…
የፀሎተ ሃሙስ ምሽት ነው። በመጨረሻው እራት ላይ መምህሩና ደቀ መዛሙርቱ የሆድ፣ የሆዳቸውን ይጨዋወታሉ። ያኔ የሰርጉ ቀን እንግዳ ሆኖ “ምንቸቶቹ ሁሉ ውሃ ይሞሉ” በማለት ውሃውን  በተአምራቱ ወደ ወይን ጠጅ የቀየረው መምህር፤ተከታዮቹን ዛሬ የስንብት እየጋበዛቸው ነው። በጨዋታቸው መሃል ይሁዳ ብድግ ብሎ በከረጢት የያዘውን ሰላሳ ዲናር እያሳያቸው፤ (የዳቪንቺን Last  supper  ልብ ይሏል)…
“ወይን ይጨመር እንዴ?... ገንዘብ አለንኮ” ይላል
“ባንዳፍ!” አሉ … ሁሉም። አጅሬም ከጁምዓው የሚለይበት ሰበብ በማግኘቱ… “ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ” ወደ ጥሪው ተፈተለከ። በዚህን ጊዜ መምህሩ ብድግ ብሎ…
“ከመሃላችሁ አንዱ አሳልፎ ለጠላቶቼ ይሰጠኛል” አላቸው።    
ጉዳዩ ሃሜት የመሰለው ወንጌላዊ ተነስቶ…
“ጌታ ሆይ፤ ጓደኛህን እንደ ራስህ ውደደው ብለህ አላስተማርክም?” በማለት ጠየቀው።
“እና?”  
“ሃሜት ጥሩ አይደለም”
መምህሩም፤ “የራስክን ጉድ አላወቅህምመ፣ ለሌላው ትሟገታለህ; አለው
“ምን አጠፋሁ?”
“ዶሮ ከመጮሁ በፊት ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ”
“ማን እኔ?”
“አዎ አንተ፤ ጊዜው ሲደርስ ይሆናል” አለ መምህር።
በዚህን ጊዜ ጴጥሮስ ምን እንዳለው ታውቃለህ?... አልተፃፈም። እኔ ግን መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ። በነገራችን ላይ የእራትና የክህደት ነገር ሲነሳ፣ የሰሜኑን ድንበር አስከባሪ ጦር ሲመሩ የነበሩትን ወገኖቻችንን፣ "እራት እጋብዛችኋለሁ" ብለው ጥይት የጋበዙትን ይሁዲዎች ምን ትላችዋለህ?...  ሰው የመሆን ነገር ሲፈተን እንደዛ ነው። ምን ትላቸዋለህ?
ወዳጄ፡- የአይሁድ እምነት ምንም እንኳ ከባህላዊው የኦርቶዶክስ ክርስትና ጋር እንደ ሲዖል (Sheol)  እና ነፍስ (Nefesh) የመሳሰሉትን ቃላት ጨምሮ ብዙ የሚመሳሰሉበት ውሁድ ባህሪያትና ለዛ አሉት። የእምነቱ መሰረት የቆመበት ስር ግን ከሂንዱ በተለይ ደግሞ ከእስልምና ሃይማኖት ጋር ተመሳሳይ ወይም /Monotheist/ ለመሆኑ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
አይሁዳውያን ጆሹዋ፣ ሙስሊሞች ኢሳ፣ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሚሏቸውን ጨምሮ በሰው ልጅነት የሚታወቁትን ነቢያት እንደ ጉዳይ አስፈጻሚ ወይም መልእክተኛ እንጂ እንደ አካለ አምላክ አያይዋቸውም። የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አንድነትና ልዩነት ወይም የትርኒቲን ስነ መለኮታዊ ባህሪ አይቀበሉም። ፈጣሪ አምላክ አይወልድም፣ አይዋለድም ባይ ናቸው። እንደ ምሳሌም የአይሁዳዊ ስርዓተ ዕምነት (Synagogue) አስኳል በመሆን የሚታወቀው ፀሎተ ሸማ (Shema…confession of one  God) እንዲህ በማለት ይጀምራል።
“O… Israel, The Lord (YHWH), Our God ,Is one”
ወዳጄ፡- አይሁዳውያን በሂብሩ፣ አርማይክና ዬዲሽ ቋንቋዎች የተፃፉ ብዙ ድርሳናት ባለቤት ናቸው። በዋነኝነት የሚጎላውና የሚጠቀሰው ግን “Ta Na Kh” የተባለው ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ። “ታናክ” ሶስቱ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ከሚጠሩባቸው ስሞች የመጀመሪያ ፊደሎችን በመውሰድ የተመሰረተ ቃለ ድርሳን ነው።
ታ (Ta)፡- አምስቱ መጽሃፈ ሙሴን፣ ስነ-ፍጥረትን፣ ትውፊቶችን፣ ታልሙድን (Mishnah + Gemora) እና ሌሎች ህግጋትን ሲያጠቃልል።
ና(Na)፡- ታላላቅ ከሚባሉት ነቢያቶቻቸው፡- ጆሽዋ፣ ኢሳያስ፣ ኤርሚያስና ህዝቅኤል ጀምሮ በሆሳ (Hosae) እና ማላኪ (Malachi) መሃል ያሉትን አስራ ሁለት ተከታታይ ነቢያት ስራዎችን ሲያካትት… ክ (Kh) ደግሞ ምሳሌዎችን፣ አባባሎችን፣ የሩት፣ የአስቴር፣ የዳንኤልን፣ የዕዝራ፣ የነኸሚያና መሰል ፀሃፍትን ጥበባዊ ስራዎች ይዟል።
ወዳጄ፡- በዚህ ዘመን ጁዳኢዝም ልማድ የቆለፈበትን አግላይና ባዕድ ሳጥን ሰብሮ አለም ዐቀፋዊ  አንድነት ለመገንባት ቀደም ሲል ከተከናወኑ የተሃድሶ  ንቅናቄዎች የቀጠለ አዲስ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ በዚህ ሰሞን ከምናያቸው ዲፕ ሎማሲያዊ ውጣ ውረዶች መረዳት አያዳግትም።
የጁዳኢዝም ሶስት የንቅናቄ አንጃዎች የመጀመሪያ በመሆን ኦርቶዶክስ ጁዳኢዝም ይጠቀሳል። የዚህ ንቅናቄ መሰረት የተገነባው በ”ታናክ” አስተምሮት ላይ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የወግ አጥባቂነት መንፈሱ እየደበዘዘና እየቀነሰ መምጣቱን ታሪክ አጥኚዎች ይናገራሉ። በቀጣይነት የምናገኘው ደግሞ በአስራ ስምንተኛው ክ/ዘመን  በተለይ በምስራቅ  አውሮፓ ሲካሄድ የነበረውን የሃሲዲም (Hasidim) ተሃድሷዊ ንቅናቄ ነው። ሐሲዲዝም ከጥበብ ፍቅር በሚገኝ ረቂቅ የደስታ ሃይል(The Mystic power of happiness) የሚያምን፣ እንደ ካባላ (Kabbala) ባሉ መፃህፍት ላይ በሰፈሩ ፍሬዞች የሚመሰጥ፣ በእስራኤል ቤን ኤሊዘር የተመራ ንቅናቄ ነው።
ሶስተኛው የተሃድሶ መንገድ ሪፎርም ጁዳኢዝም ነው። ሪፎርም ጁዳኢዝም ከሌሎቹ ንቅናቄዎች የሚለየው ሊበራልና ዘመናዊ በመሆኑ ነው። በሞሰስ ሜንደልሰን ሃሳቦች ላይ የሚያጠነጥነው ይህ ንቅናቄ፤ እስራኤላውያን ከምዕራባውያኑም ሆነ ከሌሎች ህዝቦች ወግና ልማድ ጋር እንዲዋሃዱና ተቻችለው እንዲኖሩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ሪፎርም ጁዳ ኢዝም፤ “እስራኤል ወዳጅ የላትም” የሚለው የቀደሙት ብሶቶች የወለዱት አስተሳሰብ፣ ጊዜ ያለፈበትና ከዓለማቀፋዊ አብሮነት ጋር እንደማይራመድ ለማሳመን ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። የጋራ ዕድገትን ማዕከል ላደረገ ፅዮናዊነትም ጥርጊያ መንገድ ሆኗል።
ወዳጄ፡- እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ እየተገፉና እየተገለሉ የኖሩ ህዝቦች ነበሩ። በሮማውያን፤በስፓንያርድስ፣ በቱርኮችና በሌሎች ባለ ጊዜ ወራሪዎች ሰበብ፣ መፈናቀልና መጋዝን ጨምሮ፣ ብዙ  በደል ደርሶባቸዋል። የናዚው ሆለከስት ደግሞ የቅርብ ጊዜ ጥቁር ታሪክ ነው፡፡
ወዳጄ፤ ያቺ እስራኤል ግን ዛሬ የለችም። የአዲስቱ እስራኤል መሪዎች፣ የአክራሪዎችን ጫና ተቋቁመው፣ አገሪቱን ወደ ዘመናዊ የአስተሳሰብ ስልትና ወደ ስልጣኔ ጎዳና መርተዋል፡፡ ታላቁ ዴቪድ ሞንጎሪዮን፤ ከአይሁድ እምነት ያፈነገጠና ምናልባትም ለቡዲሂዝም ሲያዳላ እንደነበረ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ወ/ሮ ጐልዳሚየር በፃፉት የህይወት ታሪክ መፅሃፋቸው ላይ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ወዳጄ፡- የዓለምን ኋላ ቀር ገፅታ ለውጠዋል የሚባሉት እንደ  ሲግሙንት ፍሮይድ፤ ካርል ማርክስና ዳርዊን የመሳሰሉት ታላላቅ ሊቃውንት፣ ሌሎች ይሏቸዋል  እንጂ አንዳቸውም አንድም ጊዜ #እኔ አይሁድ ነኝ; ሲሉ ተሰምተው አያውቁም፡፡ ታላቁ አንስታይንን #ጀርመኖችና አሜሪካኖች “አንስታይን የኛ ነው፣ የኛ ነው” ይባባላሉ፤ አንተ ምን ትላለህ?;  ሲሉ ጠየቁት፡፡
“አንስታይን ባልሆን ኖሮ፣ ሁለቱም አናውቀውም ይሉ ነበር”  በማለት መለሰ… አጅሬው፡፡
እየሱስና ስፒኖዛም አንደዛ ናቸው፡፡
*   *   *
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፡- መምህሩ ጴጥሮስን፤
“ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ“ ሲለው
“አንተ ደግሞ ሞቅ ሲልህ የልብህን ትናገራለህ” በማለት ነበር የመለሰለት፡፡
ወዳጄ፤ ለማንኛውም red red wine የሚለውን የዩቢ  ፎርቲን ዘፈን መርጬልሀለሁ።
ሻሎም!!

Read 965 times