Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 August 2012 10:17

“የስልጣን ሽግግር”፣ ከባድ ስራ ነው - “ጣጣ” አያጣውም

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ስልጡን ፖለቲካ ባልሰፈነባቸው እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ኋላቀር አገራት ውስጥ፤ “የስልጣን ሽግግር” ራሱን የቻለ ከባድ ስራ ነው። በስልጣኔ ደህና በተራመዱት የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትማ፤ በየአራት አመቱ መሪዎች ይለዋወጣሉ፤ ፓርቲዎች ይፈራረቃሉ። “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” የተለመደ የዘወትር ስራ ነው (ከፖለቲካ ነፃነትና ከምርጫ ጋር እግረመንገድ የሚከናወን ቀላል ስራ)። ለኢትዮጵያ ግን ከባድ ስራ ከመሆኑም በተጨማሪ ብርቅና እንግዳ ነገር ነው - ቢያንስ ቢያንስ ባለፉት 200 አመታት ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አንዴም ተሳክቶ አያውቅም። ይሄም ብቻ አይደለም።

“የስልጣን ሽግግር” ጣጠኛ ነው - ሌሎች ችግሮችን ጎትቶ ያመጣል ወይም ያባብሳቸዋል። ለምሳሌ የሙስና ወረርሽን መፈጠሩ አይቀሬ ነው። አለመረጋጋትም ይኖራል። በኢህአዴግ ቋንቋ፤ “መንገራገጭ” የግድ ነው። የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የጤና እክል ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል። መጥፎነቱ ደግሞ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፤ መንግስት ብዙ ነገር ውስጥ እጆቹን ስላስገባ የሙስና መንገዶችና እድሎች እንደጉድ ተበራክተዋል። መንግስት “ሲንገራገጭ”፤ ሁሉም ነገር “ይንገጫገጫል” ቢባል ማጋነን አይሆንም።

እንዲህ አይነት ስጋቶችን ሲሰሙ፣ አንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች በቁጣ እንደሚገነፍሉ  አያጠራጥርም። ግን፤ “የስልጣን ሽግግር” በኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑን፤ ራሱ ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ሲናገረው የነበረ ጉዳይ ነው። በ”ስልጣን ሽግግር” ዙሪያ (ወይም በኢህአዴግ ቋንቋ በ”መተካካት” ዙሪያ) ለበርካታ አመታት ውይይትና ጥናት እንዳካሄደ ኢህአዴግ ራሱ ገልጿል - የኢህአዴግ መፅሄት አዲስ ራዕይ የህዳር 2003 እትም መመልከት ትችላላችሁ። ስለዚህ ቁጣውንና ቱግ ማለቱን ትተው ስለችግሮቹና ስለመፍትሄዎቹ ብንነጋገር ይሻላል።

ኢህአዴግ በመፅሄቱ እንደሚለው፤ በአምስት አመታት ውስጥ እሰራቸዋለሁ ካላቸው ሁለት ነገሮች መካከል አንዱ፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በእጥፍ ማሳደግ ነው። ይሄ ከባድ ነው። በመፅሄቱ የተጠቀሰ ሁለተኛው ከባድ ስራ፤ በ”ስልጣን ሽግግር” ላይ ያተኮረ ነው። በአምስት አመታት ውስጥ፣ ነባር መሪዎቹን በሙሉ በአዳዲስ እተካለሁ ብሏል። በእርግጥ፤ እንዲህ አይነቱ “የስልጣን ሽግግር”፤ በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ እንደሚታየው አይነት አይደለም። በስልጡን ፖለቲካ ውስጥ ፓርቲዎች እየተፎካከሩ ስልጣን ላይ ይፈራረቃሉ። በአገራችን ግን የኢህአዴግ መሪዎች ናቸው የሚለዋወጡት። ባለስልጣናት ቢቀያየሩም፤ ፓርቲው እዚያው ስልጣን ላይ ይቆያል ማለት ነው። እንዲያም ሆኖ፤ ቀላል ስራ አይደለም።

በኛ አገር “የስልጣን ሽግግር” ከባድ ስራ ከመሆኑም በተጨማሪ ጣጠኛ ነው - ሌሎች ችግሮችን ይጎትታል ወይም ያባብሳል። ታስታውሱ እንደሆነ፤ በ93 ዓ.ም የኢህአዴግ ትኩረት በመሪዎቹ የስልጣን ሹክቻ ላይ ነበር። በ97 ዓ.ም ደግሞ ከምርጫ ቀውስ ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ ትኩረት በፓርቲዎች የስልጣን ሹክቻ ላይ ነበር ያነጣጠረው። ከእነዚህ “የስልጣን ሽግግር” ችግሮች ጋር ነው፤ የሙስናና የግጭቶች ወረርሺኝ ሲባባስ ያየነው - ተጨማሪ ጣጣ። አሁንስ? አሁንም የኢህአዴግ ትኩረት “የስልጣን ሽግግር” (የመሪዎች መተካካት) ላይ ሲያነጣጥርና ሲጠመድ፤ በየአቅጣጫው ሌሎች ችግሮች መባባሳቸውና መፈልፈላቸው ይቀራል?

እውነትም፤ “የስልጣን ሽግግር” ለኢህአዴግ ፈታኝና ከባድ ስራ ነው።  “ይሄ የጠላት ወሬ ነው” ብለው ለማጣጣልና ለማንቋሸሽ የሚሽቀዳደሙ አንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች መኖራቸው አይቀርም፤ ጨርሶ ለማሰብም ሆነ ሃሳብ ለመስማት አይፈልጉም። ነገር ግን፤ እነሱ ማሰብ ስላልፈለጉ ብቻ፤ ፈተናውና ከባዱ ስራ ብን ብሎ አይጠፋም። ምናልባት የራሱ የኢህአዴግ መፅሄት “አዲስ ራዕይ” ውስጥ የተፃፈውን ብጠቅስላቸው ይሻል ይሆን? በህዳር 2003 ዓ.ም የታተመውን መፅሄት ተመልከቱ፡፡

ኢህአዴግ ነባር መሪዎቹን በአዳዲስ ለመተካት እቅድ እንዳወጣና የስልጣን ሽግግሩ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ የሚገልፀው ይሄው መፅሄት፤ በአምስት አመታት ውስጥ ሁሉም ነባር መሪዎች ከስልጣን እንዲገለሉ ተወስኗል ይላል (ገፅ 18)። ውሳኔው ለምን እንዳስፈለገ መፅሄቱ ሲያስረዳ፤ መንገራገጭ ያልበዛበት የስልጣን ሽግግር በፍጥነት የሚፈፀምበትን ሁኔታ ለመፍጠር የታሰበ ነው ብሏል (ገፅ 20)። እንግዲህ አስቡት። በኢትዮጵያ የሁለት መቶ አመታት ታሪክ ውስጥ የተከናወኑ የስልጣን ሽግግሮች በሙሉ በቀውስ የታጀቡ ናቸው (“መንገራገጭ” የበዛባቸው ናቸው - በኢህአዴግ ቋንቋ)።

የቅርብ ጊዜ ታሪክም መጥቀስ ይቻላል። በ93 ዓ.ም በርካታ ነባር የኢህአዴግ መሪዎች ወርደው በሌሎች የተተኩት፤ በከፍተኛ ቀውስና ፀብ መሃል ነው። የስልጣን ሽግግርን ሰላማዊ ለማድረግ የሚያስችል የፓርቲዎች ፉክክርና ምርጫም በሰላም ሊጠናቀቅ አልቻለም - የ97ቱ ምርጫ በቀውስ የታመሰ ነበር። እነዚህን ክስተቶች በመጥቀስ የጉዳዩን ከባድነት ለማሳየት የሞከረው የኢህአዴግ መፅሄት፤ መንገራገጭ ያልበዛበት የስልጣን ሽግግር እንዲኖር አዲስ ስርአት መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል በማለት ያስረዳል (ገፅ 21)። አዲስ የመተካካት ስርዓት መፍጠር ለኢህአዴግ ከባድ ስራ እንደሆነ ይበልጥ ለማሳየትም መፅሄቱ ተጨማሪ ማብራሪያ አቅርቧል።

በኢህአዴግ አመራር ውስጥ (36 መሪዎችን በያዘው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ) የስልጣን ሽግግር ጉዳይ ለበርካታ አመታት ሲነሳ መቆየቱን መፅሄቱ ጠቅሶ፤ በአጀንዳ ተይዞ ተደጋጋሚ ውይይት እንደተካሄደበት ይገልፃል። መፅሄቱ እንደሚለው፤ የስልጣን ሽግግር ጉዳይ ሰፊ ጥናት ያስፈልገዋል ተብሎ ከመሪዎቹ መካከል የጥናት ቡድን ተሰይሟል። ቡድኑ ባቀረበው ጥናት ላይ ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ በተደጋጋሚ ውይይት አካሂዶበታል፤ በየጊዜው በሚሰነዘሩ ሃሳቦች እየተከለሰና ለውጥ እየተደረገበት በተደጋጋሚ ተመርምሯል፤  በመጨረሻም አዲስ የስልጣን ሽግግር (የመተካካት) መርህ ተሰናድቶ ውሳኔ ተላለፈ ይላል - መፅሄቱ (ገፅ 23)። ይህ የሆነው በ1999 ዓ.ም ነው።

ነገር ግን፤ ነባር የፖርቲ መሪዎች በሙሉ በአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ ከስልጣን ወርደው በአዳዲስ መተካት አለባቸው ተብሎ ቢወሰንም፤ እልባት ላይ ለመድረስ ተጨማሪ ሁለት አመታትን ፈጅቷል። ማን ቀድሞ ይውረድ? ማን እስከ መቼ ይቆይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ በርካታ ስብሰባዎች እንዳስፈለጉ የኢህአዴግ መፅሄት ይገልፃል - (ገፅ 23)።

ኢትዮጵያ፤ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ መንገራገጭ ያልበዛበት የስልጣን ሽግግር የምታካሂድበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰች መፅሄቱ ሲናገር፤ በርካታ አስርት አመታትን የሚፈጅ ከባድ ስራ እንደሆነ ይጠቅሳል። በስልጣን ላይ ሃያ አመታትን የቆየው ኢህአዴግ፤ አገሪቱን እዚህ ደረጃ ላይ ሳያደርሳት መቆየቱና ወደፊትም በኋላ ቀር ፖለቲካ ውስጥ ለበርካታ አስር አመታት እንደምትቆይ መናገሩ ያሳዝናል። “አንድም፤ ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ስልጡን የፖለቲካ ስርአት ለመፍጠር ኢህአዴግ አይፈልግም። አልያም የመፍጠር አቅሙ ደካማ ነው” ያስብላል።

የሆነ ሆኖ፤ ለመጪዎቹ በርካታ አመታት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰት የስልጣን ሽግግር በኢህአዴግ ውስጥ ብቻ የታጠረ እንደሚሆን መፅሄቱ ያትታል። ግን፤ በኢህአዴግ ውስጥ የሚካሄደው የስልጣን ሽግግርም ከባድ ስራ እንደሆነ መፅሄቱ ማብራራቱን አላቋረጠም - መንገራገጭ ያልበዛበት የስልጣን ሽግግር ለአገራችን አዲስ ነው በማለት። አዲስ በመሆኑም ምክንያት፤ ነባር መሪዎች ከስልጣን እንዲወርዱ ሲወሰን፤ ፓርቲው በመሪዎች ሹክቻ ተከፋፍሎ የመንገራገጭ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚሉ ስጋቶች እንዲሁም ምኞቶች እንደተፈጠሩ መፅሄቱ ይገልፃል (ገፅ 24)። ይህም ስራውን እንደሚያወሳስበው መፅሄቱ ጠቁሞ፤ ነባር መሪዎች ስልጣን እንዲለቅቁ ካልተደረገ፤ መንገራገጭ ያልበዛበት የስልጣን ሽግግር ሊኖር አይችልም በማለት የውሳኔውን አስፈላጊነትና የስራውን ከባድነት ያስረዳል።

እናም በመጀመሪያው ዙር፤ ከ18ቱ የህወሃትና የብአዴን ነባር መሪዎች መካከል ግማሾቹ (ዘጠኙ) በ2003 ዓ.ም ስልጣን ለቀቁ። ቀሪዎቹና ሌሎቹ ነባር መሪዎች ደግሞ እስከ 2007 ዓ.ም ከስልጣን እንደሚወርዱ መፅሄቱ ይገልፃል (ገፅ 31)። የመጀመሪያው ዙር ያለአንዳች ችግር መጠናቀቁ ለኢህአዴግ ታላቅ ድል ነው የሚለው ይሄው መፅሄት፤ ለአገሪቱም አዲስና ታላቅ ባህል የሚፈጥር ነው ሲል ታሪካዊ ድል መሆኑን ያበስራል (ገፅ 33)።

ይሄን ሁሉ የዘረዘርኩት፤ ከፓርቲ ወደ ፓርቲ ይቅርና፤ በፓርቲው ውስጥ የሚከናወን የስልጣን ሽግግርም ከባድ፣ ውስብስብና አደገኛ መሆኑን ኢህአዴግ እንደሚያምን ለማሳየት ነው። እንዲያው የሰውን ሃሳብ መስማት የማይፈልጉና የሚቆጡ የፓርቲው ሰዎች፤ ከራሱ ከኢህአዴግ መፅሄት ስጠቅስላቸው ይሰሙ እንደሆነ ብዬ እንጂ፤ ጉዳዩ ያን ያህልም ለግንዛቤ የሚያስቸግር አይደለም። በቃ...  ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትና ስልጣን ላይ የሚፈራረቁበት ታሪክ ይቅርና፤ በፓርቲ ውስጥ አልያም በቤተሰብ ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተከናወነበት ታሪክ በኢትዮጵያ ታይቶ አይታወቅም - ባለፉት ሁለት መቶ አመታት። ለነገሩ፤ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የጤና ችግር ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሁኔታ ማየት በቂ ነው - ብዙዎች ከሚጋሩት ሃዘኔታ ጋር፤  በአንድ በኩል የወሬ መአት፤ በሌላ በኩል የዝምታ መአት... በዝቷል።

በአንድ በኩል፤ ጠ/ሚ መለስ ስልጣን ከለቀቁ አገሪቱ ምን ይውጣታል ብለው የሚሰጉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የአገሪቱ ኋላቀር ባህል ሳይለወጥ የመንግስት መሪዎች ወይም ገዢ ፓርቲዎች ስለተቀየሩ ብቻ አንዳች ተአምር ይፈጠራል ብለው የሚጠብቁ አሉ። በአንድ በኩል ስልጣንና ጥቅም እናጣለን ብለው የሚብሰለሰሉ የስልጣን ጥመኞችና ጥገኞች ይኖራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣንና ጥቅም ለመቀራመት የሚያቆበቁቡ ስልጣን ናፋቂዎችና ተስፈኞች  ይኖራሉ።

በአንድ በኩል፤ በብሄረሰብ እና በሃይማኖት የመቧደን ጭፍንነት እንዳይባባስና እንዳይፈነዳ የሚሰጉ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በጭፍን የመቧደንና ግጭት የመፍጠር አባዜ የሚያቅበዘብዛቸው አሉ - በ1993 ዓ.ም የኢህአዴግ መሪዎች ተከፋፍለው ፀብ ውስጥ የገቡ ጊዜ በየአቅጣጫው የተፈጠሩትን ግጭቶች ማስታወስ ይቻላል። በአንድ በኩል አለመረጋጋት እንዳይከሰት፣ ስራ እንዳይስተጓጎል፣ ኑሮ እንዳይመሳቀል የሚጨነቁ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ለመቦጨቅ የሚቁነጠነጡ የሙስና ረሃብተኞች አሉ። በ97ቱ የምርጫ ቀውስ ማግስት የተከሰተው የመሬት ወረራና የሙስና ወረርሺኝን መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የስልጣን ሽግግር በፈተና የተሞላ ነው። ኢህአዴግ ይህንን ፈተና ማለፍ ይችላል? ከፓርቲ ወደ ፓርቲ የሚደረግ የስልጣን ሽግግር ነው ከባዱ ፈተና። መፍትሄውስ? ፈተናውን ማለፍ የሚቻለው ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ነው። ኢህአዴግ እዚህ ላይ ፈተናውን አላለፈም። ፓርቲዎች የተሟሟቀ ፉክክር ያካሄዱበት የ97 ምርጫ ሰላማዊ አልሆነም። በ2002 የተካሄደው ሰላማዊ ምርጫ ደግሞ በፓርቲዎች ፉክክር የተሟሟቀ አልሆነም (99.6 በመቶ ኢህአዴግ አሸንፏል፤ እንዲህ አይነት ምርጫ የትም አገር የለም - የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ካልሰፈነ በቀር)። እናም፤ ኢህአዴግ እስካሁን ይህንን ከባድ ፈተና አላለፈም።

ነገር ግን፤ ኢህአዴግ ቢያንስ ቢያንስ በፓርቲ ውስጥ የሚካሄደውን የስልጣን ሽግግር፤ በራሱ ቋንቋ ብዙ “ሳይንገራገጭ” በማከናወን ትንሹን ፈተና ማለፍ ይኖርበታል። በ2002 ዓ.ም. ጀምሮታል - ነባር መሪዎችን በከፊል ከስልጣን በማውረድ። ያኔ መጀመሩ ምን ያህል እንደጠቀመው ገና አሁን በደንብ የሚገነዘበው ይመስለኛል። ሌላው ቢቀር፤ የአቅጣጫ ጭላንጭል ለማየት የሚያስችል ነውና። እንዲያም ሆኖ አሁን እንደምናየው በመጠኑ መንገራገጩ አልቀረም። ይህም ብቻ አይደለም።

ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት የኢህአዴግ መሪዎች ዋና ትኩረት በዚሁ የስልጣን ሽግግር ዙሪያ ላይ የሚያነጣጥር ከሆነ፤ በሌሎች አቅጣጫዎች ሌሎች ችግሮች የሚፈጠሩበት ወይም የሚባባሱበት እድል ይፈጠራል። በምርጫ 97 ቀውስ እንዲሁም በ93ቱ የመሪዎች ሽኩቻ ወቅት ከተፈጠሩትና ከተባባሱት ችግሮች ጋር የሚመሳሰል ጣጣ ማለቴ ነው፤ ለምሳሌ የሙስና ወረርሽኝ። ለዚያውምኮ ያኔ ብዙ የሙስና እድሎች አልነበሩም። ዛሬ ግን የሙስና እድሎች በብዙ እጥፍ ጨምረዋል፤ ሰፍተዋል።

መንግስት የቱን ያህል በቢዝነስ ስራ ውስጥ እንደገባ ተመልከቱ - በየአመቱ ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅስ ሆኗል። የስኳር ኮርፖሬሽንን፣ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን፣ የባህር ትራንስፖርት እስከ መሃል ከተማ፣ በየክልሉ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች...  ብዙ ቢሊዮን ብሮች ወዲህ ወዲያ የሚሉበት የቢሮክራሲ መረብ ውስጥ ሊፈጠር የሚችለው የሃብት ብክነትና የሙስና አይነት ለቁጥር ያስቸግራል። ይህም ብቻ አይደለም።

መንግስት የግል ቢዝነሶች ላይ የቱን ያህል አላስፈላጊ ጣልቃ ገብ ቁጥጥሮችን እንዳበራከተ አስተውሉ። በተለይ ባለፉት አምስት አመታት አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥሮች እንደአሸን ፈልተዋል። ከንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ጀምሮ፣  የዋጋ ቁጥጥር፣ የጡረታ ታክስ፣ የጋዜጣ የማስታወቂያ ቁጥጥር፣ የታክሲ ቀጣና ቁጥጥር፣ የባንክ ቦንድ ግዢ ቁጥጥር... በየአቅጣጫው የመንግስት ገናናነት እየገዘፈ ሲሄድ፤ የባለስልጣናትና የቢሮክራቶች የሙስና እድሎችም በዚያው መጠን ይሰፋሉ፤ ይስፋፋሉ። የተመቸ ጊዜ ያገኙ ሲመስላቸው ደግሞ የሙስና እድሎች የሙስና ወረርሺኝ ይሆናሉ።

ግን መፍትሄ አላቸው። አላስፈላጊዎቹን ቁጥጥሮች አንድ በአንድ ለመሰረዝ ከባድ አይደለም። መንግስት ቢዝነስ ውስጥ የመግባት ዘመቻውን እንዲገታ ማድረግም ቀላል ነው። ቀስ በቀስም፤ በመንግስት የተቋቋሙትን ቢዝነሶች በፕራይቬታይዜሽን ወደ ግል ማዛወር ይቻላል። የመንግስት ገናናነት ሲቀንስ፤ ቢዝነስ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪነቱ ሲከስም፤ ከዜጎች እየወሰደ የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ገደብ ሲበጅለት ...፤ ለዘለቄታውም ጥሩ ይሆናል - የሙስና እድሎች ከመጥበባቸውም በላይ፤ የመንግስትን ስልጣን መያዝ ያን ያህልም አጓጊና አስጎምጂ መሆኑ ይቀንሳል። እናም ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አመቺ ይሆናል።

 

 

Read 5000 times Last modified on Saturday, 11 August 2012 10:31