Saturday, 26 December 2020 10:14

አገሬ ለእኔ… ሁሉ ነገሬ!

Written by  ትዕግስቱ በለጠ
Rate this item
(2 votes)

ግርም ድንቅ ይለኛል… አገሬ ለእኔ ሁሉ ነገሬ! የአገሬ ነገር…የእኔ ነገር ነው። የራሴ… የግሌ… የብቻዬ!! ወድጄ አይደለም። ሁሌም የሚሰማኝ እንደዛ
ነው። እኔ ማለት ያለ አገሬ ምንም ነኝ። ከተፈጠርኩ አንስቶ… ከልጅነት እስከ ዕውቀት እንደ ወላጅ ጠንቅቄ አውቃታለሁ… አገሬን። ወደ ምድር
ከመጣው ወዲህ… ከአገሬ ውጭ ሌላ ምድር አላውቅም። የባዕድ መሬት አልረገጥኩም፡፡ በሰው ሰማይ ላይ አልበረርኩም። ዕድሜ ዘመኔን… አገሬ ላይ
ነኝ። ባዝን ብደሰት፣ ባለማ ባጠፋ፣ ብማር ብራቀቅ፣ ባገባ ብወልድ፣ ብለግስ ብሰስት፣ ባገኝ ባጣ፣ ባስብ ባሰላስል፣ ባፈቅር ብጠላ… እዚሁ ነው። ሌላ
አገር የለኝም። ብደግፍ ብቃወም፣ ብጠግብ ብራብ፣ ብኖር ብሞት…  እዚሁ አገሬ ላይ ነው፡፡ ሌላ አገር የለኝም። አንድ እናት ብቻ እንዳለኝ ሁሉ…
አንድ አገር ብቻ ነው ያለኝ፡፡ ለእናቴ የምሳሳላትን ያህል፤ ለአገሬም እሳሳላታለሁ፡፡ አገሬን እወዳታለሁ! ስል… አባባል አይደለም። ከምር በቃ
እወዳታለሁ፡፡  ኢትዮጵያ ለእኔ ክብሬም… ሞገሴም…  ሁሉ ነገሬ ናት፡፡ ሰላሜም ፍቅሬም…ሃብቴም… ርስቴም ወጌም ማዕረጌም…ናት!! ስለዚህ ሁሌ
እሰጋለሁ፤ ሁሉ ሃሳብ ይገባኛል፡፡ ሁሌ እሳቀቃለሁ። ከተፈጠርኩ አንስቶ የማውቃት ይቺን ውብ ድንግል አገር፣ አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ ባጣትስ?
እያልኩ እሰጋለሁ… አስባለሁ… እጨነቃለሁ፡፡ ደሞ ቅዠት አይደለም፡፡ እውነቴን ነው። አገራቸውን ያጡ ብዙ ዜጎች አውቃለሁ፡፡ ዕትብታቸው  
የተቀበረበትን መሬት ጥለው ከአገር አገር የሚንከራተቱ ብዙ ምስኪኖች አይቼአለሁ። ወደው ሳይሆን ተገደው፡፡ አንዳንዶች አገራቸውን ማን እንደነጠቃቸው
እንኳን አያውቁም፡፡  ሌላው፣ ቀርቶ መቼ አገራቸውን እንዳጡ እንኳ ቢጠየቁ መልስ የላቸውም። አገር እንደነበራቸው ግን በእርግጠኛነት ይናገራሉ።
አንዳንዶቹ አገራቸውን ዘረኝነት፣ ጠባብነት፣
ጥላቻ፣ድንቁርና፣ስግብግብነት የስልጣን ጥመኝነት፣ አመፅ፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ወዘተ…እንዳሳጣቸው  ጠንቅቀው ያውቃሉ። እኔም ብዙ መሰል  አሳዛኝ
ታሪኮችን አውቃለሁ፤ ሰምቻለሁ። እናም ሁሌ ለአገሬ እሰጋለሁ - እጨነቃለሁ። ከአፍንጫቸው አርቀው በማያስቡ ቅርብ አዳሪ ፖለቲከኞች…
አክቲቪስቶች… ፅንፈኞች… አብዮተኞች…ባለተራዎች ወዘተ ሀገሬን እንዳትጠፋብኝ፤ እንዳትፈርስብኝ እፈራለሁ፤ እሰጋለሁ …..እጨነቃለሁ፡፡
ፖለቲካ…ዲሞክራሲ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ… ምርጫ… … ብሄርተኝነት ፅንፈኝነት… መንግስት….ቤተ መንግስት ስልጣን… ዲሞክራሲ …. የመናገር ነፃነት ወዘተ
 የመሳሰሉትን አልወዳቸውም፡፡ በሰበብ አገሬን እንዳያፈርሱብኝ …እናቴን እንዳይነጥቁኝ እፈራለሁ፡፡ የሩዋንዳ ዕጣ እንዳይገጥማት… የእነ ሶሪያ… የእነ
የመን… የእነ ሶማሊያ ዕድል እንዳይደርሳት… ፈራርሳ አገር አልባ እንዳልሆን ….እጨነቃለሁ - እንቅልፍ አጣለሁ፡፡
 ሁሌም፣… ምንጊዜም አስባለሁ። አሰላስላለሁ፡፡ አንዲት እናቴን ርስቴን እንዳይነጥቁኝ… እሰጋለሁ… እጨነቃለሁ… አምላኬን እማለዳለሁ… እለምናለሁ።
ምክንያቱም እኔ ያለ አገሬ ምንም ነኝ። ምንም!!  
ፈጣሪ አገሬን ኢትዮጵያን ይጠብቅልኝ።

Read 7515 times