Saturday, 26 December 2020 17:28

ፓርቲውና፣ ዲስፒሊኑ”፣ ሀሳብና ምርጫው፡፡

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)


          ብልፅግና ፓርቲ በሰሞኑ ስብሰባው፣ ዋና ዋና የውሳኔ ሃሳቦችን አጽድቆ፣ አንድ ሁለት ብሎ በመግለጫ ነግሮናል። ሃሳቦቹን እንያቸው
1. አራቱ ሃሳቦች፣ “ዘንድሮ ይከናወናል” ተብሎ በሚጠበቀው የፖለቲካ ምርጫ ላይ ያተኮሩ ሃሳቦች ናቸው። ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የሚያሳስቡ። በእርግጥም፣ (ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አገራት፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ የሰላም ተስፋ ከመሆን ይልቅ፣ የአደጋ ስጋት ነው። ይህን መገንዘብ፣ ብልህነት ነው።)
2. ሁለት ነጥቦች፣ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ዘመቻ የሚመለከቱ ናቸው። ሌሎች ሁለት ሃሳቦች ደግሞ፤ በብሔረሰብ ፖለቲካ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው። “የማንነት ጥያቄ” በሚል ስያሜ የሚቀጣጠሉ ውዝግቦች፣ እንዲሁም የዘረኝነት ጥቃቶች ላይ ያተኩራሉ።
3. ቀሪዎቹ ሁለት ነጥቦች፣ በራሱ በፓርቲው መሪዎችና አባላት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። በአንድ በኩል፣ በፓርቲ መሪዎች አማካኝነት የሚለኮሱ የእርስ በርስ ውዝግቦችን ማርገብ አለብን ብሏል። ከዚህም ጋር፣ “በዲሲፒሊን” እና በፅናት መስራት ይገባናል የሚሉ ሁለት የውሳኔ ሃሳቦች በመግለጫው ተጠቅሰዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎች፣ ከሞላ ጎደል፣ በቀጥታ፣ ከሰላም ጋር የተሳሰሩ ወይም ከሰላም እጦት ጋር የተያያዙ መሆናቸው አይገርምም። በየእለቱ የምናየው ነገር ምን ሆነና! የአገራችንን ሁኔታ ተመልከቱ። ትናንት አመፅ ነው። ዛሬ ጦርነት ነው፣ … ነገ የታጣቂዎች የግድያ ዘመቻ፣ የንብረት ውድመት፣ ከኑሮ ተነቅሎ መሰደድ… በአጠቃላይ የሰላም ፋታ ርቋታል - አገሪቱ። ማብቂያ የሌለው፣ እረፍት የማይሰጥ የቀውስና የጥፋት አዙሪት ሆኖባታል - ፖለቲካው። ምንድነው ችግሩ? እናስበዋ! • ዲስፒሊን ከአፈና፣ ነፃነት ከመረን ይለያል። በአንድ በኩል፣ መረጃዎችን ለማጣራትና
ለማመሳከር፣ ሃሳቦችን ለማገናዘብና ለመፈተሽ፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማረም የሚጥር ሰው እንደ ጠላት ይፈረጃል። የተዛቡ ሃሳቦችንም ለመተቸትና ለማስተካከል መሞከርም፣ እንደ ክህደት ተቆጥሮ ይወገዛል። ቅንጣት ታህል ትችት እንዳይነገር እንዳይጻፍ እንመኛለን፤ በዚህም አፈናን እንጋብዛለን።
ግን ምን ዋጋ አለው? አፈና፣ ለጊዜው እንጂ አያዛልቅም። እናስ? “አፈና ይብቃ”፣ “ለውጥ ይምጣ” የሚል ጩኸት ይበረታል። በቃ፣ አፈናን ስንጋብዝ የነበርን ሰዎች፣ ዞር ብለን፣ “የሃሳብ ነፃነት፣… ነፃ ውይይት፣… ክርክር” የሚሉ መፈክሮችን እናራግባለን። ጥሩ ይመስላል። ምን ማለት እንደሆነ
በተግባር ሲታይ ነው ችግሩ። “የሀሳብ ነጻነት” ማለት፣ … “እንደልብ መዋሸት፣ በዘፈቀደ መወንጀል” እየመሰለን፣ ሰማይና ምድሩን እናናውጠዋለን። አገሪቱን እንንጣታለን። ሌላ የተሻለ ውጤት እንደማይኖረው አትጠራጠሩ። ውሸትና አሉባልታ፣ ጭፍን ፕሮፖጋንዳና ውዝግብ፣ ስድብና ብሽሽቅ፣ እንዲሁም የዘፈቀደ ውንጀላ፣ … ውሎ አድሮ፣ መጨረሻው ሊያምር አይችልም። ወደ ጥላቻና ዛቻ፣ ወደ ጥቃት ቅስቀሳና ዘመቻ እንደሚያመራ፣ ቅንጣት አትጠራጠሩ። “የሃሳብ ነፃነት” ተብሎ የተጀመረ ንትርክና ብሽሽቅ ሁሉ፣ ሁሌም በጥፋትና በትርምስ ይታጀባል። “የሃሳብ ነፃነት”፣ … ያለ ሃሳብ፣ ብዙ እድሜ የለውማ። ለምን? ለእውነትና ለእውቀት ክብር የሚሰጥ አእምሮ ነዋ የነጻነት ስረ-መሰረት። ይሄ፣ የነፃነት ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህን ማሟላት፣ የሁላችንም የስነምግባር ሃላፊነት እንደሆነ እንገንዘብ። አለበለዚያ ግን፣ እለት በእለት እንደምናየው፣ ከእውቀት ጋር የተጣላ ሃሳብና ከእውነት የሚሸሽ ንግግር፣ አገርን ያሳክራል። የቀውስና የጥፋት አዙሪት ይሆናል። ይህ ችግር፣ ሁ ሉንም ሰ ው፣ ሁ ሉንም ፓ ርቲና ፖለቲከኛ የሚመለከት ችግር ነው።
ለብልጽግና ፓርቲም፣ ትልቅ ፈተና መሆኑ አይገርምም። “ዲሲፕሊን” ያስፈልጋል ማለቱ አይደንቀም። በአንድ በኩል፣ የፓርቲ ዋና ዋና አላማዎችንና ሃሳቦችን፣ “በዲሲፕሊን” እና “በጽናት” መተግበር የማይፈልግ ካልሆነ፤ በየትኛውም አላማና ሃሳብ ተስማምቶ የፓርቲ አባልና አመራር ለመሆን ገባ?
በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ዲሲፕሊን” የሚሉት ነገር፣ ልክ ሲያጣ፣ መታፈንና መታጀል ይሆናል። የዲስፒሊን ልኩ ምንድን ነው? በዋና ዋና የፓርቲ አላማዎችና ሃሳቦች ላይ ተስማምቶ በአባልነት ወይም በአመራር ቦታ የገባ ሰው፣ የፓርቲው ዋና ዋና አላማዎችንና የውሳኔ ሃሳቦችን፣ በየዘርፉና በየመስኩ የመተግበር ሃላፊነት አለበት። ይሄው ነው፤ ተገቢ የፓርቲ “ዲስፕሊን”። ዲሲፕሊን፣ ልክ ሲያጣ ግን፣ በሁሉም ነገር ላይ፣ አንድ አይነት ቃል እያነበነቡ ማጨብጨብ እንደ ማለት እየሆነ፣ ፓርቲው ከላይ እስከታች ሁለመናው ይታፈናል። ይሄ፣ ትልቅ ችግር ነው። ይህንን “አፈና አስወግዳለሁ” ብሎ ሲሞከርስ?
“የሃሳብ ነፃነትንና ግልጽነትን ማስፋፋት” ማለት፣ እንደልብ በአደባባይ መሰዳደብ፣ መበሻሸቅና በዘፈቀደ መወነጃጀል ማለት እየመሰለን፣ እንደገና አገሪቱ ትቀወጣለች። ከዚህ አጣብቂኝ መውጣት ከባድ ነው። ሳያሰልሱ፣ ለረዥም ጊዜ፣ በብርቱ፣ በቅንነትና በፅናት መስራትን ይጠይቃል። ከባድ ቢሆንም
ግን፣ የግድ ነው። ሌላ አማራጭ የለም። አዎ፤ የሃሳብና የመነጋገር ነጻነት ያስፈልጋል። ነጻነትን በእውን ማስፋፋት የሚቻለው ግን፣ በትክክል ማሰብና እውነትን የመናገር “የስነ-ምግባር ሃላፊነትን” በመወጣት ብቻ ነው። ይ ህ የ ሁሉም ሰው፣ የ ሁሉም ፓ ርቲና ፖለቲከኛ የስነ-ምግባር ሃላፊነት እንደሆነ
ካልተገነዘብን፣ ከችግር አዙሪት አንወጣም። እና የስነምግባር ሃላፊነታችንን እንወጣለን? የያንዳንዳችን ምርጫ ነው። ለፓርቲውም ምርጫ ነው።
.የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና የማንነት ጥያቄ፣ ምን ለያቸው! የዘረኝነት አስተሳሰብንና ጥፋትን የሚያስፋፋ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ከዋና ዋናዎቹ አደገኛ የአገራችን ችግሮች መካከል አንዱና ቀዳሚው ሆኗል። በአገሪቱ ውስጥ ከዳር እስከዳር፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተደጋጋሙ የሚፈጠሩ ቀውሶችንና
ጥፋቶችን መመልከት ትችላላችሁ። የብልፅግና ፓርቲ፣ በብሔር ብሔረሰብ የሚያቧድን አደረጃጀት ላይ ከመቆየት ይልቅ፣ ወደ አገራዊ የፓርቲ አደረጃጀት
ለመጓዝ መምረጡና መጀመሩ ትልቅ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም። ዛሬም ድረስ፣ በብሔር ብሔረሰብ የተቧደኑ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ብዙ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም። ለዘረኝነት ቅኝት ሰፊ ቦታ የሚከፍቱ ተጓዳኝ አስተሳሰቦችን፣ በጥንቃቄ መጋፈጥና ማስተካከል ያስፈልጋል። ለዚህም፣ አንድ
በግልፅ መገንዘብ የሚገባን ነገር አለ። የሰው መሰረታዊ ማንነት፣ የግል ማንነት ነው። ወደዚህ ትክክለኛ አስተሳሰብ መጓዝ ያስፈልጋል።
በተቃራኒው፣ የግል ማንነትን በሚያደበዝዝ መንገድ፣ “የማንነት ጥያቄ” የሚል አስተሳሰብን ማስተጋባት፣ ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ለምን?”የማንነት ጥያቄ” የሚለው መፈክር፣ ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ምንም አይሻልም። እናም፣ ለዘረኝነት ተጨማሪ ሰበብ የሚሰጥና አመቺ መንገድ የሚያስፋፋ ስህተት ይሆናል። ከዚህ ውጪ፣ የአስተዳደርና፣ የወሰን ጥያቄዎች ወይም የአከላለል ጉዳዮች፣ ቀላል ችግሮች ናቸው። ለምን? በትክክኛ መንገድ፣
የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት የማስከበር ዋና አላማ ላይ ባተኮረ፣ ሕግና ስርኣትን ለማስከበር በሚጠቅም ትክክለኛ መንገድ፣ መልክ ማስያዝና መፍትሄ መስጠት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካንና መዘዞቹን መግታት፣ ከዚያም ማስወገድ የሚቻለው፣ “የማንነት ጥያቄ” በሚል ተመሳሳይ የፖለቲካ ቅኝት አይደለም። የግል ማንነትን ወደ ሚያከብር ወደ ስልጡን አስተሳሰብ መራመድ ይኖርብናል። ይሄም የእያንዳንዳችን ምርጫ፣ የፓርቲዎችም
ምርጫ ነው። የምርጫው ነገርስ ከላይ እንደጠቀስኩት፣ የፖለቲካ ምርጫ፣ ልክ እንደ ሃሳብ ነጻነት፣ የስነ-ምግባር ሃላፊነቶች ያስፈልጉታል። አለበለዚያ ግን፣ የሃሳብ ነጻነት፣ ያለ ስነ-ምግባር ከእውቀትና ከእውቀት ጋር ተጣላልቶ፤ እንደ ልብ የመዋሸትና በዘፈቀደ የመወነጃጀል ትርምስ ሆኖ ያርፈው የለ? የፖለቲካ ምርጫውስ? ምርጫውም ከተዛማጅ ቁምነገሮች ከተነጠለና በቁንጽል ከተራገበ፣ የቀውስና የብጥብጥ፣ የአፈናና የትርምስ ሰበብ ሆኖ ይቀራል። ከዚህ
መጠንቀቅ ያስፈልጋል። መጠንቀቅ እንዴት? ብለን በመጠየቅም፣ ዝርዝር የጥንቃቄና የመፍትሄ መንገዶችን ማበጀት፣ ተግተንም መስራት ይገባናል።

Read 11202 times