Saturday, 26 December 2020 19:15

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

  "ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ለሰባተኛ ጊዜ በአገራችን ተከብሯል። ሙስና ስር በሰደደበት፤ በዓይነትና በስፋት በተዛመተበት እንደኛ ባለ ሃገር፣ ዓለም አቀፉን የፀረ ሙስና ቀን ማክበር “ፌዝ” እንዳይሆን እሰጋለሁ።"
           
           ባለፈው ሰሞን የተከበረውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ሰበብ አድርጌ ካነበብኳቸው አንድ ሁለት ቀልዶች ጀባ ልበላችሁ። “ከፍሪጅ ውስጥ አንድ ቢራ አምጣልኝ” ይላል አባት። “የሚሸጥ ስለሆነ እማማ ትቆጣለች” በማለት ይመልሳል ልጅ። “አትንገራት፣ ለራስህም አይስክሬም ውሰድ” አለ አባት መልሶ። ልጁም እየፈነጠዘ የተባለውን አደረገ። በሚቀጥለው ቀን ልጁ ከት/ቤት ሲመለስ፣ አባቱን በትላንትናው ቦታ ላይ ተደብሮ ያገኘዋል።
“አባዬ”
“አቤት”
“አይስክሬም ልውሰድ?”
“አይቻልም”
“ለምን?”
“የሚሸጥ ስለሆነ እናትህ ትቆጣለች”
“ላንተምኮ ቢራ አመጣልሃለሁ”
“አልፈልግም”
“ለምን?”… አባት ዝም አለ።
ልጁ ምን ያህል አይስክሬም እንዳለ ለማየት ማቀዝቀዣውን ሲከፍት፣ ምንም ቢራ አለመኖሩን እግረ መንገዱን አረጋገጠ። አባቱ ቀደም ብሎ ፍሪጅ ውስጥ ቢራ አለመኖሩን እንዳወቀ ገባው። ቢኖር ኖሮ…
***
ወዳጄ፡- ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ለሰባተኛ ጊዜ በአገራችን ተከብሯል። ሙስና ስር በሰደደበት፤ በዓይነትና በስፋት በተዛመተበት እንደኛ ባለ ሃገር፣ ዓለም አቀፉን የፀረ ሙስና ቀን ማክበር “ፌዝ” እንዳይሆን እሰጋለሁ። እንደ ሌላው ነገራችን፣ “ሆድ እያወቀ ጥርስ ይገለፍጣል” እንደሚባለው የምናስመስል እንዳይሆን፡፡ ሙስና በአብዛኛዎቹ የንግድ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ መኖሩ እርግጥ ነው። ሙስና በህንፃ፣ በመንገድና ግድብ ስራዎች ላይ በተሰማሩ ተቋራጮችና ተቆጣጣሪ ቢሮዎች ውስጥ መኖሩ አያጠራጥርም። በትምህርት ተቋማት፣ በመንግስት መስሪያ ቤትና
በልማት ድርጅት ውስጥ ሙስና አብቧል። የግል ኩባንያዎችና የሽርክና ማህበራት፣ ባንኮችና መሳይ የፋይናንስ ተቋማት በሙስና ተበክለዋል። አሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎችና የድለላ ጽህፈት ቤቶች በሙስና የነቀዙ ናቸው። የመከላከያ፣ የፀጥታ፣ የፖሊስና የፍትህ አካላት ሙስና ፖዘቲቭ ሆነዋል። በልማት ማህበራት፣ በወጣት ሊጎችና ጾታዊ አደረጃጀቶች ውስጥ መጠኑ ይነስ፣ ዓይነቱ ይለይ እንጂ ሙስና አለ። አገራችን ከግል፣ ከማህበራዊ፣ ከስነ-ልቡና
ውዝግብ፣ ከችግር፣ ከፍራቻና ከግንዛቤ ማነስ በሚመነጩ የተለያዩ የሙስና ቀለሞች እስከ አንገቷ ተነክራለች። የውሸት ማስታወቂያ፣ የውሸት ኦዲት ሪፖርት በሽበሽ ነው። በተለይ በመንግስት ስራ ላይ ሁሌም የሚገርመኝ፣ በትክክል አቅዶ፣ ያቀደውን ያላሳካ አንድም ተቋም እንደሌለ፣ ተወካዮች
ምክር ቤት ቀርቦ ሲያረጋግጥ ማየታችን ነው። ወዳጄ፡- በትክክል ታቅዶ፣ የታቀደው ከሞላ ጎደል ከተሳካ፣ ዕድገትና መሻሻል ይከተላል። እኛ ግን አላደግንም፣
አልተሻሻልንም።… ለምን? አብዛኛዎቹ የልማት ድርጅቶች በመንግስት ድጎማ የሚተዳደሩ ናቸው። የተለፋበት፣ የተደከመበት፣ ተሳካ የተባለበት ውጤትና
ትርፍ ታዲያ ወዴት ሄደ? የት ገባ? ሌላው ቢቀር “ችግሩ ምንድን ነው?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። የችግሩን ምንጭ ወይም ምክንያት ማወቅ በራሱ ግማሽ የመፍትሄ አካል እንደሆነ ይቆጠራልና! ከዓመታት በፊት አንድ የአገር ውስጥ ገቢ ከፍተኛ ባለስልጣን በሙስና ተጠርጥረው ሲታሰሩ ጥሩ ጥያቄ ጠይቀው ነበር። “ወዴት እየሄድን ነው?” የሚል። የሰውየው ቤት ሲበረበር ግን የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ገንዘቦች ተደብቀው እንደተገኙ በብሔራዊ ቴሌቪዢን ተመልክተናል። ሰውየው ካልተሳሳትኩ፣ ከሶስትና አራት ዓመታት በኋላ በመንግስት መልካም
ፈቃድ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል። እስከሚገባኝ ድረስ፣ ለጥያቄያቸው መልስ ያገኙት ግን አሁን ነው። እውነት ወዴት እየሄድን ነበር?
ወዳጄ፡- እኛም እንደ ዜጋ ይህንን ከላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ደግመን፣ ደጋግመን ጠይቀናል። መልሱ ግን “ጊዜ” ውስጥ ተደብቆ ከርሟል። ወዴት እየሄድን እንደነበርን ለማወቅ አሁን ከደረስንበት ጊዜ ላይ ቆመን፣ ወደ ኋላ መልሶ ማየት ብቻ ይሆናል። የችግሩ አስኳል ደግሞ ተጠያቂዎች ጠያቂ፣ ጠያቂዎች ተጠያቂ መሆናችን ላይ ነበር። ወዳጄ፡- ከታቀደላቸው ጊዜና ከተመደበላቸው በጀት እጥፍ ድርብ በላይ ወጪ የጠየቁ፤ በሙስና የተጨማለቁ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አቅደን አሳክተን፣ አምርተን ሸጠን፣ እኛ ግን ከብድርና ከድጎማ አልወጣንም፣ አገራችንም አላደገችም እያሉ ግራ ለሚያጋቡትም የዋሀን መልሱ ከሞላ
ጎደል “የውጤቱ ተጠቃሚዎች ባለመሆናችን ነው” የሚል ነው። በውጤቱ ሲጠቀም የነበረው፣ ግብር ሳይከፍል ግብር ሲሰበሰብ የነበረው፣ ፀረ
እንድነትና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነው አፋኝ ስርዓትና ስርዓቱን በበላይነት ሲዘውር የነበረው ሃይል ነው። ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይኸን “እውነት”
እያወቀ ደብቆብናል። ወዳጄ፡- “እውነት” ካልን ዘንዳ የኛ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ትንንሾቹን ሌቦች የሚያስፈራራ፣ ለትልልቆቹ ጌጥ የሆነ፣ ጥርስና ጥፍር
እንዳይኖረው ተደርጎ የተፈጠረ ተቋም ነበር ቢባል ያስኬዳል። ምክንያቱም የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ የሚዘረፍባቸው፣ እንደ ሃሰተኛ የቦንድ
ሰርተፍኬቶች ሽያጭ፣ በአጫጭር የመልዕክት ቁጥሮች (ለዓባይ ግድብ.፣ ለመቄዶኒያ ወዘተ) የሚላኩ የእርዳታ ገንዘቦችን አቅጣጫ ማስቀየር ወይም ሽልማት የሚያስገኙ ዕጣ ቁጥሮችን ያለ ክፍያ በተደጋጋሚ (To increase probability) ሊጠቀሟቸውና ማነካካት ለሚፈልጓቸው ሰዎች በስልክ ማስተላለፍን የመሳሰሉ የረቀቁ ወንጀሎችን ቀርቶ፣ ፊት ለፊት የሚታዩትን፣ ዓይን ያወጡ ስርቆቶችን እንኳ ማጋለጥ አልቻለም። ወዳጄ፡- በርግጥ ሙሰኞች የፈለጉትን የማድረግ ዓቅም እንዳላቸው እንረዳለን። በጎረቤት ኬኒያ ሙሰኞች የሚመቻቸውን ባለስልጣን ሚኒስትር ሆኖ እንዲሾም የማድረግ ጉልበትና ትስስር እንዳላቸው፣ ንፁህና አገር ወዳድ የሆኑ የህዝብ አገልጋዮችን ደግሞ ከተቀመጡበት ወንበር ስር የተዘረጋውን ምንጣፍ በመሳብ፣ ማንገጫገጭ እንደሚችሉ - ሚቸል ሮንግ “መብላት የኛ ተራ ነው (It is our turn to eat)” በሚለው መድሐፏ በዝርዝር ገልፃዋለች። ይሁን እንጂ በቀደም የተከበረው
ዓለም አቀፉ የፀረ ሙስና ቀን እጅ ከመስጠት ለእውነት መውደቅ እንደሚሻል ቢያንስ ዕቅድ መሆኑን አስታውሶን በማለፉ፣ “ፌዝ ነው” ያልነውን ቅሬታ፣ ከኮሚሽናችን ላይ በጊዜያዊነት እንድናነሳ አድርጎናል። አንድ ቀልድ ልጨምር፡- በተለያዩ ሃገራት የሚኖሩ ሶስት አዛውንቶች እግዜር ዘንድ ሄዱና
የመጀመሪያው ሰውዬ፡ “መቼ ነው ሃገሬ ስራ አጥነት የሌለባት የምትሆነው?” በማለት ጠየቁት። “ከመቶ ዓመት በኋላ” አላቸው። ሽማግሌውም ያንን ጊዜ ለማየት ባለመታደላቸው አለቀሱ። ሁለተኛው ሽማግሌ በተራቸው፡- “አገሬ አድጋና በልጽጋ ለሌሎች የምትተርፈው መቼ ነው?" አሉት “ከሃምሳ ዓመት በኋላ” ሲል መለሰላቸው። እሳቸውም እንደ ጓደኛቸው ህልማቸውን ለማየት ባለመታደላቸው አለቀሱ። በሙስና ከተዘፈቀ አገር የሄዱት ደግሞ…
“አገሬ ከሙስናና ከራስ ወዳድነት የጸዳች የምትሆነው መቼ ነው?” ብለው ጠየቁ። ይሄኔ እግዜር ማልቀስ ጀመረ። “ምነው?” ሲሉት “ያን ለማየት እኔም አልታደልኩም" (I will not live that long) ብሎ ተንሰቀሰቀ አሉ። ሠላም!!

Read 866 times