Print this page
Saturday, 02 January 2021 11:21

አለማችን - ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት

Written by 
Rate this item
(0 votes)


         በ2020 የፈረንጆች አመት በአለም ዙሪያ በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊው ዘርፍ የተከሰቱ ቁልፍ ጉዳዮችን መራርጠው የቃኙት መገናኛ ብዙሃኑ፣ “የአመቱ የአለማችን ዋነኛ ጉዳይ ምን ነበር?” ለሚለው ጥያቄ እንደ ዘንድሮ በአንድ ድምጽ ተመሳሳይ መልስ ሰጥተው እንደማያውቁ ተነግሯል - “ኮሮና”፡፡
አለማችን ከምንም ነገር በላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ከዳር እስከ ዳር በቀውስ እየተናጠች በጭንቅ ውስጥ ሆና በሸኘችው 2020 ከተፈጸሙት ሌሎች እጅግ በርካታ አሳዛኝና አስደሳች፣ ተስፋ ሰጪና ተስፋ አስቆራጭ፣ አስጨናቂና አዝናኝ ጉልህ ክስተቶችና ሁነቶች መካከል፣ መገናኛ ብዙሃን በቀዳሚነት የጠቀሷቸውን መራርጠን እነሆ ብለናል!

ኮሮና ቫይረስ
የጎርጎሪሳውያንን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ የአለማችን አገራት፣ አዲሱን አመት 2020፤ በርችትና በፈንጠዝያ በመቀበል ላይ ሳሉ፣ ከወደ ቻይና እንደዋዛ ለተሰማው ነገር እምብዛም ጆሮ የሰጠው አልነበረም። የተቀረው አለም በቻይናዋ ሁዋን ግዛት የታየው እንግዳ ጉንፋን መሰል ህመም ጉዳይ፣ የሁዋንና የቻይና ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ በቅጡ ይረዳና ይደነግጥ ዘንድ ወራት መፈራረቅ ነበረባቸው፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ጉዳዩን ሲያድበሰብስ ቆይቶ፣ መጋቢት ወር ላይ ኮሮና ቫይረስ አለማቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን ማወጁንና ድንበር ሳያግደው በመላው አለም መሰራጨቱን፣ በቫይረሱ የሚያዙና ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ነጋ ጠባ ማሻቀቡን ተከትሎ ግን፣ አገራት ከምንም ነገር በላይ ኮሮናን ዋነኛ አጀንዳቸው ማድረጋቸውና ድንበር ከመዝጋት አንስቶ ወሳኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ መጣደፋቸው አልቀረም፡፡  
ቀን ከቀን እየተስፋፋ የአለምን ንግድና ኢኮኖሚ ክፉኛ እያናጋና በቀውስ ማዕበል እየናጠ ከፍተኛ ጥፋት ማድረሱን የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ድሃና ሃያላን ብሎ ሳይለይ የአለም አገራትን በማዳረስ፣ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት የዳረገበት ክፉ አመት ነበር - 2020።

ከፖለቲካው ጎራ
በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ክስተቶችና ውዝግቦች የተስተናገዱበትና የባይደንን እና የትራምፕን ትንቅንቅ አለም በግርምትና በትኩረት የተከታተለበት የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ከአመቱ አይረሴ ፖለቲካዊ ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኖ ማለፉን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ ተራ በተራ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣልና የንግድ ማዕቀብ በማድረግ አመቱን የገፉት የአሜሪካና የቻይና ውጥረት ከአመቱ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ሲሆን፣ እንግሊዝ አመታትን ከፈጀ ድርድር በኋላ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ መውጣቷም ሌላኛው የአመቱ ጉልህ ክስተት ነው፡፡
የፈረንጆች አዲስ አመት 2020 በጠባ በሶስተኛው ቀን ኢራን በጀግንነቱ የምትኮራበትና የምትመካበት ቁልፍ የጦር መሪዋ ጄኔራል ቃሲም ሶሊማኒ፣ ባግዳድ ውስጥ ከአሜሪካ በተፈጸመበት የድሮን ጥቃት መገደሉንና ቴህራን የአጸፋ የበቀል እርምጃ እወስዳለሁ ብላ ከመዛት አልፋ ከቀናት በኋላ የዩክሬንን የመንገደኞች አውሮፕላን በስህተት መትታ መጣሏን፣ በዚህም 176 ሰዎችን ለሞት መዳረጓንና በአገራቱ መካከል ውጥረት መካረሩን ተከትሎ፣ “3ኛው የአለም ጦርነት ሊጀመር ነው” የሚል ስጋት መፈጠሩም ከአመቱ ተጠቃሽ የፖለቲካ ትኩሳቶች አንዱ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከስልጣን ለማንሳት (ኢምፒች ለማድረግ) የተጀመረው ሙከራ ከጫፍ ደርሶ የከሸፈበት 2020፣ የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጁንግ ኡን ከአደባባይም ሆነ ከቴሌቪዥን መስኮት ራቅ ብለው መሰንበታቸውን ተከትሎ፣ ከእስያ አልፎ ወደተቀረው አለም የተናፈሰው #ሰውዬው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል# የሚል ድንገተኛ መረጃ ለሁለት ሳምንታት ያህል ሲያነጋግር ቆይቶ፣ ንፋስ ያመጣው ወሬ መሆኑ የተረጋገጠበት አመትም ነበር፡፡

ንግድና ኢኮኖሚ
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የንግድ ግንኙነት ክፉኛ የተስተጓጎለበትና በርካታ ኩባንያዎች ስራ ለመፍታት የተገደዱበት የፈረንጆች አመት 2020፣ የአለማችን ኢኮኖሚ እድገት በ4.4 በመቶ ያህል የቀነሰበት እንደሆነ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ያስታወቀበት የቀውስ አመት ሲሆን፣ አለማችን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በመጪዎቹ አምስት አመታት፣ በድምሩ 28 ትሪሊዮን ዶላር ያህል እንደምታጣም አስታውቋል፡፡
ከኮሮና ጋር በተያያዘ ከ150 በላይ አገራት የጉዞ እገዳዎችንና የእንቅስቃሴ ገደቦችን በጣሉበት ያለፈው የፈረንጆች አመት 2020፣ የቱሪዝም መስኩን ጨምሮ የተለያዩ የኢኮኖሚው መስክ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ መስተጓጎላቸውንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም ከስራ ገበታቸው መፈናቀላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አመቱ ለነዳጅ አምራች አገራት ወይም አምራች ኩባንያዎች መልካም እንዳልነበር የሚያስታውሱ ዘገባዎች፣ የነዳጅ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ተከትሎ በአንዳንድ አገራት የነዳጅ ዋጋ አሽቆልቁሎ እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡
በርካታ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ለኪሳራ በተዳረጉበትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞቻቸውን ባሰናበቱበት ያለፈው አመት፣ የመድሃኒት አምራቾችንና የቴክኖሎጂው ዘርፍ ኩባንያዎችን ጨምሮ አንዳንድ ኩባንያዎች ግን በተለየ መልኩ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኙበት እንደነበር የሚያስታውሱ ዘገባዎች፤ አፕል፣ ማይክሮሶፍት፣ አማዞን፣ አልፋቤትና ፌስቡክ በአመቱ በድምሩ 12 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ሃብት ማፍራታቸውንም ለአብነት ያነሳሉ፡፡

የተቃውሞ ንፋስ
በመጋቢት ወር መጨረሻ ላይ በነጭ አሜሪካውያን ፖሊሶች መንገድ ላይ ጭካኔ በተሞላበትና በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው የ46 አመቱ አፍሪካ አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይ፣ መላ አሜሪካን በተቃውሞ ማዕበል ከማጥለቅለቅ አልፎ “ብላክ ላይቭስ ማተር” ለተሰኘው አለማቀፍ የጸረ-ዘረኝነትና የቀለም መድልዖ ንቅናቄ መፈጠር ሰበብ የሆነ የአመቱ አነጋጋሪ ክስተት ነበር፡፡
አምባገነን አገዛዝ ያንገሸገሻቸው እንዲሁም ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የናፈቃቸው ቤላሩሳውያን አደባባይ ወጥተው ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁበት ተቃውሞ፣ ለወራት የዘለቀው የሆንግ ኮንግ ተቃውሞ፣ በቬንዙዌላው ፕሬዚድንት ኒኮላስ ማዱሮ ላይ ያነጣጠረው የአደባባይ ተቃውሞና በህንድ አዲሱ የዜግነት ህግ የቀሰቀሰው ተቃውሞ በአመቱ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከታዩ በርካታ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  
ባለፉት 12 ወራት ከኮሮና ቫይረስ የእንቅስቃሴ ገደቦችና ሌሎች እገዳዎች ጋር በተያያዘ ተቃውሞዎች ከተቀሰቀሱባቸው የአለማችን አገራት መካከልም፣ ቦሊቪያ፣ እስራኤል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሰርቢያ፣ ኡጋንዳ፣ ብራዚልና ማላዊ ይገኙበታል፡፡

የተለያዩ አደጋዎች
ክርስቲያን ኤይድ የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋም ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ በ2020 የፈረንጆች አመት በተለያዩ የአለማችን አገራት የተከሰቱት ዘጠኙ እጅግ አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች እያንዳንዳቸው 5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥፋት አስከትለዋል፡፡
ምስራቅ አፍሪካን ክፉኛ ሲያስጨንቅ የከረመውና 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጥፋት ያስከተለው የበረሃ አንበጣ መንጋ፣ በአሜሪካዎቹ ግዛቶች ካሊፎርኒያ፣ ኦሪገንና ዋሽንግተን ተከስተው ከ5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደን ያወደሙት እሳቶች እንዲሁም በአውስትራሊያ የተከሰቱትና ከአንድ ቢሊዮን በላይ የዱር እንስሳትን ለሞት የዳረጉት የደን ቃጠሎዎችም በአመቱ ከተከሰቱ እጅግ አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች መካከል ይገኙበታል፡፡
በፓኪስታን ከ410 በላይ ሰዎችን፣ በደቡብ ሱዳን ደግሞ 138 ሰዎችን የገደለውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ተጎጂ ያደረገው የወንዝ ሙላትና ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋም፣ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱ የአመቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ተርታ እንደሚሰለፉ ተነግሯል፡፡
በአመቱ በመላው አለም ከተከሰቱት አስደንጋጭ አደጋዎች መካከል፣ በነሃሴ ወር መጀመሪያ ላይ በሊባኖስ መዲና ቤሩት የተከሰተውና ከ200 በላይ ሰዎችን ለሞት፣ 6 ሺህ 500 ያህል ሰዎችን  ለመቁሰል አደጋ የዳረገውና ከ300 ሺህ በላይ ሰዎችን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለው አሰቃቂ ከባድ ፍንዳታ አንዱ ነበር፡፡
ሌሎች ጉዳዮች
ብዙዎች ለኪሳራ የተዳረጉበት ያለፈው አመት ለአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ የበዛ ትርፍ ያካበተበትና ታሪክ የሰራበት ልዩ አመት ነበር፡፡ የኩባንያቸው አማዞን የአክሲዮን ዋጋ በአንድ ቀን በ2 በመቶ መጨመሩን ተከትሎ አጠቃላይ የተጣራ ሃብታቸው 204.6 ቢሊዮን ዶላር የደረሰላቸው የ56 አመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ፣ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ የተጣራ ሃብት በማፍራት በአለማችን ታሪክ የመጀመሪያው ባለጸጋ በመሆን አዲስ ታሪክ የሰሩት፣ ብዙዎች በኪሳራ በተመቱበት ያለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ነበር፡፡
የአለማችንን ከተሞች የኑሮ ውድነት ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት በበኩሉ፣ የስዊዘርላንዷ ዙሪክ፣ የፈረንሳዩዋ ፓሪስና የቻይናዋ ሆንግ ኮንግ የአመቱ የአለማችን እጅግ ውድ ከተሞች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከሚጠቀሱ የአመቱ ጉልህ አለማቀፍ ክስተቶች መካከልም፣ የእንግሊዙ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ለንደን፣ ተመራማሪዎች በአለማችን የኢንተርኔት ፍጥነት ያስመዘገቡት አዲስ የአለም ክብረ ወሰን አንዱ ሲሆን፣ በአንድ ሰከንድ 178 ቴራባይት መጠን ያለው መረጃ ማስተላለፍ የሚያስችለው ይህ አዲስ የምርምር ውጤት፣ ከዚህ በፊት በክብረ ወሰንነት ተይዞ ከነበረው የኢንተርኔት ፍጥነት በ20 በመቶ ያህል እንደሚበልጥ ተነግሯል፡፡
በ2020 በተለያዩ የሙያ መስኮች ታዋቂነትን ያተረፉ ከዚህ አለም በሞት የተለዩ የአለማችን ዝነኞችን ገቢ ይፋ ያደረገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን በ48 ሚሊዮን ዶላር ገቢ 1ኛ ደረጃን መያዙን ከሳምንታት በፊት አስታውቋል።
አመቱ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጊዜ ብቻ ሲቀረው አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ይፋ ያደረገው ሌላ መረጃ ደግሞ፣ 2020 በመላው አለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች የታሰሩበት እንደነበርና በአለም ዙሪያ በድምሩ ከ274 በላይ ጋዜጠኞች በስራ ገበታቸው ላይ ሳሉ ለእስር እንደተዳረጉ የሚያስታውስ ነው፡፡

Read 11033 times
Administrator

Latest from Administrator