Sunday, 03 January 2021 00:00

ጠባችን ውስጥ የድኅነታችንም እጅ አለበት!

Written by  ጤርጢዮስ ዘ-ቫቲካን
Rate this item
(1 Vote)

    ከትናንት በስቲያ አመሻሹ ላይ ኦሎምፒያ አካባቢ ያጋጠመኝ ነገር ነው  እንደ ግለሰብም እንደ ቡድንም  ጠባችን ውስጥ ድኅነታችን ድርሻ እንዳለው ያስታወሰኝ። የሁሉም ጠባችን መነሻ ድኅነት ነው ባይባልም በተለያየ መንገድ  እጁን የምናይበት አጋጣሚ ግን ብዙ ነው። ይኼን ገጠመኜን ያጋራሁት አንድ ወዳጄ፣ ስሜን በቁልምጫ ጠርቶ “...ዬ ቀደም ባለው ጊዜኮ ድኅነታችን የጠባችን ሳይኾን ተሳስበንና ተፋቅረን የመኖራችን ምክንያት ነበር። ተካፍሎ መብላትም ኾነ እንግዳን መቀበል ከድህነታችን ባልተናነሰ መታወቂያችን ነበር። ላለፉት 30 ዓመታት የምናየው ጠባይ  ግን እጅግ ባዕድ  ነው” ሲል በሰጠኝ አስተያየትም እስማማለሁ።
በእርግጥም ዘውጌነት ያጠላበት ፖለቲካችን ለዘመናት አብሮን  የኖረውን  ሰናይ ባሕርያችንን  አሳጥቶ፣ የሥነ ምግባር እሴቶቻችንን ሰልቦ ራቁታም  እንዳደረገን እሙን ነው። የ”እኛ” እና “ኬኛ” ፖለቲካ እንደ አንድ ሀገር ልጆች ተፋቅረንና ተሳስበን እንዳንኖር እየተጫወተ ያለው ሚናም ቀላል አይደለም። ይሁንና ሰሞነኛው ገጠመኜም  ቢኾን በራሱ ዐውድ ከታየ በደኅ ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦችን የእርስ በእርስ ጠብ  ሌላኛው ገጽታ ለመታዘብ ያስችላል። የጠባችን መነሻ ጥጋብና ስግብግብነት ብቻ ሳይኾን ድኅነት ከሚያደርስብን  የኑሮ ጫና  ጋር የተያያዘም እንደኾነ ፍንጭ ይሰጣል። ድኅነት የማፋቀሩን ያህል ላልተፈለገ ጠብ አጫሪነት መነሻ ሊሆን እንደሚችል ጥሩ ምሳሌም  ነውና  ወደ ገጠመኜ ትረካ  ልዝለቅ።  
ከፍ ብዬ በጠቀስኩት ምሽት  ከመስቀል ፍላወር አቅጣጫ  ወደ  ኦሎምፒያ በእግሬ እያዘገምኩ ነበር። የሥራ መውጫ ሰዓት ስለኾነ መንገዱ  በሰው ተሞልቷል። የጎዳና ላይ ገበያ የአላፊ አግዳሚውን ዓይንና ጆሮ ይስባል። ምንም እንኳ የሜክሲኮ አደባባዩንና የመገናኛውን ያህል ባይበዙም፣ “መቶ ብር ነው ይላል ... ሁለት መቶ ብር ነው ይላል... አጋጣሚ ነው ይላል” እያሉ ዐይንና ጆሮ አማላይ ማስታወቂያ የሚሠሩ ጥቂት  ሸቅሎ አዳሪ የጎዳና ነጋዴዎች ኦሎምፒያም አካባቢ ነበሩ።  ወደዚያ “የደራ ገበያ” ከመድረሴ በፊት ያጋጠመኝ ጠብ ደግሞ የዚህ መጣጥፌ መነሻ ነው።
በዕለቱ በአንዳች ጉዳይ ጠብ ውስጥ የገቡ ሁለት ሰዎች ቀልቤን ስበውት ስለነበር ከርምጃዬ ተናጥቤና አጠገባቸው ቆሜ  ጭቅጭቃቸውን ማዳመጥ ጀመርኩ። ጠበኞቹ አንድ ጎልማሳና አንዲት ወጣት ልጃገረድ ናቸው። ጎልማሳው ለፍቶ  አዳሪ፣  የጎዳና ላይ ነጋዴ ነው። ተሽከርካሪ ጎማ ባለው የብረት ሰንዱቁ የደረደረውን ሳንቡሳ ለአላፊ አግዳሚው የሚሸጥበትን ገዢ መሬት በማግኘቱ ቢደሰትም “ክልሌ ውስጥ ገብተሃልና ወጊድልኝ!” የሚል ብርቱ ተቀናቃኝ  ገጥሞታል።
ተቀናቃኙ በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያለች፣ ለምና አዳሪ ዐይነ ሥውር ልጅ ናት። ሲያይዋት አንጀት ታላውሳለች። በፍጹም ለማኝ አትመስልም።  ባጭሩ የተከረከመ ጸጉር፣ ጥቁር መነጽር፣ ንጹህ ሰማያዊ ሹራብ፣ ንጹህ  ጥቁር ሱሪ፣ ጽድት ያለ ጫማ  አድርጋለች። ጎልማሳው ሳንቡሳ ሻጭ በአንድ በኩል የብረት ሰንዱቁን በሳንቡሳ መቆንጠጫው ብረት እየጠበጠበ “አለ ትኩስ ሳምቡሳ...ትኩስ ሳምቡሳ...” እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ለተቀናቃኙ ምላሽ ይሰጣል።
ዐይነ ስውሯ ለማኝም በተመሳሳዩ በግራ እጇ መንገድ መምሪያ ተጣጣፊ በትሯን አጥብቃ ይዛ፤ በቀኝ እጇ መዳፍ ውስጥ የገቡትን ጥቂት የብር ሳንቲሞች እያቅጨለጨለችና ቸርነት የሚያደርግላትን ሰው እያሰበች ከጎልማሳው ነጋዴ ጋር ከፍተኛ ጠብ ውስጥ ገብታለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ነው አጠገባቸው የደረስኩት። ልጅቱ በጎልማሳው ነጋዴ ላይ ያነሳችው ተቃውሞ “ሰው አይቶ እጁን እንዳይዘረጋልኝ ጋርደኸኛል” የሚል ነው። በመደጋገም ከአንደበቷ የሚወጣው  ቃልም  ይኸው ነው።
ተከሳሹ ጎልማሳ “ኧረ አልጋረድኩሽም” ቢላትም አልተቀበለችውም። “ምን አልጋረድኩሽም ትለኛለህ፣ ጥላህኮ ይታወቀኛል፣ ስለዚህ ከአጠገቤ ሂድልኝ፣ መጣህብኝ እንጁ አልመጣሁብህም” በማለት መፍትሔው ከአጠገቧ መራቁ ብቻ እንደኾነ ደምድማ እየሞገተችው ነው። (ዐይነ ሥውራን ሰዎች “የማየትን ያህል” ከባቢያቸውን የሚገነዘቡበት ክህሎት ይገርማል) ጎልማሳው ሳንቡሳ ሻጭ የወጣቷን አካል ጉዳተኝነት ከግምት ውስጥ አስገብቶ፣ አንድም በአጸፋ አሰጣጡ እንዳያስከፋት፣ አንድም  ለንግዱ አመቺ  የኾነለትን ቦታ ላለማጣት በጸባይ እየለመናት ነው ። ሁለቱም በጣም አሳዘኑኝ ። ሁለቱም በተለያየ መንገድ በልቶ ለማደር ከኑሮ   ጋር እየታገሉ ነው።  
ስለዚህም በጊዜው ወደ ልቤ እንደመጣልኝ ወጣቷ ዐይነ ሥውር ልጅ አጠገብ ቁጢጥ እንደ ማለት ብዬ መዳፏ ላይ እየተቅጨለጨሉ ካሉት ሳንቲሞች በብዙ እጥፍ የሚበልጥና  ከወቅቱ ስሜቷ ሊያወጣት የሚችል የወረቀት ገንዘብ አስጨበጥኳት። በራሷ የማጣሪያ መንገድ ስንትነቱን መለየት እንደምትችል ብረዳም ቀልቧ ግና ከጎልማሳው ጋር በጀመረችው እሰጥ አገባ ላይ ስላረፈ “የኔ እናት ክርክራችሁን ቆሜ እየሰማሁ ነበር። ዛሬ በዚህ ወንድማችን መጋረድ የምታጪውን ሳንቲም እኔ ሸፍኛለሁ። መቶ ብር ነው እሺ?!”  ባልኳት ቅጽበት ፊቷ ፍክት ብሎ አንድም የደስታ፣ አንድም ለካስ ሌላም ሰው እየሰማኝ ኖሯል  ዓይነት  ቀጭንዬ  የሳቅ  ድምጽ አሰማች።
በዚያው ቅጽበት ግን ስሜቷ ልውጥ ብሎ፦ ”እኔኮ እንዲህ የሚያናግረኝ...” ብላ የጀመረችውን ሳትጨርስ ሳግ ሲተናነቃት፣  አንጀትን የሚበላ የሀዘን ከል ፊቷ ላይ  ሲከለበስ ተመልከትኩ።
ስሜቷ በቀላሉ ወደ ሰው የሚጋባ ዓይነት ነበር። እኔም በዚያው ቅጽበት ሰቅዞ ለያዘኝ የሀዘን ስሜቴ መግለጫ የሚሆን ቃል ስላጣሁ “ የኔ እናት ገብቶኛል...” ብያት ሁለቱንም ተሰናብቼ መንገዴን ቀጠልኩ። አዎ ገብቶኛል፤  ያቺን ምስኪን ልጅ እንዲያ ያደረጋት ድኅነት እንጂ ሰው ጠልነት አልነበረም።
ዛሬም በሀገራችን  በጥቂቶች እብሪተኝነት በሚዘወረው  ጠብና ጦርነት ውስጥ፣ ከሰው አራጅ የዘረኝነት ልክፍትና  ከስግብግብነቱ ሚነሳው ጠብ እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ለአንዳንድ ጠቦቻችን የድኅነታችንም እጅ ከዓይነ ሥውሯ ልጅ  ሁኔታ መታዘብ እንችላለን። ከእኛም መካከል ከፊሎቻችን በዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴዎቻችን በሚገጥሙን  ጠቦችና ጭቅጭቆች ውስጥ   የድኅነታችን እጅ የለበትም ትላላችሁ?
የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሎ ለነበረው የአረቡ ዓለም አመጽ (The Arab Spring) ዋናው አቀጣጣይ ቱኒዚያዊው የጎዳና ላይ ነጋዴ  ዘግናኝ አሟሟት መኾኑም የሚዘነጋ ዓይደለም።  
ሙሐመድ ቡአዚዝ  የተሰኘው ይኼ የጎዳና ላይ ነጋዴ፣ አባቱን በህጻንነት ዕድሜው በሞት በመነጠቁ ምክንያት እናቱንና ስድስት የሙት ልጆች ያስተዳድር የነበረው ጎዳና ላይ ቆሞ በሚሸጠው አትክልትና ፍራፍሬ ነበር። ይሁንና በተጠቀሰው ዓመት “ጎዳና ላይ ለመነገድ የሚያስችል የንግድ ፈቃድ የለህም፣" በሚል ሰበብ ከፖሊስ ጋር በገጠመው አምባጓሮ በጣም በመበሳጨቱ  ሰውነቱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎና ክብሪት ለኩሶ  ራሱን አቃጥሎ  ሞቷል። መሐመድ ቡአዚዝ  ወደዚህ  እርምጃ ገብቶ ራሱን  ለማጥፋቱ ሌሎች ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም ድኅነት የአንበሳውን ድርሻ መውሰዱም  የሚታበል ዓይደለም።

Read 2897 times