Monday, 04 January 2021 00:00

የብልፅግና ፓርቲና የተቃዋሚ የምርጫ ካርዶች።

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የብልጽግና ፓርቲ ብልጫ-“ከትናንት የመጣ አቅም” (“ግን በትናንት የተበከለ!”)
ስልጣን የያዘ ፓርቲ ነው። ብዙ ነገር ማድረግና አለማድረግ ይችላል።  የስልጣኑ መነሻው፤  ከትናንት ወዲያ ይሆናል  እንደ ቅርስ። የትናንት ውጤትም ነው እንደ ጥሪት።
ከላይ እስከታች የተዋቀረ፣ ከሚሊዮን በላይ አባላትን የመለመለ ፓርቲ ነው- በጣም የተደራጀው። ከትናንት የተወረሰ ስንቅ ነው ልትሉት ትችላላችሁ።
የሃሳብና የአሰራር ሰነዶች፣ እንዲሁም ልምዶች አሉት።
“ያን እቅድ አሳክቻለሁ፤ ይሄን ግንባታ ጀምሬአለሁ። ያን ጥፋት አስወግጃለሁ፤ ለውጥ አምጥቻለሁ። ይሄን ችግር ቶሎ  አጠፋለሁ” ብሎ መከራከር ይችላል። የትናንት ታሪኩን እንደማሳያ እየጠቀሰ፣የነገን ተስፋ ለማሳየትና ቃል ለመግባት ቢሞክር አይገርምም፡፡
“አቅምና ብቃት አለኝ”። አረረም መረረም፤ ተወደደም ተጠላም፤… “ከኔ በቀር፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች አቅመቢስ ናቸው” የማለት እድልም አለው።
የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ብልጫ፤  “ከትናንት የፀዳ”፤( “ግን ጥሪት አልባ”!)
“አገሬው ደህይቷል። ዋጋ እየናረ ነው፣ ኑሮ ተወዷል፤  ኢኮኖሚ ተናግቷል። ወጣት ሁሉ ስራ አጥቷል። ተመራቂዎች እንኳ እቤት ውለዋል። ብዙዎች በስደት በየበረሃው ቀርተዋል። ባህር በልቷቸዋል። መኖሪያ ቤት የለም፤ ታክሲና አውቶቡስ፣ ስንዴና ዘይት አይገኝም። ይሄ ሁሉ የመንግስት ጥፋት ነው” በማለት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በደፈናው ገዥው ፓርቲ ላይ ውግዘት መከመር ይችላሉ።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስልጣን ስላልያዙ፤ “ያን ሰርተን፣ ይሄን አሳክተናል” ብለው መከራከር አይችሉም። ነገር ግን “ጥፋት አይገኝብንም፤ በጭራሽ  የለንበትም”  በማለት፣ ሁሉንም አይነት ችግር በመንግስት ላይ ለመከመር የሚሞክሩ እንደሚኖሩ አያጠራጥርም። “አለማወቅ ከጭንቀት፤ አለመስራትም ከስህተትና ከጥፋት ያድናል!” እንደ ማለት ይመስላል። ቢሆን ግን፣ “ሁሉም ችግር የመንግስት ጥፋት ነው” በሚል ስሜት ገዢውን ፓርቲ ማስጠቆር አይከብዳቸውም። ማንም ቢሆን፣ በስራ መሃል፣ ጥፋት ይሰራል።  ምንም ያልስራስ ፣ ጥፋት ሰርተሃል ይባላል?
መንግስት፣ “ሰላም አላሰፈነም። ህግ አላስከበረም። ሰዎች እየተገደሉ፣ ንብረታቸው እየወደመና እየተሰደዱ፤ ህጋዊ እርምጃ አልተወሰደም” የሚል  የተቃውሞ ውግዘት እንደሚኖር አያጠያይቅም። በሌላ በኩል ደግሞ ፣ “ወታደሮችን አዘመተብን፤ ፖሊሶችን አሰማራብን፤ እከሌን አሰረ፣ እገሌን ከሰሰ። ለውጥ አምጥቻለሁ ቢልም፤ እንደድሮው እርምጃ እየወሰደብን ነው” በማለት ቢያወግዙ፤ ሰሚ አያጡም። መንግስት፣ ሕግ ቢያስከብር ባያስከብር፣ ይወገዛል። መስራትም አለመስራትም ያስኮንናል። “Damned if you do, damned if you don’t”  ይባል የለ? ይሄ የመንግስት እዳ ነው።
“ድሮም ስልጣን ላይ ነበሩ። ዛሬም ስልጣን ላይ አሉ። ታዲያ  የታለ ለውጡ?” በማለት በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብልፅግና ፓርቲን መክሰሳቸውስ ይቀራል? መቼም፤ ብልጽግና ፓርቲ “ኢህአዴግ ሌላ እኔ ሌላ። አላውቀውም። አያውቀኝም” ብሎ አይከራከርም። ቢሞክርስ ያዋጣዋል? “የቀድሞው ኢህአዴግ የፈጸማቸው ጥፋቶች ላይ የለሁበትም። ጥፋቶቹንም አላውቅም ነበር” የሚል ምላሽም ብዙ አያስኬድም። ዋና ዋናዎቹ የኢህአዴግ ስህተቶች፣ ድብቅ ሴራዎችና ሚስጥራዊ ተንኮሎች አይደሉም። “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ”፣ በይፋ የተራገበ እጅግ መጥፎ ሃሳብ ነው እንጂ፣ በድብቅ የተሸበረ ሴራ አይደለም። መንግስት ኢኮኖሚውን በሰፊው  ሲቆጣጠርና በብዛት ወደ ቢዝነስ ሲገባ፣ ብዙ ሃብት በብክነት እንደሚጠፋና ሙስና እንደሚስፋፋስ፣ ሚስጥር ነው? አይደለም።  የመንግስት ፕሮጀክቶች በድብቅ የተወጠኑና የተጀመሩ አይደሉም፡፡ በጭብጨባና በድጋፍ ታጅበው የመጡ ናቸው። እንዲውም፤ አብዛኞቹ ፓርቲዎች፣  ትናንትም ዛሬም፣ አስተሳሰባቸው ከዚህ የተለየ አይደለም። መንግስት በሰፊው ወደ ቢዝነስ መግባቱን አያቃወሙም፤ እንዲውም ይደግፋሉ። እንዲያም ሆኖ፣በሃሳብ የተለያ ባይሆኑም፤ጥፋት ሁሉ የመንግስት ነው ብለው መከራከር አያቅታቸውም፡፡
በአጠቃላይ፣ “እኛ ንፁህ ነን፤ ለውጥ ያስፈልጋል” የማለት እድል አላቸው- ተቃዋሚ ፓርቲዎች። የተሻለ ሃሳብ ማቅረብና ማብራራት፣ የስራ ብቃታቸውንና ውጤታማነታቸውን ማስመስከር አይጠበቅባቸውም- በደፈናው፤ “ለውጥ ያስፈልጋል” ብለው ቢናገሩ፣ አነሰም በዛ ሰሚ ማግኘታቸው አይቀ ርም።Read 4388 times