Print this page
Wednesday, 06 January 2021 00:00

“የብልጽግና ፓርቲ” ፈተና! የውርስ ባለ እዳ ወይስ ባለ ቅርስ? “The party is dead. Long live the party`

Written by  ዮሃስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   • ከትናንት ጋር ፀብ እየፈለገ፣ ከትናንት ጋር ለመተኛት ይናፍቃል።
        • የትናንት ችግኝ፣ የትናንት ችግር፣ የትናንት ጥፋት… ብዙ ነው አይነቱ።
        • አወዛጋቢው ትናንት- ድፍርስ ነው- የቅንነትና የክፋት ቅይጥ።
              
          “ለውጥ”፣ ለደጉም ለክፉም፣ ከባድ ነው። አይነቱ ግን ይለያያል።
“መጥፎ ለውጥ”፣ ብዙ ጥረት ላያስፈልገው ይችላል። አያደክምም። መፍዘዝና መደንዘዝ፣… ለመጥፎ ለውጥ በቂ ነው። እጅን አጣጥፎ፣ አፍን ዘግቶ በመቀመጥ ብቻ፤ መጥፎ ለውጥ ይመጣል።
ያለ ሃሳብ በዘፈቀደ እየዘባረቁ፣ በደመ ነፍስ እየተቅበዘበዙ፣ ያለ ብዙ ድካም፣ ገደል መግባት አይከብድም። ታዲያ ምኑ ላይ ነው ክብደቱ?
መዘዙ ነው፣ ከባዱ ነገር። ገደል ገብቶ ማን ይድናል? ቢድን እንኳ፣ ጎድሎና ተሰብሮ ነው። እንደ አጋጣሚ፣ ከጉዳት ቢተርፍ እንኳ፣ ከገደል መውጣት፣ ገደል እንደመግባት፣ ቀላል አይሆንም። የመጥፎ ለውጥ መዘዝ፣ ከባድ ነው።
ነገር ግን፣ “ጥሩ ለውጥ”፣ ቀላል ነው ማለት አይደለም። ከባድ ነው። “ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን አስተሳስሮ፣ በጥራትና በምልዓት ማሰብ፣ ምኑ ይከብዳል?” የሚል ይኖራል። መነሻን፣ መሸጋገሪያንና መድረሻን የሚያገናኝ፣ ተስተካክሎ የተቃና፣ የሚያዋጣና የሚያዛልቅ፣ የስኬት መንገድ መተለምስ?
አንደኛ ነገር፣ የትናንት ሁኔታችንና መነሻ አቅማችን፣ ያን ያህልም የሚያወላዳ እንደማይሆን አትርሱ። ሁለተኛ ነገር፣ ዛሬ ሲሰሩ ውለው ቢያድሩ፣ የዛሬ ከባድ አድካሚ ጥረት፣ ዛሬውኑ ለፍሬ የማይደርስ መሆኑስ? ለነገ የታሰበው አላማ፣ እጅግ ርቆ፣ መንገዱ የማያልቅ፣ ሌሊቱ የማይነጋ እየመሰለ ፅናታችንን ሲፈታተንና መንፈሳችንን ሲያጨልምብንም አስቡት። “መልካም ለውጥ”፣ ውጤቱ አስደሳች የመሆኑ ያህል፣ ስራው ከባድ ነው። እንዴት በሉ።
የእለት ተእለቱን ጥረትና ድካም፣  ለጊዜው እንተወው። ለችግር ሳይበገሩና ተስፋ ሳይቆርጡ ለዓመታት በፅናት የመጓዝ ፈተና…. ይሄን ሁሉ ለጊዜው እናቆየው። “ትናንት” የሚባለው ነገር ራሱ፣ ምን ያህል እንደሚፈትነን አስቡት። ከትናንት ባገኘነው አቅም ነው፤ ዛሬን የምንኖረው፤ ለነገ የምንገነባው። እንዲህ ሲታይ፣ ነገሩ ሁሉ፣ በጣም ቀላልና ግልፅ ይመስላል።
ታዲያ፣ ለምንድነው የሚፈታተነን? ለምንድነው የሚያምታታን? በችኮላ ለመፍረድ ፈልጌ አይደለም።
“ትናንት”፣ በተፈጥሮው፣ ግራ የሚያጋባ ባሕርይ አለው። እዚያው በዚያ፣ በወዲህ በኩል “መከራ”፣ በወዲያ በኩል “ፀጋ” ይሆንብናል። ስለ “ትናንት” ስናስብ፣ ጥሩም መጥፎም፣ አስደሳችም አስቀያሚም፣ የተጣላም የተወደደም እየመሰለ ያምታታናል። በእርግጥም፣ “ትናንት”፣ በተፈጥሮው ጉራማይሌ ነው።
በአንድ በኩል፣ መልካም ነው። “ትናንት”፣ አንዳች ዋጋና ፋይዳ ባይኖረው ኖሮ፣ “ዛሬ” ትርጉም አይኖረውም፤  “ህልውና የለሽ ኦና” ይሆናልና። አነሰም በዛ፣ ለዛሬ ህልውናችን የሚጠቅም አንዳች ፀጋ፣ ለነገ እድገታችን መነሻ የሚሆን ቅንጣት አቅም፤ ልናገኝ የምንችለው፣ ከትናንትናችን ነው። “የኋላው ከሌለ፣ የወደፊቱ የለም” እንደተባለው ነው።
በሌላ ገፅታው ደግሞ፣ “ትናንት”፣ አንዳች “ጉድለት” ወይም “እጦት” ባይኖረው ኖሮ፣ ነገን የሚያሻሽል “መልካም ለውጥ” ወይም “እድገት” ብሎ ነገር የለም።
የትናንቱን ነገር፣ በጥሩ ገፅታው ካልወደድነው፣ ለነገ የመስራት፣ የማሳደግ፣ የማሻሻል፣ የማቃናት፣ የማስተካከል፣ የማሳመር ሃሳብም ሆነ ፍላጎት አይኖረንም።
ግን ደግሞ፣ የትናንቱ ነገር፣ ይብዛም ይነስ፣ ቅር የሚያሰኝ “ጉድለት” ወይም አስቀያሚ “ብልሽት” ባይኖረው ኖሮ፣ “መልካም የማሻሻያ ለውጥ” ብንል፣ ምን ትርጉም አለው?
ልብ በሉ። “ጉድለት” መስሎ የሚታየን የትናንት ሁኔታ፣ አንዳንዴ፣ የጥፋትና የብልሽት ጉዳይ ላይሆን ይችላል። በተፈጥሯቸው፣ ረዥም ጊዜ የሚጠይቁ ነገሮች አሉ።
የቡና ችግኝ፣ የወይን ተክል፣ የእህል ቡቃያ፣…. ቅንጣት ጉድለትና ብልሽት ባይኖራቸውም እንኳ፣ “ብዙ ይቀራቸዋል”። አድገው ለፍሬ አልበቁም። ገና ናቸው።
 እየተገነባ የሚገኝ ግድብ ወይም ፋብሪካ፣ ትምህርት ቤት የገባ ሕጻን፣ የተጀመረ ጉዞ፣ ውጥን እቅድ፣ ጅምር ጥናት፣…. እነዚህ ሁሉ፣ ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬም ነገ፣ በትክክልና በስርዓት፣ እያደረጉና እየተሻሻሉ መሄድ አለባቸው።
መልካም ለውጥ ያስፈልጋል ማለት ነው። ለምን? ሕይወት፣ በተፈጥሮ እንዲህ ነው። ሕይወት፣ እውነትም፣ “የመደመር” ሂደት ነው። በትናንት ጅምር ላይ የዛሬ ይጨመርበታል። ብልህ ገበሬ፣  ችግኝ ይተክላል። ስራው እንዳላለቀ ግን ያውቃል። ችግኝ ወይም ቡቃያ፣ ብቻውን በቂ አይደለም። ገና ይቀረዋል። ችግኙ ፀድቆ፣ ቡቃያው አድርጎና አብቦ፣ ለፍሬ እንዲያበቃ፣ ጎበዝ ገበሬ ይጥራል - “በመልካም ለውጥ” ወደ ውጤት ለመድረስ።
ፋብሪካው ወይም ግድቡ፣ ትናንት በተተከለ አንድ የመሰረት ድንጋይ ላይ መቅረት የለበትም። ዛሬ እየተገነባ፣ ነገ ስራ እየጀመረ፣ በብቃት ለማምረትና አገልግሎት ለመስጠት፣ ማለትም ወደ ትርፋማነት የሚያደርስ መልካም ለውጥ ያስፈልገዋል። ያለ ለውጥ፣ “ትናንት” ላይ ቆሞ መቅረት የለበትም።
የልጆች የአካልና የአእምሮ፣ የሙያና የእውቀት እድገት፣ ወደፊትም እንዲበለጽግ ከተፈለገ፣ ዛሬና ነገ፣ “መልካም ለውጥ” ሊኖር ይገባል። ከፊደልና ከቁጥር፣ ወደ ንባብና ወደ ሂሳብ ስሌት፣ ከዚያም ወደ ቲዎሪና ወደ ቀመር ይበለፅጋል። እንዚህን በመሳሰሉት ተፈጥሯዊ ሂደቶች፣ ነገ ከትናንት የተሻለና የላቀ መሆን ይኖርበታል።
ግን፣ የትናንቱ ነገር መጥፎ ነበር ማለት አይደለም። ችግኙ ለፍሬ፣ ቡቃያው ለአዝመራ ባይደርስም፤ በዚያው መቅረት ባይኖርበትም፣ ለነገው ጣፋጭ ፍሬ፣ ለከርሞው የአዝመራ በረከት፣ ትናንትናችን ለነጋችን፣ መልካም መነሻና ስረመሰረት ነው። “ትናንት”፣ ገና ያልተሟላ ቢሆንም፣ ተወዳጅና ንፁህ ፀጋ እንጂ፣ “ጎዶሎ” ወይም “ብልሹ” ተብሎ የሚወቀስ አይደለም።
በተወለድኩ ጊዜ፣ ለበርካታ ወራት፣ “የመራመድ ጉድለት” ነበረብኝ፤…. በሦስት ዓመቴ፣ “ማንበብ የማልችል መሃይም ነበርኩ” ብሎ ራስን  መውቀስና ማውገዝ ምን ይባላል? ቅዠት ወይም ስካር!
ነገር ግን፣ ሁሉም የትናንት ጅምር፣ ሁሉም የአምና ህልውና፣ “እንከን ያልነካካው ንፁህ መነሻ” አይሆንም።
ብዛቱና ስፋቱ ቢለያይም፣ የትናንት ህልውናና ተግባር፣ የትናንት ልምድና ታሪክ፣… በአብዛኛውና በአመዛኙ፣ ቅይጥ ድንግዝግዝ ነው። ከመልካም ገጽታ ጋር መጥፎ ገጽታንም የሚያዳብል፣ ከጠራ ምንጭ የፈለቀውን ውሃ የሚያደፈርስ፣ ወይም በቆሻሻ የሚበርዝ ነው - “ትናንት”። የትናንቱ ውሎ፣ የከርሞው ልማድ፣ የአምና የካቻናው ታሪክ፣ በአብዛኛው፣ “ቅይጥ” መሆኑ፣ ጉዳት አለው።  ግን እጣ ፈንታ አይደለም። ጥፋት ነው። ግን፣ እርግማን አይደለም።
በዚያ ላይ፣ ሁሉም ጥፋት እኩል አይደለም። አንዳንዱ ጥፋት ከቁጥር አይገባም። ለተወሰኑ ቀናት የተዘናጋ ታታሪና ብሩህ ተማሪ፣ ዛሬና ነገ፣ ተጨማሪ እውቀት ለመጨበጥና በአእምሮ ለመበልፀግ፣ የተወሰነ ያህል ችግር ይገጥመዋል።
ዛሬ በእውቀት እየበለጸጉ ለማደግ፣ የትናንት ደልዳላ መሰረት ያስፈልጋል። እናም ትናንት ትንሽ የተዘናጋ ተማሪ፣ በዚያው ልክ ዛሬ ይደነቃቀፋል።
በእርግጥ ከዚህ ችግር የሚላቀቀውም፣ የትናንት መልካም ገፅታውንና እስከ ትናንት ድረስ በታታሪነት የተማረውን እውቀት በመጠቀም ሲጥር ነው። የትናንት ውርሱ፣ ትንሽ የሚያደናቅፍ ገፅታ ቢኖረውም፣ በአብዛኛው ግን፣ ለነገ የሚጠቅም ውድና ድንቅ ገፅታ አለው። የዛሬ ያዛ እውቀቱ በሙሉ፣ ከትናንት የተገኘ ነውና።
ከዚህ ባስ ያለ ችግር አለ። ጎበዝና አዋቂ አስተማሪ፤ ግልፍተኛ እየሆነ ቁጣ ቢለምድ አስቡት። የአስተማሪያችሁ ጉብዝና ጠቅሟችኋል… ለእውቀት። ቁጡ ግፍተኛ መሆኑ ደግሞ፣ ይጎዳል… ወይም የትምህርት ጊዜን በከፊል ያባክናል። በአጭሩ፣ አስተማሪያችሁ፣ “የጥሩና የመጥፎ ገፅታ ቅይጥ” ይሆንባችኋል።
የሕይወት ጉዞ፣ በአብዛኛውና በአመዛኙ፣ እንዲህ “የተበረዘና የተቀየጠ” መሆኑ ያሳዝናል።
በተለይ፣ ብዙ ሰዎች የሚሳተፉበት የህይወት መስክ ላይ፣ ችግሩ የከፋ ይሆናል። የአንድ  አስተማሪ ወይም የአንድ ፖሊስ ብቃትና ጉድለት ከማየት አልፈን፣ የትምህርት ቤትና የፖሊስ ጣቢያ ሁኔታን ወደማየት ስንሻገር፣ “የባሰበት ቅይጥ” ይገጥመናል።
ከቤትና ከጎረቤት አልፈን፣ ወደ ሰፈርና መንደር፣ ከቀበሌና ከመሬት ካርታ፣ ከከንቲባና ከከተማ፣ ወደ መንግስትና ወደ ፓርቲ፣ ወደ አገርና ወደ ፓርላማ፣ ስንመለከት፣ “ቅይጥነቱ” ይጨምራል። በአንድ በኩል ሰርቶ መኖርና አምርቶ መገበያየት ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ በመንግስት ሳቢያ የሚፈጠር የስኳር እጥረት የታክሲ ወረፋ ይመጣል።  በአንድ በኩል ከጠራራ ፀሃይ ዝርፊያና ከሽፍትነት የሚያድን ህግና ስርዓት አለ። ግን ኪስን የሚያራቁት ተደራራቢ ታክስና ግብር አለ። ስራ ለመጀመር የተንዛዛ ቢሮክራሲና ንብረት የማስከበር የፍርድ ቤት ክርክርም አለ። ከተቀዋሚ አመጽና ውንብድና ጋር፣ የመንግስት አፈናና አስር፣ ድንበር  ጠባቂና ህግ አስከባሪ፣… ወራሪን የመከተ ታሪክና  የአገር ነጻነት አለ። የፖለቲካ ሽኩቻና የጭፍን ጥላቻ ውጥቅጥ፣…. የሰላም  እጦትና የቀውስ አዙሪት፣ የጨዋነትና የተስፋ ምድር፣ የድህነትና የረሃብም አገር አለ። አብዛኛው ነገር ቅይጥ ነው።
ከአንድ ሰው የትናንት ውሎና አዳር ጀምሮ፣ እስከ ረዥሙ ታሪክና እስከ ሰፊው አገር፣  ቤተሰብና እድር፣ ማህበርና ፓርቲ፣.. ይብዛም ይነስ፣ የቅይጥ ታሪክ ባለቤት፣ የቅይጥ ውርስ ተቀባይ መሆኑ አይገርምም። አሳዛኝ ነው። አለመታደልም ነው።
ግን ደግሞ፤ ለአንድ አፍታ  ለአንድ ቀን መዘናጋት መጥፎ ቢሆንም፣ በዚህ ሳቢያ፣ “የተማሪነት ዋጋ” አይሰረዝም። የአስተማሪ የቁጣ ልማድ፣ ከባድ ብልሽት ቢሆንም፤ በዚህ ሰበብ፣ “የአስተማሪነትና የአዋቂነት ክብር” አይደመሰስም። ፖሊስ ጣቢያው፣ አላግባብ ንጹህ ሰዎችን ቢያንገላታና ቢያስርስ?  ራሱ መርማሪና ከሳሽ፣ ራሱም ፈራጅ፣ እንዳሻው ፈላጭ ለመሆን ሲቃጣውስ?
በስንፍናና  በሙያ እጥረት፣ በስነምግባር ድክመትና ከዚያም አልፎ በክፍት ሳቢያ፣ ወንጀልን ባይከለከል፣ አጥፊዎችን ለህግና ለዳኝነት ባያቀርብስ? አገሬው የነውጠኞች መፈንጫ እየሆነ፣ በሰላም ወጥቶ መግባት ይጠፋል።
እንዲህም ሆኖ፤ የህግን ፋይዳና የህግ አስከባሪዎችን ጠቃሚነት፣ የፖሊስ ጣቢያንና የፍ/ቤትን አስፈላጊነት የሚያስክድ ሊሆንም አይችልም፤ ሊሆን አይገባውም። መፍትሄም አይሆንም።  ይልቅስ፣  የትናንት ስህተቶችና ጥፋቶች በጣም መጥፎ የመሆናቸውን ያህል፤ ከትናንት የምናገኛቸው አገርና መንግስት፣ ህግና ስርዓት፣ ትልቅ ፋዳ እንዳላቸው መገንዘብ ነው መፍትሔው።  
አገር እንደዘበት አይገነባምና። ትናንት የተገነባውን አገር ካከበርንና ከወደድን ብቻ ነው፤ ወደፊት አገርን ማሻሻልና ማደግ የምንችለው። በተቃራኒውስ?
ትናንት የተሰራና የተገነባ ነገር ሁሉ፣ ጉድለትና እንከን ስለማያጣው፣ ይህን መጥፎ ገጽታ ከማስተካከል ይልቅ፣ ትናንትን በጭፍን ይጠላሉ። ለማፍረስ ይጣደፋሉ።
“ትናንት የነበረ ሁሉ ይደምሰስ!”
“ትምህርት ቤትና ፍርድ ቤት ይውደሙ!”
“የተፃፈ ህግና የስራ መመሪያ፣ የእስር ቅጣትና ፖሊስ ጣቢያ፣ ይጥፋ፤ ይቃጠሉ።”
“አገርና መንግስት ይፍረሱ” የሚል ቅዠት ውስጥ መዘፈቅ፣ መፍትሄ ይሆናል? ይሄ፣ ትናንትን በጭፍን የመጥላት አባዜ፣ የስንፍናና የክፋት አዙሪት ነው።
ይህም ብቻ አይደለም። የዚህ ተቃራኒ ጭፍንነትም አለ። “ትናንት” እንደ መነሻ ጥሩ መንደርደሪያ ሳይሆን፣ እንደ ወጥመድ የኋሊት የሚያስቀር የእስር ሰንሰለት እንዲሆን እናደርገዋለን። እንዴት?
ከትናንት የተገኙ መልካም ነገሮችን ለይቶ መገንዘብና መውደድ፣ ማክበርና ማሳደግ፤ ነው ቀናው መንገድ። መጥፎ ነገሮችን ደግሞ እንደየክብደታቸው አመዛዝኖ፣ የአቅሙን ያህል ለማሻሻል፤  በሚያዋጣና በሚያዛልቅ መፍትሄ ችግሮችን ለማቃለልና ብልሽቶችን ለማስወገድ መትጋት ነው ብልህነት። ከዚህ ይልቅ፤  ጭፍንነት ሲጠናወተውስ?
“ትናንት ይውደም” የሚሉ ሰነፍና ክፉ ሰዎችን ለመቃረን ብቻ፣ ሌላ የስንፍናና የክፋት አዘቅት ውስጥ ይገባል።  “ትናንት፣ እንከን የለሽ፣ እፁብ ድንቅ፣ ንፁህ ፈጹም ነበር” የሚል መፈክር ያመጣል።
አንዱ፣ “የትናንት ጭፍን ጠላት”፣ ሌላኛው “የትናንት ጭፍን ምርኮኛ” ሆነው፤  ቦታ ያጣብባሉ።
አንዱ፤ “ትናንት፣ የእዳ ውርስ፣ የመከራ ሰንሰለት ነው” ይላል።
ሌላኛው ፤ “ትናንት ውድ የስጦታ ቅርስ፣ የነገ ስንቅ ነው”  ይላል።

Read 6398 times