Saturday, 02 January 2021 14:01

ፍላሎት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

    --ግራ ቀኝ እጁን በካቴና ታስሮ የተረከቡት የደህንንት ሰዎች፣ እውነተኛ የግንቦት ሰባት አባል ነበር የመሰላቸው። ምንም በማያውቀው ነገር ከታሰረበት ቀን ጀምሮ በየእለቱ ከሁለት ወር በላይ ልብሱን አስወልቀው እውነቱን አውጣ እያሉ ሞሽልቀው ገረፉት፡፡ እሱ ግን በመረብ ኳስ ጨዋታ ከተዋወቃቸው ጓደኞቹ  በስተቀር አንድም የፖለቲከኛ ሰው ስም ጠርቶ ማጋለጥ አልቻለም፡፡ በተፈጸመበት ሁለት ወር ተከታታይ ግርፋት መላ ሰውነቱ ተልቶ ሸተተ፡፡ የታሰረበትን ምክንያት አንድም ሰው ሳይጠይቀው፣ ፍርድ ቤትም ሳይቀርብ አራት ዓመት ታስሮ ተለቀቀ፡፡
እሱ ሲታሰር የአምስት ወር ነፍሰጡር የነበረችውን ፍቅረኛውን ወደ አድዋ አክስቷ ቤት መሄዷን ወንድ ልጅም መገላገሏን ሰምቷል፡፡ ያለ ፍርድ አራት አመት በእስር ቤት ሲማቅቅ ቆይቶ ሲፈታ፣ ፍቅረኛውንም ልጁንም ፤ማግኘት አልቻለም፡፡ ከአባቱ ቤት ሲመለስ የፍቅረኛውን ፎቶ ይዞ የሞተ ያህል ወር ሙሉ ቤቱን ዘግቶ አለቀሰ፤ ከልቡም አዘነ፡፡ በልጃቸው ሁኔታ ግራ የተጋቡት አባቱ፤ ቀበሌ 07፣ በ250 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ አዲስ ቤት ሰርተው ሰጡትና ከወንድ ጋር መኖር ጀመረ፡፡
ይሁን እንጂ ቆንጆና ህፃን ባየ ቁጥር ይንሰፈሰፋል፡፡ የውስጥ በደሉን የማያውቁት ጓደኞቹ፣ “ቆንጆ አይቶ የማያሳልፍ ዛር አለበት” እያሉ ያሾፉበታል፡፡ በእስር ቤት ቆይታው የልብስ ስፌት ስራ ተምሮ ስለነበር ካንዱ የብትን ጨርቅ መሸጫ ሱቅ ተጠግቶ፣ ልብስ እየሰፋ መተዳደር ጀመረ፡፡ የልብስ ስፌት መኪና ለመግዛትና  ለመነሻ የሚሆን ካፒታል ስላስፈለገው ነበር የአባቱን ቤት በባንክ ሲያስዝ፣ ለገ/ስላሴ ሃያ ሺ ብር ጉቦ የከፈለው፡፡
ሞጌው ሲወጣና ሲገባ እየየ እያለ ቢያስቸግራቸው አባቱ እግሩ ላይ ወድቀው የፍቅረኛውን ፎቶ ቀሙትና አርፎ ስራውን እንዲሰራ ቃል አስገቡት፡፡ እንኳን ሴት ወንድ በቁሙ የሚያሸና የነበረው ጀግና፣ ሁሉን ነገር ትቶ የአባቱን ቃል አክብሮ፣ የሆዱን በሆዱ አድርጎ መኖሩን ቀጠለ፡፡
የአንችናሉ የአረቄ ደንበኛ ከሆነ በኋላ በዝምታው ውስጥ አንዳች የሆነ በቀል አርግዞ እንደሚኖር ራሷ አንችናሉ ትጠራጠር ነበር፡፡ ምክንያቱም አልፎ ወደ ቤቷ በመጣ ቁጥር አዝማሪ ይዞ መጣና የውስጥ ብሶትን የሚገልፁ ግጥሞች ሲገጥም ያመሻል፡፡ በግጥሞቹ ውስጥ አንዳች የታመቀ ፍላጎት እንዳለበት አፍ አውጥታ ባትነግረውም ገምታ ነበር፡፡
ሞጌው ወረታው አንችናሉን ለውሽምነት የጠየቃት እንደ ፍቅረኛው ቆንጆ ሆና ስላገኛት ነበር፡፡ ነገር ግን እሺ አላለችውም። ምክንያቱም ያው የድሮ ስም ስላለ፣ የእሱ ናት ከተባለ ወደ ቤቷ ዝር የሚል አረቂ ጠጭ አይኖርም ብላ ሰግታ ነው፡፡ እሱ ግን ከአባቱ መሃላ በኋላ፣ እንኳን ዱላ ሃይለ ቃልም ተናግሮ አያውቅም፡፡ ውሽምነቷን እምቢ ብትለውም የአረቂ ደንበኝነቱ ግን አላቋረጠም፡፡ እንዲያውም ሳይነጋገሩ የሚተዛዘኑ --ጓደኛሞች ሆኑ፡፡ ወደ ቤቷ በመጣ ቁጥር ሲኖረው ከፍሎ፣ ሲያጣ ደግሞ ዱቤ ይጠጣል፡፡ ገንዘብ በኪሱ ካለው ቸር ነው፤ ከበር መልስ የሚጋብዝ፡፡
የህጻኑ ለቅሶ ከገባበት የሀሳብ ሰመመን መለሰውና ወተት ፍለጋ ባይኑ አማተረ፡፡ አንችናሉ መረጋጋት ጀምራ ስለነበር ወተቱ ያለበትን ቦታ ባይኗ አመለከተችው፡፡
“ለምን የኋላውን በር ሳትዘጊ ተውሽው?”
“ሮንዶች ባጋጣሚ ሰምተው በዋናው በር ሊገቡ ሲታገሉ በኋላው ዞሬ ለማምለጥ የዘየድሁት ዘዴ ነበር፡፡ የሞኝ መላ እንጂ፡፡… ግን ለምን እንዲህ እስከደማ መታኸኝ? ለምን እንደዚህ ጨከንክብኝ? እንዴትስ መጣህ?; አፏን እየጠራረገች አከታትላ ጠየቀችው፡፡
“ህፃኑን ብቻ ሳይሆን እኔንም አትምሪኝም ብዬ ስለሰጋሁ ነው የመታሁሽ፡፡ ወደዚህ ያመጣኝ ግን የለም ያልሽው የዚህ ህፃን አምላክ ነው፡፡ ይህን እንቦቃቅላ ጨቅላ ከመቀሰፍ፤ አንችን ከእድሜ ልክ እስር ሊያድናችሁ ነው አምላክ ባክኖ ያመጣኝ። ህፃናትን ከፊትም ከኋላም ሆኖ ከአደጋ የሚከላከል ጠባቂ መልአክ ስለአላቸው ነው በሩን ከፍተሽ እንድትተይው ያደረገሽ፡፡ ከገባሽ ይህ የእሱ ስራ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ዘዴ የዘየድሽ ሰው ጠፍተቶሽ አይመስለኝም፡፡”
“እኔስ በልጅነቴ ኤደል እናቴን፣ አባቴን፣ እህቴን አጥቼ ብቻዬን የቀረሁት! እኔስ ህፃን አልነበርኩም? ለምን ለእኔስ ፈትኖ አልደረሰልኝም? እኔስ የእሱ ፍጡር አይደለሁም? ለምን ለእኔ ጠባቂ መላክ የለኝም?”
“አትሳሳች፣ አምላካችን ትእግስተኛ አምላክ ነው፡፡ እንደ እኛ ድንደ ሰዎች  ችኩል አይደለም፡፡”
በሃይል ተነፈሰና ወደ ጠቆመችው አቅጣጫ ሄዶ ወተቱን “ቅመሽው!” አላት፡፡
“ለምን? መርዝ አርጋበታለች ብለህ ነው?” ቀመሰችለት፡፡
“በዚህ ጎራዴ መሰል ጩቤ ጨክነሽ ልታርጅውም አልነበር”
“የህፃኑ ሞት ለእኔ ምኔም አይደል፡፡ ዋናው ከሞቱ በኋላ በገ/ስላሴ ላይ ልፈጽም ያሰብኩት የበቀል ቅጣት ነበር፡፡”
“ምንድን ነበር ያሰብሽው?”
“አሁንማ እድሜ ላንተ እንጂ አበላሽተኸዋል፤ ምን ዋጋ አለው?”
“ከተስማማን ህፃናቱ ሳይሞቱ እሱን መበቀል ይቻላል”
“እሱ ተራ ሞት መሞት የለበትም፤ በምድር ተንገላቶ አይሞቱ ሞት ሞቶ ነው መቀበር ያለበት፡፡”
“ለማንኛውም ይህ ሚስጢር ከአንችና ከእኔ እንዳያልፍ፡፡”
(ከጌጡ በላቸው "ፍላሎት" ልብወለድ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 2015 times