Saturday, 02 January 2021 14:16

እኛ ጦርነቱ ውስጥ አልገባንም፤ ከኋላ ደጀኑ ጋር ነበር የምንሄደው

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 አስፈሪውን በሰው ላይ የደረሰውን ነገር የማየት ጥልቅ ፍላጐት ነበረኝ ከ350 በላይ ቤተሰቦች ከጭንቀት እፎይ ብለዋል

         ህወሃት በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ፤ መንግስት በጀመረው የህግ ማስከበር ዘመቻ  ወደ ግንባር ተጉዘው ከዘገቡ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር ጋዜጠኛ ሀይለ ሚካኤል ዴቢሳ፤  በግንባር ከ25 ቀናት በላይ ቆይታ ያደረገው ጋዜጠኛ ሀይለ ሚካኤል ዴቢሳ፤ የሙያ ሀላፊነቱን ከመወጣት ጎን ለጎን በርካታ ቤተሰቦችን ከጭንቀት ያሳረፈ ተግባር አከናውኗል፡፡ እንዴት? በቆይታው ያየውን፣ የታዘበውንና የገረመውን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ አውግቷታል። እነሆ፡-

               ወደ ግንባር የተጓዝከው በፍላጎት ነው ወይስ ተመድበህ?
መጀመሪያ ዋና አዘጋጁ “መሄድ ትፈልጋህ ወይ?” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ በሙሉ ፍላጎት “አዎ እሄዳለሁ” አልኩኝ፡፡ ለምን ፍላጎት አደረብኝ መሰለሽ… ገና ጋዜጠኛም ሳልሆን ከማያቸው ነገሮች ተነስቼ ወደፊት ጋዜጠኛ ከሆንኩኝ፣ እንደዚህ አይነት ቦታዎች ላይ ሄጄ ብዘግብ እያልኩ  እመኝ ነበር።
ምን አይነት ነገሮች ነበሩ እንዲህ እንድታስብ ያደረጉህ?
ገና ልጅ ሆኜ የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት፣  እንዲሁም የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትን እከታተል ነበር፡፡ እነዚህን እየሰማሁ እና በተለያዩ ሚዲያዎች እያየሁ በማደጌ ጋዜጠኛም ከሆንኩ በኋላ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ተገኝቼ ብዘግብ ብዬ እመኝ ነበረ። “ወደ ግንባር ትሄዳለህ ወይ?” ተብዬ ስጠየቅ፣ ይህን ፍላጎቴን ያሳካሁ ስለመሰለኝ  በደስታ ተስማማሁ።
እሺ ካልኩኝ በኋላ ግን ሁለት አይነት ስሜት ልቤን ይከፍለው ጀመር። አንደኛው የልጅነት ህልሜ ተሳካ የሚል የደስታ ስሜት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፍፁም ፍርሃት ነበር። ፍርሃቱ የመጣው ከየት መሰለሺ… ወደ ግንባር  ሄጄ ለመዘገብ እንዳሰብኩ ለቤተሰቤና፣ ለጓደኞቼ ስነግር  ሁሉም በጣም አዘኑ። “መሄድ የለብህም፣ ብትሞትስ፣ መቅረት አለብህ” የሚሉ በዙ። ሆኖም  በሁለቱ ሀሳብ ውስጥ ስዋልል ከቆየሁ በኋላ መሄድ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ነገሩ ጥቅምት 24 ተከስቶ እኔ በ26 ነው ተዘጋጅ የተባልኩት። ይህ ወቅት ውጊያው የተፋፋመበትና አስፈሪ ወቅትም ነበረ።  ተዘጋጅ ከተባልኩ በኋላ ግን ሳንሄድ ከሳምንት በላይ ቆየን። ከዚያ በኋላ ነው ድንገት ውጡ የተባልነው። የሄድነውም ወደ ራያ ግንባር ነበር። ራያ ግንባር በወቅቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረ ግንባር ነው። ግንባሩን የሚያስተባብሩት ጄነራል ባጫ ደበሌ ናቸው። ራያ ግንባር ቆቦ ሄደን ማረፊያችንን አደረግን። ግንባር እንውልና ተመልሰን ቆቦ ነበር የምናድረው።
የራያ ግንባር ጦር ሁለት መስመር አለው። አንዱ በራያ አድርጎ በግራካሶ በኩል ይሄዳል። ሁለተኛው በአላማጣ ዋጃ፣ ጥሙጋ መሆኒ ጉጉፍቱ አድርጎ ወደ መቀሌ ይገባል። እኛ በነዚህ መስመሮች ነው እየገባን እየወጣን ስንሰራ የቆየነው።
ምን ያህል ቀን ነበር ግንባር ላይ  የቆያችሁት? በቆይታችሁ ከጦር መሪዎቹ መረጃ እየተቀበሉ ማስተላለፍ ነው ወይስ ውጊያውን በአይን ታዩት ነበር?
እንግዲህ ከአዲስ አበባ ከወጣን በኋላ ለ26 ቀን ነው በአጠቃላይ የቆየነው። እኛ እንሄድ የነበረው ጦሩ ከፊት ለፊታችን የሚያስለቅቃቸው ቦታዎች ላይ ነው። ከጀርባ ነው የምንገባው። እውነት ለመናገር፤ እኔ  በሄድኩበት ጊዜ ከርቀት መድፍ ሲተኮስ እሰማ ነበር እንጂ ውጊያው ሲካሄድ በአይኔ አላየሁም። ከፊት ለፊት የሚዋጋ ሰራዊት አለ፣ ቀጥሎ የኋላ ደጀን አለ። እኛ ከኋላ ደጀኑ ጋር ነው የምንሄደው። ከዚያ ጦሩ ነፃ ባደረጋቸው ቀጠናዎች ላይ ገብተን እየሰራን እንከታተላለን፡፡
በሌላ ግንባር ጦሩ ቀድሞ መቀሌ ገብቷል። በራያ ግንባር በኩል ከተሰለፉት ውስጥ በጋዜጠኛ ደረጃ ቀድመን መቀሌ ገብተን፣ መረጃ ለህዝብ ያደረስነው እኛ ነን። ከእኛ በፊት ራያ ግንባር ላይ የነበሩ ሰዎች ጦርነቱን የማየት አጋጣሚ ነበራቸው። ከባድ መሳሪያ የተተኩሶባቸው አሉ። እኛ በደረስን ጊዜ የከባድ መሳሪያ ድምፅን ይሰማናል እንጂ ጦርነቱ ውስጥ አልገባንም።
ወደ ግንባር ከሄድክ በኋላ ሁኔታውን ስታይ ባልመጣሁ በቀረብኝ አልክ ወይስ በወኔ ተሞላህ…?
እንደነገርኩሽ፤ ቤተሰብና ጓደኞቼ “ባትሄድ ጥሩ ነው፤ ችግር ሊገጥምህ ይችላል” እያሉኝ ስለነበር… ደንግጬና ተረብሼ ነበር። እዛ ከሄድኩኝ በኋላ ግን እንኳን ፍርሃት ሊሰማኝ ጭራሽ ያልተፈቀደ ቦታ ድረስ እየገባሁ አስቸግር ነበር። በተደጋጋሚም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኛል። ያለ ወታደር የማይኬድበት ቦታ ሁሉ ርቄ እሄድ ነበር። ለምን መሰለሽ? ይሄ ነገር ታሪክ ነው። በታሪክ አጋጣሚ እዚህ ቦታ ላይ ተገኝቻለሁ፤ ብዙ ነገሮችን የማየትና በውስጤ የማስቀረት ጉጉቴ እየጨመረ መጣ። ቦታው ደግሞ የጦር ቀጠና በመሆኑ ብዙ ቦምብ የተጠመደበትና ገና ያልፀዳ ነው። እኔ ግን በነዚህ ቦታዎች እየሄድኩ ነገሮችን፣ ጦርነቱ ጥሏቸው ያለፈውን አሻራዎች የማየት ጥልቅ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በዚህም የተነሳ በቦታው ላይ የነበሩ ሃላፊዎች “የምንልህን ካልሰማህ አትሰራም፤ ወደ አዲስ አበባ እንመልስሃለን” እስከ ማለት ደርሰው ነበር። አስፈሪውን በሰው ላይ የደረሰውን ነገር የማየት ፍላጎት ስለነበረኝ ነው ገፍቼ እሄድ የነበረው። ምንም አይነት ፍርሃት በውስጤ አልነበረም።
ተሳካልህ ታዲያ… ምን ተመለከትክ?
እኔ የሰው አስክሬን አይቼ የማውቀው በሳጥን ውስጥ  ነው። እዛ ቦታ ላይ የወታደር  አስክሬን በአሞራ ሲበላ አይቻለሁ፡፡ የተቆረጠ እጅ፣ እግር፣ ብቻ ምን ልበልሽ…. በጣም ያሳዝናል … ይሰቀጥጣል። በአንድ በኩል ወታደር ለሀገሩ ምን ማለት እንደሆነ በጥልቀት ተገንዝቤ ተደምሜአለሁ፡፡ በሌላ በኩል፤ “ይመጣል ይመለሳል” ብለው የሚጠብቁትን ልጆቹን፣ ሚስቱን፣ እናቱን፣ አባቱን እያሰብኩ….እንባ ይተናነቀኛል። ይሄ በጣም በጣም የተፈተንኩበት አጋጣሚ ነው።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን፣ በአንተ አማካኝነት ብዙ ወላጆችንም ከጭንቀት እፎይ ብለዋል፡፡ ትልቅ ስራ ነው የሰራኸው፡፡ ግን እንዴት  ሃሳቡ መጣልህ?
በጦር ግንባሩ ዘጠኝ ወይም አስር ቀን ከቆየን በኋላ ነው መቀሌ የገባነው። ቅድም እንደነገርኩሽ፤ መቀሌ ከተማ በመግባት የመጀመሪያዎቹ እኛ ነን፡፡ እዛ ከገባን በኋላ ወታደሩ መቀሌን እንዳልተቆጣጠረ ተደርጎ በህውሃት በኩል ባሉ ሚዲያዎች ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ነበር፡፡ ይህንን ለህዝብ ማረጋገጥ ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ህዝቡ እየተደነጋገረ ነበረ፡፡ የመጀመሪያው ትኩረታችን መከላከያ ሰራዊት መቀሌን መቆጣጠሩን የሚያሳይ ዘገባ መስራት ነበር፡፡ እሱን ዘገባ ከሰራሁ በኋላ በቀጥታ ወደ ዩኒቨርስቲው ሄድኩ፡፡
ለምን? ወደ ዩኒቨርስቲው ለመሄድ ምን አነሳሳህ?
አንደኛ ዩኒቨርስቲ ከተለያዩ ማህበረሰቦችና አካባቢዎች የሄዱ ተማሪዎች የሚገኙበት ነው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ንፁሃን ናቸው፤ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ነው የቆዩት፣ ደህንነታቸውን ለቤተሰብ የሚያሳውቁበት ምንም አይነት መንገድ አልነበራቸውም። ግንኙነታቸው ተቋርጧል። በዚህ ስንቱ ቤተሰብ ሊጨነቅና ሊረበሽ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ እኔ አንድ ወይም ሁለት ቀን ስልኬ ዝግ ሆኖ፣ ምን ያህል ቤተሰቤ  ሲጨነቅ እንደነበር አውቃለሁ። እነዚህ ተማሪዎች ደግሞ ከአንድ ወር በላይ ሆኗቸዋል፤ ከቤተሰብ ሳይገናኙ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ አንድ ነገር መስራት አለብን በሚል መጀመሪያ ዋናው ካምፓስ “አሪድ” ሄድን። የዜና ዘገባ ሰራን። ዜናውን ከላኩኝ በኋላ በቂ ስላልነበረ ተመልሰን ሄድን፡፡ እዛ መኖሬን የሚያውቁ የተማሪ ቤተሰቦች “ልጄን ልጄን” እያሉ መጠየቅ ሲጀምሩ፣ አንዲት ተማሪን ለመፈለግ አይደር ካምፓስ ሄድኩኝ። ከዚያ ተማሪዎቹን ስመለከት በጣም ያሳዝናሉ። መጀመሪያ አይደር ካምፓስ የገባሁት በሁለት ጠባቂዎች ታጅቤ ያለ ካሜራ ነበር።  ምክንያቱም ቦታው ገና አልፀዳም፣ ብዙ አስፈሪ ነገሮች በከተማው ውስጥ አሉ፡፡ እኔ ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ፊት ለፊት የምታይ ጋዜጠኛ ስለሆንኩና በቀላሉ ስለምለይ የጥቃት ኢላማ ልሆን እችላለሁ የሚል ስጋት ነበረኝ። በሌላ በኩል፤ የህውሃት ሃይሎች ሲቪል ለብሰው ከማህበረሰቡ ጋር ተመሳስለው ይንቀሳቀሳሉ የሚባል ነገር በስፋት ይነገር ነበር። በዚህ ሁሉ ፍርሃት ውስጥ ነው አይደር ካምፓስ የገባሁት። እንደገባሁ ሶስት አይነት ተማሪዎች ነው ያኘሁት።
አንደኛ የህክምና ተማሪዎች፣ ሁለተኛ የጤና ሳይንስ ተማሪዎች (ተመራቂዎች ናቸው)፣ ሶስተኛ ደግሞ ሰብ ስፔሻላይዝ ለማድረግ የገቡ ዶክተር ተማሪዎች ናቸው። እነዚህ ዶክተሮች ውጪ ቤት ተከራይተው እየተመላለሱ፣ እየተማሩ የሚያክሙ ናቸው። ያሉበትን ሁኔታ ያሳዝን ነበር  ቢበዛ  8 ተማሪ በሚይዝ ትንሽ ክፍል ውስጥ አስራ ምናምን ሆነው ነበር ያገኘኋቸው። በዚያ ላይ የሚለበስ ነገር የላቸውም፡፡ እነዚህ ለሀገራቸው ስንት አበርክቶ ያላቸው ሀኪሞቻችንን፣ በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሳያቸው ልቤ  ክፉኛ ተረብሿል።
ከነዚህ ሀኪሞች መካከል ህጻናት ልጆች ያሏቸው ሁሉ አሉ። ስለዚህ ቢያንስ ለቤተሰቦቻቸው በስልክም ቢሆን መኖራቸውን ማሳወቅ አለብኝ ብዬ፣ “ቶሎ ቶሎ ብላችሁ የእናንተን ስምና የቤተሰቦቻችሁን ስልክ ቁጥር ጻፉልኝ” አልኳቸው። ከዛ ወጣሁና ወደ ህክምና ተማሪዎች ሄድኩኝ፡፡  የጤና ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎችም አሉ፤ በብዛት ሴቶች ናቸው። በጣም ነው ተጨንቀው ነበር። ስለዚህ የእነሱንም ቤተሰቦች ስልክ ተቀብዬ፣ ቤተሰብ እንዲያምነኝ ከሶስቱም ቡድን ጋር አብሬ ፎቶ ተነስቼ ተለያየን። ኢንተርኔት ማግኘት የምችለው ከመቀሌ 220 ኪ.ሜ ወደ ራያ አላማጣ ቆቦ መጥቼ ነው።  የዛን ቀን መደበኛ ስራዬን ሰርቼ የጨረስኩት ትዝ ይለኛል.. ከምሽቱ 3፡00 ላይ ነበር፡፡  ከዚያ በኋላ ከ3፡00-5፡00 … ስራዬ ስልክ መደወል ሆነ።
ባልሳሳት ተማሪዎቹ 350 ያህል ናቸው፡፡ የዚያን ሁሉ ተማሪ ቤተሰብ ስልክ መደወልና መልዕክት መንገር አይከብድም?
በእርግጥ ተማሪዎቹ ከ 350 በላይ ናቸው፤ በሁለት ዙር ነው ያገኘኋቸው። የመጀመሪያው ዙር ተማሪዎች 200 ነበሩ። የእነዛን ተማሪዎች ቤተሰቦች ስልክ መደወል ጀመርኩ፡፡ “እከሌ እባላለሁ፤ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያለው ልጅዎ ሰላም መሆኑን ንገርልኝ ብላኝ (ብሎኝ) ነው፤ ልጅዎ ሰላም ነው” እያልኩ ከአንድ ደቂቃ ያልበለጠ  መልዕክት ነው የማስተላልፈው። ከዚህ በላይ ከሆነ ቤተሰብ ዝርዝር ሁኔታ መጠየቅና ማወቅ ይፈልጋል። እንደሱ ከሆነ ደግሞ  ለሁሉም ማዳረስ  አልችልም። ስልክ ለማያነሱ ቤተሰቦች የጽሁፍ መልዕክት ነበር የምልከው፡፡
ይህን በማደርግበት ጊዜ ካርድ አልቆብኝ በምሽት ወጥቼ ካርድ ገዝቼ እደውል ነበር። ከ40 በላይ  ለሚሆኑ ቤተሰቦች የጽሑፍ መልዕክት ልኬያለሁ። መልዕክቱን ሲያዩ መልሰው ይደውላሉ። በዚያ ምሽት ሌሊቱን ሙሉ ስልክ ሳወራ ነው ያደርኩት። የሆነ ሰዓት ላይ ግን ስልኬን አጥፍቼ መተኛት ነበረብኝ፤ ምክንያቱም እንደገና በሌሊት ለመደበኛው ስራዬ መነሳት ይጠበቅብኝ ነበር፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ መቀሌ ስሄድ አሪድ ካምፓስም ሌላውም ካምፓስ ገብቼ የተቀሩትን ተማሪዎች ቤተሰብ ስልክ እየደወልኩ መልዕክት አስተላለፍኩ።
ከ350 በላይ ቤተሰቦች በዚህ መልኩ ነበር ከጭንቀት እፎይ ያሉት። እዚህ አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውጪም ዘመድ ላላቸው በቴሌግራም መልዕክት አድርሻለሁ፤ መልሰው የደወሉም ነበሩ። ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከቤተሰብ ጋር ያልተገናኙና የሰሜን እዝ ወታደሮችን መልእክት ከመቀሌ ለቤተሰብ አድርሻለሁ። ተከዜም በሄድን ጊዜ ተከዜ ላይ የሚሰሩ የሰራተኞችን መልዕክትም አድርሻለሁ። ከውጪም ለቤተሰብ ገንዘብ ስጥልኝ ያለች አብራኝ የተማረች ልጅ ነበረች። ከጓደኞቼ ሰብስቤ 15 ሺህ ብር መቀሌ ላሉ ዘመዶቿ ሰጥቻለሁ። እሷም በሂሳብ ቁጥሬ ገንዘቡን አስገብታልኛለች። ብቻ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ።  እኔ ይህንን ሳደርግ ምንም ጠብቄ አልነበረም፤ ግን 350 ቤተሰብ፣ እህትና ወንድም አግኝቼበታለሁ። ከወላጆችና ቤተሰቦችም  ብዙ ምርቃት…. ብዙ በረከት ደርሶኛል፡፡  ደስታው በቃላት የሚገለጽ አይደለም።
የግንባር ቆይታህን በመፅሀፍ ለማውጣት አላሰብክም?
እውነት ለመናገር አስፈሪውንና የተከለከለውን ቦታ ሁሉ እየጣስኩ  እገባ የነበረው ይሄንን የታሪክ አጋጣሚ በመጽሐፍ እፅፈው ይሆናል በሚል ነው፤ እናም እግዜር ሲፈቅድ መጻፌ አይቀርም።


Read 891 times