Saturday, 09 January 2021 11:42

ኳሳችን በቲቪና በውርርድ አዳዲስ ምዕራፎችን ከፍቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

   • በደቡብ አፍሪካ የብሮድካስትና በናይጄርያ የስፖርት አወራራጅ ኩባንያዎች አጋርነት እየተካሄደ ነው፡፡ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ከ68 ሚሊዮን ዶላር         በላይ ኢንቨስት ይደረግበታል፡፡
      • ለውርርድ 140 ሚሊዮን ብር ገደማ ከዜጐች ኪስ አስወጥቷል፡፡ በስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች በኩል በዓመት እስከ 70 ሚሊዮን ብር ለመንግስት        ገቢ ሆኗል
      • የስፖርት ውርርድ በዓለም ዙርያ እስከ 3 ትሪሊዮን ዶላር ይንቀሳቀስበታል፡፡ በአፍሪካ በ27 አገራት ከ2ሺ በላይ ኩባንያዎች በሚሳተፉበት የስፖርት         ውርርድ ተጧጡፏል፡፡

           የኢትዮጵያ ከፍተኛ የክለቦች ውድድር በናይጄርያዊ የስፖርት አዋራራጅ ኩባንያ ቤትኪንግ አብይ ስያሜውን ከያዘና በግዙፍ የደቡብ አፍሪካ የብሮድካስት ኩባንያ ሱፕርሱፖርት ቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሲተላለፍ ሁለት ወራት አልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ 74ኛ ዓመቱን በያዝነው የውድድር ዘመን ላይ ያስቆጠረ ሲሆን ክለቦች በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ሲወዳደሩ ዘንድሮ ለ22ኛ ጊዜ ነው፡፡
የሊግ ውድድሩን በበላይነት እያስተዳደረ የሚገኘው ከተመሰረተ መንፈቅ ያልሞላው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሸር ካምፓኒ ነው፡፡ የሊግ ኩባንያው ስራውን እንደጀመረ የክለቦች ውድድሩን በቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስተላለፍና በአብይ ስፖንሰር ለመሰየም ወስኖ በአጋርነት ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን በጨረታ አወዳድሯል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሸር ካምፓኒ የሊጉን የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት እና አብይ ስያሜ  በ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመሸጥ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት ችሏል፡፡ ኮንትራት ስምምነቱም ለሚቀጥሉት አምስት አመታት እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በአጋርነት ለመስራት ያሸነፈው የደቡብ አፍሪካው ግዙፍ የብሮድካስት ኩባንያ መልቲ ቾይዝ MultiChoice Group (MCG) ሲሆን የሊጉን አብይ ስያሜ ሊወስድ የበቃው ደግሞ የናይጄርያው ቤትኪንግ ነው፡፡ መልቲቾይዝ የሊጉን ውድድር በዲ ኤስ ቲቪ ለማስተላለፍ ተመራጭ ሆኖ የውድድር ዘመኑ ሲቀጥል በተጨማሪ ለስልጠና፣ ለአቅም ግንባታ፣ ለፕሮዳክሽን፣ ለአየር ሰዓት ወጪ እና ለአይ ሲ ቲ መሠረተ ልማት ግንባታ ከ45 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የኢትዮጵያን ኳስ ይደግፋል ተብሏል፡፡  በአጠቃላይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ68 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ መልቲቾይዝ  በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ኢንቨስት ማድረጉ ነው የተገለፀው። የሀገሪቱን ስፖርት ደረጃ ለማሻሻል በታዳጊ ወጣቶች ላይ፣ የዳኞች እና አሠልጣኞች አቅም ግንባታ፣ ከስታዲም አካባቢ ፀጥታ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግም የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ሱፕር ስፖርት የኢትዮጵያን የክለብ እግር ኳስ ከዛምቢያ እና ከደቡብ አፍሪካ ሊጎች በሚስተካከል ደረጃ  ሽፋን እየሰጠው ይገኛል፡፡ የስርጭት ሽፋኑ በማልው የሰብሰሃራን አፍሪካ አገራት እና በአህጉሪቱ አጎራባች ደሴቶች የሚደርስ ሲሆን የኢትዮጵያን ስፖርት ለማስተዋወቅ አመቺ መድረክ እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡
የመልቲቾይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ካልቮ ማዌላ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው  በወቅቱ ሲናገሩ ሱፐር ስፖርት በአፍሪካ ግንባር ቀደም የብሮድካስት ኩባንያ እንደሆነና በሚሰጠው የስርጭት ሽፋን በአህጉሪቱና በአጓራባች ስፍራዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እየተመለከቱ መሆናቸውን አስቀድመው ጠቅሰዋል፡፡ በብሮድካስት ኩባንያ በሚሰራጭ  ይዘት ላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ መጨመራችን እድገት ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው ፤ ሽርክናው ከመላ አህጉሪቱ የኳስ አድናቂዎችን በመሳብ የላቀ እይታን ይፈጥራል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬርሊግ ሊቀመንበር መቶ አለቃ ፈቃደ አዘዘ በበኩላቸው የሊግ ውድድሩን ደረጃ ለማሳደግ እና በአገር አቀፍ ደረጃ ተሰጥኦ ያላቸውን ለማፍራት ከትክክለኛ አጋሮች  ጋር መስራት አስፈላጊና አስተዋፅኦውም ከፍ ያለ ማስገንዘባቸው ተወስቷል፡፡ "ከመልቲቾይዝ ጋር የተደረገው ስምምነት  ለሊጉ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ ለተጫዋቾች፣ ለኢንዱስትሪው ብሩህ የወደፊት እድል የሚፈጥር እና የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደ ዓለም የሚያቀራርብ ነው።" በማለትም መቶ አለቃ ፈቀደ ተናግረዋል፡፡በኢትዮጵያ ለሚገኙ ደንበኞቻቸው  አስደሳች ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው አስተያየት የሰጡት ደግሞ የመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ዋና አስፈፃሚ ገሊላ ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ የስፖርት አድናቂዎች አገልግሎትና ምርቶቻቸውን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ እንከን የለሽ ተሞክሮ የምናገኝበት ነውም ብለዋል፡፡ መልቲቾይስ እና የኢትዮጵያ ፕሪሚዬርሊግ ሼር ካምፓኒ ባደረጉት ስምምነት መሰረት  ሱፕር ስፖርት ለኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ ስርጭቶችን በማዘጋጀት እና በማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የተለያዩ ተግባራት እንዲከናወኑ በማብቃት የሚሰራ ይሆናል፡፡
መልቲቾይዝ ግሩፕ በስሩ ግዙፉን የደቡብ አፍሪካ የብሮድካስት ኩባንያ  መልቲቾይዝ ደቡብ አፍሪካን፤ መልቲቾይዝ አፍሪካን ሆልዲንግስ፤ ሾውማክስ አፍሪካ እና ኢሬዳቶ ያቀፈ ነው፡፡ መልቲ ቾይዝ ደቡብ አፍሪካ በስሩ ሱፕር ስፖርት ኤም ኔት እና ዲኤስቲቪ የሚዲያ ሽያጭን እንደሚያንቀሳቅስ ይታወቃል፡፡ ሱፕር ስፖርት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለክፍያ-ቴሌቪዥን ተመዝጋቢዎች የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ስፖርትን አዘጋጅቶ ያሰራጫል። በአፍሪካ በስፖርት ብሮድካስት ቀዳሚም ነው። እግር ኳስ፣ ራግቢ፣ ክሪኬት፣ ቴኒስ፣ ጎልፍ፣ ሞተርስፖርት፣ ብስክሌት መንዳት፣ ቦክስ፣ ነፃ ትግል እና አትሌቲክስ በ ‹SuperSport› ቻናሎች የሚተላለፉ ስፖርቶች ሲሆኑ የዓለም ዋና ዋና የስፖርት ዝግጅቶች፤ ክስተቶች እና ሊጎች ይተላለፉበታል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሼር ካምፓኒ ከመልቲቾይዝ ጋር በፈፀመው ስምምነት በኢትዮጵያ የክለቦች ታሪክ የሊግ ውድድሩ አብይ ስያሜ ለመጀመርያ ጊዜ በውጭ ኩባንያ ስር እንዲሆን ምክንያት ነበር፡፡ የውድድር ዘመኑ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በሚል ስያሜ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ BetKing በዲጂታል ኢንተርቴይመንት እና ቴክኖሎጂ ንግድ ላይ አተኩሮ የሚሰራው በናይጄርያዋ ከተማ ሌጎስ ተቀማጭነቱን ያደረገ ኩባንያ ነው፡፡ ያለፉትን 3 ዓመታት በአፍሪካ አህጉር ላይ መንቀሳቀስ የጀመረው ቤትኪንግ በአፍሪካ ውስጥ የእግር ኳስ ሊግን በስያሜ ስፖንሰር በማድረግ ሲሰራ በአይነቱ የመጀመርያው ሲሆን ማኔጂንግ ዲያሬክተሩ አለን ማክሌነነስ "ከኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጋር በስያሜ ስፖንሰርነት ለመስራት መወሰናችን አኩርቶናል። እግር ኳስ የንግዳችን ዋና ማዕከል ነው፡፡ አዲስ የገበያ አድርሻን የፈጠረልን ሲሆን በምንወደው የእግር ኳስ እድገት ላይ የበኩላችንን አስተዋፅኦ ለማድረግ እድል የሚሰጠን ነው" ማለታቸውን ሱፕርስፖርት በድረገፁ ዘግቦታል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ አብይ ስፖንሰር ቤትኪንግ በናይጄርያ የስፖርት ውርርድ ኢንዱስትሪ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል፡፡ ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሆኪ፤ ክሪኬት፤ ቴኒስ እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች አወራራጅነትም የሚሰራው ኩባንያው በቲቪዎቻቸው ውድድሮችን የሚያሳዩ  የስፖርት ውርርድ ሱቆችን በማደራጀት እየሰራ ነው፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 13 የኢትዮጵያ ክለቦች እየተወዳደሩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ሃድያ ሆሳና፤ ፋሲል ከነማ፤ ወልቅጤ፤ ኢትዮጵያ ቡና፤ ባህርዳር ከነማ፤ ሰበታ፤ ድሬደዋ ከነማ፤ አዳም ከነማ፤ ወላይታ ዲቻ፤ ሃዋሳ ከነማ፤ ሲዳማ ቡና እና አባ ጅፋር ናቸው። የውድድር ዘመኑ አምስተኛና ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲካሄዱ በ5 ጨዋታዎች ባስመዘገበው 13 ነጥብና 6 የግብ ክፍያ ሃድያ ሆሳና መሪነቱን ይዟል፡፡ እያንዳንዳቸው 6 ጨዋታዎችን ያደረጉት ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ በእኩል 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሶስትኛ ደረጃን ሲይዙ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ5 ጨዋታዎች 9 ነጥብ እንዲሁም ወልቂጤ ከነማ በ6 ጨዋታዎች በእኩል 9 ነጥብ አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል።  በሊጉ የመጀመርያ ሳምንት ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተካሄዱ ጨዋታዎች ላይ የኮቪድ 19 ህጎችን በመጣስ የሊጉ ሼር ኩባንያ የጤና ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ ቀርቦበት ነበር፡፡ ከዚያን በኋላ የሊጉ ውድድሮች ያለተመልካች በባዶ ስታድዬም እንዲቀጥሉ የተደረገ ሲሆን ከአዲስ አበባ ስታድዬም ባሻገር የባህርዳርና የጅማ ስታድዬሞች የውድድር ዘመኑን ለማካሄድ ተመራጮች ሆነዋል፡፡ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግን በሱፕር ስፖርት ቀጥታ ስርጭት ግን መከታተል ይቻላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱፕር ስፖርት እና ቤቲንግ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ አዳዲስ ምዕራፎችን በመክፈት መግባታቸው በስፖርቱ እድገት ላይ  አስተዋፅኦ ቢኖረውም ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች መኖራቸውን ማስተዋል ይገባል፡፡ በተለይ በአገር አቀፍ፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የስፖርት ውርርዶች የቲቪ እና የኦን ላይን ስርጭት የሚካሄደው የስፖርት ውርርድ በሁለቱ ኩባያዎች እየተባባሰ ሄዶ በስፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ማህበረሰባዊ ተፅእኖዎችን ሊፈጥር እንደሚችል አስተያየቶች እየተሰጡ ናቸው፡፡ በዓለም ታላላቅ የእግር ኳስና ሌሎች የስፖርት  ውድድሮች በተለይ ደግሞ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ላይ ባተኮረ ተመልካችነት ለአህጉሪቱ ስፖርት እድገት ትኩረት ነፍጓል የተባለው የአፍሪካ ወጣት ትውልድ አሁን ደግሞ በስፖርት ውርርድ በመጠመድ ለቁማር ሱስ እንዲሁም ለስፖርተኛነት ፍላጎቱን በማጣት ተጠቂ እየሆነ ይገኛል። የስፖርት ውርርድ ለተለያያዩ ማህበራዊ ቀውሶች የሚያጋልጥባቸው ሁኔታዎች እየበዙ መሄዳቸውን ብዙዎችን ያሰጋቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ  በስፖርት አወራራጅ ኩባንያ አብይ ስፖንሰር መሆኑ በተመልካች እጥረት የሚሰቃየውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ የባሰ አደጋ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ያስጨነቃቸው ጥቂት አይደሉም። በስፖንሰርሺፕ የገባው ኩባንያው የውርርድ ባህሉን በማስፋፋት የስፖርት አፍቃሪውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህልውና በማናጋትም ችግሮችን ሊፈጥር ይችላል የሚልም ጥርጣሬ አለ፡፡
የስፖርት ውርርድ በአዲስ አበባ ህጋዊ ንግድ እየሆነ ከመጣ በኋላ ከብሄራዊ ሎተሪ ፈቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የውርርድ ድርጅቶች  ከ15 በላይ  ናቸው፡፡ ብዙዎች ከ10 እስከ 20 በላይ ቅርንጫፎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመመስረት የስፖርት አፍቃሪያን ከሁለት ቡድኖች (ተፎካካሪዎች) መካካል የቱ እንደሚያሸንፍ፣በምን ያክል የጎል መጠን እንደሚረታ ፣እና የመሳሰሉ ሁነቶች ቀድመው በመገመት ብሎም ገንዘብ በማስያዝ እንዲወራረዱ እያደረጉ ናቸው፡፡ የስፖርት ውርርድ ተጫዋቾች ከ10 ብር ጀምረው  በመጫወት እስከ 500ሺ ብር ድረስ  ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ የስፖርት ውርርድን ከቁማር ጋር በማያያዝ በአፍሪካ ብዙ አገራት የሚያወግዙ ሲሆን ውርርዱን የሚያካሂዱ ድርጅቶች ግን ቁማር የሚያከናወኑ አለመሆናቸውን በመግለፅም ይሟገታሉ፡፡ በኢንዱስትሪው የሚንቀሳቀሱት አወራራጅ ድርጅቶች  እንደሚባሉና ተሳታፊ የስፖርት አፍቃሪዎች  ደግሞ “የስፖርት ውርርድ አጫዋቾች” የሚል ስያሜ እንደሚሰጣቸውም የገለፃል፡፡ ከስያሜ ባሻገር የስፖርት ውርርድ፣ የወጣቶችን እውቀት እንደሚያሰፋና ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣም በማስረዳት ኢንዱስትሪውን ለማጠናከር ያስባሉ፡፡ በቅርቡ ይህን አስመልክቶ የቀረበ አንድ ዘገባ እንዳተተው ኢትዮጵያ ውስጥ ከስፖርት ውርርድ ጋር በተያያዘ በዓመት 140 ሚሊዮን ብር ገደማ ከዜጐች ኪስ ወጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት፣ በቁማር ድርጅቶች በኩል በዓመት፣ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እያገኘ መሆኑንና ከኮሚሽን ብቻ 20 ሚሊዮን ብር መቀበሉንም አስታውቋል፡፡  
የስፖርት ውርርድ በዓለም ዙርያ እስከ 3 ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀስበት ኢንዱስትሪ ሲሆን በአፍሪካ ከ27 አገራ ትበላይ  የስፖርት ውርርድ በተጧጧፈ ሁኔታ ይካሄድባቸዋል፡፡ በአፍሪካ የሚሰሩ የስፖርት ውርርድ ተቋማት ብዛታቸው ከ2ሺ  በላይ ሲሆን በደቡብ አፍሪካ፤ ናይጄርያና ኬንያ በብዛት ይገኛሉ፡፡
የስፖርት ውርርድ ሁሉንም ማህበረሰብ ሊያሳትፍ የሚችል በስፖርት ውጤቶች ላይ በመንተራስ የሚካሄድ አዝናኝና ገቢ የሚያስገኝ ጨዋታ እንደሆነ በመግለፅም ተቋማቱ ስለ እንቅስቃሴያቸው ይከራከራሉ። የውርርድ ተጨዋቾች እና ተሳታፊዎች የስፖርት ውድድሮችን በመመልከት ከሚኖራቸው መዝናናት ባሻገር፤ በተለያዩ የመወራረጃ መስፈርቶች በሚሰጧቸው ግምቶች የገንዘብ ተሸላሚ የሚሆኑበትን እድል እንደሚፈጥርላቸውም ያስገነዝባሉ፡፡ አወራራጅ ተቋም በተለያዩ የስፖርት ውድድሮች የውርርድ ዝርዝሮችን በመግለፅ እና የሚሸልመውን ገንዘብ በማሳወቅ የሚሰራ ሲሆን አጠቃላይ አካሄዱም በህግና ስርዓት የተመራ እንዲሆን ግን ከአጋሮቻቸው ጋር በመስራት መፍጠር አለባቸው፡፡ በስፖርት የተለያዩ ሁኔታዎች በመወራረድ በህጋዊ መንገድ እየተዝናኑ በመጫወት ለሀገር የገቢ ምንጭ ከመሆኑም በላይ  የስራ እድሎችን የሚፈጥር መስክ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ የስፖርት ውርርዱን በህጋዊ መንገድ መካሄዱ በህብረተሰቡ ዘንድ ህገወጥ በሆነ መንገድ በመወራረድ የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ችግሮች ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑ ግን መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ  የሚካሄዱ የስፖርት ውርርዶች በሌሎች የአፍሪካ  አገራት ባሉበት ደረጃ ላይ አይገኝም። ለዚህም ነው የናይጄርያው ቤትኪን ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ መግባት ይህን ሁኔታ በማሻሻል ሊሰራበት የሚቻለው፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪ አፍሪካውያን ዓለም አቀፋዊ ግጥሚያዎችን ለመመልከት ኦንላይን እና የቀጥታ ቴሌቭዥ ስርጭቶችን መከታ አድርገዋል፡፡ ይህ ልምድም ብዙዎችን የአገራቸውን እግር ኳስ ስታድዬም ገብቶ ከመመልከት ይልቅ  በኦንላይን እና በቴሌቭዥን በመከታተል አተኩረዋል፡፡ ይህም የስፖርት ውርርድን እንዲያዘወትሩ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡
ኦንላይን የስፖርት ውርርዶች ከተስፋፋባቸው አገራት መካከል ኬንያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ሞሪሽየስ፤ ጋና፤ ኡጋንዳና ዛምቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የስፖርት ውርርድ በአፍሪካ ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ የተለየ ገፅታ አለው፡፡ በአውሮፓ እና በአሜሪካ አህጉራት የውርርድ ህጉ ኢንቨስተሮችን ከአገር ውጭ የሚያስገባ አይደለም፡፡ አፍሪካ ግን በስፖርት ውርርድ ብዙዎቹን ኢንቨስተምንት ከውጭ እያገኘች ነው፡፡ በአፍሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 10 የስፖርት ውርርድ  ኩባንያዎች በዓመት እስከ 37 ቢሊዮን ዶላር በኢንዱስትሪው እያንቀሳቀሱ ናቸው፡፡
በአፍሪካ ከሚንቀሳቀሱ ግዙፍ የስፖርት ኩባንያዎች መካከል በናይሮቢ ተቀማጭነቱን ያደረገው ስፖርት ፔሳ SportPesa ይጠቀሳል።  ከተመሰረተ 7 ዓመታትን ያስቆጠረው ኩባንያው፤ በታንዛኒያ ደቡብ አፍሪካ፤ ጣሊያን ፤ እንግሊዝ እና አየርላንድ ውስጥም ይንቀሳቀሳል፡፡ ስፖርትፔሳ የእንግሊዙን ክለብ ኤቨርተን ማልያ ስፖንሰር ከማድረጉም በላይ የፎርሙላ ዋንም ስፖንሰር ነው፡፡ በሌላ በኩል በናይጄርያ ግዙፉ የስፖርት ውርርድ ተቋም Bet9ja ሲሆን በወር ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚሽከረከርበት ነው፡፡

Read 1043 times