Saturday, 09 January 2021 11:51

“በትግራይ የተፈፀመው ድርጊት ሁሉ በገለልተኛ አካል መጣራት አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  • መከላከያ የወሰደው እርምጃ እጅግ የተጠናና ሳይንሳዊ ነው
 • አብዛኛው ሰው ህወኃት እንድትመለስ አይፈልግም
  • የህወኃትን አመለካከት ከነቀልን ሁሉም መስተካከሉ አይቀርም

           በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋሙን ተከትሎ በአስተዳደሩ እንዲሳተፉ ጥሪ ከቀረበላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አንዱ ኢዜማ ነው፡፡ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ከአስተዳደሩ ጋር በተደረገው ውይይቱ ተሳታፊ ሲሆን የተሰጣቸውን ሹመት ግን አልተቀበሉም።
አቶ ተክሌ ለምን ይሆን ሹመቱን ያልተቀበሉት? ትግራይ ከጦርነቱ በኋላ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ትገኛለች? ጦርነቱና ውጤቱ ምን ይመስላል? በሚሉትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አቶ ተክሌ በቀለን አነጋግሯቸዋል፡፡

            ሰሞኑን ወደ ትግራይ  አምርተው ነበር። በምን ምክንያት ነው የሄዱት?  ትግራይ ከጦርነት በኋላ ምን ትመስላለች? ህዝቡ ምን ይላል? እርሶዎ ምን ታዘቡ?
ወደ ትግራይ ያቀናነው በትግራይ ጉዳይ ላይ ለመምከር ነው፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው፤ ህውሐት ለውጡን በመቃወም እንደ ድርጅትም እንደ መንግስትም ትግራይ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ከህግ ጋር የሚቃረኑ በርካታ ጉዳዮችን ይፈፅም ስለነበር፣ በትግራይ ምናልባት ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት ነበረን። ይሄንንም ለፌደራል መንግስቱም ሆነ ለክልሉ መንግስት በተደጋጋሚ ስናሳስብ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን ከህወሃት ባህሪ አንጻር ጉዳዩ በእርቅ ሳይሆን በግጭት ሊያልቅ እንደሚችል ጠብቀን ነበር፤ ስለዚህ የትግራይን  ጉዳይ በጥብቅ ስንከታተልና ስንወያይበት ነበር የቆየነው፡፡ ያው የተሰጋው አልቀረም፤ የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ህወሃት ጥቃት በመፈፀሙ  ወደ ግጭት ተገባ፡፡ በወቅቱ እኛም እንደ ፓርቲ ከመከላከያ ጎን ነው የቆምነው፤ ጥቃቱንም በይፋ አውግዘናል፡፡ መጨረሻ ላይም  ህወሃት በለኮሰው እሳት ራሱ ተለብልቧል። በመከተልም ጊዜያዊ አስተዳደር ነው  የተቋቋመው፡፡ ይህ ጊዜያዊ አስተዳደር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ሲያቀርብ፣ እኛም  ጥሪውን ተቀብለን የሂደቱ  አካል  በመሆን፣  ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማገዝና በሂደቱ ለመሳተፍ ነበር የሄድነው፡፡
በትግራይ ምን ታዘባችሁ?
በርካታ አሳዛኝ ነገሮች ነው የታዘብነው። በእርግጥ ጦርነት ወይም ግጭት የታወቀ ነው፤ የኳስ ውርወራ ወይም ጨዋታ አይደለም፡፡ በነፍስ ወከፍ እስከ ከባድ መሳሪያዎች ይተኮሳሉ፡፡ በዚህ መሃል ሲቪል ሰዎች ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ በጦርነቱ የወደሙ ነገሮች ይሄን ያህል ናቸው ማለትም አይቻልም፡፡ በእርግጥ መከላከያ የወሰደው እርምጃ እጅግ የተጠናና ሳይንሳዊ ነው፡፡
ለምሳሌ በመቀሌ በእርምጃው የተጎዱ ሲቪል ሰዎችና ቤቶች ቢኖሩም፣ ያን ያህል ውድመት ሊባል አይችልም፡፡ በጣም የተጠና እርምጃ ነበር የተወሰደው፡፡ በጣም ጉዳት የተከሰተው ሌሎች የታጠቁ ሃይሎች በክልሉ ሲንቀሳቀሱ የነበረ በመሆኑ ነው። በተለይ የኤርትራ ሰራዊት ገብቷል ብሎ ማህበረሰቡ ያምናል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች ወይም የኤርትራ ወታደሮች  ታከው የመጡ የታጠቁ ሀይሎች ብዙ ውድመት አድርሰዋል ብሎ ህብረተሰቡ ያምናል፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ ተፈፅመዋል፡፡ ሰዎች ተገድለዋል፤ ጾታዊ ጥቃቶች ተፈፅመዋል፤ መሰረተ ልማቶች ተጎድተዋል፣ ፋብሪካዎች ተነቅለዋል፣ ለምሳሌ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣ ውቅሮ የሚገኘው ሼባ ሌዘርስ፣ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ሙሉ ለሙሉ ስራ መስራት በማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይሄን መንግስትም ያረጋገጠው ነው። አዲግራት የሚገኘው አዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ ተዘርፏል፣ የግለሰብ ፋብሪካዎችና ቤቶች ሳይቀሩ ወድመዋል፡፡ በዚህ የትግራይ ህዝብ አሁን በከፍተኛ ሀዘን ላይ ነው ያለው፤ የመጠቃት ስሜት ላይ ነው። ያም ሆኖ ከመከላከያው ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ጥሩ የሚባል ነው፡፡ ህወኃት የሚባል ድርጅት ተመልሶ እንዲመጣ አይፈልግም፤ ምክንያቱም ለዚህ ሁሉ ያበቃው ህወሃት መሆኑን ያምናል፡፡ በመሆኑም ከመከላከያ ጋር ተሰልፎ ህወኃት እንዲወድቅ አድርጓል፡፡ ግን በሰሜን ሻዕቢያ፣  በደቡብ አማራ ወይም ፌደራል መንግስት ያጠቃሃል ከሚለው የህወሃት ፕሮፓጋንዳ አንጻር፤ አሁን  በተግባር የኤርትራ ወታደሮች አጥቅተውናል የሚል የቁጭት ስሜት መኖሩን ነው ታዝበን የመጣነው፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ገብተዋል የሚለውን አለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ሲዘግቡት የነበረ ጉዳይ ነው። መንግስት ግን ግልጽ ምላሽ ሲሰጥበት አልተስተዋለም። እርስዎ የኤርትራ ወታደሮች ስለመግባታቸው ለማረጋገጥ ሞክረዋል? ማን ነው ፋብሪካዎችን የነቀለው?
መከላከያው በብዙ አውደ ውጊያዎች የተጠመደ በመሆኑ በአንድ በኩል እየተዋጋ በሌላ በኩል የፖሊስ ስራ መስራት አይችልም ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ዋናው መንስኤ ህወሃት ሲፈርስ ወይም እየፈረሰ ሲሄድ ተተክቶ ትግራይን የሚጠብቅ አካል አለመኖሩ ነው። የጉዳቱ መጠን በጣም ከፍተኛ ነው፤ የህዝቡ ስሜት በጣም የተጎዳ ነው። አሁንም በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል፡፡ የገንዘብ ችግር አለ፡፡ ቀደም ብሎ ከ600 ሺህ በላይ ህዝብ በእርዳታ የሚኖር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ነው ተጨማሪ ተረጂ የተፈጠረው፡፡ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ዝግ በመሆናቸው ህዝቡ በከፍተኛ ችግርና ሰቆቃ ውስጥ ነበር ያሳለፈው፡፡ የረሀብ አደጋም አንዣብቧል። ከዚህም በላይ ግን ሰውን የጎዳው ጥቃቱ ነው፡፡ የስነ ልቦና ስብራቱ ቀላል አይደለም፡፡ መንግስት ይሄን ጉዳይ ሊደብቀው አይገባም፡፡ ገለልተኛ የሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶችም ቢሆኑ ቦታው ድረስ ተገኝተው ማጣራት አለባቸው፡፡ የመንግሰት ስህተት ካለ፣ መንግስት ይቅርታ የሚጠይቅበት፣ ሌሎች ጥፋት የፈፀሙ ካሉ ደግሞ የሚጠየቁበትና የተዘረፈ ንብረት የሚመለስበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሚዲያውም ለዚህ መስራት አለበት ብዬ አስባለሁ፤ ካልሆነ ቅሬታዎች እየፈጠሩ ሊሄዱ ይችላሉ። ይሄ ደግሞ ለአካባቢው አለመረጋጋት የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ ህወሃትን የትግራይ ህዝብም የአማራ ህዝብም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላት ነው፡፡ ይሄን ጠላት በጋራ መንቀል ግዴታ ነው፡፡ ህውሃትን ነቅለን ምን ዓይነት ስርአት ነው የምንከተለው የሚለው ነው አሳሳቢ የሚሆነው፡፡ አሁን ህወሃትን በመንቀል ደረጃ ተሳክቷል፡፡ ህወሃት ሲነቀል ግን የትግራይ ህዝብ ስነልቦናው ደህንነቱ ሃብቱ ንብረቱ መጠበቅ ነበረበት፡፡ የአማራ ልዩ ሀይልና የአፋር ልዩ ሃይል ትግራይን እንዲጠብቅ ቢደረግ ምን ነበረበት? ለዚህ የሚሆን ህግ የፌደራል መንግስት ማመቻቸት ለምን አቃተው፡፡ ህወሃት የተወገደው በጉልበት እርምጃ ነው፤ በዚሁ የጉልበት እርምጃ ውስጥ ግን ማህበረሰቡ አለመጠበቁ በእጅጉ ያሳዝናል ያሳስባልም፡፡ የአማራ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ተከዜን  ተሻግሮ ትግራይን ቢጠብቅ፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ልዩ ክንውን ይሆን ነበር እንጂ የሚፈጠረው ችግር አልነበረም፡፡ ይሄ ቢደረግ ኖሮ ህዝቡ ባልተዘረፈ ባልተጎሳቆለም ነበር፡፡
የሚባለው ዝርፊያ በህወኃት በራሱ ተፈፅሞ ቢሆንስ?
ህወሃት ከልምዷ የኤርትራ ወታደርን ልብስ አስለብሳ ወይም የአማራ ልዩ ሀይልን ልብስ አስለብሳ ጥፋት ልታደርስ እንደምትችል መገመት አይከብድም። ነገር ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች ከዚያው ከህወሃት አስተምህሮ ስላልወጡ፣ የህዝብ ደህንነት ሳይሆን የመሬት ጉዳይ ነው የሚያሳስባቸው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀሩ የአክቲቪስት ሚና እየተጫወቱ ለህዝቡ ቁስል ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ይሄ የጦርነቱ አሳዛኝ ታሪክ ነው። አሁን ወሳኙ ነገር ጥፋቶች ደርሰዋል፤ ገለልተኛ ቡድን በአስቸኳይ ተቋቁሞ ይሄን ነገር ሊያጣራው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከመንግስት ወገን መግለጫ ባይሰጥም በአልነጃሺ ጥቃት መድረሱ በማህበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይስ ላይ መረጃ አላችሁ?
ህወሃት ጦርነቱን የሙስሊምና የክርስቲያን ለማድረግ ነበር የመጨረሻ ጥረቷ። ነገር ግን ይሄን በደንብ መጣራት አለበት፡፡ ይሄን ሁሉ ሀጢያት ህወሃት ከወሰደችው ሌላውስ ፖለቲከኛ ምን እያደረገ ነው ካልን፣ እጅግ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ እኔ ህወሃት ተነቅላ ስትወድቅ ንቃዩ ላይ ምን እንስራ የሚለው ነው እንጂ የሚያሳስበኝ፣ ያን ያህል የሚያስደስተኝ አልነበረም፡፡ አንደኛ ጦርነቱ የእርስ በእርስ ነው፡፡ በአለም ፊት እኮ የተዋረድንበት ነው፡፡ በርካታ ጀነራሎች ኮሎኔሎች ተገደሉ ሲባል እኮ አንገት  የሚያስደፋ ነው፤ ነገር ግን እነሱ የመረጡት መንገድ ስለሆነ ነው ፤ወደ አሳፋሪው ተግባር የተገባው፡፡ ያን ያህል የሚያስጨፍር አይደለም፡፡ በአክቲቪስቶችና  በሌላው ሰው ብዙም አልገረምም፤ በመንግስት ደረጃ ያሉ ሀይሎች ይሄን ሲያደርጉ ግን ያሳፍራል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ነገሩ ያን ያህል የሚያስደስት አይደለም፡፡ ስሜቱን ህወሃትን ከህዝቡ ያለመለያየት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ ሳይሆን ጦርነቱን ተከትሎ በመጡ የታጠቁ ሀይሎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል።  ይሄ ህዝብ ምን ተጨማሪ ጉዳት ያርፍበት ይሆን ብሎ ከመጨነቅ ይልቅ ያን ያህል ሆይ ሆይታ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። አጠቃላይ ህዝቡ ግን የሚያዝንበት ነው፡፡
የወልቃይት ራያ ጉዳይስ? ህዝቡ  ምን አይነት ስሜት ነው ያለው? በቀጣይስ ምን አንድምታ ይኖረዋል?
በተበላሸው የፖለቲካ እሳቤያችን እያንዳንዳችን በጭንቅላታችን የፈጠርናቸው ካርታዎችና አርማዎች አሉ፡፡ ህወሃትን ከተመለከትን የትግራይን ካርታና አርማ በየትኛውም መድረክ ላይ ጎልቶ እንዲታይ ነበር የምታደርገው። ያ አርማና ካርታ በወጣቱ ጭንቅላት እንዲሳል ነው ስታደርግ የኖረችው፡፡ እኛ በተቃራኒው ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ነች፣ ድንበርና ወሰን ለአስተዳደር እንጂ ግዛት የማካለል ጉዳይ መሆን የለበትም እያልን ስንታገል ነው የኖርነው፡፡ አሁን ግን በተቃራኒው ያለው ወገን፣ የህወሃትን ግልባጭ ነው እየተከተለ ያለው፡፡ ይሄ የፖለቲካችን ብልሽት ውጤት ነው፡፡ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ሰዎች ይሄን ቢያደርጉ አልፈርድባቸውም፡፡ ይሄ የፖለቲካችን ነፀብራቅ ነው፡፡ የበርካታ አመታት ስራ ውጤት ነው፡፡ አሁንም የህወሃትን ሞዴል ነው የምንከተለው። የማንነት ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው ብዬ አስባለሁ፤ በጥያቄዎቹ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ማንነትን መጨፍለቅ ሰላም አያመጣም፡፡ የራያን ጉዳይ ካየነው አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ኦሮሞ ነኝ፣ራያ ራዩማ ነኝ የሚሉ እምነቶች አሉ፡፡ እነዚህ እምነቶች ረጋ ተብለው ነው መፈታት ያለባቸው። ዘላቂ የህብረተሰብ ግንኙነቶች እንዲፈጠር ከፈለግን ረጋ ብለን ማየት አለብን፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አስተሳሰቦች በቤተሰብ ደረጃ በተለያየ አውድ የሚቀነቀኑ ሆነዋል። የአንድ ቤተሰብ አባላት ሳይቀር አንደኛው ትግሬ ነኝ ሌላው አማራ ነኝ፣ ሌላው ኦሮሞ ነኝ፣ ሌላው ራዩማ ነኝ  እየተባባሉ መከፋፈል ውስጥ የተገባበት ጉዳይ ስለሆነ ነገሩን በእርጋታ ማየት ያስፈልጋል። ሰከን ተብሎ ታይቶ መወሰን ያለበት ይመስለኛል። ያው የማንነት ጥያቄ አሁን ባለው ህገ መንግስቱ ተሻሽሎ በቀጥታ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው። መሬት በህገ-መንግስት የግለሰብ ካልሆነ በስተቀር የቡድኖች መፋጠጫ መሆኑ አይቀርም፡፡ እኛ እየታገልን ያለነው ዜጎችን ነፃ ለማድረግና መሬት የቡድን ንብረትነቱ ቀርቶ የእያንዳንዱ ዜጋ እንዲሆን ለማስቻል ነው፡፡ ያኔ ነው ደም አፋሳሽ እየሆነ ያለው የመሬት ይገባናል ጉዳይ አስተማማኝ እልባት የሚያገኘው። በመሬት ጉዳይ  ከመንግስት ጋር በቀጥታ ውል የሚገባው ዜጋው እንዲሆን ነው እኛ እየጣርን ያለነው፡፡ አሁን ግን የብሔር ብሔረሰቦች ነው፡፡ ስለዚህ የማንነት ጥያቄ ሲመጣ አብሮ የመሬት ጥያቄ ይመጣል፡፡ በሌላ በኩል መረዳት ያለብን ለመሬቱ ሲባል ወልቃይቶችም ራያዎችም በህወሃት ሲገደሉ ሲጨፈጨፉ እንደነበር ነው፡፡ ወልቃይቶች በከፍተኛ ደረጃ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ለ46 ዓመታት ነው የተመቱት፣ ይሄ ትክክል አልነበረም። እኛ ህወሃትን በፅናት ስንቃወም የነበረውም ለዚህ ነው፡፡ ወልቃይት ድሮ በጎንደር አስተዳደር እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ በፊትም ብአዴንና ህወሃት ናቸው የሚጣሉት እንጂ ህብረተሰቡ ሁሉንም ያውቃል። ህብረተሰቡ አብሮ ለመኖር ምንም ችግር የለበትም፡፡ አሁንም የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩን ይዞት በህግ አግባብ መመለስ ነበረበት። አሁንም የፖለቲካ ገመድ መጓተቻ ነው የሆነው፡፡ በነገራችን ላይ ብልጽግና እንደጠበቅነው ውህድ ፓርቲ  አለመሆኑን የተረዳንበት አጋጣሚ ነው እየተፈጠረ ያለው። ፖለቲከኞች እርስ በእርስ የሚዘላለፉት እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ በርካታ የተከበሩ ሀገርን በአጠቃላይ የሚያዩ እንዳሉ እናውቃለን። ነገር ግን ጥቂት የማይባሉት  ዛሬም በህወሃት ነጸብራቅ ነው እያሰቡ ያሉት፡፡  ጠ/ሚኒስትሩ የሚያወሩት ሌላ፣ አንዳንድ  የበታቾቻቸው  የሚናገሩት ሌላ እየሆነ ነው የተቸገርነው ነው፡፡
የህወሃት አመለካከት አለመጥፋቱ እንጂ እነዚህ ቦታዎች ያን ያህል ችግሩን ለመፍታት አስቸጋሪ ሆኖ አይደለም። የትግራይና የአማራ ህዝብ ደግሞ በባህልም፣ በታሪክም፣ በእምነትም፣ በቋንቋም የተቀራረበ አንድ አይነት ህዝብ ነው፡፡ ለምን ጥያቄውን በውይይት ለመፍታት እንደማይሞከር እኔ አይገባኝም፡፡ ይሄ ዝም ብሎ በጉልበት ይዣለሁ የሚባለው የህወኃት ሞዴል ነው፡፡ ጥሩ አይደለም፡፡  የወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚቴ ምን ይሰራል? ጥያቄው ከቀረበለት ቆይቷል፡፡ ለምን ምላሽ መስጠት አቃተው? እነዚህ ነገሮች አሁንም በፅናት ሊመለሱ ይገባል፡፡ የራያ ጉዳይ ቀላል ነው፡፡ ለምን ለህዝቡ ውሳኔ ሁሉንም ነገር አይተውለትም? ለምን ህዝቡን እናተራምሳለን?  የወልቃይት ጉዳይ ትንሽ ለህዝብ ውሳኔ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በጉልበት  የሚለው አያስኬድም፤ ጥሩ ውጤት አይኖረውም፡፡ “ስታጠቃኝ ነበር፤ አጠቃሁ” የሚለው አይሰራም። ይሄ የህወሃት አመለካከት ነው፡፡ ነገሩ በህግ አግባብ በፍጥነት ምላሽ ሊያገኝ ግን ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ ዛሬ ሁሉም በዚህ የመታጠሩ ጉዳይ ነገ ሊያከትም ይችላል። ይሄ ድንበር የኔ ነው የሚለው ሊለወጥ ይችላል፡፡ ትግራይ በዚህ በኩል በቀጣይ ሞዴል እንድትሆን ነው እኔ የምመኘው፡፡ አማርኛ፤ አገውኛ፣ አፋርኛና ሌሎች አጎራባች ቋንቋዎች የሚነገሩባት፤ ማንኛውም ህዝብ ሄዶ እንደ ቤቱ የሚያያት፤ ኢንቨስት የሚያደርግባት ለኢትዮጵያ መልካም አርአያ የሆነች ትግራይን ነው የምመኘው፡፡ የራሷን የውስጥ አስተዳደር ወይም ማንነቶች ያከበረች፣ ምርጥ ሞዴል የሆነች ትግራይን ነው የምመኘው፡፡  
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በአባልነት እንዲሳተፉ ተጠይቀው ፈቃደኛ አልሆኑም  ለምንድን ነው?
አዎ እንግዲህ በኢዜማ የትግራይን ጉዳይ የሚከታተሉ አባሎች ተመድበዋል። የትግራይን ጉዳይ በጣም ወሳኝ አድርገን ነው ስንከታተለው የነበረውና ለትግራይ ጉዳይ እኔ ነበርኩ የተመደብኩት። ከብልፅግና ጽ/ቤት ጥሪው ሲተላለፍ ያው በጊዜዊ አስተዳደሩ እናሳትፋለን ብለውን ነበር። በኋላም ወደ መቀሌ እንድንሄድ ጥሪ ቀረበልን። እዚህም ስብሰባ ሳይጠሩን አንድ ሁለት ቀን አለፈ። በኋላም ጊዜ አመቻችተው ስብሰባ ጠሩን። ይሄ ሲሆን አስቀድሞ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተመርጦ አልቆ ነበር። በኋላም  ዋና ስራ አስፈጻሚውን አገኘናቸው። አሰራራቸው ትክክል እንዳልሆነም በወቅቱ አስረድተናቸው ነበር። የስራ አስፈጻሚ አባላት ቦታ ተደልድሎ ማለቁን፣ ነገር ግን የአንድ ስራ አስፈጻሚ፣ አንድ የቢሮ ሃላፊ፣ ሁለት የምክትል ቢሮ ሃላፊ፣ ሶስት ቦታዎች ደግሞ በቢሮ ሀላፊ ማዕረግ የኤጀንሲ ሀላፊነት መኖራቸውንና ከእነዚህ ውስጥ እንድመርጥ ጥያቄ ቀረበልኝ። አንደኛው ከኔ ጋር የሄደ የኢዜማ ወኪል በሙያው የዳይሬክተርነት ቦታ ይገባሃል ተባለ። እሱ የሙያ ጉዳይ ስለነበር ችግር አልነበረውም ነገር ግን የእኔ በተመለከተ ፓርቲው የራሱን ሰው ይመድባል ስላቸው “አይ የደህነት ማረጋገጫዎች ያደረግነው ባንተ ላይ ነው፤ ስለዚህ አንተ መሆን አለብህ” አሉት። ነገር ግን ከፓርቲዬ መርህ አንጸር ትክክል አለመሆኑን ስለማምን ልቀበለው አልቻልኩም። ሌሎች የሹመት መመዘኛዎችም ግልጽነት የጎደላቸው በመሆናቸው አልተቀበልነውም። ሆኖም በፌደራል ደረጃ በአንዳንድ ጉዳዮች ልናግዛቸው እንደምንችል ተስማምተናል። ነገር ግን ትግራይ ለኛ ለተቃዋሚዎች አስቸጋሪ የሞት ቦታ መሆኗ አብቅቶ፣ ዛሬ “የካቢኔ አባል መሆን ትችላላችሁ” መባል ደረጃ መደረሱ ትልቅ እምርታ መሆኑ አይካድም።
ህወኃት ተመልሶ ይመጣል የሚል ግምትና እምነት አሁንም ህዝቡ ውስጥ እንዳለ ይነገራል፡፡ የመንግስት ሰራተኛውም ወደ ስራ ገበታው ለመመለስ ፈቃደኛ አልነበረም የሚባል ነገር አለ…ምን ያህል እውነት ነው?
ህወኃት  ጠንካራ መዋቅርና አደረጃጀት ያለው ድርጅት እንደሆነ እናውቃለን። በእምነት ተቋማት፣ እድር፣ እቁብ፣ ለቅሶ ሁሉም ላይ  ይገባ የነበረ ሰፊ ኔትወርክ ያለው ድርጅት ነበር። አሁንም በዚሁ ኔትዎርክ ውዥንብር ይነዛሉያስወራሉ። ነገር ግን ህወኃት እንዲመለስ ግን አብዛኛው ሰው አይፈልግም። የመንግስት ሰራተኛው ግን ስጋት ላይ ስለነበር ነው። እኔ በሄድኩበት ሰዓት በከተማው አንድም ትራፊክ ፖሊስ እንኳ አልነበረም። ለምን  ስል አብዛኛውን አባል ስላደረጉት እያዛለሁ ብሎ ስለሚፈራ ነበር። ማህበረሰቡ መከላከያ ባየ ቁጥር ደስተኛ ነው። “ጥላችሁን አትሂዱ” ነው የሚሉት፤ ነገር ግን ፖሊስ  የበቀል እርምጃ ሰለባ እሆናለሁ በሚል ስጋት ሳይሆን አይቀርም ወደኋላ ያለው። ከሰሞኑ ግን መቀሌ ከባንኮች መከፈት ጋር ተያይዞ ወደ ሙሉ እንቅስቃሴዋ ገብታለች። በርካቶች ያነጋገርኳቸው ህወሃት እንድትመለስ አይፈልጉም። ወጣቶች  በድፍረት በአደባባይ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ሲደግፉ አይቻለሁ።  የመንግስት ሰራተኛው  ግን በአብዛኛው ችግር ላይ የከረመ ነው። ሁለት ወርና ከዚያ በላይ ደመወዝ አልነበረውም፤ አባልም የሆነ አለ። መንግስት ከዚህ አንፃር በድርጊቱ እነማን ናቸው የሚጠየቁት? የማይጠየቁትስ እነማን ናቸው? የሚለውን ግልፅ ማድረግ አለበት። ይሄ ከሆነ ሰው የበለጠ በድፍረት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው ይመለሳል የሚል እምነት አለኝ።
በቀጣይ ትግራይ ምን መልክ ይኖራታል?
አሁን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ ስራዎች ከፊቱ ተደቅነዋል። አንደኛው ማረጋጋት ነው። ሌላው የተፈጸሙ ድርጊቶችና የደረሰው ጉዳት በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ መቅረብ አለበት። ትግራይን መልሶ መገንባት የሁላችንም ስራ ነው። በመላ ኢትዮጵያ ያለው የብሄርተኝነት አመለካከት ገደብ ሊኖረው  ይገባል። ይሄ በመላ ሃገሪቱ መፍትሄ ሲያገኝ ነው በትግራይም ገቢራዊ  የሚሆነው። በሌላ በኩል፤ የቀድሞ የትግራይ ም/ቤት ህጋዊ እንደመሆኑ እሱ መስሏቸው የነበሩ እና በሱ ስር ይተዳደሩ የነበሩ ነገሮች በሙሉ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር መሆን አለባቸው። ምንም ይሁን ምን ንብረትም ቢሆን ኢፈርትም ቢሆን። አለበለዚያ የመነጠቅ ስሜት ነው ህዝቡ ላይ የሚፈጥረው። ለምሳሌ ኢፈርትን ብንወስድ የትግራይ ህዝብ ምንም ላይጠቀምበት ይችላል። ነገር ግን ያንተ ነው ሲሉት ነው የኖረው። ስለዚህ እንዲነኩበት አይፈልግም። ስማቸው ያለአግባብ እንዲጠፋ አይፈልግም። ለምሳሌ ወጋገን ባንክ ላይ የተፈጸመው  የሚያሳዝን ነው። ማንም ባልሆነበት ነው ስሙ የጠፋው። ሌሎች ተቋማትም ላይ ተመሳሳይ አዝማሚያዎች ናቸው የሚታዩት። ይሄ አካሄድ ህዝቡን የማጥቃት ተደርጎ ነው እየተወሰደ ያለው። ስለዚህ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የቀድሞ መንግስት ሲያስተዳድራቸው የነበሩ ነገሮችን በሙሉ ማስተዳደር መቀጠል አለበት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትግራይ መጠበቅ አለበት። የፌደራል ሃይል ከሌለ ከክልሎች የተውጣጣ ልዩ ሃይል ሊጠብቅ ይገባል። ችግር ያለባቸው እንደ መተከል ያሉ አካባቢዎች በዚህ አይነት ሃይሎች መጠበቅ አለባቸው፡፡ የህወኃት አመለካከት  ከነቀልን በኋላ ደረጃ በደረጃ ሁሉም መስተካከሉ አይቀርም።

Read 8425 times