Saturday, 09 January 2021 12:03

እስራኤል ለብዙ ሰዎች የኮሮና ክትባት በመስጠት አለምን እየመራች ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  አፍሪካ በ3 አመታት 60 በመቶ ህዝቧን ለመከተብ አቅዳለች

             የተለያዩ የአለም አገራት ዜጎችን መከተብ በጀመሩበት በአሁኑ ወቅት፣ ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘችው እስራኤል መሆኗ ተነግሯል፡፡
እስራኤል እስከ ሳምንቱ መጀመሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ፋይዘር የተባለውን የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መስጠቷንና ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 11 በመቶ ያህል እንደሚደርስ ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ እስራኤል 11 በመቶ ያህል ሰዎችን በመከተብ ከአለማችን አገራት ብዛት ላላቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመስጠት ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ 3.49 በመቶ፣ እንግሊዝ 1.47 በመቶ ሰዎችን በመከተብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
አሜሪካ 2020 ከመጠናቀቁ በፊት ለ20 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ክትባት ለመስጠት ብታቅድም፣ ለመከተብ የቻለችው 2.78 ሚሊዮን ያህሉን ብቻ እንደሆነም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዜና ደግሞ፤ እስከ መጪዎቹ ሶስት አመታት ድረስ ከአጠቃላዩ የአፍሪካ ህዝብ ለ60 በመቶው ወይም ለ980 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የኮሮና ክትባት ለመስጠት መታቀዱንና ለዚህም 9 ቢሊዮን ዶላር  እንደሚያስፈልግ መነገሩን ሮይተርስ ዘገቧል፡፡
1.3 ቢሊዮን ያህል ህዝብ በሚኖርባት አፍሪካ እስካሁን ድረስ 2.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአውሮፓና አሜሪካ የኮሮና ክትባቶች መሰጠት ቢጀመርም በአፍሪካ አገራት ግን እስከ መጨው አመት አጋማሽ መደበኛ ክትባት ይጀመራል ተብሎ እንደማይጠበቅ የአፍሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል ከሰሞኑ የሰጠውን መግለጫ ጠቅሶ አመልክቷል፡፡

Read 8120 times