Print this page
Saturday, 09 January 2021 16:08

የአሜሪካ ም/ቤት በነውጠኞች መጥለቅለቅ ዓለምን ጉድ አሰኝቷል እነቻይና የምዕራቡን ዲሞክራሲ አብጠልጥለዋል

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(4 votes)

 ባለፈው ረቡዕ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ፣ የተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የአገሪቱን ም/ቤት ጥሰው መግባታቸውን ተከትሎ፣ በተፈጠረው ሁከትና ግርግር፤አንድ ፖሊስን ጨምሮ አምስት ሰዎች ለሞት መዳረጋቸው ታውቋል።  በነውጡ በተፈጠረው ግጭት ከ10 በላይ ፖሊሶች ቆስለው ሶስቱ ሆስፒታል እንደገቡም ነው የተገለፀው፡፡
ካፒቶል ሂል ተብሎ በሚጠራው የም/ቤቱ ህንፃ ላይ በነውጠኛ የትራምፕ ደጋፊዎች የተፈፀመውን ወረራ ተከትሎ  በተፈጠረው ግጭት   አንዲት ሴት በፖሊስ ተተኩሶባት እንደሞተች የተዘገበ ሲሆን በኋላ ላይ ደግሞ ተጨማሪ አራት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
የትራምፕ ነውጠኛ ደጋፊዎች በግንብ ተንጠልጥለውና መስተዋቶች ሰብረው ወደ ካፒቶል ሂል  በመግባት ነው። ለሰዓታት ህንፃውን ወርውረውና ተቆጣጥረው የቆዩት ተብሏል። በርካታ ንብረቶችንም ሲያወድሙ መታየታቸው ተጠቁሟል።
በወቅቱ የአገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ተሰብስበው በቀጣዩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምርጫ ውጤት ላይ በመነጋገር ላይ ሳሉ ነው በድንገት የነውጠኞቹ ወረራ የተፈፀመው። በስብሰባ ላይ የነበሩ የህዝብ እንደራሴዎችም ለደህንነታቸው ሲባል በፖሊስ ታጅበው ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደው እንደነበር ተዘግቧል። በተቀሰቀሰው ግርግር ሳቢያም የዋሺንግተን  ከንቲባ በከተማዋ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ለመጣል ተገደው ነበር።
ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተፈጠረውን ድርጊት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤”በካፒቶል ሂል የታየው ነውጥ ትክክለኛውን አሜሪካ አያንፀባርቅም፤ እኛን አይወክልም፤ ያየነው ጥቂት ህገ-ወጥ ፅንፈኞችን ነው። ይህ ተቃውሞ ሳይሆን ቀውስ ነው። አሁኑኑ መቆም አለበት። ይሄ ቡድን ከድርጊቱ ታቅቦ ለዲሞክራሲ መንገድ እንዲጠርግ  አሳስባለሁ።” ብለዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የተቀሰቀሰው ነውጥ በራሳቸው በዶናልድ ትራምፕ አነሳሽነትና ገፋፊነት የተፈጠረ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች፤ በኋላ ላይ ግን ፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎቻቸውን በማረጋጋት ወደ የቤታቸው እንዲገቡ የሚያሳስብ መልዕክት ማስተላለፋቸውንም አመልክተዋል።
ከነውጡና ግርግሩ ጋር በተገናኘም ፕሬዚዳንቱ ከፌስቡክና ትዊተር ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸው ተጠቁሞ የነበረ ሲሆን ከ12 ሰዓት በኋላ ላይ የትዊተር  እገዳው ተነስቶላቸው መልዕክት ማስተላለፍ ችለዋል።
የህግ መምሪያውና የህግ መወሰኛው ም/ቤት አባላት በጋራ ተሰብስበው በሚነጋገሩበት ወቅት ነውጥ በመነሳቱ የጆ ባይደንን የምርጫ ድል የማፅደቅ   ውይይት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ሁኔታው  ከተረጋጋ በኋላ ግን የጆ ባይደንን የምርጫ ውጤት አረጋግጠዋል። የሁለቱም ም/ቤቶች እንደራሴዎች የተሰጡትን የውክልና ድምጾች በመቁጠር፣ ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት፣ ካሚላ ሃሪስ ደግሞ ም/ፕሬዚዳንት በማድረግ ያገኙትን ድምጽ አጽድቀዋል።
ባለፈው ሐሙስም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመራጩ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አገሪቱን የመምራት ሃላፊነቱን እንደሚረከብ በይፋ ተናግረዋል። የአዲሱን ፕሬዚዳንት ባይደን ስም ሳይጠቀሱ ለ3 ደቂቃ ባደረጉት የቪዲዮ ንግግር፣ “ጃንዋሪ 20 አዲስ አስተዳደር ስልጣን ተረክቦ ስራ ይጀምራል” ብለዋል።
“አሁን ትኩረቴን የማደርገው ስርዓቱን የጠበቀ፣ የተቃናና እንከን የለሽ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ በማመቻቸት ተግባር ላይ ነው” ብለዋል - ነውጡ በካፒቶል ሂል ከተከሰተ በኋላ ፕሬዚዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዲሞክራት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ለመውጣት ከምትቀራቸው 10 ቀን ያልበለጠ ጊዜ አስቀድሞ ከስልጣን እንዲወገዱ የተለያዩ ዘመቻዎችን ከፍተዋል የሚሳካላቸው ባይመስልም፡፡

“በዲሞክራሲ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት”
የካፒቶል ሂል ንህፃ በነውጠኛ ተቃዋሚዎች መወረሩን ተከትሎ፣ አስተያየት ያልሰጠ የዓለም መሪ የሉም ማለት ይቻላል። ከእንግሊዝ እስከ ዚምባቡዌ፤  ከሩሲያ እስከ እስራኤል እንደ ቻይና ኢራንን የመሳሰሉ መንግስታት ደግሞ የአሜሪካን ዲሞክራሲና የምርጫ ስርዓት እስከ መንቀፍና ማጥላላት አድርሷቸዋል የዋሺንግተን ነውጥ፡፡
ድርጊቱ በዲሞክራሲ ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው ያሉት የእንግሊዙ ጠ/ሚኒስት ቦሪስ ጆንሰን፤ “አሜሪካ በመላው ዓለም ለሞክራሲ የቆመች አገር ናት፤ እናም አሁን ሰላማዊና የተቃና የስልጣን ሽግግር መካሄድ አለበት” ሲሉ  በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል በበኩላቸው፤ የአሜሪካ የህግ ምክር ቤትን የወረሩት “ጥቃት ፈፃሚዎችና ነውጠኞች” እንዲሆኑ በመጠቆም፤ ድርጊቱን  ከተመለከቱ በኋላ ንዴትና ሃዘን እንደተሰማቸው ገልፀዋል።
ከጀርመን ወግ አጥባቂዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ቻንስለሯ ባደረጉት ንግግርም፤ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሁንም ሽንፈትን ከመቀበል ይልቅ በምርጫው  ውጤት ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጉን  በመቀጠሉ በእጅጉ አዝኛለሁ” ብለዋል።
ሩሲያ ደግሞ ባለፈው ረቡዕ ለታየው ነውጥና ግርግር ተጠያቂ ያደረገችው “ዘመን ያለፈበት” ያለችውን የአሜሪካ የምርጫ ሥርዓትና የሚዲያው የፖለቲካ ትግል መሳሪያነት እየሆነ ነው።
“በአሜሪካ የምርጫ ስርዓቱ ጊዜ ያለፈበት ነው፤ ዘመናዊ የዲሞክራሲ መስፈርቶችን አያሟላም፤ በዚህም የተነሳ ለበርካታ ጥሰቶች ዕድል ይከፍታል፤ የአሜሪካ ሚዲያም የፖለቲካ ትግል መሳሪያ ሆኗል” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይዋ ማርያ ዛክሃሮቫ።
ሌሎች የአውሮፓ አገራት መሪዎችም በዋሺንግተን የተከሰተውን ነውጥ በዲሞክራሲ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው ሲሉ አጥብቀው አውግዘውታል።
የስፔን ጠ/ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በሰጡት አስተያየት፤ “በአሜሪካ ዲሞክራሲ ጥንካሬ ላይ ፅኑ እምነት አለኝ። አዲሱ ፕሬዚዳት ጆ ባይደን የአሜሪካንን ህዝብ አንድ በማድረግ ይህን ውጥረት ያልፉታል” ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳት ኢማኑኤል ማርኮን በበኩላቸው፤ “በዋሺንግተን ዲሲ የታየው ፈፅሞ አሜሪካን አይገልፃትም። በዲሞክራሲያችን ጥንካሬ  ላይ እምነት አለን። በአሜሪካ ዲሞክራሲ ጥንካሬ ላይ እምነት አለን” ብለዋል በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፡፡
የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ መሪዎችም ዝም አላሉም። የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል በሰጡት አስተያየት፤ “አሜሪካ ለባይደን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንደምታረጋግጥ አምናለሁ” ብለዋል።
የኔቶ ወታደራዊ አጋርነት ዋና ፀሃፊ ጄንስ ስቶልቴንበርንግ በበኩላቸው፤ “የምርጫ ውጤት መከበር አለበት” ሲሉ መክረዋል።
የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው አውስትራሊያ ጠ/ሚኒስትር ስኮት ሞሪሶን፤ አሳዛኝ ያሉትን “ነውጥ” አውግዘው፤ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ይደረጋል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የአሜሪካን ቅቡልነት ያላገኘው  የቬንዝዌላ መንግስት በሰጠው መግለጫ፤ “በዚህ አሳዛኝ ሁነት፣ አሜሪካ በጠብ አጫሪነት ፖሊሲዋ በሌሎች አገራት ላይ የፈጠረችው ዓይነት ችግር ነው የገጠማት” ብሏል።
እ.ኤ.አ በ2006 ኩዴታ ያስተናገደችው የፊጂ ጠ/ሚኒስትር ፍራንክ ባይኒማራማ፤ በዋሺንግተን የተፈጠረውን በተከሰተው ነውጥ አስመልክቶ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮሃኒ በቴሌቪዥን በተሰራጨ ንግግራቸው፤ “አሁን በአሜሪካ  የታየው ሁነት የምዕራቡ ዲሞክራሲ ምን ያህል የከሸፈ መሆኑን ያረጋገጠ ነው… ህዝበኛው መሪ የገዛ አገሩን መልካም ስምና ዝና ጥላሸት ቀብቷል" ሲሉ አብጠልጥለዋል።
አፍሪካዊቷ ሀገር ዚምባቡዌም አሜሪካንና ዲሞክራሲዋን አብጠልጥላለች። ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት አስተያየት፤ “ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ የዚምባቡዌ የዲሞክራሲ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው በመጥቀስ፤ በአገራችን ላይ ወገብ የሚቆርጥ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥለውብናል። ረቡዕ  የተስተዋለው ክስተት አሜሪካ የዲሞክራሲን ጠበቃ ነኝ በሚል ሽፋን ሌላ አገር ላይ ቅጣት የመጣል የሞራል ብቃት እንደሌላት አረጋግጧል" ብለዋል።

Read 2059 times